በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥቃት ዒላማ የሆነው ነጩ ሻርክ

የጥቃት ዒላማ የሆነው ነጩ ሻርክ

የጥቃት ዒላማ የሆነው ነጩ ሻርክ

ሰዎች የዓለማችን ትልቁ ሥጋ በል ዓሣ የሆነውን ነጩን ሻርክ ያህል የሚፈሩት ሌላ ፍጥረት ያለ አይመስልም። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በአውስትራሊያ፣ በብራዚል፣ በናሚቢያ፣ በደቡብ አፍሪካና በዩናይትድ ስቴትስ ዙሪያ በሚገኙት በሁሉም ወይም በተወሰኑት የውኃ አካላት እንዲሁም በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጥበቃ የሚደረግለት ዝርያ ሆኗል። ሌሎች አገሮችም የተጠናከረ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰቡ ነው። ይሁን እንጂ በገዳይነቱ የታወቀውን ይህን ዓሣ መጠበቅ ለምን አስፈለገ? ቀጥሎ እንደምናየው ጉዳዩ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ሰዎች ስለ ነጩ ሻርክ ያላቸው ግንዛቤም ቢሆን ሁልጊዜ በእውነታ ላይ የተመረኮዘ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ኪለር ዌይል እና ስፐርም ዌይል እንደሚባሉት ዓሣ ነባሪዎች ሁሉ ነጩ ሻርክም * በባሕር ውስጥ ከሚኖሩ ግንባር ቀደም አዳኞች አንዱ ነው። የሻርክ ዝርያዎች ንጉሥና አለቃ ነው። ዓሦችን፣ ዶልፊኖችን፣ አልፎ ተርፎም ሌሎች ሻርኮችን ጨምሮ ያገኘውን ሁሉ ይሰለቅጣል። ሆኖም እየጠና፣ እየገዘፈና ዝግተኛ እየሆነ ሲሄድ አቆስጣዎችን፣ ፔንግዊኖችን እና ጥምብ በተለይ ደግሞ የሞቱ ዓሣ ነባሪዎችን መመገብ ይመርጣል።

አብዛኞቹ ሻርኮች ምግባቸው የሚገኝበትን ቦታ ለመለየት ልዩ የሆነ የማየት ችሎታቸውን ጨምሮ ሁሉንም የስሜት ሕዋሶቻቸውን ይጠቀማሉ። የማሽተት ችሎታቸውን ካነሳን ሻርኮቹ ራሳቸው የሚዋኝ አፍንጫ ናቸው ቢባሉ ይመረጣል! በዚህ ላይ ደግሞ ከጆሯቸው የሚያመልጥ ነገር ባለመኖሩ የሚዋኝ ጆሮ ናቸው ተብለውም ሊገለጹ ይችላሉ።

የሻርክ ጆሮዎች በሁለቱም ጎኑ ላይ በሚገኙ ግፊትን በቀላሉ በሚለዩ ሕዋሳት ይታገዛሉ። በተለይ ለማምለጥ እየተፍጨረጨረ ያለ አንድ አካል የሚፈጥረውን እርግብግብታ ወዲያውኑ የሚለየው ይህ ስውር ማዳመጫ ምንም የሚያመልጠው ነገር የለም። ለምሳሌ ያህል በጦር ተወግቶ እየተንፈራገጠ ያለ ዓሣ የሚፈጥረውን እርግብግብታ ወዲያውኑ ይለያል። ስለዚህ ውኃ ውስጥ ሆነው በጦር ዓሣ የሚያጠምዱ ሰዎች እየደማና እየተንፈራገጠ ያለን ዓሣ በተቻለ ፍጥነት ከውኃው ውስጥ ማውጣታቸው ብልህነት ነው።

