በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ውጥረት ውስጥ መግባት

“ግማሽ የሚሆኑት ካናዳውያን ማለት ይቻላል፣ ሥራቸውንና የቤተሰብ ሕይወታቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጎን ለጎን ለማስኬድ በሚያደርጉት ጥረት ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ ውጥረት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ” ሲል ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። “ይህ ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጥፍ ጨምሯል።” ሊጨምር የቻለው ለምንድን ነው? የካናዳ የኮንፈረንስ ቦርድ ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው የቤተሰብ አባሎቻቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው ካናዳውያን ሠራተኞች ቁጥር ጨምሯል። ብዙዎቹ በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው ላይ ልጅ የሚወልዱ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ “ልጆቻቸውንና ወላጆቻቸውን በአንድ ላይ የመንከባከብ” ፈታኝ ሁኔታ ይገጥማቸዋል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት በሥራቸው የሚረኩ ቢሆንም የቤተሰብ ኃላፊነታቸውና ሥራቸው የሚጠይቁባቸውን ነገሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማሟላት በሚቸገሩበት ጊዜ “በመጀመሪያ የሚወስዱት እርምጃ የእንቅልፍ ሰዓታቸውን ጨምሮ የራሳቸውን ጊዜ መሥዋዕት ማድረግ ነው” ይላል ዘገባው። “በዚህም ሳቢያ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ፤ ጤንነታቸውም ይቃወሳል” ሲል የኮንፈረንስ ቦርዱ ገልጿል።

የኮላ ሱሰኞች?

ሜክሲኮያውያን በየዓመቱ በአማካይ 160 ሊትር የኮላ መጠጦች ይጠጣሉ ሲል ሜክሲካን አሶስዬሽን ኦቭ ስተዲስ ፎር ኮንስዩመር ዲፌንስ ዘግቧል። በየዓመቱ ለኮላ መጠጦች የሚውለው ገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ለሆኑት አሥር መሠረታዊ ምግቦች በጠቅላላ ከሚውለው ገንዘብ ይበልጣል። አንዳንዶች በሜክሲኮ ውስጥ ለሚታየው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ እነዚህን ለስላሳ መጠጦች በከፍተኛ መጠን የሚወስዱ መሆናቸው ነው። ከኮላ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ካልሲየምና ብረት ከሰውነታችን ጋር እንዳይዋሃድ እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ኮላ ከመጠጣት ጋር ዝምድና አላቸው ተብለው የሚታሰቡት ሌሎች ችግሮች ደግሞ ለኩላሊት ጠጠር በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጥን፣ የጥርስ መቦርቦርን፣ ከመጠን በላይ መወፈርንና ከፍተኛ የደም ግፊትን እንዲሁም እንቅልፍጦትን፣ የጨጓራ አልሰርንና ጭንቀትን ይጨምራሉ። ‘በፊት በፊት “አፍቃሬ በቆሎ” እንባል ነበር’ ይላል ኮንስዩመርስ ጋይድ ማጋዚን፣ ‘ዛሬ ዛሬ ግን “አፍቃሬ ኮላ” ሆነናል።’

ቲማቲምና ካንሠር

በቅርቡ በአሜሪካ የካንሠር ምርምር ማኅበር የተካሄዱት ጥናቶች ቲማቲም የፕሮስቴት ካንሠርን እድገት ሊገታ እንደሚችል አመልክተዋል። ቲማቲምን ቀላ ያለ ቀለም የሚያላብሰው ላይኮፒን የተባለው ንጥረ ነገር ካንሠር የሚያስከትሉ የፕሮስቴት እብጠቶችን (tumors) መጠንና ካንሰሩ ወደ ሌሎቹ የሰውነት ህብረህዋሳት ሊዛመት የሚችልበትን አጋጣሚ ሊቀንስ ይችላል። በዩ ኤስ ብሔራዊ የካንሠር ተቋም ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት “ቲማቲምና የቲማቲም ውጤቶች በሙሉ የፕሮስቴት ካንሠርን ብቻ ሳይሆን የጣፊያ፣ የሳምባና የደንዳኔ ካንሠርንም በመከላከል ረገድ ጥሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ሲል ገልጿል።”

