በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የአእምሮ ጤና በአፍሪካ

“ከሳሃራ በታች በሚገኙት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከሚኖረው 600 ሚልዮን ሕዝብ መካከል 100 ሚልዮን የሚሆነው በአእምሮ ሕመም እንደሚሠቃይ” ዘ ስታር የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ከሆነ ለዚህ ከፍተኛ ቁጥር መንስኤዎቹ ጦርነትና ድህነት ናቸው። ሌላው ምክንያት ደግሞ የዘመድ አዝማድ ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ ነው። ናይጄሪያዊው ፕሮፌሰር ማይክል ኦላታዉራ እንዳሉት ከሆነ “እርስ በርስ ለመረዳዳት ያገለግል የነበረው ይህ ባሕላዊ የአፍሪካ መረብ” በምዕራባውያን የአኗኗር ሥርዓቶች፣ በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች እንዲሁም በእርስ በርስ ብጥብጥ ሳቢያ በመበጣጠስ ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ አባላት ሥራ ለማግኘት ሲሉ ከቤተሰባቸው ርቀው ይሄዳሉ። “የአፍሪካ መንግሥታት ያሉባቸው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጤና ረገድ የሚገባንን ያህል እርዳታ እንዳናደርግ እንቅፋት ሆኖብናል” ይላሉ ፕሮፌሰር ኦላታዉራ።

ምላስን መንከባከብ

ከምላስህ በስተጀርባ የሚከማቹ ባክቴሪያዎች መጥፎ ጠረን የሚያመጡ የሰልፈር ጋዞች ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ፕሪንስ ጆርጅ ሲትዝን በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ገልጿል። “ባክቴሪያዎች ደረቅና ከኦክስጅን ነፃ የሆነ ቦታ ይስማማቸዋል። ወደ ሳንባችን ከምናስገባው አየር ርቀው በየስንጥቁና ክፍተት ባለበት ቦታ የሚኖሩት ለዚህ ነው” ይላል ዘገባው። ጥርስን በብሩሽና በክር ማጽዳቱ ችግሩን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ቢሆንም በዚህ ዘዴ የሚወገዱት 25 በመቶ የሚሆኑት ባክቴሪያዎች ብቻ ናቸው። የጥርስ ሐኪም የሆኑት አላን ግሮቭ በአውሮፓ በጥንት ዘመን ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው ምላስን መፋቅ “መጥፎ ጠረንን ለማስወገድ የሚያስችል ዋነኛ መንገድ” እንደሆነ ያምናሉ። “ከጥርስ ብሩሽ ይልቅ” የፕላስቲክ መፋቂያ መጠቀም “የምላስን ንጽሕናም ሆነ ተፈጥሯዊ ቀለም ለመጠበቅ የተሻለ ዘዴ ነው” ይላል ሲትዝን።

ማንጎራጎር መንፈስን ያነቃቃል

ዘፈን ማንጎራጎር ዘና እንድትልና እንድትደሰት የሚያደርጉ ኬሚካሎች በአንጎልህ ውስጥ እንዲመነጩ የሚያደርግ መሆኑን ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል ሲል ሽቱትጋርተ ናክሪክተን የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። ማንጎራጎር በአንጎል ውስጥ የሚገኙት “የስሜት ሞሊኪውሎች” እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል ይላሉ ተመራማሪዎች። በመሆኑም “ማንጎራጎር ስሜትን ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ስሜት ለመፍጠርም ያገለግላል መባሉን” ዘገባው ገልጿል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ማንጎራጎር “ጊዜ ያለፈበት ነገር” እንደሆነ ወይም ድምፃቸው ጥሩ እንዳልሆነ እንደሚሰማቸውና በዚህም ሳቢያ ዘፈኑንና ሙዚቃውን ለመገናኛ ብዙሃን እንደሚተዉት የሙዚቃ አስተማሪዎች ይናገራሉ። ይህ ጥናት እንዳመለከተው ግን ሰዎች ራሳቸው በሚያንጎራጉሩበት ጊዜ በእጅጉ ይጠቀማሉ።

ውጥረት ያለባቸው እናቶች —⁠ውጥረት ያለባቸው ሕፃናት

አንዲት የጸነሰች እናት የዕለት ተዕለት ሕይወቷ በውጥረት የተሞላ ከሆነ በማኅፀኗ ያለው ሕፃን ዕድገት ከባድ እክል ሊገጥመው እንደሚችል ናሽናል ፖስት የተባለው የካናዳ ጋዜጣ ዘግቧል። ሌክሲንግተን ኬንታኪ ውስጥ የሚገኘው የኬንታኪ የሕክምና ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፓቲክ ዋድዋ እንዳሉት ከሆነ በማኅፀን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች “በሕፃኑ ዕድገት ላይ እክል ይፈጥራሉ። እናቲቱ ብዙ ውጥረት ካለባት ደግሞ ሕፃኑ ለበሽታ በእጅጉ የተጋለጠ እንዲሆን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።” በተጨማሪም ውጥረት ያለባቸው እናቶች “ብዙውን ጊዜ ያለጊዜያቸው የመውለድ እድላቸው ከፍተኛ ነው” በማለት ዘገባው ይገልጻል። በደቡብ ካሮላይና በሚገኘው ክሌምሰን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች “ራስን ዘና የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ውጥረት ያለባቸውን የጸነሱ ሴቶች የደም ግፊት በመቀነስ በማኅፀናቸው ውስጥ ጤናማ ሁኔታ እንዲኖር ሊረዷቸው” እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የትምህርት ወዮታ በአፍሪካ

ትምህርት ቤት መግባት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ከሳሃራ በታች ባሉ አገሮች የሚኖሩ ከ40 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች አይማሩም ሲል የመላው አፍሪካ የዜና አገልግሎት ድርጅት ዘግቧል። በክልሉ የትምህርት ሥርዓት ላይ ውድቀት ያስከተሉ በርከት ያሉ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ባለው የኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ ብዙ ትምህርት ቤቶች ውኃ የላቸውም፤ ያሏቸው መጸዳጃ ቤቶችም ጥቂት ናቸው አለዚያም ደግሞ ከናካቴው ላይኖራቸው ይችላል። የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ያለ ከመሆኑም በላይ አስተማሪዎቹም በቂ ሥልጠና ያገኙ አይደሉም። ከኢኮኖሚያዊ ወዮታዎች በተጨማሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጃገረዶች የሚጸንሱ በመሆኑ ትምህርት ለማቋረጥ ይገደዳሉ። ኤድስም በተማሪዎች ቁጥር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ገና በአፍላ ዕድሜያቸው የጾታ ግንኙነት ስለሚፈጽሙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎረምሶች በኤድስ ይለከፋሉ” ይላል የአፍሪካ የዜና አገልግሎት ድርጅት። አንዳንድ ጊዜ ኤድስ ያልያዛቸው ልጃገረዶችም በዚህ በሽታ የተለከፉ ዘመዶቻቸውን እቤት ሆነው እንዲያስታምሙ ይደረጋል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ኤክስፐርት የሆኑ ዶክተር ኤድዋርድ ፊስክ “ትምህርት እምብዛም የማይሰጥባቸው ከሳሃራ በታች የሚገኙት የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች የወደፊት ዕጣ አስተማማኝ አይደለም” ብለዋል።

ረጅም ሌሊት

“ግርማዊ ሌሊት።” ኖርዌያዊው የምድር ዋልታ ተመራማሪ ፍሪችኦፍ ናንሰን “ሞርኬቲት”ን ወይም ፀሐይ በሰሜናዊ ኖርዌይ ጨርሶ የማትወጣበትን ወቅት በዚህ መልኩ ነበር የገለጹት። ለሁለት ወራት ያህል እኩለ ቀን ላይ ለጥቂት ሰዓታት ወደ ግራጫነት የሚወስደው ቀይ ወጋገን ብቻ ይታያል። ሆኖም ይህን የጨለማ ወቅት በፀጋ የሚቀበለው ሁሉም ሰው አይደለም። ኢብንቡረንር ፎልክስሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ በምድር ዋልታ ክልል የሚኖሩ 21.2 በመቶ የሚሆኑ ኖርዌያውያን በክረምት ወር ከሚኖረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሚከሰትባቸው የመንፈስ ጭንቀት ይሠቃያሉ። ለዚህ መንስኤው በአንጎል ውስጥ የሚመነጨው ሜላቶኒን የተባለ ሆርሞን እጥረት ሊሆን ይችላል። ብቸኛው መፍትሔ ብርሃን ነው። ይሁን እንጂ ጨለማው ጋባዥ የሚሆንላቸውም ሰዎች አሉ። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በርካታ ጎብኚዎች ብልጭ ድርግም በሚለው ወጋገን፣ በጨረቃ ብርሃን በሚያንጸባርቀው በረዶና ተበታትነው በሚገኙት መንደሮች በሚታየው ደስ የሚል ብርሃን ተማርከው ወደ ምድር ዋልታ ይሄዳሉ።

