በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰማይ ካርታ መሥራት—ጥንትና ዛሬ

ለሰማይ ካርታ መሥራት—ጥንትና ዛሬ

ለሰማይ ካርታ መሥራት—ጥንትና ዛሬ

ኔዘርላንድ የሚገኝ የንቁ ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ጥርት ባለ ጥቁር ሰማይ ላይ ተረጭተው የሚታዩ ከዋክብት ብዙውን ጊዜ ሰውን በግርምት ያስደምማሉ። የሰው ልጅ ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ለእንዲህ ዓይነቱ ውበት ፈጣሪ ያለውን አድናቆት ለመግለጽ ተገፋፍቷል። ከረጅም ዘመናት በፊት አንድ ባለ ቅኔ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 19:​1) ይሁን እንጂ በምሽት ሰማይን ይመለከቱ የነበሩ የጥንት ሰዎች ከውበትም ባሻገር ያስተዋሏቸው ነገሮች ነበሩ።

በሰማይ ላይ ምስል መፍጠር

በቀድሞ ዘመን የነበሩ የስነ ፈለክ አጥኚዎች መላው የከዋክብት አካል ሥርዓት ባለው መንገድ የሚንቀሳቀስ እንደሚመስል አስተውለው ነበር። ከዋክብት በሰማይ ላይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚጓዙ ቢሆንም አቀማመጣቸው አይለወጥም። * በሌላ አነጋገር በእያንዳንዱ ሌሊት የሚታዩት እነዚያው የከዋክብት ስብስቦች ናቸው። የሰው ልጅ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን እነዚህን ከዋክብት በሥርዓት ለመከፋፈል ስለፈለገ ከዋክብትን በቡድን መለየት ጀመረ። ትንሽ ቆም ብሎ በማሰብ የእነዚህን ቡድኖች ቅርጽ ከእንስሳት፣ ከሰዎችና ግዑዝ ከሆኑ አካላት ጋር ማመሳሰል ይቻላል። በዚህ መንገድ በቋሚነት የተወሰኑ የከዋክብት ሙቅረቶችን (configurations of stars) እንደ ህብረ ከዋክብት መመልከት ተጀመረ።

በዛሬው ጊዜ እኛ ከምናውቃቸው ህብረ ከዋክብት መካከል ስለ አንዳንዶቹ በመጀመሪያ ዝርዝር መግለጫ የተሰጠው በጥንቷ ባቢሎን ነው። ከእነዚህ መካከል የዞዲያክ ምልክቶችን የሚወክሉት 12ቱ ህብረ ከዋክብት ይገኙበታል። እነዚህ ህብረ ከዋክብት በኮከብ ቆጠራ ማለትም ከዋክብት በሰዎች ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ በሚል እምነት በሚካሄደው የጥንቆላ ሥራ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሲሆን አሁንም ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በከዋክብት አማካኝነት ገድን ለማወቅ መሞከር በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘ ልማድ ነው። (ዘዳግም 18:​10-12) ሆኖም ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎችም የህብረ ከዋክብትን ሕልውና ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ያህል የኢዮብ መጽሐፍ ይሖዋ “ድብ፣ ኦሪዮንና ፕልያዲስ የተባሉትን ከዋክብት [“ህብረ ከዋክብት፣” NW  ]” እንደፈጠረ ይናገራል።​—⁠ኢዮብ 9:​9 የ1980 ትርጉም

በዛሬው ጊዜ የምናውቃቸው የብዙዎቹ ህብረ ከዋክብት ስሞች የመጡት ከግሪክ አፈ ታሪክ ነው። እንደ ሲፊውስ፣ ካሶፒያ፣ አንድሮሜዳ እና ሄርኩለስ ያሉትን መጠሪያዎች አሁንም ድረስ በዘመናዊ የኮከብ ቻርቶች ላይ ማግኘት ይቻላል።

