በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ ሞላ የሚስፈነጠሩት ካንጋሮዎች

እንደ ሞላ የሚስፈነጠሩት ካንጋሮዎች

እንደ ሞላ የሚስፈነጠሩት ካንጋሮዎች

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“በየቀኑ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስመለስ ለማዳው ካንጋሮዬ ጆዪ የግቢያችን በር ላይ ተቀምጦ ይጠብቀኛል” ሲል ጆን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል። “በሩን እንደከፈትኩ ይዘልና በፊት እግሮቹ ያቅፈኛል፣ እኔም አቅፈዋለሁ። ሁለታችንም ‘ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል!’ የሚል መልእክት ያዘለ አካላዊ መግለጫ እንለዋወጣለን። ከዚያም ጆዪ ጥቂት ሜትሮች ፈንጠር ብሎ ልክ እንደሚቦርቅ ውሻ ወደፊትና ወደ ኋላ እየዘለለ ወደ ቤት እናመራለን።”

በአውስትራሊያ ገለልተኛ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ልክ እንደ ጆን ቤተሰብ ካንጋሮዎችን ቤታቸው እንዲያሳድጉ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል። ሰዎች በአብዛኛው ቤታቸው ወስደው የሚያሳድጉት እናቶቻቸው ምናልባት መንገድ ለማቋረጥ በሚሞክሩበት ጊዜ የሞቱባቸውን ግልገሎች ነው። ጆን ካንጋሮውን “ጆዪ” ብሎ ይሰይመው እንጂ ቃሉ የካንጋሮ ግልገሎች የሚጠሩበት የተለመደ ስም ነው።

ጆዪውን የሚያሳድገው ቤተሰብ ግልገሉ ወዲያውኑ እንዲላመድ ማድረግ እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ ከሚያዘጋጁለት ነገር አንዱ ኪስ ነው። ጥሩ መጠለያ ያለው ቦታ ይመርጡና ከምድጃ የሚወጣውን ሙቀት ተስማሚ በሆነ መጠን ሊያገኝ በሚችልበት ርቀት ላይ ከካንጋሮ ኪስ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ጠባብ ቀዳዳ ያለው አንድ ጠንካራ የሆነ ትልቅ የጨርቅ ከረጢት በምስማር ይመታሉ። ከዚያም ጆዪውን ለየት ባለ መንገድ የተዘጋጀ ሞቅ ያለ ወተት የያዘ ጡጦ አስታቅፈው እዚህ ኪስ ውስጥ ያስቀምጡታል። በዚህ መንገድ ብዙ ጆዪዎችን ከሞት ማትረፍ ተችሏል። ጆዪዎቹ ከአዲሱ ኪስ ጋር ወዲያው ይላመዱና የእናታቸውን ኪስ ያገኙ ይመስል ጭንቅላታቸውን አስቀድመው ጥልቅ ይላሉ።

ካንጋሮዎችን እንዴት አድርገህ ትገልጻቸዋለህ?

ግልገሎቻቸውን ኪሳቸው ውስጥ የሚያሳድጉ እንስሳት ኪሴዎች (marsupials) በመባል ይታወቃሉ። ኪሴዎች ወደ 260 የሚጠጉ ዝርያዎች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል ካንጋሮ፣ ኮአላ፣ ዎምባት፣ ባንዲኩት እና ከኪሴ ዝርያዎች መካከል በተፈጥሮ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ብቸኛው የኦፖሰም ዝርያ ይገኙባቸዋል። መገመት እንደሚቻለው የጥንቶቹ አገር አሳሾች ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ እነዚህን ለየት ያሉ እንስሳት በተለይ ደግሞ ካንጋሮን ለአገራቸው ሰዎች ገልጾ ለማስረዳት ተቸግረው ነበር። “ካንጋሮ” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝኛ ጽሑፍ ያሰፈረው ብሪታንያዊው አሳሽ ካፒቴን ጀምስ ኩክ ነው። ይህን እንስሳ ‘እንደ ጥንቸል ወይም አጋዘን ከሚዘል ግሬይሆውንድ የተሰኘ ውሻ’ ጋር ነበር ያመሳሰለው። ከጊዜ በኋላ አንድ ሕያው ካንጋሮ ለንደን ውስጥ ለሕዝብ እይታ በቀረበበት ጊዜ በሕዝቡ ዘንድ ልዩ ስሜት ፈጥሮ ነበር።