ሻርኮች ስድስተኛ የስሜት ሕዋስም አላቸው። በአፍንጫቸው ዙሪያ ተበታትነው በሚገኙ ትናንሽ ቱቦዎች አማካኝነት ከልብ ትርታ፣ ከስንጥብ እንቅስቃሴ ወይም ሊታደን ከሚችል እየዋኘ ያለ ሕያው አካል ጡንቻዎች የሚመነጩ አነስተኛ ኃይል ያላቸውን የኤሌክትሪክ አውዶች መለየት ይችላሉ። እንዲያውም ይህ ስድስተኛ የስሜት ሕዋስ በጣም ንቁ ከመሆኑ የተነሳ የምድር መግነጢሳዊ አውድ ከውቅያኖሱ ጋር የሚኖረውን መስተጋብር እንዲለዩ ሊያደርጋቸው ይችላል። በዚህም ሳቢያ ሻርኮች ሰሜን በየት በኩል እንደሆነና ደቡብ በየት በኩል እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ።

ነጩን ሻርክ ለይቶ ማወቅ

ነጭ ሻርክ ነጭ ይባል እንጂ ነጣ ያለ መልክ ያለው የታችኛው አካሉ ብቻ ነው። ጀርባው ጠቆር ያለ ግራጫ ነው። ሁለቱ ቀለሞች መስመሩን ባልጠበቀና ከሻርክ ወደ ሻርክ በሚለያይ ሁኔታ በዓሣው ጎን ላይ ይገናኛሉ። ይህ ገጽታው ከሚኖርበት አካባቢ ጋር እንዲመሳሰል ያደርገዋል። ሆኖም ሳይንቲስቶች አንዱን ሻርክ ከሌላው መለየት እንዲችሉም ይረዳቸዋል።

ነጫጭ ሻርኮች ምን ያህል ያድጋሉ? “የትልቁ ነጭ ሻርክ ትክክለኛ ርዝማኔ” ይላል ግሬት ዋይት ሻርክ የተባለው መጽሐፍ፣ “ከ5.8 እስከ 6.4 ሜትር ይደርሳል።” ይህን የሚያክል መጠን ያለው ዓሣ ከ2, 000 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ግዙፍ ፍጥረታት አካላቸው ላይ በተያያዙትና በትንሹ ወደ ውስጥ አጠፍ ያለ የሦስት ጎን ቅርጽ ባላቸው ክንፎቻቸው በመጠቀም በውኃ ውስጥ እንደ ሚሳይል ይተኮሳሉ። የነጫጭ ሻርኮች ጅራት የተመጣጠነ ቅርጽ ያለው መሆኑም ከሌሎቹ የተመጣጠነ የጅራት ቅርጽ ከሌላቸው ሻርኮች ልዩ የሚያደርጋቸው ሲሆን ይህም ጉልበት ይጨምርላቸዋል።

ግዙፍና ሾጣጣ ጭንቅላቱ፣ ስሜት አልባ የሆኑት ጥቋቁር ዓይኖቹና እጅግ ስል በሆኑና ዘርዘር ብለው በመደዳ በተተከሉ የሦስት ማዕዘን ቅርጽ ባላቸው ጥርሶች የተገጠገጠው አፉ ነጩ ሻርክ ተለይቶ የሚታወቅባቸውና በጣም አስፈሪ ያደረጉት እሴቶቹ ናቸው። እነዚህ ሁለት አፍ ያላቸው “ቢላዎች” ሲሰበሩ ወይም ሲወልቁ ከበስተጀርባ በኩል ያሉት ተተኪ ጥርሶች ወደፊት በመምጣት ይተኳቸዋል።

ሞቅ ባለ ደም ኃይል የሚንቀሳቀሱ

ማኮ እና ፐርቢግል ተብለው የሚጠሩትን ሻርኮችና ነጩን ሻርክ ጨምሮ ላምኒዴ ተብሎ በሚጠራው የሻርኮች ዝርያ የታቀፉት ሻርኮች የደም ዝውውር ሥርዓት ከአብዛኞቹ ሌሎች ሻርኮች በእጅጉ የተለየ ነው። የደማቸው የሙቀት መጠን ከውኃ የሙቀት መጠን ከ3 እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይበልጣል። ሞቅ ያለው ደማቸው የሚመገቡት ምግብ በፍጥነት እንዲፈጭ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ብርታትና ጥንካሬ ይጨምርላቸዋል። እንደ ቱና ያሉ ፈጣን የባሕር ዓሦችን የሚመገበው ማኮ በውኃ ውስጥ አጭር ርቀት በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ ይችላል!

