በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባድ እክል ቢኖርብኝም አስደሳች ተስፋ አለኝ

ከባድ እክል ቢኖርብኝም አስደሳች ተስፋ አለኝ

ከባድ እክል ቢኖርብኝም አስደሳች ተስፋ አለኝ

ኮንስታንቲን መሮዞፍ እንደተናገረው

ሐምሌ 20, 1936 ስወለድ ከራስ ቅልና ከአከርካሪ በስተቀር ሰውነቴ ውስጥ አንድም የዳበረ አጥንት አልነበረም። የሰውነቴ አፅም ባጠቃላይ ከአንድ ጎልማሳ የጆሮ ልማፅም (cartilage) ብዙም በማይጠነክር ልፍስፍስ በሆነ ልማፅም የተገነባ ነበር። የሰውነቴ ክብደት ግማሽ ኪሎ አይሞላም ነበር። በሕይወት እንዳለሁ የሚጠቁሙት ምልክቶች ደካማ የልብ ምት፣ ስልል ያለ እስትንፋስና ጥቂት እንቅስቃሴዎች ብቻ ነበሩ።

በማዕከላዊ ሩሲያ፣ ኡልያኖፍስክ ኦብላስት ውስጥ በምትገኝ ሳራ በምትባል መንደር ውስጥ ይኖር የነበረ ዘጠኝ ልጆች ያሉት የአንድ ቤተሰብ ሰባተኛ ልጅ ነኝ። ሦስት ሳምንት ሲሞላኝ ወላጆቼ እኔን ለማስጠመቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘውኝ ሄዱ። ቄሱ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ይሞታል ብለው ስላሰቡ በችኮላ ውኃ ረጩኝና በተቻለ ፍጥነት ወደ ቤት እንዲወስዱኝ ለወላጆቼ ነገሯቸው።

በጥር 1937 ወላጆቼ የሩስያ ሪፑብሊክ በሆነችው በታታርስታን ዋና ከተማ በካዛን የሚገኙ አንዳንድ የሕክምና ስፔሻሊስቶች እንዲመረምሩኝ ወደዚያ ወሰዱኝ። በዚህ ጊዜ “ማማ፣” “ፓፓ” እና “ባቡሽካ” (አያቴ) ማለት እችል የነበረ ሲሆን የወንድሞቼንም ስም እጠራ ነበር። ዶክተሮቹ ከመረመሩኝ በኋላ ለወላጆቼ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደምሞት ነገሯቸው። ለሕክምና ተማሪዎች መማሪያ ሆኜ እንዳገለግል ሕይወቴ እንዲያልፍ ተደርጎ በግልጽ በሚያሳይ ዕቃ ውስጥ እንድቀመጥ ሐሳብ አቀረቡ። ውድ ወላጆቼ ያላንዳች ማወላወል እምቢተኛ በመሆናቸው ምንኛ አመስጋኝ ነኝ!

በስቃይ የተሞላ የልጅነት ሕይወት

እስከማስታውሰው ድረስ ማቆሚያ በሌለው የሕመም ስሜት እሰቃይ ነበር። ሆኖም ልጅ በነበርኩበት ጊዜም አዎንታዊ አስተሳሰብ ለመያዝ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ለመሳቅና በሕይወት ለመደሰት እጥር ነበር። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ነው ይዤ የኖርኩት። ቀስ በቀስ አፅሜ እየጠነከረ ስለሄደ መቀመጥና በመጠኑ መዳህ ቻልኩ። ጤናማ ልጆች ያላቸው ዓይነት እድገት ያልነበረኝ ከመሆኑም በላይ የሰውነቴ ቅርጽ ክፉኛ ተወለጋግዶ ነበር። ሆኖም ጥሩ ችሎታ ያለኝ ተማሪ የነበርኩ ሲሆን በአምስት ዓመቴ ማንበብና መጻፍ እችል ነበር።