ካንጋሮዎች ከአጋዘን ጋር በሚመሳሰለው ጭንቅላታቸው ላይ ወዲያና ወዲህ የሚዞሩ ትልልቅ ጆሮዎች አሏቸው። ትንንሽ ሆኖም ኃይለኛ የሆኑት የፊት ቅልጥሞቻቸው በተለይ ቀጥ ብለው በሚቆሙበት ጊዜ ከሰው ክንድ ጋር ይመሳሰላሉ። በተጨማሪም ካንጋሮዎች ትልልቅ የሆኑና በጡንቻ የፈረጠሙ ዳሌዎች፣ ረጅም፣ ወፍራምና ጠመዝማዛ ጅራት እንዲሁም “ረጅም እግር” የሚል ትርጓሜ ያለው “ማክሮፖዲዴ” የሚል ሌላ ስያሜ ያሰጣቸው ትልቅ እግር አላቸው።

ወደ 55 የሚጠጉት የማክሮፖዲዴ ዝርያዎች በሰው ቁመት ልክ ካሉት አንስቶ አይጥ እስከሚያክሉት ድረስ የተለያየ መጠን ያላቸው ናቸው። ሁሉም የማክሮፖዲዴ ዝርያዎች አጫጭር የፊት ቅልጥሞችና ለመዝለል የሚያገለግሉ ረጃጅም የኋላ ቅልጥሞች አሏቸው። ትልልቆቹ ዝርያዎች ቀይ ካንጋሮዎች፣ ግራጫ ካንጋሮዎች እና ዎላሩዎች ወይም ዩሮዎች ናቸው። አንድ ተባዕት ቀይ ካንጋሮ ከአፍንጫው አንስቶ እስከ ጅራቱ ጫፍ ድረስ 200 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ የሚኖረው ሲሆን 77 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ትንንሾቹ የካንጋሮ ዝርያዎች ደግሞ ዎላቢዎች በመባል ይታወቃሉ።

በዛፎች ላይ የሚኖር ካንጋሮ አይተህ ወይም ስለ እንዲህ ዓይነቱ ካንጋሮ ሲነገር ሰምተህ ታውቃለህ? የዛፍ ካንጋሮ የሚባል “ጦጣ” የካንጋሮ ዝርያ መኖሩን ስታውቅ በጣም ትገረም ይሆናል። በኒው ጊኒና በሰሜናዊ ምሥራቅ አውስትራሊያ ጥቅጥቅ ባለው የሐሩር ክልል ጫካ ውስጥ የሚገኙትና መኖሪያቸው ከሆኑት ዛፎች ጋር የተላመዱት እነዚህ አጭር ቅልጥም ያላቸው እጅግ ቀልጣፋ የሆኑ እንስሳት 9 ሜትር ያህል ከአንዱ ቅርንጫፍ ወይም ዛፍ ወደ ሌላኛው መዝለል ይችላሉ። ሌሊት ሌሊት በአብዛኛው የሚመገቧቸውን ቅጠላ ቅጠሎችና እጮች ለማግኘት ወደ መሬት ይወርዳሉ።

ፈጣኖች፣ ለዓይን የሚማርኩና ጉልበታቸውን የሚቆጥቡ

ካንጋሮዎች ቀስ ብለው በሚጓዙበት ጊዜ ቀርፋፋና ገልጃጃ ሊመስሉ ይችላሉ። የኋላ ቅልጥሞቻቸውን ወደፊት በሚያነሱበት ጊዜ የፊት ቅልጥሞቻቸውና ጅራታቸው ልክ እንደ ባለ ሦስት እግር በርጩማ ሆነው የሰውነታቸውን ክብደት ይደግፋሉ። ይሁን እንጂ በሚሮጡበት ጊዜ በጣም ይማርካሉ። እንደ ሞላ እየተስፈነጠሩ በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር በሚጓዙበት ጊዜ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ትልቁን ጅራታቸውን ይጠቀሙበታል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚለው ከሆነ “በሰዓት እስከ 60 ኪሎ ሜትር [38 ማይልስ] ሊጓዙ ይችላሉ።” አንድ ትልቅ ካንጋሮ በከፍተኛ ፍጥነት በሚጓዝበት ጊዜ በአንዴ ከ9 እስከ 13.5 ሜትር ድረስ ሊዘል ይችላል። ይህ ከበረራ ተለይቶ የሚታይ አይደለም!

