በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥቁር ሞት—በመካከለኛው ዘመን አውሮፓን የመታው ቸነፈር

ጥቁር ሞት—በመካከለኛው ዘመን አውሮፓን የመታው ቸነፈር

ጥቁር ሞት—በመካከለኛው ዘመን አውሮፓን የመታው ቸነፈር

ፈረንሳይ የሚገኝ የንቁ ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ዓመቱ 1347 ነው። በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙትን አገሮች ሲያዳርስ የቆየው ቸነፈር አቅጣጫውን ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ዳርቻዎች አዙሯል።

ሞንጎላውያን በክራይሚያ የምትገኘውና በአሁኑ ጊዜ ፊዮዶሲያ ተብላ የምትጠራው የካፋ የንግድ ልውውጥ ማዕከል የሆነችውን የተመሸገችውን ከተማ ጄኖዊዝን ከብበዋል። ሞንጎላውያኑ ራሳቸው ምሥጢራዊ በሆነው በሽታ በማለቃቸው ጥቃታቸውን አቆሙ። ከማፈግፈጋቸው በፊት ግን ከፍተኛ እልቂት የሚያስከትል አንድ ዓይነት ጥቃት ሰነዘሩ። ግዙፍ ማስወንጨፊያዎችን በመጠቀም የቸነፈሩ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ትኩስ አስከሬኖች በከተማዋ ቅጥሮች ላይ እያሻገሩ ወረወሯቸው። ከተማቸውን ከጠላት ጥቃት ሲከላከሉ ከነበሩት የጄኖዊዝ ነዋሪዎች መካከል ጥቂቶቹ በቸነፈር ከተወረረችው ከተማቸው ለመሸሽ በመርከቦቻቸው ተሳፍረው ሲሄዱ በሽታውን በሄዱበት ወደብ ሁሉ አሰራጩት።

በጥቂት ወራት ውስጥ መላው አውሮፓ በሞት ቸነፈር ተመታ። ቸነፈሩ ወደ ሰሜን አፍሪካ፣ ኢጣሊያ፣ ስፔይን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ሃንጋሪ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ስካንዴኔቪያና ወደ ቦልቲክ አገሮች በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ። ከሁለት ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነው የአውሮፓ ሕዝብ ማለትም ወደ 25 ሚልዮን የሚጠጉ ነፍሳት “የሰው ልጅ ከገጠሙት ሕዝበ ጽፋዊ (demographic) መቅሰፍቶች ሁሉ እጅግ የከፋ” ተብሎ የተጠራው ጥቁር ሞት ሰለባ ሆኑ። *

ለአደጋ ምቹ ሁኔታ መፍጠር

ጥቁር ሞት ያስከተለው አሳዛኝ ሁኔታ በራሱ በበሽታው ብቻ የተከሰተ አልነበረም። ለአደጋው መባባስ ምክንያት የሆኑ በርከት ያሉ ነገሮች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ ሃይማኖታዊ ስሜት ነበር። የመንጽሔ መሠረተ ትምህርት አንዱ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው። “በ13ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የመንጽሔ እምነት በሁሉም ቦታ ተስፋፍቶ ነበር” ይላሉ ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ዣክ ለ ጎፍ። በ14ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ዳንቴ ስለ ሲኦልና መንጽሔ የሚገልጹ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሉትን ዘ ዲቫይን ኮሜዲ የተባለውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ የሥነ ጽሑፍ ሥራውን አዘጋጅቶ አወጣ። በመሆኑም ሰዎች ቸነፈሩ ከራሱ ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንደሆነ አድርገው በመመልከት በሚያስገርም ሁኔታ ግድየለሾች እንዲሆኑና ቸነፈሩን በጸጋ እንዲቀበሉት የሚያደርግ ሃይማኖታዊ መንፈስ ሰፈነ። ቀጥሎ እንደምንመለከተው እንዲህ ዓይነቱ አፍራሽ ዝንባሌ እንደ እሳት እየተቀጣጠለ በነበረው በሽታ ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ የሚቆጠር ነበር። በፊሊፕ ዚግለር የተዘጋጀው ዘ ብላክ ዴዝ የተባለው መጽሐፍ “ከዚህ ይበልጥ ለቸነፈር መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነገር ሊኖር አይችልም” ሲል ይገልጻል።

ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓ በተደጋጋሚ የምግብ ምርት እጥረት ተከስቶ ነበር። በዚህም ሳቢያ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የነበረው የአህጉሪቱ ሕዝብ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ስለገጠመው በሽታውን መቋቋም የሚችልበት አቅም ሊኖረው አልቻለም።

ቸነፈሩ ተዛመተ

የሊቀ ጳጳሳት ክሌመንት ስድስተኛ የግል ሐኪም የነበረው ጊ ደ ሾልያክ እንዳለው ከሆነ አውሮፓን የመታው ቸነፈር ሁለት ዓይነት ነበር:- ኑሞኒክ እና ቡቦኒክ። እነዚህን በሽታዎች በዝርዝር በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የመጀመሪያው ለሁለት ወራት የቆየ ሲሆን የማያቋርጥ ትኩሳት የሚያስከትልና ደም የሚያስተፋ ነው። በዚህ የተያዘ ሰው በሦስት ቀናት ውስጥ ይሞታል። ሁለተኛው በቀሪዎቹ ቸነፈሩ በቆየባቸው ጊዜያት ሁሉ የነበረ ሲሆን ይኼኛውም በሽታ የማያቋርጥ ትኩሳት የሚያስከትል ሆኖ በውጫዊ የሰውነት ክፍሎች ላይ በተለይ በብብትና በብሽሽት ላይ ምርቅዝና ንፍርቅ እባጭ የሚፈጥር ነው። በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው በአምስት ቀን ውስጥ ይሞታል።” ዶክተሮች የዚህን ቸነፈር ስርጭት ለመግታት ምንም ሊያደርጉት የቻሉት ነገር አልነበረም።

ብዙ ሰዎች በሺዎች የሚቆጠሩትን በበሽታው የተለከፉ ሰዎች በኋላቸው ትተው እግሬ አውጪኝ ብለው ሸሹ። መጀመሪያ ላይ ከሸሹት መካከል ባለጠጎች የሆኑ መኳንንትና ባለሙያዎች ይገኙበታል። አንዳንድ ቀሳውስትም የሸሹ ቢሆንም እንኳ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ሥር ያሉ ሌሎች ብዙዎች ራሳቸውን ከብክለት ለመጠበቅ ሲሉ በየገዳሞቻቸው ተወሸቁ።

በዚህ ሁሉ ሽብር መካከል ሊቀ ጳጳሳቱ 1350ን ቅዱስ ዓመት ብለው ሰየሙት። ወደ ሮም ጉዞ የሚያደርጉ ተሳላሚዎች የመንጽሔ ሥርዓት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ ወደ ገነት እንደሚገቡ ተነገረ! በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተሳላሚዎች ለጥሪው ምላሽ በሰጡበት ወቅት በሄዱበት ቦታ ሁሉ ቸነፈሩን አዛመቱ።

ከንቱ ድካም

በሽታው እንዴት እንደሚተላለፍ በትክክል ማወቅ የቻለ ሰው ባለመኖሩ ጥቁር ሞትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገው ጥረት ሁሉ አልሰመረም። አብዛኞቹ ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው አልፎ ተርፎም ከልብሱ ጋር ንክኪ መፍጠር አደገኛ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች በበሽታው የተለከፈ ሰው ትኩር ብሎ ካያቸው በሽታው እንደሚይዛቸው አድርገው አስበው ነበር! የጣሊያኗ ከተማ የፍሎረንስ ነዋሪዎች ግን ቸነፈሩን የሚያዛምቱት ድመቶችና ውሾች ናቸው የሚል እምነት አድሮባቸው ስለነበር እነዚህን እንስሳት እያሳደዱ መፍጀቱን ተያያዙት። እንዲህ በማድረጋቸው የበሽታው አስተላላፊ ለሆኑት አይጦች ነፃነት እያወጁ መሆናቸውን አልተገነዘቡም ነበር።

