በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ ወላጅ ኑሮን መግፋት የምችለው እንዴት ነው?

ያለ ወላጅ ኑሮን መግፋት የምችለው እንዴት ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ያለ ወላጅ ኑሮን መግፋት የምችለው እንዴት ነው?

“ወላጆቼ የተፋቱት እኔ የሦስት፣ እህቴ ደግሞ የአራት ዓመት ልጅ እያለን ነበር። እኛን የማሳደግ መብት ለማግኘት በፍርድ ቤት ሲሟገቱ ከቆዩ በኋላ ከእናታችን ጋር እንድንኖር ተወሰነ። ሆኖም ሰባት ዓመት ሲሞላኝ እኔና እህቴ ከአባታችን ጋር ለመኖር ወሰንን።”​—⁠ኦራሲዮ

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የኦራሲዮ አባትና አብራው የምትኖር ሴት ጓደኛው ኦራሲዮንና እህቱን ጥለዋቸው ሄዱ። ኦራሲዮ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “የ19 ዓመት እህቴን፣ ከእኛ ጋር ለመኖር የመረጠችውን የ12 ዓመት ግማሽ እህቴንና እኔን ያቀፈውን ቤተሰብ በ18 ዓመቴ ላስተዳድር የቻልኩት በዚህ ሁኔታ ነበር።”

ከዚህ በፊት በወጣ ርዕስ ላይ እንደተገለጸው በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ያለ ወላጅ ይቀራሉ። * እንደ ኦራሲዮ ሁሉ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው ጥለዋቸው ይሄዳሉ። ሌሎች ደግሞ ወላጆቻቸውን በሞት አጥተዋል አሊያም በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ከወላጆቻቸው ተነጥለዋል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ያለ ወላጅ መቅረት አስቸጋሪም አሳዛኝም ሊሆን ይችላል። እንዲሁም በርካታ ኃላፊነቶች ሊያስከትልብህ ይችላል።

‘ማን ይደግፈኛል?’

ሁኔታውን ተቋቁመህ ማለፍ መቻልህ በአመዛኙ በእድሜህና በሁኔታዎችህ ላይ የተመካ ነው። ገና በልጅነት ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ከሆነ ሁኔታው ይበልጥ እንደሚከብድ የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ በራስህ አልተተውክ ይሆናል። ምናልባት አጎትህ፣ አክስትህ አሊያም ታላቅ ወንድምህ ወይም እህትህ አብረሃቸው እንድትኖር ይፈቅዱልህ ይሆናል።

የይሖዋ ምሥክሮች ወላጅ የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን የመንከባከቡን ኃላፊነት የአምልኳቸው ክፍል አድርገው ይመለከቱታል። (ያዕቆብ 1:​27፤ 2:​15-17) አብዛኛውን ጊዜም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እርዳታ ያበረክታሉ። ለምሳሌ ያህል ኦራሲዮና እህቶቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጥንተው የነበረ ሲሆን በስብሰባዎቻቸውም ላይ ይገኙ ነበር። እዚያም እርዳታ የሚሰጣቸው አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ አገኙ። ኦራሲዮ እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ በየዕለቱ ለሚሰጠኝ አመራርና ፍቅራዊ እንክብካቤ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! በጉባኤው ውስጥ የሚገኝ የእኛ እኩያ የሆኑ ልጆች ያሉት አንድ በጣም መንፈሳዊ የሆነ ቤተሰብ ባደረገልን እርዳታ በእጅጉ ተጠቅመናል። እንደ ልጆቻቸው አድርገው ስለተመለከቱን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልንመካበት የምንችል የአንድ ቤተሰብ ክፍል እንደሆንን ተሰማን።”

ሆኖም እንዲህ ዓይነት ግሩም አጋጣሚ የሚያገኙት ሁሉም ልጆች አይደሉም። በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት የተጠናቀረ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ደጋፊ የሌላቸው ልጆች አካላዊ በደል የሚፈጽሙባቸው፣ ክፍያ ወይም እድገት ማግኘት የሚችሉበት ምንም ዓይነት አጋጣሚ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲሠሩ የሚያስገድዷቸው፣ በዝሙት አዳሪነት የሚያሰማሯቸው አልፎ ተርፎም በባርነት የሚገዟቸው ቤተሰቦች ያጋጥሟቸዋል።” ስለዚህ በመጠኑም ቢሆን ጥሩ እንክብካቤ የሚያደርግልህ ሰው ካገኘህ አመስጋኝ ሁን።

