ዘመናዊ ባርነት—የሚያበቃበት ጊዜ ቀርቧል!
ዘመናዊ ባርነት—የሚያበቃበት ጊዜ ቀርቧል!
“የአንድ ሰው ነፃነት በዓለም አቀፋዊው ነፃነት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። የአንድ ሰው ነፃነት አደጋ ላይ ሲወድቅ የሌላውም ነፃነት መናጋቱ አይቀርም።” ቪክቶር ሾለር፣ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ፣ 1848
“የሰው ልጅ መሰሎቹ የሆኑትን ሰዎች የሚንቀው፣ የበታች አድርጎ የሚገዛውና የሚያዋርደው ምን ዓይነት ክፋት ቢኖረው ነው?” ሲሉ ዘ ዩኔስኮ ኩሪየር የተባለው መጽሔት አዘጋጆች ጠይቀዋል። “ለሰብዓዊ መብቶች ትልቅ ቦታ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ እንኳ በእንዲህ ዓይነቱ ኢሰብዓዊ ድርጊት ላይ እንዴት እርምጃ ሳይወሰድ ቀረ?”
መልሱ በጣም የተወሳሰበ ነው። ሰዎች ርካሽ የሆነውን የሕፃናት ጉልበት እንዲበዘብዙና ዕዳ ውስጥ ያስገቧቸውን ሰዎች በባርነት ቀንበር አስረው እንዲይዙ የሚገፋፋቸው ነገር ስግብግብነት ነው። ልጃገረዶች ለዝሙት አዳሪነት የሚሸጡትና ከባርነት ተለይቶ የማይታይ ትዳር እንዲመሠርቱ የሚደረገው በድህነትና በመሃይምነት ሳቢያ ነው። ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ባሕላዊ ጽንሰ ሐሳቦች ለሃይማኖታዊ ባርነት አስተዋጽኦ አድርገዋል። በርካታ ወንዶች በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ከኤድስ ነፃ የሆኑ ወንዶች ልጆችን ወይም ልጃገረዶችን ፍለጋ ወደ ባንኮክ ወይም ማኒላ የሚጎርፉት ልቅ የሆነ ወሲባዊ ስሜትና ብልሹ ሥነ ምግባር ስላላቸው ነው። ይህ ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሕግ ተማሪ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በገለጸው መሠረት “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች” የሆኑ ሰዎች የሚኖሩበት ዓለም ገጽታ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሰሎሞን የተባለው ጥንታዊው መራሔ መንግሥት እንዳለው ‘ጠማማ ይቀና ዘንድ፣ ጎዶሎም ይቆጠር ዘንድ የማይችልበት’ ዓለም ገጽታ ነው።—መክብብ 1:15
የአስተሳሰብ ለውጥ
ይህ ማለት በጥንታዊ መልኩም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በያዛቸው የተለያዩ ቅርጾች ተንሠራፍቶ የሚገኘውን ባርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ ሊደረግ የሚችልም ሆነ የሚደረግ ነገር አይኖርም ማለት ነውን? በፍጹም፣ እንደዚያ ማለት አይደለም!
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ (ኦ ኤች ሲ ኤች አር) ባርነት “የአስተሳሰብ ሁኔታ” ነው ሲል ከገለጸ በኋላ “በሚወገድበት ጊዜም እንኳ ርዝራዡን ትቶ ማለፉ አይቀርም። በሕግ ከታገደ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ የባርነት ሰለባ በሆኑት ሰዎችና በዘሮቻቸው እንዲሁም ድርጊቱን ይፈጽሙ የነበሩት ሰዎች ወራሾች በሆኑ ግለሰቦች አእምሮ ውስጥ በአስተሳሰብ ደረጃ ሰርጾ ሊቀር ይችላል” በማለት አክሎ ተናግሯል።
ስለዚህ ባርነትን ማስወገድ የሚቻልበት አንዱ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ ማለትም የልብ ለውጥ በመፍጠር ነው። ይህ ደግሞ የትምህርት ለውጥ በማድረግ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱና አንዳቸው የሌላውን ክብር እንዲጠብቁ
ማስተማር ይጠይቃል። ሰዎች ስግብግብነትን ከልባቸው ነቅለው እንዲያወጡና ከፍተኛ በሆኑ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲመሩ መርዳት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት ሊሰጥ የሚችለው ማን ነው? ኦ ኤች ሲ ኤች አር “ኢሰብዓዊ የሆነን የጉልበት ብዝበዛ ፈጽሞ የማይታገሥ ዓለም ለመፍጠር እያንዳንዱ ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት” ብሏል።በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ በዓለም ዙሪያ ሲካሄድ የቆየውን የትምህርት ፕሮግራም ተመልከት። ይህ ፕሮግራም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ኢሰብዓዊ የሆነውን የጉልበት ብዝበዛ የሚታገሥ ወይም ችላ ብሎ የሚያልፍ አንጀት ሊኖራቸው እንደማይገባ በደንብ አስተምሯቸዋል። በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሰል ሰዎችን በሙሉ በአክብሮት መያዝ እንዳለባቸው ተምረዋል። ይህ ፕሮግራም ስኬታማ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?