በግንቦት 1941 እናቴ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰደችኝ። በቦታው የተወሰኑ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ሁሉም ተንበርክከው እየጸለዩ ነበር። አንዲት ሴት አገልጋይ ወደ እናቴ መጣችና ለምን እንዳልተንበረከከች ጠየቀቻት። እናቴ እኔን ስታሳያት ቄሱን ለማነጋገር ሄደች። አገልጋይዋ ተመልሳ መጥታ ወደ መውጫው ወሰደችንና ከበሩ ውጪ አስቀምጣኝ ብቻዋን እንድትገባ ለእናቴ ነገረቻት። ወላጆቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት “እርኩስ በሆነው አካል” የተሰጠኋቸው እንደሆንኩ አድርጋ ተናገረች። እናቴ እያለቀሰች ወደ ቤት ተመለሰች። ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ይከነክነኝ ነበር። ‘ይህ “እርኩስ የሆነው አካል” ማን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር።

በ1948 የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ እማዬ ከቤታችን ወደ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወዳለው ቹቫሽ ሪፑብሊክ ውስጥ ወደሚገኘው ሜሬንኪ የተባለ መንደር ይዛኝ ሄደች። በዚያ ሥፍራ ጠበል ይገኝ የነበረ ሲሆን እማዬ ውኃው ሊያድነው ይችላል የሚል ተስፋ ነበራት። መዳን እንድችል ቄሶቹ ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ለሦስት ቀን ምግብ አለመመገብን የሚጠይቅ ነበር። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከሚሰጠው ቁርባን መካፈል ነበረብኝ። ምንም እንኳ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ያን ያህል እምነት ባይኖረኝም ቅድመ ሁኔታዎቹን ለማሟላት ተስማማሁ። ጉዞው ረጅምና አድካሚ ቢሆንብኝም የመልክዓ ምድሩን ውበት በማየት ራሴን አስጠምጄ በጽናት ተወጣሁት።

ቤተ ክርስቲያኑ በሕዝብ ተሞልቶ ነበር። እማዬ አዝላኝ በሕዝቡ መካከል ስታልፍ አንዲት አሮጊት ሴት ከረሜላ ሰጡኝ። ከረሜላውን ተቀብዬ ኪሴ ውስጥ ከተትኩት። ቁርባን የምወስድበት ተራዬ ሲደርስ አሮጊቷ “አባ፣ ለልጁ ቁርባን እንዳይሰጡት! ከጥቂት ጊዜ በፊት ከረሜላ በልቷል!” ሲሉ ጮክ ብለው ተናገሩ። ከረሜላው ኪሴ ውስጥ መሆኑን ብነግራቸውም ቄሱ “አንት ዓይን አውጣ ጎዶሎ! ብለህ ብለህ ደግሞ ትዋሻለህ? ከቤተ ክርስቲያኑ አስወጡት!” ሲሉ ጮሁብኝ። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ቀን አንድ ሌላ ቄስ የቁርባን ሥነ ሥርዓቱን ያከናወኑ ሲሆን “በተአምራዊው” ውኃም አጠቡኝ። ሆኖም አንድም ተአምር አልተሠራም። የነበሩብኝ እክሎች አልተወገዱም።

በእውቀት መስክ ያከናወንኳቸው ነገሮች

ምንም እንኳ ከባድ የአካል ጉዳተኛ ብሆንም በአሥራዎቹ እድሜዬ በርካታ ትምህርት ነክና ምሁራዊ ግቦችን ተከታትያለሁ። በ1956 የኮምሶሞል (የወጣት ኮሚኒስቶች ማኅበር) አባል ሆንኩና ከጊዜ በኋላ የኮምሶሞልን ታሪክ ለወጣቶች ማስተማር ጀመርኩ። በአካል ጉዳተኞች መኖሪያ በሚገኘው የቤትና የባሕል ኮሚሽን አባል ነበርኩ። እንዲሁም በዚያ የራዲዮ ዲሬክተርና አስተዋዋቂ ሆኜ ሠርቻለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ማየት ለተሳናቸው የተዘጋጁ የቴፕ ክሮችን የያዘ የአንድ ተንቀሳቃሽ ላይብረሪ ኃላፊ ነበርኩ። እንዲሁም የአልኮል መጠጦችን ያላግባብ የመጠጣት ልማድን ለመዋጋት የተቋቋመው የዳኞች ኮሚሽን አባል እንድሆን ተመርጬ ነበር። በአማተር የአርቲስቶች ክለብ እሳተፍ የነበረ ሲሆን በርካታ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እጫወት፣ እዘፍንም ነበር።