የሟቾቹ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ አንዳንዶች አምላክን መማጸን ጀመሩ። ወንዶችና ሴቶች አምላክ ከበሽታው ይታደገናል ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ብንሞት እንኳ የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት ይሰጠናል በሚል ተስፋ ጥሪታቸውን በሙሉ ለቤተ ክርስቲያን ሰጡ። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን የከፍተኛ ሀብት ባለቤት አደረጋት። በተጨማሪም ብዙዎች በሽታውን ይከላከልልናል በሚል ተስፋ ክታቦችንና የክርስቶስን ምስል ያጠልቁ ነበር። ሌሎች ደግሞ ፈውስ ለማግኘት ሲሉ ወደ መናፍስታዊና አስማታዊ ድርጊቶች ዞር ከማለታቸውም በላይ መድኃኒት ናቸው የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ይወስዱ ነበር። ሽቶ፣ ኮምጣጤና አስማታዊ መድኃኒቶች በሽታውን እንደሚያስወግዱ ይነገር ነበር። ሰውነትን መብጣትም ሌላው ተመራጭ የሕክምና ዘዴ ተደርጎ ተወስዷል። በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የሕክምና ምሁራንም እንኳ ሳይቀር ቸነፈሩ የተከሰተው በፕላኔቶች አቀማመጥ ሳቢያ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር! ይሁን እንጂ የተሳሳቱ ትንተናዎችና ትክክለኛ ያልሆኑ “የሕክምና ዘዴዎች” ይህ ቀሳፊ ቸነፈር የሚያደርገውን ግስጋሴ ለመግታት ምንም የፈየዱት ነገር አልነበረም።

ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መዘዝ

ጥቁር ሞት ከአምስት ዓመት በኋላ እየከሰመ ሄደ። ሆኖም ምዕተ ዓመቱ ከመገባደዱ በፊት ቢያንስ ቢያንስ አራት ጊዜ በድጋሚ መከሰቱ አልቀረም። በመሆኑም ጥቁር ሞት ያስከተለው መዘዝ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ነው። “በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረው ቸነፈር ከ1348 በኋላ በነበረው ጊዜ በኢኮኖሚው ላይም ሆነ በኅብረተሰቡ ላይ ትልቅ መዘዝ ያስከተለ መሆኑን በዘመናችን ያሉ ታሪክ ጸሐፊዎች በሙሉ ይስማሙበታል” ሲል ዘ ብላክ ዴዝ ኢን ኢንግላንድ የተባለው በ1996 ታትሞ የወጣው መጽሐፍ ይገልጻል። ቸነፈሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ የረፈረፈ ሲሆን አንዳንድ አካባቢዎች እስኪያገግሙ ድረስ የተወሰኑ መቶ ዘመናት ተቆጥረዋል። የሠራተኛ ኃይል ከተመናመነ ሠራተኞችን በቀላል ዋጋ ማግኘት እንደማይቻል የታወቀ ነው። በአንድ ወቅት የናጠጡ ከበርቴዎች የነበሩ ሰዎች ባዶ እጃቸውን ቀሩ። በመካከለኛው መቶ ዘመን ሰፍኖ የነበረው የፊውዳል ሥርዓትም ተንኮታኮተ።

