በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ነግሦ እንደነበር ያመኑት ዛሬ ነው

ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ነግሦ እንደነበር ያመኑት ዛሬ ነው

ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ነግሦ እንደነበር ያመኑት ዛሬ ነው

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“ታኅሣሥ 11, 1998 ታትሞ የወጣው የብሪታንያው ካቶሊክ ሄራልድ “ጳጳሳት ንግሥት ሜሪ ለፈጸመቻቸው ‘አሰቃቂ ወንጀሎች’ ይቅርታ ጠይቀዋል” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ወጥቶ ነበር። የእንግሊዝና የዌልስ የሮማ ካቶሊክ ጳጳሳት “በታላቋ ብሪታንያ በተሃድሶ ዘመን በፕሮቴስታንቶች ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ጨምሮ በካቶሊክ ሃይማኖት ስም ከባድ ስህተቶች እንደተፈጸሙ” አምነዋል። ንግሥት ሜሪ ማን ናት? እንዲህ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያነሳሳቸው ምን ዓይነት ስህተት ብትፈጽም ነው? የእግሊዝና የዌልስ ጳጳሳት ቃላቸውን ለመስጠት ይህን ጊዜ የመረጡትስ ለምንድን ነው?

ሜሪ ቱዶር የሮማ ካቶሊክን እምነት ታራምድ በነበረችው እንግሊዝ ውስጥ የተወለደችው በ1516 ነበር። ሜሪ የንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ የመጀመሪያ ሚስትና የአራጎን ተወላጅ ከሆነችው ከካተሪን ልጆች መካከል በሕይወት የተረፈች ብቸኛ ልጅ ስትሆን እናቷ ቀናተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታይ አድርጋ ነበር ያሳደገቻት። አባቷ ወንድ አልጋ ወራሽ ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ካተሪን ወንድ ልጅ አልወለደችም ነበር። ሄንሪ ከካተሪን ጋር የነበረውን ትዳር በሕግ እንዲያፈርሱለት ለሮማው ሊቃነ ጳጳሳት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሁሉን በራሱ ቁጥጥር ሥር በማድረግ በእንግሊዝ ውስጥ ለተካሄደው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ጥርጊያውን አመቻቸ። በ1533 የካንተርበሪው ሊቃነ ጳጳሳት ቶማስ ክራንመር የሄንሪ የመጀመሪያ ጋብቻ መሻሩን ከማሳወቃቸው ከአራት ወራት በፊት አን ቡሊንን አገባ።

በቀጣዩ ዓመት ዕብሪተኛው ሄንሪ ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጠና የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ራስ ሆነ። በዚህ ወቅት ከሕግ ውጪ እንደተወለደች ተደርጋ መታየት የጀመረችው ሜሪ ቀሪ የሕይወት ዘመኗን ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ተገልላ ለመኖር የተገደደችውን እናቷን ዳግመኛ አላየቻትም።

የፕሮቴስታንት ጽንፈኛነት

በቀጣዮቹ 13 ዓመታት ሄንሪን የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ አድርገው ለመቀበል ወይም በሮማው ሊቃነ ጳጳሳት ሥልጣን ላይ ያላቸውን እምነት ለመተው አሻፈረኝ ያሉ አንዳንዶች ይገደሉ ነበር። ሄንሪ በ1547 ሲሞት ከስድስት ሚስቶቹ መካከል ከሦስተኛዋ የተወለደው ብቸኛው ሕጋዊ ወንድ ልጁ የሆነው የዘጠኝ ዓመቱ ኤድዋርድ ተተካ። ኤድዋርድና አማካሪዎቹ እንግሊዝን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ለማድረግ ሞክረው ነበር። የሮማ ካቶሊክ ተከታዮች በሃይማኖታቸው ሳቢያ ስደት ይደርስባቸው የነበረ ሲሆን በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የነበሩ ምስሎችና መሠዊያዎች እንዲወገዱ ተደርጓል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ማተምንና ማንበብን ያግድ የነበረው ሕግ ወዲያውኑ የተነሳ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበብባቸው የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች በላቲን ሳይሆን በእንግሊዝኛ እንዲካሄዱ መመሪያ ወጣ። ሆኖም በ1553 ኤድዋርድ ገና በ15 ዓመቱ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ሕይወቱ አለፈ። ሜሪ ሕጋዊ ወራሽ ሆና በመገኘቷ የእንግሊዝ ንግሥት ሆነች።