በአካል ጉዳተኞች መኖሪያ

በ1957 ሃያ አንድ ዓመት ሲሞላኝ ያሉብኝ አካላዊ ችግሮች ለአካል ጉዳተኞች እንክብካቤ ወደሚደረግበት መኖሪያ እንድገባ አስገደዱኝ። ሆኖም እጅ ላለመስጠት ቆርጬ ነበር። ጥቅምት 1963 በሞስኮ ወደሚገኘው ሰው ሠራሽ የአካል ክፍሎች ወደሚዘጋጁበት የሳይንስ ምርምር ተቋም ሄድኩ። እዚያም እግሮቼን ለማስተካከል በድምሩ 18 ቀዶ ሕክምናዎች ተደረጉልኝ።

በመጀመሪያ እግሮቼ ተዘረጉ። ከዚያም ከስምንት ቀናት በኋላ ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ። ከዚያም እስከሚቀጥለው ቀዶ ሕክምና ድረስ እግሮቼ ቦታቸውን እንዳይለቁ ለማድረግ ጀሶ ታሰረልኝ። ነርሷ ስቃዬን እያየች ታለቅስ ነበር።

ከዚያ በኋላ በነበሩት አራት ወራት ውስጥ በምርኩዝ መራመድ ቻልኩ። ምርኩዝ ተደግፌ ቁመቴ 110 ሴንቲ ሜትር እስኪጠጋ ድረስ ቀጥ ብዬ መቆም እችል ነበር። የሰውነቴ ክብደት ከ25 ኪሎ ግራም እምብዛም አይበልጥም ነበር። በደንብ አድርጌ በምርኩዝ መራመድ ከቻልኩ በኋላ በ1964 ወደ አካል ጉዳተኞች መኖሪያ ተመለስኩ። የሚያሳዝነው ግን ደካማ የሆኑት የእግሬ አጥንቶች የሰውነቴን ክብደት መሸከም ስላቃታቸው ብዙም ሳይቆይ እንደገና በእንብርክክ አሊያም በተሽከርካሪ ወንበር እርዳታ ለመንቀሳቀስ ተገደድኩ። እስካሁን ድረስ በአብዛኛው ከቦታ ቦታ የምንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ነው።

በድጋሚ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ አላውቅም። እንዲህ ያለ እክል ይዤ የተወለድኩት “እርኩስ በሆነው አካል” እንደሆነ ተደርጎ የተነገረኝ ነገር አሁንም እረፍት ይነሳኝ ነበር። አባቴንና እናቴን በጣም እወዳቸዋለሁ፤ ለደረሰብኝ እክል ተጠያቂዎቹ እነሱና አምላክ ናቸው የተባለው ግን ፈጽሞ ሊዋጥልኝ አልቻለም። አሳዛኝ ሁኔታ ቢገጥመኝም ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ጥሬአለሁ። ለሌሎች ጥሩ ነገር የመሥራት ፍላጎት ነበረኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔም ጭምር እንዲህ ማድረግ እንደምችል ለራሴ ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር።

ራስን ችሎ መኖር

በ1970 ከልጅነቷ አንስቶ ግማሽ አካሏ ሽባ የሆነውን ሊዲያን አገባሁ። ለ15 ዓመታት የኖርንበት አንድ ትንሽ ቤት አገኘን። በዚህ ጊዜ ሁለታችንም መተዳደሪያ ለማግኘት እንሠራ ነበር። የእጅ ሰዓትና ሌሎች ትናንሽ የሆኑና አነስተኛ ማስተካከያ ማድረግ የሚጠይቁ ዕቃዎችን ማደስ ተማርኩ።

ለተወሰነ ጊዜ በርከት ያሉ ጠቃሚ ነገሮችን በሚያከናውንልኝ የሰለጠነ ውሻ ተጠቅሜአለሁ። እንዲያውም እኔና አንድ የውሻ አሰልጣኝ በውሻው አካል ላይ የሚታሰር ዕቃ ለመጎተት የሚያገለግል ለየት ያለ ጠፍር አዘጋጅተን ነበር። ሁለት ውሻዎች የነበሩኝ ሲሆን አንደኛው ቩልካን ሌላዋ ደግሞ ፓልማ ይባሉ ነበር። ፓልማ ለብዙ ዓመታት ታማኝ ጓደኛዬ ነበረች። የገበያ አዳራሽ ውስጥ የታሸጉ ምግቦችን እያነሳች ታመጣልኝ ነበር። የማያስደስታት ነገር ቢኖር ሒሳብ ለመክፈል ተሰልፈን ተራ የምንጠብቅበት ጊዜ ነበር። የኪስ ቦርሳዬን በአፍዋ ትይዝ የነበረ ሲሆን አንገቷ ላይ ዕቃ መያዣ ቦርሳዬን የምትሸከምበት አንዲት ትንሽ ማንጠልጠያ ነበራት።

