በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

“ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።”​—⁠ዕብራውያን 11:​6

እምነት ምንድን ነው? አንዳንዶች እምነት ስለ አምላክ ሕልውና ተጨባጭ ማስረጃ ሳይዙ በአምላክ ላይ ሃይማኖታዊ ትምክህት መጣል እንደሆነ ይናገራሉ። አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኤች ኤል ሜንኬን እምነት “ሊሆን የማይችለው ነገር እንደሚሆን በማሰብ ምክንያታዊ ያልሆነ ትምክህት መጣል” ማለት እንደሆነ አድርጎ ገልጿል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተገለጸው መሠረት እውነተኛ እምነት ነውን? እምነት ምን እንደሆነ በግልጽ መረዳታችን ወሳኝ ነገር ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደተጠቀሰው ‘ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም።’

መጽሐፍ ቅዱስ ‘እምነት ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር እርግጠኛ መሆን’ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 11:​1) ስለዚህ እምነት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተና ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ተጨባጭ ሐቆች ያቀፈ ነው። አምኖ መቀበልን ብቻ ሳይሆን ለማመን የሚያበቁ ምክንያቶችን የሚጠይቅ ነገር ነው።

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ምናልባት “እሱን አምነዋለሁ። ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ነኝ። ችግር ቢያጋጥመኝ እንደሚደርስልኝ አውቃለሁ” በማለት ደፍረህ የምትናገርለት አንድ ጓደኛ ይኖርህ ይሆናል። በአንድና በሁለት ቀን ትውውቅ ብቻ ስለ አንድ ሰው እንዲህ ብለህ እንደማትናገር አያጠራጥርም። አይደለም እንዴ? ሰውዬው እምነት ሊጣልበት የሚችል መሆኑን በተደጋጋሚ ማስመስከር የቻለ መሆን አለበት። ሃይማኖታዊ እምነትን በተመለከተም ጉዳዩ ተመሳሳይ ነው። ጠንካራና አስተማማኝ በሆነ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ተስፋና የጸና እምነት ማፍራት አለበት።

እምነት ወይስ ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል?

ዛሬ በአመዛኙ እንደ እምነት ተደርጎ የሚቆጠረው ነገር በትክክል ሲታይ አሳማኝ መሠረት ወይም ምክንያት ሳይኖር ለማመን ፈቃደኛ ከመሆን፣ ማለትም ሁሉን አሜን ብሎ ከመቀበል ተለይቶ የሚታይ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ጭፍን እምነት የሚገነባው ዘላቂ ባልሆነ ስሜትና በአጉል እምነት ላይ ነው። ይህ እምነት ለመጣል የሚያበቃ አስተማማኝ ማስረጃ ስለሌለው ጥብቅ መሠረት ያለው እምነት አይደለም።

ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል አንድ ሰው በችኮላ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የማይስማማ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ሊያደርገው ይችላል። ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ አሳማኝ መሠረት ስለሌለው እምነት ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ይላል:- “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።” (ምሳሌ 14:​15) ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” ሲል ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 5:​21) መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን አሜን ብሎ መቀበልን አያበረታታም። ከዚህ ይልቅ በማስረጃ የተደገፈ እምነትን ያበረታታል።

እውነተኛን እምነት ጭፍን ከሆነ እምነት መለየት መቻል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። አንድ ግለሰብ ሃይማኖተኛ ሆኖ እያለም እንኳ እውነተኛ እምነት ላይኖረው ይችላል። ጳውሎስ ‘እምነት ለሁሉም እንደማይሆን’ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:​2) ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ያላቸው ሲሆን ይህም በሕይወታቸው ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ።

እውነተኛ እምነት ሰውን ከአምላክ ጋር ያስተሳስራል

እምነት ሰው እርግጠኛ ሆኖና ተማምኖ ከአምላክ ጋር እንዲተሳሰር የሚያደርግ ሰንሰለት ነው ማለት ይችላል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ እምነት ኮትኩተን የምናሳድገው እንጂ አብሮን የሚወለድ ነገር አይደለም። እውነተኛ እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” በማለት ይገልጻል።​—⁠ሮሜ 10:​17

ስለዚህ አምላክንና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸውን ነገሮች ለማወቅ ጊዜ ያስፈልግሃል። ይህ እውቀት ያለ ጥረት የሚገኝ ነገር አይደለም። (ምሳሌ 2:​1-9) መጽሐፍ ቅዱስ ትምክህት የሚጣልበት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምነህ መቀበል እንድትችል መጽሐፉ ምን እንደሚል ለመመርመር ጥረት ማድረግ አለብህ።

ይሁን እንጂ እውነተኛ እምነት እንዲሁ እውቀት ከማካበት ወይም አንድ ነገር እውነት መሆኑን በደፈናው አምኖ ከመቀበል የበለጠ ነገር ያካትታል። የውስጣዊ ግፊት መቀመጫ የሆነውን ልብንም የሚመለከት ነገር ነው። ሮሜ 10:​10 ‘ሰው በልቡ ያምናል’ ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? አምላካዊ በሆኑ ነገሮች ላይ በማሰላሰል አድናቆትህን ስትገነባ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወደ ልብህ ጠልቆ እንዲገባ ታደርጋለህ ማለት ነው። አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች መሠረት በማድረግ ለሥራ ስትነሳሳና የእሱን በረከት ለማግኘትህ ማረጋገጫ ስታገኝ እምነትህ እያደገና ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል።​—⁠2 ተሰሎንቄ 1:​3

እውነተኛ እምነት እንዴት ያለ ውድ ሀብት ነው! አምላክ አካሄዳችንን ለመምራት ባለው ችሎታና የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ባለው ፈቃደኝነት ላይ በመታመን በእሱ ላይ ትምክህት ጥለን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ በመቻላችን እንጠቀማለን። ከዚህ በተጨማሪ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ስለሚያስገኘው አንድ ዘላቂ ጥቅም ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:​16፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እምነት ያላቸው ሰዎች የሚያገኙት የዘላለም ሕይወት ስጦታ ምንኛ አስደናቂ ነው!

አንድ ሰው አምላክ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ለመክፈል በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ማሳደሩ ለሕይወት አዲስ አመለካከት እንዲይዝ ያደርገዋል። ዕብራውያን 11:​6 እውነተኛ እምነት አምላክ ‘ለሚፈልጉት’ ወሮታ ለመክፈል ባለው ችሎታ ላይ ማመንን እንደሚያካትት ይናገራል። ስለዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እውነተኛ እምነት ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል አይደለም። እንዲሁም በደፈናው በአምላክ መኖር ከማመን የበለጠ ነገር ይጨምራል። አምላክ ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ለመክፈል ያለውን ችሎታ አምኖ መቀበልን ያካትታል። በእርግጥ አምላክን ከልብ የማወቅ ፍላጎት አለህ? ፍላጎቱ ካለህ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ቅሰም፤ እምነትህ ወሮታ ያስገኝልሃል።​—⁠ቆላስይስ 1:​9, 10

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Drawings of Albrecht Dürer/Dover Publications, Inc.