ካንጋሮዎች ፈጣኖች ብቻ ሳይሆኑ በጉልበት አጠቃቀማቸውም የተዋጣላቸው ናቸው። በአውስትራሊያ ሜልቦርን ውስጥ የሚገኘው የሞናሽ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ዩቬ ፕሮስኬ ካንጋሮዎች በዝቅተኛ ፍጥነት ከሚጓዙበት ጊዜ ይልቅ በከፍተኛ ፍጥነት በሚጓዙበት ጊዜ የሚኖራቸው የኦክስጅን ፍጆታ ይበልጥ ጉልበት እንዲቆጥቡ ያስችላቸዋል ይላሉ። በተጨማሪም ፕሮስኬ እንዳሰሉት ከሆነ “እየዘለለች የምትሄደው ካንጋሮ በሰዓት 20 ኪሎ ሜትር [12 ማይልስ] ወይም ከዚያ በላይ ለመጓዝ የምታወጣው ጉልበት በተመሳሳይ ፍጥነት የሚሮጥና አንድ ዓይነት ክብደት ያለው ከእንግዴ ልጅ ጋር ተያይዞ የተወለደ አራት እግር ያለው አጥቢ እንስሳ [ዕድገቱን ሙሉ በሙሉ ጨርሶ የተወለደ እንደ ውሻ ወይም አጋዘን ያለ አጥቢ እንስሳ ማለት ነው] ከሚያወጣው ጉልበት ያነሰ ነው።” ካንጋሮ ጉልበቷን በመቆጠብ የምታደርገው እንቅስቃሴ ሳትደክም ረጅም ርቀት መጓዝ ያስችላታል። ይሁን እንጂ ካንጋሮ ጉልበቷን ቆጥባ መሮጥ የምትችለው እንዴት ነው?

ምስጢሩ ያለው ረጃጅም በሆኑት አኪለስ ጅማቶቿ ላይ ነው። “ሁኔታው ካንጋሮዎች በተጠቀለሉ ጥንድ ሞላዎች አማካኝነት የሚዘሉ ያህል ነው” ይላሉ ፕሮስኬ። ከሰው ልጅ የባት ጡንቻ ጋር ተያይዘው እንደሚገኙት ጅማቶች ሁሉ የካንጋሮ አኪለስ ጅማቶችም ካንጋሮዋ በምታርፍበት ጊዜ ይዘረጋሉ፣ በምትነሳበት ጊዜ ደግሞ ይኮማተራሉ። ካንጋሮዎች በአብዛኛው በሰከንድ ውስጥ የሚዘሉት ዝላይ ብዛት አንድ ዓይነት (ቀይ ካንጋሮ ሁለት ጊዜ ያህል) ነው። ፍጥነታቸውን መጨመር ሲፈልጉ እያንዳንዱን ዝላይ ያስረዝሙታል። ለየት ያለ ሁኔታ የሚኖረው በሚደነብሩበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለመሸምጠጥ ሲሉ አጠር አጠር ያሉ ፈጣን ዝላዮችን በመጠቀም ሊፈተለኩ ይችላሉ።

በተጨማሪም ካንጋሮዎች የተዋጣላቸው ዋናተኞች ናቸው። ኃይለኛ ቅልጥሞቻቸውን በመጠቀም ብቻ ሳይሆን ጅራታቸውን ወዲያና ወዲህ በማወዛወዝ ወደፊት የሚያስወነጭፍ ተጨማሪ ኃይል ያገኛሉ። ካንጋሮዎች ውሾች በሚያሳድዷቸው ጊዜ የውኃ ጉድጓድ ወይም ወንዝ ውስጥ ዘለው በመግባት ያሏቸውን ልዩ ችሎታዎች ይጠቀማሉ። ካንጋሮዋን ተከትሎ ለመግባት የደፈረ ማንኛውም ውሻ ወዲያውኑ በጡንቻ በፈረጠሙት የፊት ቅልጥሞቿና የተሳሉ ጥፍሮች ባሏቸው ባለ አምስት ጣት መዳፎቿ ይደፈቃል። መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆን ሁለት ውሾች የነበሩት ሲሆን በአንድ ወቅት አንድ የዱር ካንጋሮ የቤተሰባቸው ንብረት በሆነው አነስተኛ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ደፍቆ ሊገድላቸው ነበር።