የካቶሊክ ጽንፈኝነት

መጀመሪያ ላይ ሕዝቡ የ37 ዓመቷን ሜሪ በደስታ ተቀብሏት የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ተወዳጅነቷ እየጠፋ ሄደ። የምታስተዳድረው ሕዝብ ከፕሮቴስታንት እምነት ጋር ተላምዶ የነበረ ሲሆን ሜሪ ሥልጣን ላይ ከወጣች በኋላ አገሪቷን ዳግመኛ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ለማድረግ ቆርጣ ተነሳች። ኤድዋርድ አውጥቷቸው የነበሩት ሁሉም ሃይማኖታዊ ደንቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሻሩ። ሜሪ በአገሯ ሕዝብ ስም የሮማውን ሊቃነ ጳጳሳት ይቅርታ ጠየቀችና እንግሊዝ ዳግመኛ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ሆነች።

ከሮም ጋር የተፈጠረው ዕርቅ በፕሮቴስታንቶች ላይ አዲስ የስደት ማዕበል አስነሳ። ፕሮቴስታንቶች በመላው አካል ላይ ችግር ከመፍጠሩ በፊት መወገድ እንዳለበት አደገኛ ብጉንጅ ተደርገው መታየት ጀመሩ። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች ለመቀበል አሻፈረን ያሉ ብዙዎች በሕይወት እያሉ እንጨት ላይ ተሰቅለው እንዲቃጠሉ ተደርጓል።

በመናፍቃን ላይ የተፈጸመ ቅጣት

በሜሪ የግዛት ዘመን በመጀመሪያ የተገደለው ጆን ሮጀርስ ነው። ጆን ሮጀርስ ለኪንግ ጀምስ ቨርሽን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆኖ ያገለገለውን የማቲዉ መጽሐፍ ቅዱስ አጠናቅሮ ነበር። “መርዘኛ ከሆነው የካቶሊክ እምነት፣ ከጣዖት አምልኮና ከአጉል እምነቶች” እንዲጠበቁ በማስጠንቀቅ የሮማ ካቶሊክ እምነትን የሚያወግዝ የስብከት ንግግር ከሰጠ በኋላ ለአንድ ዓመት ታስሮ የካቲት 1555 ላይ በመናፍቅነት ተወንጅሎ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተደረገ።

የግሎስተርና የዉስተር ጳጳስ የነበሩት ጆን ሁፐርም መናፍቅ ተብለዋል። እኚህ ጳጳስ ቀሳውስት የማግባት ሕጋዊ መብት እንዳላቸውና ምንዝር የፈጸመን የትዳር ጓደኛን መፍታት እንደሚቻል የገለጹ ሰው ናቸው። በተጨማሪም ክርስቶስ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ በአካል ይገኛል የሚለውን እምነት አስተባብለዋል። ሁፐር በቁማቸው በእሳት ተጠብሰው እንዲሞቱ ተደርጓል። ከፍተኛ ሥቃይ የተሞላበት አሟሟታቸው አርባ አምስት ደቂቃ ገደማ የወሰደ ነበር። የ70 ዓመቱ የፕሮቴስታንት ሰባኪ ሁው ላቲመር ለእሳት አልፈው የሚሰጡበት ተራ በደረሰ ጊዜ የተሃድሶ አጋራቸው የሆነውንና ከጎናቸው የተሰቀለውን ኒኮላስ ሪድሊ በሚከተሉት ቃላት አበረታትተውታል:- “መምህር ሪድሊ፣ በርታ፣ ወንድ ሁን። በዛሬዋ ዕለት በአምላክ ፀጋ እንግሊዝ ውስጥ የምናበራው ሻማ ለዘላለም አይጠፋም።”

በሄንሪ እና በኤድዋርድ የግዛት ዘመን የመጀመሪያው የካንተርበሪ የፕሮቴስታንት ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቶማስ ክራንመርም መናፍቅ ተብለው ተወገዙ። የፕሮቴስታንት እምነቶቻቸውን ክደው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻዋ ሰዓት በሕዝብ ፊት አቋማቸውን በመለወጥ የሮማውን ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቶስ ጠላት ብለው ከማውገዛቸውም በላይ እምነታቸውን በካዱበት ጊዜ የፈረሙበትን ቀኝ እጃቸውን በመዘርጋት መጀመሪያ ላይ እንዲቃጠል አድርገዋል።