በቀድሞ ዘመን የተዘጋጁ የኮከብ ቻርቶች

በ150 እዘአ ገደማ ላይ ግሪካዊው የስነ ፈለክ አጥኚ ቶለሚ በዘመኑ የነበረውን የስነ ፈለክ እውቀት ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ነበር። አልማጄስት የሚል ርዕስ ያለው ይህ ጽሑፍ የ48 ህብረ ከዋክብት ዝርዝር ይዟል። ከቶሎሚ ዘመን በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት የተዘጋጁት የሰማይ ቻርቶችና አትላሶች በአብዛኛው እነዚህን 48 ህብረ ከዋክብት የያዙ ናቸው። እንዲያውም እስከ 16ኛው መቶ ዘመን ገደማ ድረስ የህብረ ከዋክብቱ ቁጥር አልተለወጠም ነበር። * ከጊዜ በኋላ ሌሎች 40 ህብረ ከዋክብት ተጨመሩ። በ1922 ዓለም አቀፉ የስነ ፈለክ ምርምር ኅብረት የእነዚህን 88 ህብረ ከዋክብት ዝርዝር በይፋ ተቀብሏል።

የቶለሚ ጽሑፍ ከህብረ ከዋክብት በተጨማሪ ስለ ድምቀታቸውና በሰማይ ላይ ስላላቸው ቦታ የሚገልጽ መረጃ የያዘ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ከዋክብት ዝርዝር አለው። ቶለሚ ከዋክብቱ ያላቸውን አቀማመጥ የገለጸው ከሰማያዊ ኬንትሮስና ኬክሮስ አንጻር ብቻ አይደለም። ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫም ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል ኡርሳ ሜጀር ወይም ትልቅ ድብ ተብሎ በሚጠራው ህብረ ከዋክብት ውስጥ የሚገኝ አንድ ኮከብ “በጅራቱ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ” ተብሎ የተገለጸ ሲሆን የአንድ ጅራታም ኮከብ ቦታ ደግሞ “ከአንድሮሜዳ የቀኝ ጉልበት በስተግራ” ተብሎ ተገልጿል። በመሆኑም “እያንዳንዱ ብቁ የስነ ፈለክ አጥኚ” ይላል አንድ የመማሪያ መጽሐፍ፣ “የራሱን የሰማይ አካላት አናቶሚ ማወቅ ነበረበት!”

ይሁን እንጂ ከጥንቶቹ ህብረ ከዋክብት መካከል አብዛኞቹ በሰሜናዊው ሰማይ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው? ይህ ሊሆን የቻለው የተወሰኑ የከዋክብት ቡድኖችን በህብረ ከዋክብት የመከፋፈል ልማድ የተጀመረው ሰሜናዊው ሰማይ በሚታይበት በሜድትራንያን አካባቢ ስለሆነ ነው ሲሉ የሰማይ አካላትን ካርታ የሚሠሩ አንድ ባለሙያ ገልጸዋል። አዳዲስ ህብረ ከዋክብት የተገኙት ከጊዜ በኋላ የሰው ልጅ ደቡባዊውን ሰማይ ማጥናት ሲጀምር ነው። ከእነዚህ አዳዲስ ህብረ ከዋክብት መካከል አንዳንዶቹ እንደ ኬሚካል ፈርኔስ፣ ፔንዱለም ክሎክ፣ ማይክሮስኮፕ እና ቴሌስኮፕ ያሉ ስያሜዎች ተሰጥተዋቸዋል።

“ክርስቲያናዊው የከዋክብት ሰማይ”