በሰው ልጅ ፈጣሪ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰብዓዊ ክብር ትልቅ ቦታ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት የትምህርት ፕሮግራም አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን የተማሩ ሰዎች ፈጣሪያችን ይሖዋ ራሱ የክብር አምላክ መሆኑን ይገነዘባሉ። (1 ዜና መዋዕል 16:27) ፍጥረታቱን ሁሉ ክብር አላብሷል። ይህ ከሁሉም ዘር፣ ማኅበራዊ ደረጃና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተውጣጡ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን የሚጨምር ነው።—“የሰብዓዊ ነፃነትና ክብር ምንጭ ማን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
እኩልነትና የሌላውን ሰው ክብር መጠበቅ
አምላክ “በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ” እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ሥራ 17:26፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በመሆኑም ማንም ሰው በየትኞቹም መሰል ሰዎች ላይ የበላይ ነኝ ወይም ሌሎችን የመጨቆንና ጉልበታቸውን የመበዝበዝ መብት አለኝ ሊል አይችልም። ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያዳላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ” ይገነዘባሉ። (ሥራ 10:34, 35፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሁሉም ሰዎች ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና የመመሥረት መብት ያላቸው በመሆኑ የአምላክ ፍቅር ሁሉን አቀፍ እንደሆነ መገንዘብ ይችላሉ። እንዲያውም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።”—ዮሐንስ 3:16፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ባሕርያትን በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በዚህ ትምህርት አማካኝነት የሰዎች ልብና አእምሮ “ሙሉ በሙሉ አዲስ” ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 4:22-24፣ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ) መሰል ሰዎችን እንዲያከብሩና ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ ይገፋፋቸዋል። ‘ለሰው ሁሉ መልካም ለማድረግ’ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ። (ገላትያ 6:10) ማንም ሰው ቢሆን መሰል ሰዎችን እየጨቆነና ጉልበታቸውን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ እየበዘበዘ እውነተኛ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም። የይሖዋ ምሥክሮች ‘አይሁዳዊ ወይም ግሪካዊ፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የሚባል ነገር ሳይኖር ሁሉንም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው’ አድርጎ አቅፎ እንደነበረው እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ አንድ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው።—ገላትያ 3:28
የመስተዳድር ለውጥ
ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ባርነት ለዘለቄታው መወገድ እንዲችል በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ መካሄድ አለበት። ዓለም አቀፋዊው የሥራ ድርጅት የሰብዓዊ ጉልበት ብዝበዛ እንዲያበቃ ለማድረግ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት “የሚፈቅደውና የሚያስተናግደው ማኅበራዊና ባሕላዊ ሁኔታ መለወጥ” አለበት ሲል ገልጿል። ዓለም አቀፋዊ እርምጃዎች፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብርና የዓለም ማኅበረሰብ ቆራጥ አቋም ድርጅቱ ከጠቀሳቸው ተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል።
ይህ ፕላኔታችንን ስፋት ባለው ሁኔታ መቆጣጠር የሚችልና ዓለም አቀፋዊ ነፃነት ማረጋገጥ የሚችል ሥልጣን እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሐፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ፕላኔታችንን እያመሷት ያሉት ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው “በዓለም አቀፍ ደረጃ” ነው ሲሉ ተናግረው ነበር። ሆኖም ይህ ሊሆን ስለመቻሉ እርግጠኛ የሆነው ሁሉም ሰው አይደለም። በሥልጣን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ከሚገባው በላይ ራስ ወዳዶችና ለራሳቸው ጥቅምና ዓላማ ብቻ የሚሯሯጡ በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱን ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር እንደማይችሉ ቀደምት ተሞክሮዎች አሳይተዋል።
