በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?

ሚያዝያ 1999 አንድ ቀን ጠዋት ላይ ዩ ኤስ ኤ ኮሎራዶ ውስጥ ዴንቨር አቅራቢያ የምትገኘው የሊትልተን ከተማ ሰላምና ፀጥታ ተናጋ። ጥቁር የዝናብ ልብስ የለበሱ ሁለት ወጣቶች በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡና በተማሪዎችና በአስተማሪዎች ላይ የጥይት እሩምታ ከፈቱ። የያዟቸውንም ቦምቦች አፈነዱ። አሥራ ሁለት ተማሪዎችና አንድ አስተማሪ ሲገደሉ ከ20 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆሰሉ። ወጣቶቹ ጭፍጨፋውን የቋጩት የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት ነበር። ልጆቹ ገና የ17 እና የ18 ዓመት ወጣቶች ሲሆኑ ለተወሰኑ ቡድኖች ሥር የሰደደ ጥላቻ ነበራቸው።

የሚያሳዝነው ግን ከላይ የተጠቀሰው ምሳሌ የተለመደ ክስተት መሆኑ ነው። ጋዜጦች፣ ራዲዮና ቴሌቪዥን በዓለም ዙሪያ የተከናወኑ ተመሳሳይ ክስተቶችን ይዘግባሉ። የትምህርት መረጃዎች ብሔራዊ ማዕከል እንዳለው ከሆነ በ1997 በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀም ወደ 11, 000 የሚጠጉ የኃይል ድርጊቶች ተፈጽመዋል። በጀርመን ሃምቡርግ ውስጥ በ1997 ሪፖርት የሚደረጉት የኃይል ድርጊቶች ቁጥር 10 በመቶ የጨመረ ሲሆን ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው።

በፖለቲከኞችና በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ዘንድ ሙስና መፈጸም የተለመደ ነገር ነው። የአውሮፓ ኅብረት (ኢ ዩ) ኮሚሽነር የሆኑት አኒታ ግራዲን በ1998 ያወጡት ዘገባ በ1997 በኢ ዩ ውስጥ የተፈጸመው ሙስና 1.4 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እንዳስከተለ ያመለክታል። ይህ በተከለከሉ ቦታዎች ላይ መኪና ማቆም የሚያስከትለውን ክስ ከማሰረዝ አንስቶ ኢ ዩ ለግብርና ወይም ለሌሎች ጉዳዮች የሚሰጠውን የገንዘብ እርዳታ አጭበርብሮ እስከ መውሰድ የሚደርስ ነው። ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለተገኘ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሕጋዊ ሽፋን ሲሰጠውና ሕገወጥ የሆነ የጦር መሣሪያና የናርኮቲክ ዝውውር ሲካሄድ ምንም እርምጃ ያልተወሰደ ከመሆኑም በላይ የኢ ዩ ሠራተኞች ትንፍሽ እንዳይሉ ወንጀል ፈጻሚ ድርጅቶች ጉቦ ሰጥተዋቸዋል። መላው የኢ ዩ ኮሚሽን በ1999 ሥራውን በፈቃዱ ለቅቋል።

ይሁን እንጂ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙት በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኙት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ብቻ አይደሉም። የኢ ዩ ኮሚሽን ሕገወጥ ሠራተኞችን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ከኢ ዩ አጠቃላይ ብሔራዊ የምርት ውጤት መካከል 16 በመቶ የሚሆነው ሕጋዊ ዕውቅና ባላገኙና ግብር በማይከፍሉ የንግድ ድርጅቶች የሚገኝ ገቢ ነው። በሩስያ በሕገወጥ መንገድ የሚገኘው ገቢ ከጠቅላላው ገቢ 50 በመቶውን እንደሚሸፍን ተዘግቧል። ከዚህም በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉ የማጭበርበር ድርጊቶችን የሚመረምረው ማኅበር የአሜሪካ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው በሚፈጽሙት የገንዘብ ወይም የንብረት ዝርፊያ ሳቢያ በየዓመቱ ከ400 ቢልዮን ዶላር በላይ እንደሚያጡ ገልጿል።

ሕፃናትንና ልጆችን በማታለል ሕገወጥ ወሲባዊ ድርጊቶች እንዲፈጽሙ ለማድረግ የሚፈልጉ ሕፃናትን የሚያስነውሩ ብዙ ሰዎች ኢንተርኔትን መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። በስዊድን የሚገኘው የሕፃናት አድን ድርጅት ቃል አቀባይ እንዳሉት ከሆነ በኢንተርኔት የሚቀርቡት የሕፃናት ወሲባዊ ስዕሎች በጣም አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል። ይህ ድርጅት በ1997 ኖርዌይ ውስጥ በኢንተርኔት የሚተላለፉ የሕፃናት ወሲባዊ ስዕሎች የሚገኙባቸውን ዌብ ሳይቶች በተመለከተ 1, 883 ጥቆማዎች ደርሶታል። በቀጣዩ ዓመት የእነዚህ ጥቆማዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀብ 5, 000 ገደማ ደርሷል። ጽሑፉ በአብዛኛው የሚዘጋጀው መንግሥታት ወይም ባለሥልጣናት ይህን ወራዳ ድርጊት መቆጣጠር በማይችሉባቸው አገሮች ውስጥ ነው።

የቀድሞው ዘመን ይሻል ነበር?

በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ላይ በሚታየው መጥፎ የሥነ ምግባር ሁኔታ በእጅጉ የተረበሹ በርካታ ሰዎች በወላጆቻቸው ወይም በአያቶቻቸው ዘመን የነበረውን ማኅበረሰባዊ መንፈስ ይመኙት ይሆናል። በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ይበልጥ የተረጋጋ ሕይወት ይመሩ እንደነበረና ሐቀኝነትና ሌሎች የሥነ ምግባር ዘርፎች በሁሉም ደረጃ ላይ በሚገኙ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ዘንድ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣቸው እንደነበረ ሰምተው ይሆናል። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቀደም ባለው ዘመን ትጉህ ሠራተኞች እርስ በርስ ይረዳዱ እንደነበረ፣ የቤተሰብ ትስስር ጠንካራ እንደነበረ እንዲሁም ወጣቶች የመረጋጋት ስሜት እንደነበራቸውና በወላጆቻቸው የእርሻ ቦታ ወይም የእጅ ሥራዎች በሚሠሩባቸው ቦታዎች ወላጆቻቸውን ይረዱ እንደነበረ ይናገሩ ይሆናል።

ይህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል:- በእርግጥ በቀድሞው ዘመን የነበረው የሰዎች ሥነ ምግባር የተሻለ ነበር? ወይስ እንዲሁ አንዳንድ አስደሳች ትዝታዎች ላለፉት ጊዜያት ያለንን አመለካከት አዛብተውት ይሆን? የታሪክ ምሁራንና ሌሎች የማኅበራዊ ሕይወት ተንታኞች የሚሰጡትን መልስ እንመልከት።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሥነ ምግባር ፍቺ

በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ “ሥነ ምግባር” የሚለው ቃል የተሠራበት በሰው ልጅ ምግባር ረገድ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ከሚጠቁሙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በተያያዘ መንገድ ነው። ይህም ሐቀኝነትን፣ እውነተኛ መሆንንና በወሲብና በሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ የምግባር መሥፈርቶችን መጠበቅን ይጨምራል።