በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን ማምለክ ተገቢ ነውን?

ኢየሱስን ማምለክ ተገቢ ነውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ኢየሱስን ማምለክ ተገቢ ነውን?

ባለፉት መቶ ዘመናት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ክር​ስቶስን ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አድርገው ሲያመልኩት ኖረዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ ሰዎች ትኩረታቸውን በአምላክ ላይ እንዲያደርጉና ይሖዋን ብቻ እንዲያመልኩ አበረታቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን ወድቀህ ስገድልኝ ብሎ በገፋፋው ጊዜ ‘ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአል በማለት መልሶለታል። (ማቴዎስ 4:​10) ቆየት ብሎም ኢየሱስ “አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቷቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 23:​9

ሰዎች ለአምላክ መስጠት ያለባቸውን የአምልኮ ዓይነት ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ገልጾላታል። አምልኮአቸው በመንፈስና በእውነት የሚቀርብ መሆን አለበት። በእርግጥ “አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና።” (ዮሐንስ 4:​23, 24) አዎን፣ አምልኮታዊ ክብር መሰጠት ያለበት ለአምላክ ብቻ ነው። ለማንኛውም ሰው ወይም ለማንኛውም ነገር አምልኮ ማቅረብ በዕብራይስጥና በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተወገዘውን የጣዖት አምልኮ መፈጸም ማለት ይሆናል።​—⁠ዘጸአት 20:​4, 5፤ ገላትያ 5:​19, 20

አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስ ግን ኢየሱስንም ጭምር ማምለክ እንዳለብን ያመለክት የለም እንዴ? ጳውሎስ በዕብራውያን 1:​6 ላይ:- “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ [ለኢየሱስ] ይስገዱ” ሲል ተናግሮ የለምን?’ በማለት ይህን ሐሳብ ይቃወሙ ይሆናል። ታዲያ ይህንን ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጣዖት አምልኮ ከሚናገረው አንጻር እንዴት ልንረዳው እን​ችላለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ለአምልኮ የሚሰጠው ፍቺ

በመጀመሪያ ጳውሎስ እዚህ ላይ ስግደት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ኘሮስኪይኒዮ የሚል ሲሆን በአንገር የተዘጋጀው ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚገልጸው ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም “አክብሮትን ለመግለጽ የአንድን ሰው እጅ መሳም” ማለት ነው። በዊልያም ኢ ቫይን የተዘጋጀው አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንደሚለው ይህ ቃል “ለሰዎችም ሆነ ለአምላክ አክብሮት ማሳየትን ያመለክታል።” በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ኘሮስኪይኒዮ የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ሥልጣን ላለው ሰው ተጎንብሶ መስገድን የሚጨምር ነበር።

ኢየሱስ ከጌታው የተበደረውን ብዙ ገንዘብ መክፈል ስላቃተው አንድ ባሪያ የተናገረውን ምሳሌ ተመልከት። ኘሮስኪይኒዮ የሚለው የግሪክኛ ቃል ርቢ በምሳሌው ውስጥ ተጠቅሷል። ይህንን ቃል ኪንግ ጀምስ ቨርሽን “ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና (የኘሮስኪይኒዮ ርቢ ነው) [ለንጉሡ]:- ጌታ ሆይ፣ ታገሠኝ፣ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው” በማለት አስቀምጦታል። (ማቴዎስ 18:​26፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ታዲያ እንዲህ ሲባል ሰውዬው የጣዖት አምልኮ ፈጽሞአል ማለት ነው? በፍጹም! ጌታውና አለቃው ለሆነው ንጉሥ የሚገባውን አክብሮት ማሳየቱ ብቻ ነው።