በ1627 ጀርመናዊው ምሁር ዩሊየስ ሺለር ኮኢሉም ስቴላቱም ክሪስቲያኑም (ክርስቲያናዊው የከዋክብት ሰማይ) በሚል ርዕስ የኮከብ አትላስ አሳተመ። የሰማይ አካላትን ከአረማዊ እምነት ማንጻት እንደሚያስፈልግ ተሰምቶት ነበር። በመሆኑም በአረማዊ ስያሜዎች የተወከሉትን ህብረ ከዋክብት ከመጽሐፍ ቅዱስ በተወሰዱ ስያሜዎች መተካት ጀመረ። ዘ ማፒንግ ኦቭ ዘ ሄቨንስ የተባለው መጽሐፍ “አዲስ ኪዳንን ለሰሜናዊው ሰማይ ብሉይ ኪዳንን ደግሞ ለደቡባዊው ሰማይ” መደበ ሲል ይገልጻል። “የሺለር ደቡባዊ ንፍቀ ሉል ከብሉይ ኪዳን በተወሰዱ ስያሜዎች ተሞላ። ህንዳዊ በሚለው ስያሜ ምትክ ኢዮብ ተተካ። ጣኦስና ሴንታወር ደግሞ አብርሃም እና ይስሐቅ በሚሉ ስያሜዎች ተለወጡ።” በሰሜናዊው ንፍቀ ሉል “ካሶፒያ መግደላዊት ማርያም፣ ፐርሲውስ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ተብለው የተሰየሙ ሲሆን አሥራ ሁለቱ የዞዲያክ ምልክቶች በቀላሉ በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም ተተኩ።”

በዚህ የማንጻት ሂደት ያልተነካው አንድ አነስተኛ ህብረ ከዋክብት ብቻ ነበር። ይህም ኖኅ ደረቅ ምድር እንድትፈልግ የላካትን ርግብ ይወክላል የሚባለው ኮሉምባ (ርግብ) የተሰኘው ህብረ ከዋክብት ነው።

በካርታዎች ላይ የተካሄደ የለውጥ ሂደት

ከጊዜ በኋላ የኮከብ ቻርቶች መልክ ተለወጠ። በ17ኛው መቶ ዘመን ቴሌስኮፕ ከተፈለሰፈ በኋላ የከዋክብትን አቀማመጥ ይበልጥ በትክክል የሚያሳዩ ቻርቶች መሥራት አስፈላጊ ሆነ። ከዚህም በተጨማሪ በቀድሞ ዘመን የተዘጋጁትን ቻርቶች ያጨናነቁት የተንዛዙ ማሸብረቂያዎች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ ሄደና ከጊዜ በኋላ ከናካቴው እንዲቀሩ ተደረገ። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የኮከብ አትላሶች ከዋክብትን፣ የከዋክብት ክምችቶችን፣ ኔቡላዎችን፣ ጋላክሲዎችንና በምሽት የሰማይ አካላትን የሚያጠኑ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ሌሎች ነገሮችን ብቻ የያዙ ናቸው።

በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ይበልጥ ሰፊ የሆኑ ካታሎጎች መዘጋጀት ጀመሩ። የዚህ መስክ አቅኚዎች ከሆኑት መካከል ጀርመናዊው የስነ ፈለክ አጥኚ ፍሪድሪክ ቪልሄልም አርገላንደር ይገኝበታል። በርከት ካሉ ረዳቶቹ ጋር በመሆን በሰሜናዊው ሰማይ የሚገኙትን ከዋክብት ካታሎግ የማዘጋጀቱን መጠነ ሰፊ ሥራ ተያያዘው። በቴሌስኮፕ አማካኝነት ወደ 325, 000 የሚጠጉ ኮከቦች ከማግኘታቸውም በላይ የእያንዳንዳቸውን አቀማመጥና የብርሃናቸውን መጠን ለኩ። ይሠሩበት የነበረው የምርምር ተቋም ይገኝ የነበረው በጀርመን ቦን ከተማ ውስጥ ስለነበር ካታሎጉ ቦነር ዱርክሙስተሩንግ (የቦን አጠቃላይ ጥናት) ተብሎ ተሰየመ። የታተመው በ1863 ነበር። አርገላንደር ሲሞት ሥራው ከረዳቶቹ በአንዱ መካሄዱን ቀጠለ። በደቡባዊው ሰማይ ላይ የሚገኙትን ኮከቦች ካርታ አዘጋጀና ዙትሊከ ቦነር ዱርክሙስተሩንግ (የቦን የደቡብ አጠቃላይ ጥናት) በሚል ስያሜ አሳተመው። የመጨረሻው ጥናት የታተመው በ1930 ነው። የወጣው በአርጀንቲና ኮርዶባ ከተማ ውስጥ ነበር። እነዚህ ካታሎጎች ዋጋማነታቸው እንደተጠበቀ እስከ ዘመናችን ድረስ መዝለቅ ችለዋል።