ለአደጋ የሚያጋልጥ የመድኃኒት ትእዛዝ

“ባለፈው ዓመት ጀርመን ውስጥ በመድኃኒቶች ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትራፊክ አደጋዎች ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በልጦ ተገኝቷል” ሲል ሽቱትጋርተ ናክሪክተን የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። በ1998 በስህተት በታዘዙ መድኃኒቶች ሳቢያ ወደ 25, 000 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ተነግሯል። ይህ በዚያው ዓመት ውስጥ በትራፊክ አደጋዎች ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ይበልጣል። ያለ ሐኪም ትእዛዝና ክትትል መድኃኒት መውሰድ በዚህ ረገድ የበኩሉን ሚና የተጫወተ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ዶክተሮች ስለ መድኃኒቶችና መድኃኒቶቹ ስለሚያስከትሉት ውጤት በቂ መረጃና ሥልጠና ያላገኙ መሆናቸው ነው። የፋርማኮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ኢንጎልፍ ካስኮርቢ በአንድ ግምታዊ አኃዝ መሠረት “ምርምሩና ሥልጠናው በተሟላ መንገድ ቢሠራበት በጀርመን ውስጥ በየዓመቱ የ10, 000 ሰዎችን ሞትና በሰዎች ላይ የሚደርሱትን ወደ 250, 000 የሚጠጉ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች ማስወገድ ይቻል ነበር” ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል።

በተመሳሳይም ስዮንስ ኤ አቨኒር የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ እንደዘገበው በቅርቡ በፈረንሳይ በተካሄደ ጥናት ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ላላቸው ሰዎች ከታዘዙት 150, 000 መድኃኒቶች መካከል 10, 700 ገደማ የሚሆኑት አንድም የተሳሳቱ ናቸው አለዚያም ምንም ጥቅም የሌላቸው ናቸው። ከታዘዙት መድኃኒቶች መካከል ከሀምሳው አንዱ ማለት ይቻላል፣ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር አፀግብሮት በመፍጠር ወይም ሌላ ዓይነት ችግር በማምጣት አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችል ሆኖ ተገኝቷል። ፈረንሳይ ውስጥ አረጋውያን የተሰጣቸው መድኃኒት ሳይስማማቸው በመቅረቱ ምክንያት በየዓመቱ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ቀናት ሆስፒታል ውስጥ ለማሳለፍ እንደሚገደዱ ይገመታል።

“የጽድቅ ጦርነት”?

“የዩጎዝላቪያ ጦርነት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ‘የጽድቅ ጦርነት’ በሚለው አስተሳሰብ ፍቺ ላይ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል” ይላል ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ። የጽድቅ ጦርነት (ዩስ አድ ቤሉም ) የሚለው አስተሳሰብ በአምስተኛው መቶ ዘመን ይኖር ከነበረው ከኦውግስቲን ዘመን አንስቶ የኖረ አስተሳሰብ ነው። ለ ሞንድ በሚለው መሠረት ከጊዜ በኋላ ቶማስ አክዋይነስ የተባለ የካቶሊክ ፈላስፋ እንዳስቀመጠው ለእንዲህ ዓይነቱ ጦርነት የሚቀርቡት “ሥነ ምግባራዊ” መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው:- “ተቀባይነት ያለው ምክንያት” መኖር አለበት፣ ጦርነቱ “የመጨረሻ አማራጭ” መሆን አለበት፣ ጦርነቱን የሚያውጀው ወገን “ሕጋዊ ሥልጣን” ያለው መሆን አለበት፣ እንዲሁም “የጦር መሣሪያዎችን የመ​ጠቀሙ ሂደት መወገድ ካለበት ችግር የበለጠ ጉዳትና ዝብርቅ የሚያስከትል መሆን [የለበትም]።” በ17ኛው መቶ ዘመን የታከለው ሌላው ቅድመ ሁኔታ “ስኬታማ መሆን የሚቻልበት ዕድል ምን ያህል ነው” የሚለው ጉዳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት “ቅዱስ” ጦርነት የሚለውን አስተሳሰብ እርግፍ አድርገው የተዉት ቢሆንም እንደ “ጽድቅ ጦርነት” መታየት ያለበት ምን ዓይነት ጦርነት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ መሟገታቸውን ቀጥለዋል።

ወሲብ የሚፈጽሙ የብራዚል ወጣቶች

በብራዚል “33 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶችና 64 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ወንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ የፈጸሙት ከ14 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ነው” ሲል ኦ ኤስታዶ ደ ሳኦ ፓውሎ ዘግቧል። በተጨማሪም ከ15 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል ላይ እያሉ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም የሚጀምሩ ብራዚላውያን ልጃገረዶች ቁጥር በአሥር ዓመት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል። የህዝበ ነክ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ኤሊዛቤት ፌራስ እንዳሉት ከሆነ “ለወሲብ ያለው አመለካከት በእጅጉ ተለውጧል።” ለምሳሌ ያህል አንድ ሌላ ጥናት እንዳመለከተው በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ብራዚላውያን መካከል 18 በመቶዎቹ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ልጅ አላቸው አለዚያም ጸንሰዋል።

የምትታከምበት ሆስፒታል ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

“በአየርላንድ ሆስፒታል ውስጥ ታካሚዎች በኢንፌክሽን የመያዛቸው አጋጣሚ ከአንድ አሥረኛ በላይ ነው” ይላል ዘ አይሪሽ ታይምስ ያወጣው ዘገባ። ሆስፒታል አኳየርድ ኢንፌክሽን (ኤች ኤ አይ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የጤና እክል በሆስፒታል ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቶ ተጨማሪ ሕክምና መውሰድ የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪም እያንዳንዱ ታካሚ በአንድ የኤች ኤ አይ ክስተት በአማካይ 2, 200 ዶላር ሊያወጣ የሚችል ሲሆን ኢንፌክሽኑ ከዘውረ ደም ጋር የተያያዘ ከሆነ በአማካይ 11 ተጨማሪ ቀናት በሆስፒታል መተኛት ሊጠይቅበት ይችላል። ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑት ደግሞ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ከበርካታ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ጋር እየተላመዱ በመጡት ሚክሮቦች” አማካኝነት የሚከሰቱት ኢንፌክሽኖች ናቸው ይላል ጋዜጣው። ለኤች ኤ አይ ይበልጥ የተጋለጡት “አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ በሆስፒታል ለረጅም ጊዜያት የሚቆዩ፣ [እና] እንደ ልብ በሽታ ወይም ሥር የሰደደ ብሮንካይተስ ያሉ ከባድ ችግሮች ያሉባቸው” ናቸው።

በቂ እንቅልፍ ማግኘት?

“ዘወትር ቀን ቀን ማሸለብ የሚፈልጉ፣ በስብሰባ ጊዜያት የሚያንቀላፉ ወይም ሐሳባቸውን ማሰባሰብ የሚቸገሩ” ሰዎች ሌሊት ሌሊት በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች ናቸው ይላል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ። አብዛኞቹ ሰዎች ቀን ቀን በጥሩ ሁኔታ ተግባራቸውን ማከናወን እንዲችሉ በእያንዳንዱ ሌሊት ከሰባት እስከ ዘጠኝ የሚያክል ሰዓት እንቅልፍ መተኛት አለባቸው። በቂ እንቅልፍ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ጠበብት የሰጧቸው አንዳንድ ሐሳቦች ቀጥሎ ቀርበዋል:- ለእንቅልፍህ ቅድሚያ ስጥ። ከመተኛትህ በፊት ራስህን ዘና አድርግ። ወጣ ብሎ በእግር መንሸራሸር ሊረዳ የሚችል ቢሆንም ከመተኛትህ በፊት ባሉት ሦስት ሰዓታት ውስጥ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት የለብህም። በየዕለቱ የምትተኛበትና ከእንቅልፍ የምትነሳበት ሰዓት አንድ ዓይነት መሆን አለበት። ሌሊት ከነቃህ ጭንቀት ውስጥ ከመግባት ወይም አንዳንድ ችግሮችን ከማብሰልሰል ይልቅ ደስ የሚሉ ነገሮችን ለማሰብ ሞክር። ከግማሽ ሰዓትም በኋላ መልሶ እንቅልፍ ካልወሰደህ ተነስቶ ማንበብን የመሰሉ ዘና የሚያደርጉ ነገሮችን አከናውን። ልትተኛ ስትል ብዙ አትብላ እንዲሁም ብዙ አትጠጣ። እርቦህም መተኛት የለብህም።

ሲኦልን በተመለከተ የተደረገ የአመለካከት ለውጥ

ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኦል የክፉ ሰዎች ነፍሳት ለዘላለም የሚሰቃዩበት ስፍራ ነው ብላ ስታስተምር ቆይታለች። አሁን ግን ይህ አመለካከት የተለወጠ ይመስላል። ሊቀ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል ሲኦል “አምላክ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች በአሁኑ ሕይወታቸው በሚኖራቸው አመለካከት ሳቢያ የሚከሰት ሁኔታ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ ጠቅሶ ዘግቧል። “ሲኦል አንድን ቦታ የሚያመለክት ሳይሆን” አሉ ሊቀ ጳጳሳቱ፣ “መርጠውና ሆን ብለው ራሳቸውን የሕይወት ሁሉና የደስታ ምንጭ ከሆነው አምላክ የለዩ ሰዎችን ሁኔታ የሚያመለክት ነው።” በመሆኑም “ዘላለማዊ ኩነኔ” የአምላክ ሥራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “[ለአምላክ] ፍቅር ምላሽ ሳይሰጥ የሚቀረው ፍጡሩ ነው” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

ጤንነት ለማግኘት በእግር መሄድ

በእግር መሄድ ውፍረት ለመቀነስና ውጥረትን ለማርገብ የሚረዳህ ከመሆኑም በተጨማሪ “የደም ግፊትንና ለልብ ድካም የምትጋለጥበትን አጋጣሚ” ለመቀነስ ይረዳል ሲል የቶሮንቶው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል ዘግቧል። ጤንነትን ለመጠበቅ ቋሚ የሆነ ጊዜ መድቦ በእግር መጓዝ ያስፈልጋል። ምን ያህል ጊዜ መመደብ ያስፈልግ ይሆን? “ካናዳስ ፊዚካል አክቲቪቲ ጋይድ ቱ ሄልዚ አክቲቭ ሊቪንግ እንዳለው ከሆነ ልከኛ በሆነ እርምጃ የምትጓዝ ከሆነ በቀን ውስጥ በጠቅላላ 60 ደቂቃ መጓዝ ያለብህ ሲሆን እያንዳንዱ የጊዜ ርዝመት ቢያንስ ቢያንስ ከ10 ደቂቃ ያላነሰ መሆን አለበት።” በቀን ከ30 እስከ 60 ደቂቃ ፈጠን ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም ብስክሌት መንዳት አለዚያም ደግሞ በየዕለቱ ከ20 እስከ 30 ደቂቃ በዝግታ መሮጥም ጤንነትህን ለመጠበቅ ይረዳሃል። አየር የሚያስገቡ፣ እግርን በጥሩ ሁኔታ የሚደግፉና ጣት የማይዙ እንዲሁም ደረቅ ያልሆኑ ሶሎችና ምቹ ገበሮች ያሏቸው ቀላል ጫማዎች ማድረጉ ጠቃሚ እንደሆነ ግሎብ ሳይጠቁም አላለፈም።

ቅድመ ማስጠንቀቂያ

“ዓለማችን ‘ታላላቅ የተፈጥሮ አደጋዎች’ የሚከሰቱበት አሥርተ ዓመት ከፊቷ ሊጠብቃት ይችላል” ሲል የለንደኑን ፋይናንሻል ታይምስ በመጥቀስ ዎርልድ ፕሬስ ሪቪው ዘግቧል። የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበራት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን እንደ ኃይለኛ ዓውሎ ነፋሳትና የምድር ነውጥ ያሉትን የተፈጥሮ አደጋዎች በመጥቀስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን አስታውቋል። “በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት 50 የዓለማችን ከተሞች መካከል 40ዎቹ በምድር ነውጥ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከዓለም ሕዝብ መካከል ግማሽ ያህሉ እየጨመረ ለሚሄድ የባሕር ወለል በተጋለጡ የባሕር ዳርቻ ክልሎች የሚኖር ነው” ይላል መጽሔቱ። ሌላው አሳሳቢ ነገር አደጋዎች እየጨመሩ ሲሄዱ በብዙ አገሮች ውስጥ መንግሥት ለድንገተኛ አደጋ እርዳታ የሚመድበው ገንዘብ እያሽቆለቆለ መሄዱ ነው።