ሻርኮች በሚዋኙበት ጊዜ በሁለቱ ክንፎቻቸው አማካኝነት ወደ ላይ ከፍ ይላሉ። በጣም ዝግ ብለው የሚዋኙ ከሆነ ልክ እንደ አውሮፕላን ቆም ብለው ወደ ታች ይሰምጣሉ። ይህ የሚሆነው በጉበቱ ውስጥ ተከማችቶ የሚገኝ ከሻርክ አጠቃላይ ክብደት አንድ አራተኛ የሚሆነውን የሚሸፍንና ሻርኩ እንዲንሳፈፍ የሚያደርግ ዘይት እያለ ነው! ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ የሻርክ ዝርያዎች መተንፈስ እንዲችሉ መዋኘታቸውን መቀጠል አለባቸው። በዚህ መንገድ ከፍተኛ የኦክሲጅን መጠን ያለው ውኃ ወደ አፋቸውና ወደ ስንጥባቸው ይቀዝፋሉ። ከዓመት እስከ ዓመት ስሜት አልባ ፈገግታ የሚያሳዩት በዚህ የተነሳ ነው!

ሰው በሊታ?

እስከ አሁን ከሚታወቁት 368 የሻርክ ዝርያዎች መካከል አደገኛ የሚባሉት ወደ 20 የሚጠጉት ብቻ ናቸው። ከእነዚህም መካከል በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ሻርኮች በሰዎች ላይ ከሚሰነዝሯቸው ወደ 100 የሚጠጉ ጥቃቶች መካከል አብዛኞቹን የሚፈጽሙት አራቱ ዝርያዎች ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል 30ዎቹ ለሞት የሚዳርጉ ናቸው። ለእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት በአብዛኛው የሚወነጀሉት አራቱ ዝርያዎች ከሌላ ከማንኛውም የሻርክ ዝርያ በበለጠ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ የሚገመተው ቡል ሻርክ፣ ታይገር ሻርክ፣ ኦሺኒክ ዋይትቲፕ ሻርክና ነጩ ሻርክ ናቸው።

የሚያስገርመው ነገር በነጩ ሻርክ ጥቃት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ቢያንስ 55 በመቶ የሚሆኑት፣ እንዲያውም በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች 80 በመቶ የሚሆኑት ከሞት ተርፈዋል። ብዙዎች በእንዲህ ያለ አስፈሪ አዳኝ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ሊተርፉ የቻሉት ለምንድን ነው?

ነክሶ መልቀቅ

ነጩ ሻርክ ያደነውን ሕያው አካል መጀመሪያ ላይ አንዴ በኃይል ከነከሰው በኋላ ይለቅቀዋል። ከዚያ የጥቃት ሰለባውን ከመብላቱ በፊት እስኪሞት ደረስ ይጠብቀዋል። የጥቃት ሰለባዎቹ ሰዎች በሚሆኑበት ጊዜ ይህ የነጭ ሻርክ ባሕርይ መዳን የሚችሉበትን አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ከእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት በኋላ ደፋር በሆኑ አጋሮቻቸው የዳኑ ሰዎች አሉ። ይህ ሁኔታ ለብቻ አለመዋኘት ጥበብ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ይሁን እንጂ ነጩ ሻርክ አንድ ሌላ ባሕርይ ባይኖረው ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ የማዳን እርምጃ የራስን ሕይወት ከማጥፋት ተለይቶ የሚታይ አይሆንም ነበር። ነጩ ሻርክ አንዳንድ ሌሎች ሻርኮች እንደሚያደርጉት ደም ስለሸተተው ብቻ ሆዱን ለመሙላት አይክለፈለፍም። ነጩ ሻርክ እንዲህ ዓይነቱን ነክሶ የመልቀቅ ስልት የሚጠቀመው ግን ለምንድን ነው?

