በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ከቀድሞው ዘመን የከፋ ነውን?

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ከቀድሞው ዘመን የከፋ ነውን?

በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ከቀድሞው ዘመን የከፋ ነውን?

የታሪክ ምሁራንን “በዛሬው ጊዜ ያለው የሰዎች ሥነ ምግባር ከቀድሞው ዘመን የተሻለ ነው ወይስ የከፋ?” ብላችሁ ብትጠይቋቸው አንዳንዶቹ በተለያዩ ጊዜያት የነበረውን የሥነ ምግባር ሁኔታ ማወዳደር አስቸጋሪ ነው ብለው ይመልሱላችሁ ይሆናል። እያንዳንዱ ዘመን መፈረጅ ያለበት በጊዜው ከነበረው ሁኔታ አንጻር ነው የሚል እምነት ይኖራቸው ይሆናል።

ለምሳሌ ያህል ከ16ኛው መቶ ዘመን አንስቶ በአውሮፓ ውስጥ የታየውን የከባድ ወንጀሎች መበራከት ተመልከት። ከዛሬ 400 ዓመታት በፊት ነፍስ ግድያ እምብዛም ያልተለመደ ነገር አልነበረም። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ራሳቸው ፈላጭ ቆራጮች ሆነው የመሰላቸውን ያደርጉ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቂም በቀል የተለመደ ነገር ነበር።

ይሁን እንጂ የታሪክ ምሁራን የሆኑት አርነ ያሪክ እና ዮሃን ሶደርቤር ማኒስኮቫርደት ኦክ ማክተን (ሰብዓዊ ክብርና ሥልጣን) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከ1600 እስከ 1850 ድረስ የነበረው ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች “እውነተኛ የማኅበራዊ ኑሮ ሥልጣኔ የታየበት ዘመን” ነበር ሲሉ ጽፈዋል። ሰዎች የሌሎችን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ረገድ የተሻሉ ሆነው ከመገኘታቸውም በላይ ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ የሌሎችን ስሜትና ችግር የሚረዱ ሆነው ነበር። ለምሳሌ ያህል ሌሎች የታሪክ ምሁራን በ16ኛው መቶ ዘመን የነበረው ስርቆትና በንብረት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ከአሁኑ ዘመን ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይ በገጠሩ ሕዝብ መካከል ዝርፊያ የሚፈጽሙ የተደራጁ ወንጀለኞች እምብዛም አልነበሩም።

እርግጥ፣ የባርነት ሥርዓት የነበረ ሲሆን በታሪክ ውስጥ እጅግ ከባድ የሆኑ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። የአውሮፓ ነጋዴዎች ከአፍሪካ ሰዎችን እያፈኑ ይወስዱ የነበረ ከመሆኑም በላይ እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተወሰዱባቸው አገሮች ውስጥ አረመኔያዊ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል።

በመሆኑም ያለፉትን መቶ ዘመናት መለስ ብለን ከተመለከትን ከታሪክ አመለካከት አንጻር ሲታይ አንዳንዶቹ ሁኔታዎች የተሻሉ፣ ሌሎቹ ሁኔታዎች ደግሞ የከፉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ሆኖም በጣም ለየት ያለና በጣም ከባድ የሆነ፣ እንዲያውም ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ነገር በ20ኛው መቶ ዘመን የተከናወነ ሲሆን አሁንም በመከናወን ላይ ይገኛል።

ሥር ነቀል ለውጥ የታየበት 20ኛው መቶ ዘመን

የታሪክ ምሁራኑ ያሪክ እና ሶደርቤር “በ1930ዎቹ ዓመታት የነፍስ ግድያ ወንጀል እንደገና እየተበራከተ የመጣ ሲሆን የሚያሳዝነው ነገር ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህ አዝማሚያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ባለበት መልኩ ቀጥሏል” ሲሉ ገልጸዋል።