በ1973 እናቴ በጠና ታመመች። ሁልጊዜ እቤት እውል ስለነበረ እኔና ባለቤቴ ከእኛ ጋር እንድትኖር ለማድረግ ወሰንን። በዚህ ጊዜ አባቴና አምስት ወንድሞቼ በሕይወት አልነበሩም፤ ሌሎች ሦስት ወንድሞቼና እህቶቼ ደግሞ የሚኖሩት በሌሎች የሩስያ ክፍሎች ነበር። እናቴ ከእኛ ጋር በተቀመጠችባቸው ጊዜያት ላደርግላት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥሬአለሁ። በመጨረሻ በ85 ዓመቷ ሞተች።

በ1978 ራሴ የምጠቀምበት ተሽከርካሪ ለመሥራት ወሰንኩ። በርከት ያሉ የሙከራ ተሽከርካሪዎች ስሠራ ከቆየሁ በኋላ አንድ የሚስማማኝ ተሽከርካሪ ለመሥራት ቻልኩ። በአካባቢው ያለው የተሽከርካሪዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን የማሽከርከር ፈተና እንድፈተንና ተሽከርካሪዬን እንዳስመዘግብ ፈቃድ ሰጠኝ። ተሽከርካሪውን ኦሳ (ተርብ) በማለት ሰየምኩት። እኔና ባለቤቴ እስከ 300 ኪሎ ግራም ድረስ መጫን የሚችል ከተሽከርካሪው ጋር የሚገጠም አንድ ትንሽ ተሳቢ ሠራን። ሁለታችንም በዚህ ተሽከርካሪ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና ዕቃችንን ይዘን መጓዝ ችለን ነበር። እስከ 1985 ድረስ በዚህ በሞተር በሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ተጠቅመናል።

በዚህ ጊዜ ግራ ዓይኔ ማየት የተሳነው ሲሆን ቀኝ ዓይኔ ደግሞ እየደከመ መጣ። ከዚያም ሊዲያ የልብ በሽታ ያዛት። በገጠመን የአቅም ውስንነት የተነሳ ግንቦት 1985 ላይ በዲሚትሮፍግራት ከተማ ወደሚገኘው የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ለመግባት ተገደድን።

አሁን ሕይወቴ እጅግ አስደሳች የሆነበት ምክንያት

በ1990 የበጋ ወራት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ወደምንኖርበት የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ መጡ። የሚሰጡት ትምህርት በጣም ማረከኝ። በዮሐንስ ወንጌል ላይ ዓይነ ሥውር ሆኖ ስለተወለደው ሰው የሚናገረውን ምንባብ አሳዩኝ። ሰውየውን በተመለከተ ኢየሱስ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም” ብሏል። (ዮሐንስ 9:​1-3) በቅድመ አያታችን በአዳም ምክንያት ኃጢአ​ትና በሽታ የወረስን መሆናችንን አስረዱኝ።​—⁠ሮሜ 5:​12

ሆኖም ከሁሉም በላይ ያስደነቀኝ በመጨረሻ አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ስትመለስ ሕይወት የሚያገኙትን ሁሉ እንደሚፈውሳቸው ማወቄ ነበር። (መዝሙር 37:​11, 29፤ ሉቃስ 23:​43፤ ራእይ 21:​3, 4) ጉንጬ ላይ የደስታ እንባ ኩልል ብሎ ወረደ፤ “እውነትን አገኘሁ!” ስል በሹክሹክታ ድምፅ ተናገርኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለአንድ ዓመት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ አጠናሁና በ1991 ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።