ያለ ወላጅ መኖር ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው የታወቀ ነው። እንዲሁም የሚደግፍህ ወላጅ አለመኖሩ ያናድድህ ይሆናል። አንድ ዘመድህ፣ ታላቅ ወንድምህ ወይም እህትህ ምን ማድረግ እንዳለብህ ሲነግሩህ በውስጥህ ያለው የንዴት ስሜት ይባባስ ይሆናል። ሆኖም አንተን ለመርዳት ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ንዴትህን አትወጣ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ቁጣ ለስድብ አያታልልህ፤ . . . ኃጢአትን እንዳትመለከት [“ወደ ክፉ ሥራ እንዳትመለስ፣” የ1980 ትርጉም ] ተጠንቀቅ።” (ኢዮብ 36:​18, 21) በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችውን አስቴር የተባለች ወጣት ሴት አስታውስ። ወላጆቿን በሞት አጥታ ስለነበር ያሳደጋት በእድሜ የሚበልጣት የአጎቷ ልጅ መርዶክዮስ ነበር። ምንም እንኳ ወላጅ አባቷ ባይሆንም ሙሉ ሴት በሆነችበት ጊዜም ጭምር የሚሰጣትን ‘ትእዛዝ’ ታከብር ነበር! (አስቴር 2:​7, 15, 20) አንተም ታዛዥና ተባባሪ ለመሆን ጣር። ውጥረቶችን ለማርገብና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የቤተሰብ ኃላፊነት

ታላቅ ወንድም ወይም እህት ካለህ ወይም ደግሞ አንተ ራስህ ትልቅ ልጅ ከሆንክ፣ ምናልባት አንተም ሆንክ ወንድሞችህና እህቶችህ ራሳችሁን ችላችሁ መኖር አያቅታችሁ ይሆናል። ምናልባትም ሊወጡት የማይችሉት ከባድ ኃላፊነት መስሎ የሚታየው የቤተሰብ ራስ ሆኖ ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ድርሻ በአንተ ላይ ይወድቅ ይሆናል! ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸው በርካታ ወጣቶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማሳደግ ረገድ የሚደነቅ ተግባር አከናውነዋል።

በውስጥህ ያሉትን አንዳንድ የቅሬታ ስሜቶች ለማሸነፍ መታገል ሊያስፈልግህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ለወንድሞችህና ለእህቶችህ ባለህ ፍቅርና አሳቢነት ላይ ማሰላሰልህ ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዝ ሊረዳህ ይችላል። እንዲሁም ለእነሱ የምትሰጠውን ድጋፍ ከአምላክ የተቀበልከው ኃላፊነት አድርገህ መመልከትህም ሊረዳህ ይችላል። ደግሞም ክርስቲያኖች የራሳቸው ለሆኑት እንክብካቤ እንዲያደርጉ ታዝዘዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ሆኖም ለወንድሞችህና ለእህቶችህ አባት ወይም እናት ሆነህ ለመገኘት የፈለግኸውን ያህል ብትጥርም በእርግጥ የእነሱ ወላጅ መሆን አትችልም።

ወንድሞችህና እህቶችህ ለወላጆችህ ያሳዩት የነበረውን ዓይነት ታዛዥነት ለአንተም እንዲያሳዩ መጠበቅህ ምክንያታዊ አይሆንም። እንዲያውም ሁኔታውን ተቀብለው የምትሰጣቸውን አመራር መከተል እስኪጀምሩ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ በዚህ ጊዜ በነገሩ ላለመበሳጨት ጥረት አድርግ። ‘መራርነትን፣ ንዴትን፣ ቁጣን፣ ጩኸትንና ስድብን’ ማስወገድ ይኖርብሃል። ለወንድሞችህና ለእህቶችህ ምሳሌ በመሆን ‘እርስ በርሳቸው ቸሮችና ርኁሩኆች እንዲሁም ይቅር ባዮች እንዲሆኑ’ አስተምራቸው።​—⁠ኤፌሶን 4:​31, 32

ኦራሲዮ ስህተት መፈጸሙን በማመን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አንዳንድ ጊዜ በእህቶቼ ላይ በጣም ጥብቅ እሆንባቸው ነበር። ሆኖም ጥብቅ መሆኔ በተወሰነ መጠን ጥበቃ ያስገኘልን ከመሆኑም በላይ በይሖዋ ዓይን ትክክለኛ አቋም እንድንይዝ አስችሎናል።”

የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማሟላት

አንተን ለመርዳት ወላጆችህ በአጠገብህ ከሌሉ የሚያስፈልጉህን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሚሆንብህ የታወቀ ነው። ምናልባት አንዳንድ በእድሜ የበሰሉ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዴት ምግብ መሥራት፣ ቤቱን ማጽዳትና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት እንደምትችሉ በማሳየት አንተንም ሆነ ወንድሞችህንና እህቶችህን (ካሉህ ማለት ነው) ሊረዷችሁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ገንዘብ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ? ምናልባት ሥራ ከመፈለግ በስተቀር የተሻለ አማራጭ ላይኖርህ ይችላል።

ሆኖም በትምህርት፣ በተሞክሮ ወይም በሙያ ረገድ ብዙ እውቀትና ልምድ ላላካበቱ ወጣቶች ያን ያህል ክፍት የሥራ መስክ አይገኝም። ስለዚህ በሆነ መንገድ መሠረታዊ የሆነውን የትምህርት ደረጃ ማጠናቀቅ ወይም አንድ ዓይነት ተጨማሪ የሙያ ስልጠና ማግኘት የምትችል ከሆነ አጋጣሚው አያምልጥህ። ኦራሲዮ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “እኔና ታላቅ እህቴ እየሠራን፣ የእኔንና የግማሽ እህቴን የትምህርት ቤት ወጪ እንሸፍን ነበር።” በታዳጊ አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ ሥራ ለማግኘት ብልሃት መፍጠር ይኖርብህ ይሆናል።​—⁠በሚያዝያ​—⁠ሰኔ 1995 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “በታዳጊ አገሮች ሥራ መፍጠር” የሚለውን ተመልከት።