በርካታ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን የሥነ ምግባር ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። አንድ በግብረ ገብ ላይ ያተኮረ መጣጥፍ እንዲህ ይላል:- “ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ኅብረተሰቡ ለወሲብ ያለው አመለካከትና ከሥነ ምግባር አኳያ ተቀባይነት ያለው ነገር በእጅጉ ተለውጧል። በቀድሞው ዘመን ኅብረተሰቡ ጥብቅ በሆኑ ደንቦች አማካኝነት ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክል የሆነውን ነገር በግልጽ ያስቀምጥ የነበረ ሲሆን ዛሬ ዛሬ ግን ይበልጥ ነፃ የሆነና ግላዊነት የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ነግሷል።”

ይህ ማለት በዛሬው ጊዜ ሰዎች ወሲባዊ ምግባርንና ሌሎች የሥነ ምግባር ዘርፎችን በተመለከተ ሊመሩበት የሚገባውን ሥርዓት ራሳቸው ለራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል ማለት ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት መጣጥፉ በ1960 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከነበሩት ሕፃናት መካከል ከጋብቻ ውጪ የተወለዱት 5.3 በመቶዎቹ ብቻ እንደነበሩ ይጠቅሳል። በ1990 ግን ይህ አኃዝ 28 በመቶ ደርሷል።

የዩ ኤስ ሴናተር የሆኑት ጆ ሊበርማን በኖተር ዴም በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በሰጡት ንግግር ላይ በዘመናችን ያለው ሥነ ምግባር “ደንብና ሥርዓት የጎደለው ነው። . . . ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ቀደም ሲል የነበሩት አስተሳሰቦች ቀስ በቀስ እየከሰሙ ሄደዋል” ሲሉ ገልጸዋል። እንደ ሊበርማን አባባል ከሆነ ይህ ክስተት “በአብዛኛው በሁለት ትውልዶች ዘመን ሲጠነሰስ የቆየ ነው።”

ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ መላቀቅ

የታሪክ ምሁራንና ሌሎች ተንታኞች በ20ኛው መቶ ዘመን ለተከሰተው ለዚህ አስገራሚ ለውጥ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ምንድን ነው? “ባለፉት ሁለት መቶ ዘመናት በኅብረተሰቡ ውስጥ ከተከሰቱት ታላላቅ ለውጦች አንዱ ሰዎች ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ መላቀቃቸው ነው” ይላል ማኒስኮቫርደት ኦክ ማክተን የተባለው መጽሐፍ። ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ መላቀቅ ሲባል “ሰዎች በተለያዩ አመለካከቶች ላይ በራሳቸው የራሳቸውን አቋም መውሰድ የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ” ማለት ነው። “ይህን አስተሳሰብ ያመነጩት . . . ብቸኛው የእውነት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚለውን እምነት በግንባር ቀደምትነት ያጣጣሉት . . . የ18ኛው መቶ ዘመን የፍልስፍና አራማጆች ናቸው።” በዚህ ሳቢያ ኅብረተሰቡ ከሃይማኖቶች በተለይ ደግሞ ከሕዝበ ክርስትና ሥነ ምግባራዊ መመሪያ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት እየቀነሰ ሄደ።

ይሁን እንጂ በ18ኛው መቶ ዘመን የተጠነሰሰ ፍልስፍና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከ200 የሚልቁ ዓመታት የፈጀበት ለምንድን ነው? “እነዚህ አስተሳሰቦች በቀላሉ ወደ ሕዝቡ ሊሰራጩ አልቻሉም ነበር” ይላል ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ። “ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ለመላቀቅ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አዝጋሚ ነበር።”

የቆዩ የሥነ ምግባር መስፈርቶችን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ደንቦችንና ሥርዓቶችን እርግፍ አድርጎ የመተዉ ሂደት ባለፉት 200 ዓመታት በአብዛኛው አዝጋሚ የነበረ ቢሆንም በ20ኛው መቶ ዘመን ግን ከፍተኛ ፍጥነት አሳይቷል። በተለይ ደግሞ ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ይህ ሁኔታ በእጅጉ ተንጸባርቋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት

ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር በ20ኛው መቶ ዘመን በኅብረተሰቡ መካከል የታየው ፈጣን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እድገት ነው። ዲ ሳይት በተባለው የጀርመን የዜና መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ዛሬ የምንኖረው “በቀድሞዎቹ መቶ ዘመናት እንደነበረው በሰከነ ዓለም ውስጥ ሳይሆን እጅግ ተነዋዋጭ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው” ይላል። ይህም በውድድር ላይ የተመሠረተውንና በራስ ወዳድነት ግፊት የሚንቀሳቀሰውን የነፃ ገበያ ሥርዓት እንዳስከተለ ጽሑፉ ይናገራል።

“ይህን ራስ ወዳድነት” ይላል ጽሑፉ ሲቀጥል፣ “ምንም ነገር ሊገታው አይችልም። ይህም በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ጎልቶ የሚታየውን ጭካኔና በብዙ አገሮች ውስጥ መንግሥታት ሳይቀሩ የተተበተቡበትን ሙስና አስከትሏል። ሰዎች የሚያስቡት ስለ ራሳቸውና ፍላጎቶቻቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማርካት ስለሚችሉባቸው መንገዶች ነው።”

የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት የማኀበራዊ ሳይንስ አጥኚው ሮበርት ዉትናው ባካሄዱት ጥልቅ ጥናት በዛሬው ጊዜ ያሉት አሜሪካውያን ለገንዘብ የሚሰጡት ትኩረት ከቀድሞው ትውልድ ይበልጥ እንዳየለ መረዳት ችለዋል። ጥናቱ እንደሚለው ከሆነ “ብዙዎቹ አሜሪካውያን ሰዉ ገንዘብ ለማግኘት ያለው ጉጉት ለሌሎች አክብሮት ማሳየትን፣ በሥራ ቦታ ሐቀኛ መሆንን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግንና ሌሎችንም ሥነ ምግባራዊ ሥርዓቶች እያፈራረሰ ነው የሚል ስጋት አለባቸው።”

በኅብረተሰቡ ውስጥ ስግብግብነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ያደረገው ሌላው ነገር በተለያዩ ኩባንያዎች የኃላፊነት መንበር ላይ የተቀመጡ ብዙዎቹ ሰዎች በአንድ በኩል ሠራተኞቻቸው ከልክ ያለፈ የደሞዝ ጥያቄ እንዳያቀርቡ አጥብቀው እያሳሰቡ በሌላ በኩል ግን ራሳቸው ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪና ጠቀም ያለ የጡረታ ክፍያ የሚያገኙበትን መንገድ የሚያመቻቹ መሆኑ ነው። “የንግድ ድርጅት ኃላፊዎች ጥቅም የሚያሳድዱ መሆናቸው የሚያስከትለው ችግር ቢኖር አመለካከታቸው ተዛማች ከመሆኑም በላይ በጥቅሉ የሰዉን የሥነ ምግባር ደረጃ ዝቅ የሚያደርገው መሆኑ ነው” ሲሉ በግብረ ገብ ተባባሪ ፕሮፌሰርና በስዊድን የክርስቲያን ካውንስል የቲኦሎጂ ዲሬክተር የሆኑት ቼል ዩቨ ኒልሰን ተናግረዋል። “ይህ በኅብረተሰብም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በሥነ ምግባር ላይ ከፍተኛ ውድቀት እንደሚያስከትል የታወቀ ነው።”