አስደናቂው የኪሴ አወላለድ

ካንጋሮዎች ትልልቆች በሚሆኑበት ጊዜ ጠንካሮችና ብርቱዎች ቢሆኑም በሚወለዱበት ጊዜ ግን በጣም ጨቅላዎችና በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ናቸው። በሚወለዱበት ጊዜ ከሐምራዊ ትል ብዙም የማይለዩ ሲሆን ርዝማኔያቸው አንድ ኢንች፣ ክብደታቸው ደግሞ አሥራ አምስት ግራም ገደማ ይሆናል። ፀጉር የሚባል ነገር የማይታይባቸው ከመሆኑም ሌላ ማየትና መስማት አይችሉም። ሆኖም ይህ ትንሽ “ትል” አስቀድመው በሚያድጉት በጥፍር የተሞሉ የፊት ቅልጥሞቹና በማሽተት ችሎታው በመጠቀም በእናቱ ፀጉር ላይ በደመ ነፍስ እየተሳበ ኪሷ ውስጥ ይገባል። ኪሷ ውስጥ ከገባ በኋላ ከአራቱ ጡቶቿ አንዱን በአፉ ይይዛል። የጡቱ ጫፍ ወዲያውኑ በግልገሉ አፍ ውስጥ ያብጥና ለተወሰኑ ሳምንታት ባለበት አጥብቆ ይይዘዋል። እናቲቱ ጉዞ ከምታደርግበት መንገድ አንጻር ሲታይ ጠንካራ መልሕቅ መኖሩ ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ ነው! ይህ መልሕቅ በጣም ጥብቅ ከመሆኑ የተነሳ በቀደምት ዘመናት የነበሩ አጥኚዎች ግልገሉ የሚያድገው ከእናቲቱ ጡት ነው ብለው እስከ ማሰብ ደርሰው ነበር!

ውሎ አድሮ ጆዪው የእናቱን ኪስ ለቅቆ መውጣት እስከሚችልበት ደረጃ ድረስ ያድጋል። እርግጥ መጀመሪያ ላይ የሚወጣው ለጥቂት ጊዜ ነው። ይሁን እንጂ ከሰባት እስከ አሥር ወር ካለፈው በኋላ ሙሉ በሙሉ ጡት በሚጥልበት ጊዜ ለዘለቄታው ኪሷን ለቅቆ ይወጣል። ሆኖም ጆዪው መጀመሪያ ከእናቱ ጡት ጋር ወደሚጣበቅበት ወቅት መለስ እንበልና ካንጋሮዎች ከሚራቡበት መንገድ ጋር ዝምድና ያለው አንድ ሌላ አስደናቂ ሁኔታ እንመልከት።

የተወለደው ግልገል የእናቱን ጡት ከያዘ ከጥቂት ቀናት በኋላ እናቲቱ ዳግመኛ ትጠቃለች። እናቲቱ ከተጠቃች በኋላ የሚፈጠረው ፅንስ ለአንድ ሳምንት ያህል ከዳበረ በኋላ እገዳ የተደረገበት ያህል ሂደቱ ለተወሰነ ጊዜ ይቋረጣል። በዚህ ወቅት ትልቅየው በእናቱ ኪስ ውስጥ ሆኖ ዕድገቱን ይቀጥላል። ጡት ገና ያልጣለው ትልቅየው ግልገል የእናቱን ኪስ መልቀቅ ሲጀምር በማኅፀን ውስጥ ያለው ፅንስ ዕድገቱን እንደገና ይጀምራል። በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ለ30 ቀናት ከቆየ በኋላ ትልቅየው ግልገል ያልጠባውን ሌላ ጡት ይይዛል።

ሌላው የካንጋሮ ሥነ ሕይወት አስደናቂ ገጽታ ያለው እዚህ ላይ ነው። እናቲቱ ለትንሹ ጆዪ የምትሰጠው ወተትና ለትልቅየው የምትሰጠው ወተት የተለያየ ነው። ሳይንቲፊክ አሜሪካን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “በተለያዩ የወተት እጢዎች የሚመነጩት ሁለቱ የወተት ዓይነቶች በይዘትም ይሁን በስሪት የተለያዩ ናቸው። የሆርሞኖቹ ሁኔታ ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚስብ ነው።”