ይሁን እንጂ የመሰል ሰዎችን ክብር እንዲጠብቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያስተማረው መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በዓለማችን ላይ እንዲህ ዓይነት መስተዳድር ለማቋቋም ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚጠቁሙ በርካታ ተስፋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። (ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ እሱንም ሆነ ሰውን የማይወዱ ሰዎችን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት ዓላማ አለው። አምላክ ምድርን በጽድቅ የሚገዛ ዓለም አቀፍ መስተዳደር በሰው ዘር ላይ ለማቋቋም ያለውን ዓላማ ገልጿል። በተለምዶ የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ ተብሎ በሚጠራው ጸሎት ላይ ይህ መስተዳድር እንዲመጣ መጸለይ እንዳለብን ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 6:9, 10
ንጉሡ ክርስቶስ “በፍርድና [“በፍትሕና፣” NW ] በጽድቅ” የሚገዛ በመሆኑ በዚህ መስተዳድር አገዛዝ ሥር የሰብዓዊ ጉልበት ብዝበዛም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ባርነት አይኖርም። (ኢሳይያስ 9:7) መጽሐፍ ቅዱስ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል” በማለት የሚገልጽ በመሆኑ የተጨቆኑ ሰዎች በክርስቶስ ፍትሐዊ አገዛዝ ሥር እፎይታ ያገኛሉ።—መዝሙር 72:12-14
ባርነት በሁሉም ዓይነት መልኩ አብቅቶለት ለማየት የምትጓጓ ከሆነ አምላክ ይህን ነፃ የሚያወጣ የዓለም መንግሥት ለማቋቋም ስላለው ዓላማ ይበልጥ እንድትማር እንጋብዝሃለን። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ዝግጁዎች ናቸው።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የሰብዓዊ ነፃነትና ክብር ምንጭ ማን ነው?
ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ክብርና ነፃነት የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት በውስጣችን ተተክሏል። የተመድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን እንዲህ ብለው በመጠየቅ ዓለም አቀፋዊውን ስሜት አስተጋብተዋል:- “ሁላችንም ከፍርሃት፣ በቅጣት ከመሠቃየትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ ሕይወት የምንፈልግ መሆኑን ሊክድ የሚችል ይኖራል? . . . ነፃነት እንዲወገድ ጥያቄ ያቀረበ ድምፅ የሰማችሁበት ጊዜ አለ? ለባርነት ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት ያያችሁት ባሪያ አለ?”
ይህ አስተሳሰብ ከጊዜ በኋላ የመጣ አይደለም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማዊ ፈላስፋ የሆነው ሴኒካ አንዳንዶች ባሪያ እንዲሆኑ ነው የተወለዱት የሚለውን አስተሳሰብ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ሌተርስ ቱ ሉሲሊየስ በተባለው ጽሑፉ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባሪያዬ ብለህ የምትጠራው ሰው ከአንተው ዘር እንደተወለደ፣ የአንተው ዓይነት ጥሩ ሰማይ ከላዩ እንደተዘረጋ፣ እንደ አንተው እንደሚተነፍስ፣ እንደ አንተው እንደሚኖርና እንደ አንተው እንደሚሞት እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር!”
ከመሐመድ ቀጥሎ አራተኛው ከሊፋ እንደሆኑ ተደርገው በመታየት ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጣቸው ኢማም አሊ ሁሉም ሰዎች “እኩል ሆነው ተፈጥረዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር። የ13ኛው መቶ ዘመን ፋርሳዊ ባለቅኔ የሆነው ሳዲ “የአዳም ልጆች አንዳቸው የሌላው አካል ከመሆናቸውም በላይ ሁሉም ከአንድ ንጥረ ነገር የተፈጠሩ ናቸው። ዓለም አንዱን አካል ሲያሠቃየው ሌሎቹ አካላትም ዕረፍት ሊያገኙ አይችሉም” ሲል ገልጿል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪካዊ ዘገባ ሁሉም ሰዎች ያላቸውን ክብር ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 1:27 “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በማለት የሰውን አፈጣጠር ይገልጻል። ፈጣሪያችን የነፃነት አምላክ ነው። “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት [“ነፃነት፣” NW ] አለ” ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ይሖዋ ሰውን በመልኩና በምሳሌው በመፍጠር የሰው ልጆችን በተወሰነ ደረጃ የዋጋማነትና ለራስ ጥሩ ግምት የመስጠት ስሜት እንዲሁም ክብር አላብሷቸዋል። በተጨማሪም ፍጥረታቱን “ከጥፋት ባርነት” ነፃ በማውጣት ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ነፃነትና ክብር ለዘላለም እንዲጎናጸፉ ያደርጋቸዋል።—ሮሜ 8:21
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብርና ነፃነት አለው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሰብዓዊ ክብርን የመጠበቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጣል
በፓፑዋ ኒው ጊኒ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲደረግ
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአባይ ፏፏቴ ውበት ተመልሳ ለምትመጣው ገነት ጥሩ ነጸብራቅ ነው