የመገናኛ ብዙሃን ባሕል

በ20ኛው መቶ ዘመን የኋለኛ አጋማሽ ላይ ለታየው ፈጣን የሥነ ምግባር ውድቀት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ሌላው ነገር የመገናኛ ብዙሃን ባሕል ነው። “አዳዲሶቹን ደንቦችና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያሰራጩት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጂዎች፣ ታላላቅ የፊልም ሰዎች፣ የፋሽን አስተዋዋቂዎች፣ ጋንግስታ ራፕ ተብሎ የሚጠራው ሙዚቃ አቀንቃኞች እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ብዙሃን ባሕል መስክ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሌሎች በርካታ ሰዎች ናቸው” ይላሉ ሴናተር ሊበርማን። “የተለያዩ አዝማሚያዎች የሚፈጥሩት እነዚህ ሰዎች በባሕላችንና በተለይ ደግሞ በልጆቻችን ላይ በጣም ከባድ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ እያስተላለፉት ላሉት ጎጂ የሥነ ምግባር ደንብና ሥርዓት ምንም ዓይነት ኃላፊነት አይሰማቸውም።”

ሊበርማን ካኒባል ኮርፕስ ተብሎ የሚጠራ አንድ የሄቪ ሜታል የሙዚቃ ጓድ ያወጣውን አንድ ዘፈን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ዘፋኞቹ በዘፈናቸው ውስጥ አንዲት ሴት ስለት በያዘ ሰው እንዴት እንደተደፈረች አንድ በአንድ ይዘረዝራሉ። እሳቸውና አንድ ባልደረባቸው ሙዚቃውን የቀረጸው ኩባንያ ሙዚቃውን እንዲያስቀረው ተማፅነው የነበረ ቢሆንም ሰሚ እንዳላገኙ ሊበርማን ተናግረዋል።

ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች የልጆቻቸውን አስተሳሰብ ለመቅረጽና ልጆቻቸውን ኮትኩተው ለማሳደግ ከመገናኛ ብዙሃን ባሕል ጋር ከባድ ግብ ግብ ገጥመዋል። ይሁን እንጂ ጠንቃቃ ባልሆኑ ወላጆች የሚተዳደሩ ቤተሰቦችስ? “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ” ይላሉ ሊበርማን፣ “የመገናኛ ብዙሃኑ ባሕል ያላንዳች ተቀናቃኝ የራሱን የሥነ ምግባር ደንብና ሥርዓት ያራምዳል። ልጁ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የሚኖረው አመለካከት እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በአብዛኛው ከቴሌቪዥን፣ ከፊልምና ከሲዲ ማጫወቻዎች በሚማራቸው ነገሮች ላይ የተመኩ ይሆናሉ።” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደታየው ደግሞ ኢንተርኔትም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይችላል።

ወደ “ድንጋይ ዘመን ምግባር” መመለስ

እነዚህ አሉታዊ ተጽዕኖዎች የሚያስከትሉት ውጤት በወጣቶች ላይ በግልጽ እየተንጸባረቀ ያለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በሌሎች ልጆችና ዐዋቂዎች ላይ ጭካኔ የተሞላባቸው የኃይል ድርጊቶች ፈጽመዋል።

በ1998 ስዊድን ውስጥ አንድ አስደንጋጭ ድርጊት ተፈጽሟል። በአምስትና በሰባት ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሁለት ወንዶች ልጆች አብሯቸው ይጫወት የነበረን አንድ የአራት ዓመት ሕፃን አንቀው ገድለዋል! ብዙዎች ለመሆኑ ልጆች በጣም ርቀው ሲሄዱ በቃችሁ የሚል በተፈጥሮ ያገኙት የሕሊና ደወል የላቸውም? የሚል ጥያቄ አንስተዋል። አንዲት የሥነ አእምሮ ባለሙያ “ልጆች በጣም ርቀው በሚሄዱበት ጊዜ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ የሚችሉት በሚያገኙት ትምህርት ነው” በማለት ትልቅ ትርጉም ያዘለ አስተያየት ሰንዝረዋል። “ይህ ልጆች እንደ ምሳሌ አድርገው በመመልከት በሚኮርጁአቸው ሰዎች ሁኔታና አብረዋቸው ካሉት ዐዋቂ ሰዎች በሚቀስሙት ትምህርት ላይ . . . የተመካ ሊሆን ይችላል።”