በዓይኖቹ ሳቢያ ነው ሲሉ አንድ ሳይንቲስት ግምታዊ አስተያየት ሰንዝረዋል። ነጩ ሻርክ እንደ ሌሎቹ ሻርኮች ዓይኖቹን ከጉዳት የሚጠብቅ እንደ ዓይን ቆብ የመሰለ ገለፈት የለውም። በመሆኑም ግጭት ሊፈጠር ሲል ዓይኖቹን እዚያው ጉድጓዳቸው ውስጥ ያሽከረክራቸዋል። ግጭቱ በሚፈጠርበት ጊዜ ዓይኑ ለአደጋ ምናልባትም በጣም ለሚዋጉት የአቆስጣ ጥፍሮች የተጋለጠ ይሆናል። ስለዚህ ነጩ ሻርክ ፈጣን የሆነና ለሞት የሚዳርግ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ መልቀቅ የተለመደ ባሕርይው ነው።

በተጨማሪም ነጭ ሻርኮች በአብዛኛው ከሕፃን ልጅ ጋር የሚመሳሰል ባሕርይ እንደሚያሳዩ አትዘንጋ። ያገኙትን ነገር ሁሉ በመጀመሪያ የሚመረምሩት ወደ አፋቸው በመክተት ነው! “ክፋቱ፣ አንድ ትልቅ ነጭ ሻርክ [የአንድን ነገር ምንነት ለመለየት] የሚሰነዝረው ንክሻ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ነው” ሲሉ በአውስትራሊያ ሲድኒ የባሕር ውስጥ ሥነ ሕይወት ባለሙያ የሆኑት ጆን ዌስት ገልጸዋል።

ነጩ ሻርክ አደገኛ እንስሳ ቢሆንም እንኳ የሰው ሥጋ ለማግኘት የሚቋምጥ ፍጡር ነው ማለት ግን አይደለም። በውኃ ውስጥ 6, 000 ሰዓታት ያሳለፉ አንድ ተመራማሪ የተመለከቷቸው ነጭ ሻርኮች ሁለት ብቻ ሲሆኑ አንዳቸውም ቢሆኑ ጥቃት አልሰነዘሩባቸውም። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ነጭ ሻርክ ከሰዎች ይሸሻል።

በውቅያኖስ ውስጥ ምርምር የሚያካሂዱት ዣክ-ኢቭ ኩስቶ እና ባልደረባቸው በኬፕ ቨርድ ደሴቶች በውቅያኖስ ውስጥ ጥናት በሚያካሂዱበት ወቅት በአጋጣሚ ከአንድ ግዙፍ ነጭ ሻርክ ጋር ተገጣጥመው ነበር። ኩስቶ “ያሳየው ምላሽ የማይጠበቅ ዓይነት ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። “ይህ ግዙፍ እንስሳ በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ኩሱን ለቀቀውና አጀብ በሚያሰኝ ፍጥነት ተፈተለከ።” እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “ከነጭ ሻርክ ጋር የተገጣጠምንባቸውን ሁኔታዎች ቆም ብዬ ባሰብኩ ቁጥር ሰዉ ስለዚህ ፍጡር ባለው አስተሳሰብና እኛ ባየነው ሁኔታ መካከል ያለው ከፍተኛ ልዩነት በጣም ይገርመኛል።”