ስለዚህ ቸነፈሩ ለፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ለውጥ በር ከፍቷል። ቸነፈሩ ከመከሰቱ በፊት በእንግሊዝ ውስጥ የሚገኘው የተማረው ክፍል ፈረንሳይኛ ይናገር ነበር። ይሁን እንጂ በርካታ የፈረንሳይ አስተማሪዎች በመሞታቸው በብሪታንያ ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፈረንሳይኛን ሊውጠው ችሏል። በሃይማኖታዊውም መስክ ለውጦች ተከስተዋል። ፈረንሳዊዋ ታሪክ ጸሐፊ ዣክሊን ብሮሶሌ እንደገለጹት ለክህነት አገልግሎት የሚታጩ ሰዎች እጥረት በመፈጠሩ “ቤተ ክርስቲያኗ ያልተማሩና ለምንም ነገር ደንታ የማይሰጣቸውን ሰዎች መመልመል ግድ ሆነባት።” ብሮሶሌ “[የቤተ ክርስቲያን] የትምህርትና የእምነት ማዕከላት ውድቀት ለሃይማኖታዊ የተሃድሶ ንቅናቄ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ጥቁር ሞት በኪነ ጥበብ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ሞት የተለመደ የኪነ ጥበብ ጭብጥ ሊሆን ችሏል። በአብዛኛው ስለ አፅምና አስከሬን የሚያወሳው ዳንስ ማካብር የተባለው ዝነኛው የኪነ ጥበብ ሥራ የታወቀ የሞት ኃይል ተምሳሌት ሆኖ ነበር። ከቸነፈሩ የተረፉ ብዙ ሰዎች ወደፊት የሚመጣውንም አናውቅም በሚል ስሜት ሁሉንም የሥነ ምግባር ደንቦች እርግፍ አድርገው ተዉ። በዚህም ምክንያት የሰዎች የሥነ ምግባር ደረጃ በእጅጉ አዘቀጠ። ቤተ ክርስቲያን ጥቁር ሞትን መከላከል ባለመቻሏ “በመካከለኛው መቶ ዘመን የነበረው ሰው ቤተ ክርስቲያኑን እንደጠበቃት ሆና አላገኛትም።” (ዘ ብላክ ዴዝ ) በተጨማሪም በጥቁር ሞት ሳቢያ የተከሰቱት ማኅበራዊ ለውጦች ግለኝነት እንዲሰፍንና ሰዎች ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ በድፍረት አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር እንዲነሳሱ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በላይ ማኅበራዊውና ኢኮኖሚያዊው እንቅስቃሴ ይበልጥ እየቀለለ እንዲሄድ ማድረጋቸውን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለካፒታሊዝም ሥርዓት ጥርጊያውን አመቻችቷል።

በተጨማሪም ጥቁር ሞት መንግሥታት ለጤና አጠባበቅ የሚያገለግሉ ሥርዓቶችን እንዲዘረጉ አነሳስቷቸዋል። ቸነፈሩ ጋብ ካለ በኋላ ቬኒስ ጎዳናዎቿን ለማጽዳት አንዳንድ እርምጃዎች ወሰደች። ጥሩው ንጉሥ በመባል ይታወቁ የነበሩት የፈረንሳዩ ዳግማዊ ጆንም እንደዚሁ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ጎዳናዎች ጽዳት እንዲደረግላቸው አዝዘው ነበር። ንጉሡ ይህን እርምጃ የወሰዱት ጎዳናዎች እንዲጸዱና እንዲታጠቡ በማድረግ አቴንስን ከቸነፈር መታደግ ስለቻለ አንድ የጥንት ግሪካዊ ዶክተር ከሰሙ በኋላ ነበር። በመካከለኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክፍት የቆሻሻ ማስወገጃ ቦዮች የመሰሉ ብዙዎቹ ጎዳናዎች በመጨረሻ እንዲጸዱ ተደረገ።

ያለፈ ታሪክ ነውን?

ይሁን እንጂ ፈረንሳዊው የስነ ባክቴሪያ ባለሙያ አሌክሳንደር ዬርሳን ለጥቁር ሞት ምክንያት የሆነውን ባሲለስ ለይቶ ያወቀው በ1894 ነበር። ባሲለሱ ዬርሲኒያ ፔስቲስ ተብሎ በራሱ ስም ተጠራ። ከአራት ዓመት በኋላ ፖል-ልዊ ሲሞን የተባለ ሌላ ፈረንሳዊ በሽታውን በማስተላለፍ ረገድ ቁንጫ (በአይጦች ተሸካሚነት) የምትጫወተውን ሚና መገንዘብ ቻለ። ብዙም ሳይቆይ በክትባት መልክ መድኃኒት ማዘጋጀት ተቻለና በተወሰነ ደረጃ ስኬት አስገኘ።