ከባድ ወንጀለኞችም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊታይባቸው ይችላል። በስዊድን የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቴን ሌቫንደር እንዳሉት ከሆነ በዛሬው ጊዜ ካሉት እስረኞች መካከል ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት የሥነ አእምሮ ችግር ያለባቸው ማለትም ከልክ በላይ ራስ ወዳዶች የሆኑ፣ ርኅራኄ የሚባል ነገር የሌላቸውና ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተው የማይረዱ ወይም ለመረዳት ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ጤናማ መስለው የሚታዩ ልጆችና ወጣቶች እንኳ የሥነ ምግባር ስሜታቸው የደነዘዘ መሆኑን ባለሙያዎች አስተውለዋል። “ወደ ድንጋይ ዘመን ምግባር ተመልሰናል” ሲሉ የፍልስፍና ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስቲና ሆፍ ሶመርስ ተናግረዋል። ወጣት ተማሪዎቻቸው ትክክልና ስህተት የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ አብዛኞቹ ግራ የመጋባት ስሜት እንደተነበበባቸው ገልጸዋል። ከዚያም ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር የለም የሚል መልስ ሰጥተዋል። እንደ እነሱ እምነት እያንዳንዱ ሰው ለራሱ የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን ነገር መወሰን መቻል ይኖርበታል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከተማሪዎቻቸው መካከል ብዙዎቹ ለሰብዓዊ ሕይወት ለየት ያለ ክብርና ከፍ ያለ ዋጋ መሰጠት አለበት የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት መቃወም ጀምረዋል። ለምሳሌ ያህል ከቤት እንስሳቸውና ከአንድ ከማያውቁት ሰው ሕይወት አንዱን የማዳን ምርጫ ከፊታቸው ቢደቀን ምን እንደሚያደርጉ በተጠየቁ ጊዜ ብዙዎቹ እንስሳውን ማዳን እንደሚመርጡ ተናግረዋል።

“ይህ የሆነው ወጣቶች መሃይሞች፣ ተጠራጣሪዎች፣ ጨካኞች ወይም ከሃዲዎች ሆነው አይደለም” ይላሉ ፕሮፌሰር ሶመርስ። “እንደ እውነቱ ከሆነ ልጆቹ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ምንም ዓይነት ጽንሰ ሐሳብ የላቸውም።” ፕሮፌሰሯ በዛሬው ጊዜ ያሉት ብዙዎቹ ወጣቶች በእርግጥ ትክክልና ስህተት የሚባል ነገር መኖሩን እንደሚጠራጠሩ የገለጹ ሲሆን ይህ ዝንባሌ ለኅብረተሰቡ በጣም አስጊ እንደሆነ ያምናሉ።

ስለዚህ በዘመናችን የሥነ ምግባር ደረጃ እያሽቆለቆለ መሄዱ በግልጽ የሚታይ ሐቅ ነው። ብዙዎች ይህ ሁኔታ አስከፊ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለባቸው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው ዲ ሳይት በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “የሶሻሊስት ሥርዓት በቅርቡ እንደተንኮታኮተ ሁሉ” በዛሬው ጊዜ ያለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚም ቀስ በቀስ “እየተሸረሸረ ሊሄድና አንድ ቀን ሊወድቅ ይችላል” ይላል።

ይህ ሁሉ ምን ማለት ነው? ወደፊትስ ምን ዓይነት ጊዜ ይመጣል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“አዳዲሶቹን ደንቦችና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያሰራጩት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጂዎች፣ ታላላቅ የፊልም ሰዎች፣ የፋሽን አስተዋዋቂዎች [እና ] ጋንግስታ ራፕ ተብሎ የሚጠራው ሙዚቃ አቀንቃኞች . . . ናቸው”