ቢያንስ ቢያንስ 800 የሚሆኑ ባለጠጋ ፕሮቴስታንቶች ራሳቸውን ለማዳን ወደ ሌላ አገር የሸሹ ቢሆንም ሜሪ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በቀጣዩ ሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ በእንግሊዝ ቢያንስ 277 ሰዎች እንጨት ላይ ተሰቅለው በእሳት ተቃጥለዋል። ብዙዎቹ ሰለባዎች የትኛውን እምነት መከተል እንዳለባቸው ፈጽሞ ግራ ተጋብተው የነበሩ ተራ ሰዎች ናቸው። ቀደም ሲል በሮማው ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ይሰነዘር የነበረውን ውግዘት እየሰሙ ያደጉ ወጣቶች አሁን እሳቸውን ሲነቅፉ በመደመጣቸው ይቀጡ ጀመር። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው ማንበብ ተምረው የራሳቸውን ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ፈጥረው ነበር።

እንጨት ላይ ተሰቅለው በእሳት ብዙ ከተሰቃዩ በኋላ የሞቱት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አሟሟት በብዙዎቹ ሰዎች ላይ ሽብር ለቀቀባቸው። የታሪክ ምሁሯ ካሮሊ ኤሪክሰን ቅጣቱ የሚፈጸምበትን ዓይነተኛ ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ብዙውን ጊዜ እሳቱን ለማንደድ የሚጠቀሙበት እንጨት እርጥበት ያለው ይሆናል አሊያም እሳቱን ለማያያዝ የሚያገለግሉት ጭራሮዎች በውኃ የራሱ ስለሚሆኑ ቶሎ አይቀጣጠሉም። የተቀጪዎቹን ሥቃይ ለማሳጠር ተብሎ ከሰውነታቸው ጋር የሚታሰረው የባሩድ ከረጢት አንድም ሳይቀጣጠል ይቀራል አለዚያም እንዲሁ የአካል ክፍላቸውን ብቻ ቆርጦ ሳይገድላቸው ይቀራል።” ቅጣቱ የሚፈጸምባቸው ሰዎች አፋቸው ስለማይታሰር “ብዙውን ጊዜ ሕይወታቸው እስከሚያልፍበት ጊዜ ድረስ ሲጮኹና ሲጸልዩ በደንብ ይሰማል።”

ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በርካታ ሰዎች ትምህርቶቹ ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማስገደድ ሲል ሰዎችን በእንጨት ላይ እየሰቀለ በእሳት በሚያቃጥለው በዚህ ሃይማኖት ላይ ጥርጣሬ እያደረባቸው መጣ። ሰዉ ለእነዚህ ሰለባዎች የሚሰማው አዘኔታ እያደገ በመምጣቱ ገጣሚዎች የፕሮቴስታንት ሰማዕታትን የሚያወድሱ መዝሙሮች ለማቀነባበር ተነሳሱ። ጆን ፎክስ ከጊዜ በኋላ በፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጆች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ማለት ይቻላል፣ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን ቡክ ኦቭ ማርቲርስ የተሰኘውን መጽሐፉን ማጠናቀር ጀመረ። በሜሪ የግዛት ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮማ ካቶሊኮች የነበሩ ብዙዎች በግዛት ዘመኗ ማብቂያ ላይ ፕሮቴስታንቶች ሆኑ።

ሜሪ ትታው ያለፈችው ቅርስ

ሜሪ ንግሥት ከሆነች በኋላ የስፔይን አልጋ ወራሽ የሆነውን የአጎቷን ልጅ ፊሊፕን እንደምታገባ ግልጽ አደረገች። ፊሊፕ የባዕድ አገር ንጉሥ ከመሆኑም በላይ ቀናተኛ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። ይህ ደግሞ ብዙዎቹ እንግሊዛውያን ፈጽሞ የማይመኙት ነገር ነበር። ፕሮቴስታንቶች ጋብቻውን በመቃወም ያካሄዱት ዓመፅ በቁጥጥር ሥር ዋለና 100 ዓማፅያን እንዲገደሉ ተደረገ። ፊሊፕ ዘውድ ባይደፋም እንኳ ከሜሪ ጋር ሐምሌ 25, 1554 ላይ ተጋቡ። ይሁን እንጂ ልጅ አለመውለዳቸው የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነ ወራሽ ትፈልግ ለነበረችው ሜሪ ትዳራቸው የሐዘን ምንጭ ሆነባት።