ቸነፈሩ ያለፈ ታሪክ ነውን? በፍጹም። በ1910 የክረምት ወራት በማንቹሪያ ወደ 50, 000 የሚጠጉ ሰዎች በዚህ ቸነፈር አልቀዋል። በተጨማሪም በየዓመቱ የዓለም የጤና ድርጅት በሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰለባዎችን የሚመዘግብ ሲሆን ቁጥሩ ማሻቀቡን ቀጥሏል። አዳዲስ የበሽታው ዓይነቶችም የተገኙ ሲሆን የሚሰጠውን ሕክምና የሚቋቋሙ ሆነው ተገኝተዋል። አዎን፣ መሠረታዊ የሆኑ የንጽሕና አጠባበቅ መስፈርቶች እስካልተጠበቁ ድረስ ቸነፈሩ በሰው ልጅ ላይ ስጋት መፍጠሩን ይቀጥላል። በመሆኑም በዣክሊን ብሮሶሌ እና ኦንሪ ሞላሬ የተዘጋጀው ፑርክዋ ላ ፔስት? ለ ራ፣ ላ ፑስ ኤ ለ ቡቦን (ቸነፈሩ የተከሰተው ለምንድን ነው? አይጥ፣ ቁንጫና እትርፍርንት) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ደምድሟል:- “ቸነፈሩ በመካከለኛው መቶ ዘመን የነበረ የጥንቱ አውሮፓ በሽታ ብቻ ሳይሆን . . . የወደፊቱም ዘመን በሽታ ሊሆን የሚችል መሆኑ የሚያሳዝን ነው።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በዘመኑ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ታላቁ መቅሠፍት ወይም ወረርሽኝ ሲሉ ጠርተውታል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወንዶችና ሴቶች አምላክ ከበሽታ ይታደገናል ብለው ተስፋ በማድረግ ጥሪታቸውን በሙሉ ለቤተ ክርስቲያን ሰጡ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ራሳቸውን የሚቀጡ ሰዎች ሃይማኖታዊ ቡድን

አንዳንዶች ቸነፈሩ የአምላክ ቁጣ እንደሆነ አድርገው በመመልከት ይህን የአምላክ ቁጣ ለማብረድ ራሳቸውን ይገርፉ ወይም ይቀጡ ነበር። እስከ 800, 000 የሚደርሱ አባላት እንደነበሩት የሚነገርለት ራሳቸውን የሚቀጡ ሰዎችን ያቀፈው ይህ ንቅናቄ በጥቁር ሞት ዘመን ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። ይህ ሃይማኖታዊ ቡድን ከሴቶች ጋር መነጋገርን፣ መታጠብን ወይም ልብስ መቀየርን የሚከለክሉ ሕጎች ነበሩት። አባላቱ በቀን ሁለት ጊዜ በሕዝብ ፊት ራሳቸውን ይገርፉ ነበር።

“ራስን በራስ መቅጣት በፍርሃት የተዋጠ ሕዝብ ስሜቱን መግለጽ ከሚችልባቸው ጥቂት መንገዶች አንዱ ነው” ሲል ሚዲቫል ሄረሲ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። በተጨማሪም እነዚህ ራሳቸውን የሚቀጡ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን የሥልጣን ተዋረድ በማውገዝና ቤተ ክርስቲያን የምታካሂደውን አትራፊ የሆነውን የፍታት ሥርዓት በማዳከም የታወቁ ነበሩ። ከዚህ አንጻር ሲታይ ሊቀ ጳጳሳቱ በ1349 ይህን ሃይማኖታዊ ቡድን ማውገዛቸው ምንም አያስደንቅም። ውሎ አድሮ የጥቁር ሞት ዘመን ካለፈ በኋላ ሃይማኖታዊ ቡድኑ በራሱ እየከሰመ ሄደ።

[ሥዕል]

ራሳቸውን ይቀጡ የነበሩት ሰዎች አምላክን ይለማመኑ ነበር

[ምንጭ]

© Bibliothèque Royale de Belgique, Bruxelles

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈረንሳይ፣ ማርሴይ ውስጥ የተከሰተው ቸነፈር

[ምንጭ]

© Cliché Bibliothèque Nationale de France, Paris

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሌክሳንደር ዬርሲን ቸነፈሩን ያስከተለውን ባሲለስ ለይቶ ማወቅ ችሏል

[ምንጭ]

Culver Pictures