ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ያለንበትን ዘመን የሚጠቁም ችግር
ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ያለንበትን ዘመን የሚጠቁም ችግር
በአሁኑ ጊዜ እጅግ ጎልቶ የሚታየው ማኅበራዊ ችግር ምንድን ነው ትላለህ? በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተካሄደ አንድ ጥናት 80 በመቶ የሚሆኑት ማለት ይቻላል “በቤተሰብ ውስጥ የአባት አለመኖር” ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በተካሄደው ጥናት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖሩ ከ27 ሚልዮን የሚልቁ ልጆች ከሥጋ አባቶቻቸው ተለያይተው የሚኖሩ ሲሆን ይህ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት በማሻቀብ ላይ ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደገለጸው ከ1980 ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከተወለዱት ነጮች ልጆች መካከል 50 በመቶ ገደማ የሚሆኑት “ከልጅነት ሕይወታቸው ውስጥ የተወሰነውን በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ያሳልፋሉ። ከጥቁሮቹ ልጆች መካከል ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚገጥማቸው 80 በመቶ ይሆናሉ።” በመሆኑም ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ ዩናይትድ ስቴትስን “አባት አልባ በሆኑ ቤተሰቦች ቁጥር ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘች አገር” ሲል ሰይሟታል።
ሆኖም ዘ አትላንቲክ መንዝሊ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “የብዙ ቤተሰቦች ሕይወት እየተናጋ ያለው በአሜሪካ ኅብረተሰብ ውስጥ ብቻ አይደለም። ጃፓንን ጨምሮ በሁሉም ያደጉ አገሮች ውስጥ የሚታይ ችግር ነው ማለት ይቻላል” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም ምንም እንኳ አኃዛዊ መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ቢሆንም በብዙ ታዳጊ አገሮች ውስጥም ተመሳሳይ ቀውስ ያለ ይመስላል። ዎርልድ ዎች የተባለው መጽሔት እንዳለው ከሆነ “ብዙውን ጊዜ [ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ] ወንዶች እየጨመረ በሚሄደው የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ሳቢያ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ጥለው ይሄዳሉ።” እንዲያውም በካሪቢያን በምትገኝ አንዲት አገር የተካሄደው ጥናት የስምንት ዓመት ልጆች ካሏቸው አባቶች መካከል ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚኖሩት 22 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ አመልክቷል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ቢሆን አባት የሌላቸው ልጆች ነበሩ። (ዘዳግም 27:19 የ1980 ትርጉም፤ መዝሙር 94:6 የ1980 ትርጉም ) ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን ልጆች ያለ አባት ይቀሩ የነበረበት ዋነኛው ምክንያት አባቶቻቸውን በሞት ይነጠቁ ስለነበረ ነው። “በዛሬው ጊዜ” ይላሉ ደራሲው ዴቪድ ብላንከንሆርን፣ “ልጆች ያለ አባት የሚቀሩበት ዋነኛው ምክንያት አባቶቻቸው ጥለዋቸው ስለሚሄዱ ነው።” በእርግጥም ከሁኔታው ማየት እንደሚቻለው ያለ አባት የቀሩ ልጆች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው” መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ይህ ሁኔታ “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር የሚያሳይ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
ይሁን እንጂ ሕፃናት አባታቸውን ከጎናቸው ማጣታቸው አሳዛኝ ገጠመኝ ይሆንባቸዋል። ዘላቂ የሆኑ መዘዞች ሊያስከትል የሚችል የሐዘንና የሥቃይ ዑደት ይፈጥርባቸዋል። በመሆኑም የአንባብያንን ቅስም ለመስበር ሳይሆን ቤተሰቦች ይህን ጎጂ አዝማሚያ መግታት እንዲችሉ ሊረዳቸው የሚችል መረጃ ለማቅረብ ስንል በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ላይ ይህን ዑደት የሚመለከት ሐሳብ ይዘን ቀርበናል።