ምንም እንኳ ይሖዋን ለማገልገልና ስለ አስደናቂ ዓላማዎቹ ለመስበክ ጠንካራ ፍላጎት ቢያድርብኝም በርካታ እክሎች ተደቅነውብኝ ነበር። ከዚህ ቀደም ከቦታ ቦታ እንድንቀሳቀስ የሚያስገድድ ጉዳይ እምብዛም አያጋጥመኝም ነበር። አሁን ግን እምነቴን ለሌሎች ለማካፈል ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ያስፈልገኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበኩበት የአገልግሎት ክልል ከ300 ሰዎች በላይ የሚገኙበት የአካል ጉዳተኞች መኖሪያችን ነበር። በተቻለ መጠን ከብዙ ሰዎች ጋር መገናኘት እንድችል ለቤት ውስጥ ጉዳዮች አገልግሎት በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ እንዲመድቡኝ ጠየቅሁ።

በየዕለቱ ጠዋት የሥራ ቦታዬ ላይ ተቀምጬ ኃላፊነቴን እወጣ ነበር። ከሥራዬ ጋር በተያያዘ ብዙ አዳዲስ ጓደኞች ያፈራሁ ሲሆን ከእነሱም ጋር በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አስደሳች ውይይቶች አድርገናል። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲገነዘቡ የረዷቸውን መጻሕፍትና መጽሔቶች ወስደዋል። አብዛኛውን ጊዜ ለአንዳንድ ጉዳይ ለሚመጡ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች አነብላቸው ነበር። እኔና ባለቤቴ በምንኖርበት ክፍል ውስጥ በምሳ ሰዓት በአብዛኛው ብዙ ሰዎች ስለሚኖሩ አንዳንድ ጊዜ ሌሎች መግቢያ ያጣሉ።

በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ብዙ ረድተውኛል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚያመጡልኝ ሲሆን እኔና ባለቤቴንም ለመጠየቅ ይመጣሉ። በተጨማሪም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ ወደ መንግሥት አዳራሽ በማድረስ ይረዱኛል። አንድ የይሖዋ ምሥክር እኔን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ሲል የጎን መቀመጫ ያለው ሞተር ብስክሌት ገዝቷል። መኪና ያላቸው ሌሎች ደግሞ ቀዝቃዛ በሆነው የክረምት ወቅት በደስታ እየመጡ ይወስዱኛል።

እንዲህ ዓይነቱን ፍቅራዊ እንክብካቤ በማግኘቴ ከደርዘን በላይ በሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጁአቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ማለትም ትምህርት በሚሰጥባቸው ሴሚናሮች ላይ መገኘት ችያለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁት ሐምሌ 1993 ሞስኮ ውስጥ በተካሄደው ትልቅ ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሲሆን በዚያም ከ30 በላይ ከሚሆኑ አገሮች የመጡ 23, 743 ተሰብሳቢዎች ነበሩ። እኔ በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ 1, 000 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ነበረብኝ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያደርጉት አንድም የአውራጃ ስብሰባ አምልጦኝ አያውቅም።

እኛ በምንኖርበት የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ያለው የአስተዳደር ቢሮ ለእኔ ጥልቅ አክብሮት አለው፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ። ለ30 ዓመታት አብራኝ በስምምነት የኖረችው ባለቤቴ ሊዲያም ምንም እንኳ ሃይማኖታዊ አመለካከቶቼን ባትጋራም ደጋፊዬና ረዳቴ ነች። ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋ ብርቱ በሆነው ክንዱ ይደግፈኛል፤ አስደናቂ በረከቶችንም ሰጥቶኛል። በቅርቡ ማለትም በመስከረም 1, 1997 አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኜ ተሹሜያለሁ።

በሕይወቴ ዘመን የልቤ ምት አቁሞ ለሕልፈተ ሕይወት ልዳረግባቸው የምችል በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይህ ሳይከሰት በመቅረቱና የሕይወት ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ማወቅና ማፍቀር በመቻሌ አሁን ምንኛ ደስተኛ ነኝ! የልቤ ምት እስካላቆመ ድረስ በዓለም ዙሪያ ካሉት መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር እሱን በማገልገል የመቀጠል ፍላጎት አለኝ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከሊዲያ ጋር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ቤታችን ውስጥ አንድ ተማሪ ሳስጠና