ሜሪ ጤና እያጣች በመሄዷ ለአምስት ዓመት ብቻ ከገዛች በኋላ በ42 ዓመቷ ሞተች። በሐዘን ጦር እንደተወጋች ወደ መቃብር ወረደች። ባሏ በጣም ተሰላችቶ የነበረ ሲሆን አብዛኛው ሕዝብም ጠልቷት ነበር። ሜሪ ስትሞት ብዙዎቹ የለንደን ነዋሪዎች በጎዳናዎች ላይ ፌሽታ አድርገዋል። አክራሪነቷ የሮማ ካቶሊክ እምነትን ዳግመኛ ከመገንባት ይልቅ ለፕሮቴስታንት እምነት መጠናከር አስተዋጽኦ አድርጓል። ትታው ያለፈችው ቅርስ ደም አፍሳሿ ሜሪ በተባለው መጠሪያዋ ጠቅለል ባለ መልኩ ተገልጿል።

ለተሳሳተ ተጽዕኖ ያደረ ሕሊና

ሜሪ በርካታ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ያዘዘችው ለምንድን ነው? መናፍቃን አምላክን የካዱ ናቸው የሚል ትምህርት ተሰጥቷት ስለነበረና እነዚህ መናፍቃን መላውን ሕዝብ ከመበከላቸው በፊት በሌሎች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ የመቅጨት ግዴታ እንዳለባት ሆኖ ስለተሰማት ነበር። የራሷን ሕሊና ድምፅ ስትታዘዝ ሕሊናቸው ወደ ሌላ አቅጣጫ የመራቸውን ሰዎች መብት ግን አላከበረችም።

ይሁን እንጂ ፕሮቴስታንቶችም የዚያኑ ያህል ጽንፈኞች ነበሩ። በሄንሪና በኤድዋርድ የግዛት ዘመንም ሰዎች በሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው ሳቢያ ለእሳት አልፈው ይሰጡ ነበር። በሜሪ እግር የተተካችው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይዋ ቀዳማዊት ኤሊዛቤት የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆን እንደ ክህደት የሚቆጠር ከባድ ወንጀል ነው የሚል ደንብ ያወጣች ሲሆን በእሷ የግዛት ዘመን ከ180 የሚበልጡ እንግሊዛውያን የሮማ ካቶሊኮች ተገድለዋል። በቀጣዩ ምዕተ ዓመት ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሃይማኖታዊ አስተሳሰባቸው ሳቢያ ተገድለዋል።

ዛሬ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ታኅሣሥ 10, 1998 የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የጸደቀበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የተከበረበት ዕለት ነበር። በዚህ ድንጋጌ ላይ የሚገኘው 18ኛው አንቀጽ ሃይማኖትን የመለወጥ፣ የማስተማርና ተግባራዊ የማድረግ ነፃነትን ጨምሮ አንድ ሰው “የማሰብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት” ያለው መሆኑን ይደነግጋል። የእንግሊዝና የዌልስ የሮማ ካቶሊክ ጳጳሳት 50ኛው ክብረ በዓል “ካቶሊኮች በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ሕሊናቸው ምን እንደሚል ለመመርመር” እና በተለይ በሜሪ ቱዶር ዘመን የተፈጸሙትን “ከባድ ስህተቶች” አምኖ ለመቀበል “ጥሩ አጋጣሚ” እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

በሃይማኖታዊ አለመቻቻል ሳቢያ ከ450 ዓመት ገደማ በፊት ለተፈጸሙ ድርጊቶች ዛሬ ይቅርታ ቢጠየቅም እንኳ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ የተለወጠ ነገር አለ? እርግጥ ዛሬ ሰዎች በእንጨት ላይ እየተሰቀሉ በእሳት አይቃጠሉም። ሆኖም ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሰዎችን አስገድደው ይደፍራሉ እንዲሁም ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ይጨፈጭፋሉ። እንዲህ ዓይነቱ ጽንፈኛነት አምላክን አያስደስተውም። እንዲያውም የአምላክን ስብዕና ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀው ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።​—⁠ዮሐንስ 13:​35

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንግሥት ሜሪ

[ምንጭ]

ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ዘ ኢንግሊሽ ፒፕል ከተባለው መጽሐፍ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ላቲመርና ሪድሊ በእንጨት ላይ ተሰቅለው በእሳት ተቃጥለዋል

[ምንጭ]

ፎክስስ ቡክ ኦቭ ማርቲርስ ከተባለው መጽሐፍ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክራንመር መጀመሪያ ቀኝ እጃቸው እንዲቃጠል አድርገዋል

[ምንጭ]

ዘ ሂስትሪ ኦቭ ኢንግላንድ (ጥራዝ 1) ከተባለው መጽሐፍ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በዙሪያው ያለው ሥዕል:- 200 Decorative Title-Pages/Alexander Nesbitt/Dover Publications, Inc.