ዛሬና ነገ

ከአርገላንደርና ከተተኪዎቹ ሥራ በኋላ ይበልጥ የተሻሉ ካታሎጎች ተዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጠፈር ቴሌስኮፖች ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ታይተውና ተሰምተው የማያውቁ ድንቅ የካርታ ሥራዎች ማከናወን ተችሏል። በአሁኑ ጊዜ የስነ ፈለክ አጥኚዎች በሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ በመጠቀም ወደ 15 ሚልዮን የሚጠጉ ከዋክብትን ዝርዝር የያዘ ካታሎግ አዘጋጅተዋል!

የሰማይን ካርታ በመሥራት ረገድ በቅርቡ የታየው እመርታ በአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ሁለት አዳዲስ ካታሎጎች መታተማቸው ነው። እነዚህ ካታሎጎች በሂፓርኮስ ሳተላይት የጠፈር ቴሌስኮፕ አማካኝነት በተ​ካሄዱ ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። የእነዚህ ካታሎጎች ትክክለኛነት እስካሁን ድረስ አቻ አልተገኘለትም። በእነዚህ ካታሎጎች ላይ በመመርኮዝ አዳዲስ የኮከብ አትላሶች ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህ መካከል ሚሌኒየም ስታር አትላስ (የሺህ ዓመት የኮከብ አትላስ) የሚል ስያሜ የተሰጠውና በሦስት ጥራዞች የተዘጋጀው ትልቅ አትላስ ይገኝበታል።

ይህ ርዕስ ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘውን ሰላማዊውን የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እንዲያስታውሱ ያደርጋቸው ይሆናል። (ራእይ 20:​4) በዚያ ዘመን የሰው ልጅ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ትልልቆቹ የኮከብ አትላሶች እንኳ በጥቂቱ ብቻ ሊያሳዩ የቻሉትን ግዙፉን ጽንፈ ዓለም ይበልጥ ማወቅ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ከዋክብት የሚንቀሳቀሱ የሚመስለው መሬት በራሷ እንዝርት ዙሪያ የምትሽከረከር በመሆኗ ሳቢያ እንደሆነ አልተገነዘቡም ነበር። ፀሐይ የምትወጣና የምትጠልቅ የምትመስለውም በዚሁ ምክንያት ነው።

^ አን.9 እነዚህ 48 ህብረ ከዋክብት በሜሶጶጣሚያ፣ በሜዲትራንያን አካባቢና በአውሮፓ ይታወቁ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ህብረ ከዋክብት በስደተኞች አማካኝነት በሰሜን አሜሪካና በአውስትራሊያም ሊታወቁ ችለዋል። ይሁን እንጂ እንደ ቻይናውያንና የሰሜን አሜሪካ ህንዶች ያሉ ሌሎች ሕዝቦች ከዋክብትን የሚከፋፍሏቸው ለየት ባለ መንገድ ነው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአፒያን የኮከብ ቻርት፣ 1540

[ምንጭ]

By permission of the British Library (Maps C.6.d.5.: Apian’s Star Chart)

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ19ኛው መቶ ዘመን በካርታ የተዘጋጀው ደቡባዊው ንፍቀ ሉል

[ምንጭ]

© 1998 Visual Language

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ ዘመናዊ ካርታ ላይ ሠፍሮ የሚታየው የኦርዮን ህብረ ከዋክብት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከገጽ 21-3 ላይ ከበስተጀርባ የሚታየው ፎቶ:- Courtesy of ROE/Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin