በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊዎቹ ባሪያዎች እነማን ናቸው?

ዘመናዊዎቹ ባሪያዎች እነማን ናቸው?

ዘመናዊዎቹ ባሪያዎች እነማን ናቸው?

እስቲ ብዛታቸውን እንኳ አስበው። ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆነ ከ200 እስከ 250 ሚልዮን የሚገመቱ ልጆች ከእንቅልፍ ሰዓታቸው ውጪ ያለውን አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ተጠምደው ያሳልፋሉ። በ1995 እና በ1996 ብቻ እንኳ ገና የሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆች ጨምሮ ሩብ ሚልዮን የሚሆኑ ልጆች ወደ ትጥቅ ትግል እንዲሠማሩ የተደረገ ሲሆን አንዳንዶቹ በዚህ መንገድ የጦርነት ባሪያዎች ሆነዋል። በየዓመቱ ባሪያዎች ሆነው የሚሸጡት ሴቶችና ልጆች ቁጥር ከአንድ ሚልዮን እንደሚልቅ ይገመታል።

ሆኖም አኃዝ ብቻውን እነዚህ ግለሰቦች የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ ሊገልጽ አይችልም። ለምሳሌ ያህል ደራሲዋ ኤሊኖር በርኬት በአንድ የሰሜን አፍሪካ አገር ፋትማ የተባለች ከጨካኝ ጌታዋ ማምለጥ የቻለች አንዲት ወጣት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ በርኬት ፋትማን ካነጋገሯት በኋላ “በአመለካከት ረገድ ለዘላለም ባሪያ ሆና እንደምትቀር” ተገንዝበዋል። ፋትማ ስለተሻለ የወደፊት ጊዜ ማለም እንኳ ትችል ይሆን? “ለነገ ማቀድ አትችልም” ይላሉ በርኬት። “የወደፊቱ ጊዜ የሚባለው ነገር ፈጽሞ ከማይጨበጡላት በርካታ ጽንሰ ሐሳቦች አንዱ ነው።”

አዎን፣ በዚህች በአሁኗ ሰዓት እንኳ እንደ እኛው ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰብዓዊ ፍጡራን ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ባርነት በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ባሪያዎች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ባሪያዎች ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያትስ ምንድን ነው? በምን ዓይነት የባርነት ቀንበር ሥር ነው የሚገኙት?

ሰብዓዊ ፍጡራንን የሚነግዱ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚሰራጨው የጎብኚዎች ብሮሹር ከዚህ ይበልጥ በግልጽ ሊናገር አይችልም:- “የወሲብ ጉዞ ወደ ታይላንድ። ውብ ልጃገረዶችና እውነተኛ ወሲብ በርካሽ ዋጋ። . . . ድንግል ልጃገረድ ከ200 ዶላር በማይበልጥ ዋጋ መግዛት እንደሚቻል ያውቁ ኖሯል?” ሆኖም እነዚህ “ድንግሎች” በቀን በአማካይ ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ደንበኞችን ወደሚያስተናግዱባቸው የሴተኛ አዳሪ ቤቶች የተወሰዱት ታፍነው ወይም ተገድደው ሊሆን እንደሚችል ብሮሹሩ አይናገርም። ወሲባዊ አገልግሎት የማይሰጡ ከሆነ ይደበደባሉ። በደቡባዊ ታይላንድ በምትገኘውና የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ በሆነችው ፑኬት ደሴት በአንድ የሴተኛ አዳሪዎች ቤት ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ አምስት ሴተኛ አዳሪዎች ሕይወታቸው አልፏል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ባለቤቶቻቸው እንዳያመልጡ ሲሉ ከአልጋዎቻቸው ጋር አስረዋቸው ስለነበረ ነው።

እነዚህ ወጣት ሴቶች የመጡት ከየት ነው? ይሄኛው የወሲብ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ ታፍነውና ተገድደው ለዝሙት አዳሪነት በተሸጡ ከዓለም ዙሪያ በተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ሴቶች የተሞላ እንደሆነ ይነገራል። ዓለም አቀፋዊው የወሲብ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ሊስፋፋ የቻለው በታዳጊ አገሮች ያለው ድህነት፣ በሀብታም አገሮች ያለው ብልጽግናና ለዓለም አቀፋዊው ሕገወጥ ንግድና የግዳጅ አገልግሎት ትኩረት ያልሰጡ ሕጎች በጋራ በፈጠሩት ምቹ ሁኔታ ሳቢያ ነው።

በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ የሴቶች መብት ተሟጋች የሆኑ ድርጅቶች ከ1970ዎቹ አጋማሽ አንስቶ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በዓለም ዙሪያ 30 ሚልዮን ሴቶች እንደተሸጡ ይገምታሉ። ሰብዓዊ ፍጡራንን የሚነግዱ ሰዎች ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የተጋለጡ የሚመስሉ ወጣት ልጃገረዶችንና ሴቶችን ለማግኘት ዓይናቸው በባቡር ጣቢያዎች፣ የድሆች መኖሪያ በሆኑ መንደሮችና በከተሞች ጎዳናዎች ላይ ይቅበዘበዛል። ብዙውን ጊዜ የእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሰለባ የሚሆኑት ያልተማሩ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ፣ ያለ አሳዳጊና ረዳት የቀሩ ወይም የተቸገሩ ሴቶች ናቸው። ሥራ እንደሚያገኙላቸው ቃል በመግባት ያታልሏቸውና ድንበር አሻግረው ለሴተኛ አዳሪ ቤቶች ይሸጧቸዋል።

የኮሙኒስቱ ዓለም ከፈራረሰበት ከ1991 አንስቶ በድህነት አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ አዲስ የልጃገረዶችና የሴቶች ኅብረተሰብ ተፈጠረ። ከተለያዩ ደንቦች ነፃ መሆን፣ የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል ንብረትነት መዛወራቸውና የመደብ ልዩነት እየሰፋ መሄዱ ወንጀል፣ ድህነትና ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ አድርጓል። በርካታ የሩስያና የምሥራቅ አውሮፓ ሴቶችና ልጃገረዶች በከፍተኛ ሁኔታ ለተደራጀው ዓለም አቀፋዊ የዝሙት አዳሪነት ንግድ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆነዋል። “ሰብዓዊ ፍጡራንን መነገድ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን የመነገድን ያህል ለአደጋ አያጋልጥም” ሲሉ የአውሮፓ የቀድሞው የፍትሕ ኮሚሽነር አኒታ ግራዲን ተናግረዋል።

ባክኖ የቀረ የልጅነት ሕይወት

እስያ ውስጥ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የምንጣፍ ፋብሪካ ውስጥ የአምስት ዓመት ሕፃናት ሳይቀሩ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ያላንዳች ክፍያ ይሠራሉ። ብዙውን ጊዜ በጉልበት ሥራ ላይ የተሠማሩ እንዲህ ያሉ ሕፃናት ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ለሚችሉ ሁኔታዎች የተጋለጡ ናቸው:- ማሽኖች በአካላቸው ላይ ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ፣ በቂ ብርሃንና ንጹሕ አየር በሌለባቸው ክፍሎች ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ይሠራሉ፣ እንዲሁም አደገኛ ለሆኑ የፋብሪካ ኬሚካሎች የተጋለጡ ናቸው። *

ሕፃናት ለጉልበት ሥራ በእጅጉ ተፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? የሕፃናት ጉልበት ርካሽ ስለሆነና ሕፃናት በተፈጥሯቸው ታዛዦች፣ በቀላሉ ተግሳጽ የሚቀበሉና ካለባቸው ፍራቻ የተነሳ ምንም ዓይነት ቅሬታ የማያሰሙ ስለሆኑ ነው። ይሉኝታ የሚባለውን ነገር አሽቀንጥረው የጣሉት አሠሪዎቻቸው አነስተኛ ሰውነታቸውና ትንንሽ የሆኑት ቀልጣፋ ጣቶቻቸው እንደ ምንጣፍ ሥራ ላሉ አንዳንድ ሥራዎች የተመቹ ሆነው ይታዩአቸዋል። ብዙውን ጊዜ ወላጆቻቸው ሥራ አጥ ሆነው ቤታቸው ተቀምጠው ሳለ ለእነዚህ ልጆች ሥራ ይሰጣቸዋል።

መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሕፃናት ደግሞ ለጾታዊና ለአካላዊ በደል ይበልጥ የተጋለጡ መሆናቸው ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። ብዙ ልጆች ታፍነው ይወሰዱና ራቅ ብለው በሚገኙ ካምፖች ውስጥ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ሌሊት እንዳያመልጡ ታስረው ያድራሉ። ቀን ቀን ደግሞ በመንገድ ግንባታና በድንጋይ ፈለጣ ሥራ ላይ ሊያሰማሯቸው ይችላሉ።

የልጅነት ሕይወት አላግባብ ባክኖ የሚቀርበት ሌላው ሁኔታ የሚፈጠረው ልጆች ከባርነት ተለይቶ የማይታይ የትዳር ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ በሚደረግበት ጊዜ ነው። ዓለም አቀፋዊው የፀረ-ባርነት ድርጅት አንድ ዓይነተኛ ምሳሌ ጠቅሷል:- “አንዲት የ12 ዓመት ልጃገረድ ቤተሰቦቿ ለ60 ዓመት አዛውንት ሊድሯት መሆኑ ተነገራት። ለስሙ ድርጊቱን የመቃወም መብት ያላት ቢሆንም እንኳ በተግባር ሲታይ ግን ይህን መብት መጠቀም የምትችልበት ምንም አጋጣሚ የሌላት ከመሆኑም በላይ ይህን ማድረግ የምትችል መሆኑንም አታውቅም።”

በዕዳ ሳቢያ የባርነት ቀንበር ሥር መውደቅ

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የጉልበት ሠራተኞች ለእነሱ ወይም ለወላጆቻቸው በተሰጠ ብድር ሳቢያ የአሠሪዎቻቸውና የሥራ ቦታቸው እስረኞች ለመሆን ተገድደዋል። በአብዛኛው እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚከሰተው ሠራተኞች እንደ አገልጋይ ወይም ገበሬ ሆነው በሚሠሩባቸው የእርሻ ቦታዎች ነው። አንዳንድ ጊዜ ዕዳው ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ስለሚተላለፍ የቤተሰቡ አባላት ለዘለቄታው በባርነት ቀንበር ሥር ወድቀው ይቀራሉ። አበዳሪ የሆኑ አሠሪዎች ዕዳውን ለሌላ አዲስ አሠሪ የሚያሸጋግሩበት ጊዜም አለ። ይበልጥ አስከፊ በሆኑት ሁኔታዎች ደግሞ በዕዳ ሳቢያ በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁ ሠራተኞች ለሚሠሩት ሥራ ምንም ክፍያ አያገኙም። ወይም አሠሪዎቻቸው በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የሆነ ወደፊት ከሚያገኙት ገቢ ላይ የሚከፍሉት ገንዘብ በየጊዜው በመስጠት ለዘላለም የእነሱ ባሪያዎች ሆነው እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል።

ሃይማኖታዊ ባርነት

በምዕራብ አፍሪካ የምትኖረው የ12 ዓመቷ ቢንቲ ትሮኮሲ (በኤዌ ቋንቋ “የአማልክት ባሪያዎች” ማለት ነው) ሆነው ከሚያገለግሉት በሺህ የሚቆጠሩ ልጃገረዶች አንዷ ናት። በእናቷ ላይ በተፈጸመ የግዳጅ ወሲብ የተወለደች በመሆኗ እሷ ባልፈጸመችው ወንጀል፣ ለኃጢአት ስርየት በሚል ሰበብ የባርነት ሕይወት ለመምራት ተገድዳለች! በአሁኑ ጊዜ ያለባት ኃላፊነት ለአንድ የመናፍስታዊ አምልኮ ካህን የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን የተወሰነ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ቢንቲ ያለባት ግዴታ እየሰፋ በመሄድ ጌታዋ ለሆነው ካህን ወሲባዊ አገልግሎት መስጠትን የሚጨምር ይሆናል። ከዚያም ቢንቲ ትልቅ ሰው ስትሆን ካህኑ ትሮኮሲ ሆነው የሚያገለግሉ ሌሎች የሚያማምሩ ልጃገረዶች ስለሚያገኝ የአገልግሎት ዘመኗ ያበቃል።

እንደ ቢንቲ ሁሉ ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ የሃይማኖታዊ ባርነት ሰለባዎች በቅዱስ ድንጋጌ ላይ የተፈጸመ ኃጢአት ወይም በደል ተብሎ የሚተረጎምን ድርጊት ለማስተሰረይ ሲባል ከባርነት በማይለይ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲሠሩ ቤተሰቦቻቸው አሳልፈው ይሰጧቸዋል። በብዙ የዓለም ክፍሎች ልጃገረዶች ወይም ሴቶች ለአምላክ የተዳሩ ናቸው እየተባለ ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን እንዲፈጽሙና ለካህናት ወይም ለሌሎች ወሲባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሴቶች ምንም ክፍያ የማያገኙባቸውን ሌሎች አገልግሎቶችንም ይሰጣሉ። የመኖሪያም ሆነ የሥራ ቦታቸውን እንዲቀይሩ የማይፈቀድላቸው ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ በባርነት ቀንበር ሥር ሆነው ብዙ ዓመታት ያሳልፋሉ።

ጥንታዊው የባሪያ ንግድ

አብዛኞቹ አገሮች ባርነትን በሕግ እንዳስወገዱ ቢናገሩም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥንታዊው የባሪያ ንግድ አንሠራርቷል። ይህ ብዙውን ጊዜ የሚታየው በእርስ በርስ ጦርነትና በትጥቅ ትግል በሚታመሱ ክልሎች ነው። “ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሕጉ አይሠራበትም ማለት ይቻላል” ሲል ዓለም አቀፋዊው የፀረ-​ባርነት ድርጅት ዘግቧል። “ወታደሮች ወይም የታጠቁ ሚሊሺያዎች . . . ቅጣት ይደርስብናል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው ሰዎች ያለ ምንም ክፍያ እንዲሠሩላቸው ማስገደድ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች በአብዛኛው ሪፖርት የሚደረጉት ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያላገኙ የታጠቁ ቡድኖች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ነው።” ይሁን እንጂ ይኸው ድርጅት እንዳለው ከሆነ “የመንግሥት ወታደሮችም የትኛውም ሕግ በማይፈቅደው መንገድ ሲቪሎች እንደ ባሪያ ሆነው እንዲሠሩ ማስገደዳቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በቅርቡ ወጥተዋል። በተጨማሪም ወታደሮችና ሚሊሺያዎች የያዟቸውን ሰዎች ለሌሎች እንዲሠሩ አሳልፈው በመሸጥ በባሪያ ንግድ እንደተካፈሉ ተዘግቧል።”

የባርነት መቅሠፍት አሁንም ድረስ በብዙ ቅርጾችና ስውር መልኮች የሰውን ልጅ እየመታው መሆኑ የሚያሳዝን ነው። አሁንም በድጋሚ ትንሽ ቆም ብለህ በዚህ ቀንበር ሥር የወደቁትን ሰዎች ብዛት ማለትም በዓለም ዙሪያ ባሪያዎች ሆነው በመንገላታት ላይ ያሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማሰብ ሞክር። ከዚያም ታሪካቸውን በእነዚህ ገጾች ካነበብከው ዘመናዊ ባሪያዎች መካከል የአንድ ሁለቱን ምናልባትም የሊን-ሊንን ወይም የቢንቲን ሁኔታ ቆም ብለህ አስብ። በዘመናዊው ባርነት እየተፈጸመ ያለው ወንጀል የሚያበቃበትን ጊዜ ለማየት ትናፍቃለህ? ባርነት እውን የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ይህ ከመሆኑ በፊት ሥር ነቀል ለውጦች መካሄድ አለባቸው። እባክህ እነዚህን ለውጦች በተመለከተ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የተሰጠውን ሐሳብ ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 በሰኔ 1999 የንቁ ! እትም ላይ የወጣውን “የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ​—⁠የሚያከትምበት ጊዜ ሩቅ አይደለም!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መፍትሔ ለማግኘት መጣር

እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅትና ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ያሉ በርካታ ሕጋዊ ድርጅቶች ዘመናዊ ባርነትን ለማስወገድ ትጋት በተሞላበት ሁኔታ የተለያዩ ስልቶችን እየነደፉና ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ዓለም አቀፋዊው የፀረ-ባርነት ድርጅትና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዓለም ሕዝብ ስለ ዘመናዊ ባርነት ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር ለማድረግና የዘመናዊው ባርነት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ነፃ ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ነው። ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዳንዶቹ የምርት ውጤቶች በባሪያ ወይም በሕፃን ጉልበት የተመረቱ አለመሆናቸውን የሚገልጹ ልዩ ምልክቶች እንዲለጠፉባቸው ለማድረግ እየጣሩ ነው። ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ ከሕፃናት ጋር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ መከሰስ ይችሉ ዘንድ “የወሲብ ጉዞዎች” መነሻ በሆኑ አገሮች አንዳንድ ሕጎች እንዲወጡ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የቻሉትን ያህል በርካታ ባሪያዎችን ለመቤዠት ሲሉ ለባሪያ ነጋዴዎችና አሳዳሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እስከ መክፈል ደርሰዋል። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት አትራፊ የሆነ ገበያ ሊፈጥርና የባሪያዎች ዋጋ እንዲያሻቅብ ሊያደርግ ስለሚችል ውዝግብ አስነስቷል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ልጃገረዶች በግድ እንዲያገቡ ይደረጋል

[ምንጭ]

UNITED NATIONS/J.P. LAFFONT

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዕዳ ሳቢያ በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁ ሰዎች ምግብ ለማግኘት ተሰልፈው

[ምንጭ]

Ricardo Funari

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ጊዜ ትንንሽ ልጆች በውትድርና አገልግሎት እንዲሠማሩ ይገደዳሉ

[ምንጭ]

UNITED NATIONS/J.P. LAFFONT