በነጭ ሻርኮች ላይ የሚካሄድ አደን

ከጊዜ በኋላ ተወዳጅ ፊልም ሆኖ የወጣው በ1970 የተዘጋጀው ጆውስ የተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፍ ሰዉ ስለ ነጭ ሻርክ በነበረው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሰዉ ለነጩ ሻርክ የነበረው አመለካከት በአንድ ጀንበር ተለውጦ ክፉ እንስሳ አድርጎ ይመለከተው ጀመር። በተጨማሪም “ጀብዱ ለመሥራት የቋመጡ በርካታ አዳኞች የዚህን ሻርክ ጭንቅላት ወይም መንጋጭላ ከሁሉ ቀድመው ለማሳየት መሽቀዳደም ያዙ” ይላል ግሬት ዋይት ሻርክ የተሰኘው መጽሐፍ። ከጊዜ በኋላ አንድ ትልቅ የነጭ ሻርክ ጥርስ (በአውስትራሊያ) እስከ 1, 000 ዶላር ያወጣ የነበረ ሲሆን ሙሉ መንጋጭላ ደግሞ እስከ 20, 000 ዶላር ያወጣ ነበር።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ነጭ ሻርኮች የሚያልቁት ለንግድ ሲባል በሚጣሉ የዓሣ ማጥመጃ መረቦች ነው። በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሻርክ ውጤቶች በተለይም የሻርክ ክንፎች ገበያ ለማሟላት ሲባል በየዓመቱ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሻርኮች ይጠመዳሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው እየተመናመነ ሲመጣ በተለይ ነጭ ሻርኮችን ለመታደግ የማስጠንቀቂያ ደወሎች በዓለም ዙሪያ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።

ግንዛቤው እያደገ መጥቷል

ሻርኮች የታመመውን፣ በሞት አፋፍ ላይ ያለውን፣ የተዳከመውንና የሞተውን በባሕር ውስጥ እያሰሱ በመብላት የታወቁ ናቸው። በመሆኑም ጤናማ የሻርኮች ዓለም መኖሩ ለውቅያኖስ ጤናማነትና ንጽህና ወሳኝ ነው።

በተፈጥሮ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ኅብረት የተለያዩ ዝርያዎች ተንከባካቢ ኮሚሽን በሻርኮች ሕይወት ላይ የተደቀነውን አደጋ በመገንዘብ በሻርኮች ላይ የተጋረጠውን ችግር በጠቅላላ የሚያጠና አንድ የኤክስፐርቶች ቡድን አቋቁሟል። ይሁን እንጂ በነጭ ሻርክ ላይ ጥናት ማካሄድ እንዲህ ቀላል አይደለም። ነጭ ሻርኮች ወላዶች ካለመሆናቸውም በላይ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተይዘው ከተወሰዱ ይሞታሉ። ስለዚህ ጥናቱ መካሄድ ያለበት እዚያው በተፈጥሯዊ መኖሪያ ቦታቸው እንዳሉ ነው።

ሰዎች ስለ ሻርኮች ያላቸው ግንዛቤ እያደገ ሲመጣ ለእነዚህ እጅግ አስገራሚ የሆኑ ፍጥረታት የነበራቸው አመለካከት ተለውጧል። ሆኖም ይህ የነጩን ሻርክ ባሕርይ አይለውጠውም። ክፉ ባይሆንም እንኳ አደገኛ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዝና አክብሮት ሊሰጠው የሚገባው እንስሳ ነው። ያውም ከፍተኛ አክብሮት!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ትልቁ ወይም ነጩ ሻርክ የተለያዩ ስሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል በአውስትራሊያ አንዳንድ ጊዜ ዋይት ፖይንተር፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ብሉ ፖይንተር ተብሎ ይጠራል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህ ሻርኮች አስፈሪ የሆነ ትልልቅ አፍ አላቸው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

Photos by Rodney Fox Reflections

South African White Shark Research Institute