እንደዚህ የመሰሉት የእጅ መንሳት ልማዶች ወይም ሌሎች የአክብሮት መግለጫዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በሚታወቁት የምሥራቅ ሰዎች ዘንድ የተለመዱ ነበሩ። ያዕቆብ ወንድሙን ኤሳውን ሲያገኘው ሰባት ጊዜ ወደ ምድር ሰግዷል። (ዘፍጥረት 33:​3) ዮሴፍ በግብጽ ቤተ መንግሥት የነበረውን ሥልጣን በማክበር ወንድሞቹ በፊቱ ሰግደዋል ወይም እጅ ነስተውታል። (ዘፍጥረት 42:​6) ከዚህ አንጻር ኮከብ ቆጣሪዎቹ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ” በማለት የጠሩትን ሕፃኑን ኢየሱስን ሲያገኙት የተከናወነውን ነገር በተሻለ ሁኔታ መረዳት እንችላለን። የኪንግ ጀምስ ቨርሽን “ወድቀውም ሰገዱለት [ኘሮስኪይኒዮ]” በማለት ተርጉሞታል።​—ማቴዎስ 2:​2, 11

ስለዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “መስገድ” ተብሎ የተተረጎመው ኘሮስኪይኒዮ የተባለው የግሪክኛ ቃል ለይሖዋ አምላክ የሚሰጠውን አምልኮታዊ ክብር ብቻ ሳይሆን በተለምዶ ለሰው የሚሰጠውን አክብሮትም ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚያሻማ መልእክት ላለማስተላለፍ ሲሉ ዕብራውያን 1:​6 ላይ የሚገኘውን ኘሮስኪይኒዮ የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ብለው ተርጉመውታል:- “ማደግደግ” (ኒው ጀሩሳሌም ባይብል)፤ “አክብሮት ማሳየት” (ዘ ኮምኘሊት ባይብል ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ)፤ “በፊቱ መጎንበስ (ትዌንቲዝ ሴንቸሪ ኒው ቴስታመንት)፤ ወይም “እጅ መንሳት” (የአዲሲቱ አለም ትርጉም።)

ኢየሱስ ልዩ አክብሮት ይገባዋል

ኢየሱስ እንዲህ ያለ ልዩ አክብሮት ሊሰጠው ይገባልን? እንዴታ! ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ሁሉን ወራሽ” የሆነው ኢየሱስ “በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” በማለት ገልጿል። (ዕብራውያን 1:​2-4) ይህም “በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”​—ፊልጵስዩስ 2:​10, 11

በቅርቡ ኢየሱስ የተሰጠውን ይህን ከፍተኛ ቦታና በዚያ ምክንያት ያገኘውን ትልቅ ሥልጣን በመጠቀም ይህችን ምድር ዓለም አቀፋዊ ገነት ያደርጋታል። በአምላክ አመራር በመደገፍና ቤዛዊ መሥዋዕቱ ባስገኘው ውጤት በመጠቀም ለጽድቅ አገዛዙ ራሳቸውን ለሚያስገዙት ሰዎች ጥቅም ሲል ሐዘንን፣ ጩኸትንና ስቃይን ሙሉ በሙሉ ከምድር ላይ ያስወግዳል። ታዲያ ኢየሱስን ብናከብረው፣ ከፍ ከፍ ብናደርገውና ብንታዘዝለት ይበዛበታልን?​—⁠መዝሙር 2:​12፤ ኢሳይያስ 9:​6፤ ሉቃስ 23:​43፤ ራእይ 21:​3, 4

“ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የሚፈልግ አምላክ”

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያመለክተው በአምልኮ መልክ የሚቀርብ ሃይማኖታዊ ክብርና አምልኮታዊ ፍቅር ሊሰጠው የሚገባው አምላክ ብቻ ነው። ሙሴ “ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የሚፈልግ አምላክ” ነው ሲል ገልጾታል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል።​—⁠ዘዳግም 4:​24፤ ራእይ 14:​7

ኢየሱስ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ድርሻ አለው። እውነትም ሊከበርና ከፍ ከፍ ሊደረግ ይገባዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:​20, 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5) ወደ ይሖዋ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችለን ብቸኛው መንገድ እርሱ ነው። (ዮሐንስ 14:​6) በዚህ መሠረት እውነተኛ ክርስቲያኖች አምልኮታቸውን ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ ለይሖዋ ብቻ ማቅረባቸው የተገባ ነው።