ካንጋሮዎችን ማየት የሚቻልባቸው ቦታዎች

ካንጋሮዎችን በተፈጥሯዊ መቼታቸው ማየት ከፈለግክ ከተሞችን ለቅቀህ በመውጣት ወደ አውስትራሊያ ጫካዎች ወይም ገለልተኛ ሥፍራዎች ለመሄድ መዘጋጀት አለብህ። ካንጋሮዎች በነጠላና በአነስተኛ ቡድን ወይም ደግሞ በትልልቅ ተባዕት ካንጋሮዎች በሚመሩ መንጎች ደረጃ በመሰባሰብ ሣርና ትንንሽ ተክሎች ፍለጋ ተሰማርተው ሊታዩ ይችላሉ። በአብዛኛው የሚመገቡት ሌሊት በመሆኑና ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ጥላ ሥር (መኖራቸውን ለመለየት በሚያዳግት ሁኔታ ከአካባቢው ጋር በሚመሳሰሉበት ቦታ) የሚያርፉ በመሆኑ ለማየት አመቺ የሚሆነው ጠዋት ወይም አመሻሹ ላይ ነው። ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ጠባይ ወቅት ግን ቀኑን ሙሉ ሲንቀሳቀሱ ሊታዩ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ የዱር ካንጋሮዎች በጣም ፈሪዎች ስለሆኑና ሰው ስለማይቀርቡ በርቀት ያለን ነገር ማንሳት የሚችል ካሜራና አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር መያዝ ይኖርብሃል።

እርግጥ፣ በመላው አውስትራሊያና በአንዳንድ ሌሎች አገሮችም በሚገኙ በአብዛኞቹ የእንስሳት መጠበቂያዎች፣ የአራዊት መጠለያዎችና ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥም ካንጋሮዎችን ማየት ትችላለህ። እነዚህ ካንጋሮዎች አዘውትረው ሰዎችን ስለሚመለከቱ ብዙም አይሸሹም። በመሆኑም ከቅርብ ርቀት ጥሩ ጥሩ ፎቶዎች፣ ከተቻለም ኪሷ ውስጥ ሆኖ አጮልቆ የሚያይ ጆዪ የያዘች ካንጋሮን ማንሳት መቻል ይኖርብሃል። ተለቅ ተለቅ ያሉ ጆዪዎች እናታቸው ኪስ ውስጥ ተወርውረው በሚገቡበት ጊዜ ሰላላ የሆኑት የኋላ እግሮቻቸው ወደ ውጪ ተንጠልጥለው ስለሚቀሩ ለተመለከታቸው ፈገግ ያሰኛሉ። በዚህ ጊዜ እናቲቱ በዕቃ የተሞላ ዘንቢል ትመስላለች። (ግልገል ካንጋሮዎች ከቅልጥም ሌላ ምንም ሰውነት ያላቸው አይመስሉም!) አንድ ውብ ካንጋሮ ግርማ ሞገስ በተላበሰ ሁኔታ ቀጥ ብሎ ቆሞ ትመለከት ይሆናል። ማን ያውቃል? መንጎቻቸውን የሚመሩ ሁለት ትልልቅ ካንጋሮዎች የሚታጠፉት ረጃጅሞቹ ቅልጥሞቻቸው የሚፈቅዱላቸውን ያህል ቀጥ ብለው ቆመው የለየለት ቦክስ ሲገጥሙ የማየት ዕድል ይገጥምህም ይሆናል!

ይሁን እንጂ ብዙዎች ቀይ ወይም ግራጫ መልክ ያለው አንድ ትልቅ ካንጋሮ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፈነጠረ ሲሄድ መመልከትን ያህል የሚያስደስታቸው ነገር የለም። እርግጥ ነው፣ ሌሎች እንስሳት በላቀ ፍጥነት መሮጥ ወይም ከካንጋሮ በበለጠ ሁኔታ መዝለል ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከካንጋሮ ጋር በሚስተካከል መንገድ ግርማ ሞገስና ከፍተኛ ኃይል ተላብሶ በሁለት ብርቱ እግሮች ብቻ እየተስፈነጠረ የሚሄድ ሌላ አስገራሚ ፍጥረት የለም።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካንጋሮ ልዩ የመስፈንጠር ችሎታ ምስጢር ያለው በረጃጅሞቹ የአኪለስ ጅማቶቿ ላይ ነው