ይበልጥ በኢኮኖሚ በበለጸጉ አገሮች ደግሞ ከመንግሥት የገንዘብ ድጎማ ማግኘት ይቻል ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ፣ ወላጅ የሌላቸውን ወይም ወላጆቻቸው ጥለዋቸው የሄዱ ልጆችን ለመርዳት የተቋቋሙ መንግሥታዊም ሆኑ የግል ድርጅቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ድርጅቶች ቀለብ ወይም መኖሪያ ቤት እንድታገኝ ይረዱህ ይሆናል። እርግጥ የምታገኘውን ማንኛውም የገንዘብ እርዳታ በጥበብ ጥቅም ላይ ልታውለው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ” እንደሆነ ይናገራል። (መክብብ 7:​12) በመሆኑም በገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቃ ካልሆንክ ገንዘብ ወዲያውኑ ‘ለራሱ ክንፍ አበጅቶ ሊበርር’ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 23:​4, 5

የሚረዳህ አንድ ጎልማሳ ሰው ካለ የሚያስፈልጉህን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላቱ ያን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ ላይሆን ይችላል። ወደፊት ግን የሚያስፈልጉህን ነገሮች ራስህ ማሟላት የሚኖርብህ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ትምህርትህን በትጋት እንድትከታተል የሚያበረታቱ ወላጆች ስለሌሉህ ትምህርትህን በትኩረት መከታተል ከፍተኛ ጥረት ሊጠይቅብህ ይችላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ መንፈሳዊ እድገትን በተመለከተ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር በትምህርት ቤት የምትከታተለውን ትምህርት በተመለከተም ሊጠቀስ ይችላል:- “ማደግህ . . . እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​15) እንዲህ በማድረግ ከአንተ ጋር ላሉት ሰዎች ጥሩ ምሳሌ ከመተውህም በላይ ለራስህም ጥቅም ታገኛለህ።

ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር በመንፈሳዊ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማሟላትህ ነው። መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የምታደርግበት ሚዛናዊ ልማድ ለማዳበር ጥረት አድርግ። (ፊልጵስዩስ 3:​16) ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች በቤተሰብ መልክ ሆነው በየዕለቱ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ውይይት የማድረግ ልማድ አላቸው። ይህን ለምን የዕለታዊ ሕይወትህ ክፍል አታደርገውም? በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ልማድ ማዳበርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት በመንፈሳዊ ብርቱ ሆነህ እንድትቀጥል ይረዳሃል።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

ፈተናውን መጋፈጥ

ያለ ወላጅ መኖር ከባድ ነገር ነው። ሆኖም ሕይወት ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝ ይሆናል ማለት አይደለም። በሃያ ዓመት ዕድሜ ላይ የምትገኘው ፓውላ እናቷን በሞት ያጣችው ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ነበር። አሥር ዓመት ሲሆናት ደግሞ አባቷ ሞተ። አንዲት ደግ ሴት እሷንና አራት እህቶቿን አስጠጋቻቸው። ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ በመከራ የተሞላ ሆኗልን? አልሆነም። ፓውላ እንዲህ ትላለች:- “ምናልባት ቤተሰባችን ለአብነት ሊጠቀስ የሚችል ዓይነት ላይሆን ቢችልም እንኳ በተወሰነ መጠን ከሌሎች ያልተለየ ሕይወት መምራት ችለናል። እንዲያውም በመካከላችን ያለው ፍቅር ከአብዛኞቹ ቤተሰቦች ይበልጥ የጠበቀ ነው።”

የፓውላ እህት ኢሬኔ “ወላጆቻችንን ብናጣም እንኳ ከሌሎች ወጣቶች የተለየን አይደለንም” ስትል አክላ ገልጻለች። በተመሳሳይ ሁኔታ ሥር ለሚገኙ ልጆች “በሕይወታችሁ ውስጥ አንድ ትልቅ ሳንካ እንደገጠማችሁ ሆኖ አይሰማችሁ” በማለት ምክር ለግሳለች። በተመሳሳይም ኦራሲዮ እንዲህ ይላል:- “ይህ ሁኔታ በቶሎ ወደ ጉልምስና እንድደርስ አስችሎኛል።”

ወላጆችን ማጣት እጅግ የሚያሳዝን ገጠመኝ ነው። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ልትቋቋመው እንደምትችልና የእሱን በረከት እንደምታገኝ እርግጠኛ ሁን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በየካቲት 2000 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ወላጆቼን ያጣሁት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቲያን ሽማግሌዎችን ድጋፍ ማግኘት ትችላለህ