ከግብርና ሥራ ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች

በብሪታንያ የእርሻ ቦታዎች በየሳምንቱ ከአንድ ሰው በላይ የሚሞት በመሆኑ የግብርና ሥራ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት እጅግ አደገኛ ሥራዎች አንዱ ሊሆን በቅቷል ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። በ1998 በዚህ መንገድ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል የመጨረሻው ትንሹ የአራት ዓመት ልጅ ሲሆን በትራክተር ጎማ ተጨፍልቆ ሕይወቱ አልፏል። ሌሎች ሰባት ሰዎች ደግሞ በዳገታማ ቦታ ላይ በተገለበጡ ትራክተሮች ሕይወታቸው ተቀጥፏል። ገበሬዎች ለአደጋ የሚያጋልጡ ሥራዎችን ማከናወን ከመጀመራቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡና አንድን ትራክተር በዳገታማ ቦታ ላይ ከማሽከርከራቸው በፊት ሁኔታዎቹን እንዲያጤኑ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ነው። በጤናና ደህንነት መምሪያ የግብርና ዋና ተቆጣጣሪ የሆኑት ዴቪድ ማቲ “ግለሰቡ ትንሽ ቆም ብሎ ሥራው የሚጠይቀውን ነገር አስቦ ቢሆን ኖሮና ሥራውን ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ቢያከናውን ኖሮ ከእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አብዛኞቹን ማስወገድ በተቻለ ነበር” ብለዋል።

ከተጠራጠራችሁ ጣሉት

ፎርማጆ ላይ እንደሚታየው ሰማያዊ ሻጋታ ያሉ አንዳንድ ሻጋታዎች በሚበሉበት ጊዜ ምንም ችግር አይፈጥሩም። ሌሎቹ ግን በተለይ ጥሩ ጤንነት ለሌላቸው ሰዎች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ዩ ሲ በርክሊ ዌልነስ ሌተር ያስጠነቅቃል። ዳቦ ላይና የጥራጥሬ ውጤቶች ላይ የሚወጣው ሻጋታ እጅግ መርዘኛ ከሆኑት ሻጋታዎች መካከል የሚፈረጅ ነው። ብዙውን ጊዜ ከላይ የሚታየው ሻጋታ ምግቡ ውስጥ ዘልቀው የገቡ ሥር የመሰሉ ነገሮች ይኖሩታል። ከዚህም በተጨማሪ በሻጋታ የሚፈጠሩትን መርዞች ምግቡን በማብሰል ማስወገድ አይቻልም። ዌልነስ ሌተር የሚከተለውን ሐሳብ ያቀርባል:-

▪ ከተቻለ የምትመገቧቸውን ነገሮች ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀምጡ፤ በተጨማሪም ከመሻገታቸው በፊት ተመገቧቸው።

▪ እንደ እንጆሪ ወይም ወይን ያሉ ትናንሽ የሻገቱ ፍራፍሬዎችን ጣሉ። እር​ጥበት ሻጋታ የሚያስከትል በመሆኑ ፍራፍሬዎችን ማጠብ ያለባችሁ ለመመገብ በምትዘጋጁበት ጊዜ ነው።

▪ እንደ ፖም፣ ድንች፣ አበባ ጎመን ወይም ሽንኩርት ባሉ ጠንከር ያሉ ትልልቅ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ላይ የሚወጡ ትንንሽ ሻጋታዎችን ቆርጦ ማስወገድ ይቻል ይሆናል። እንደ ኮክና ሐብሐብ ያሉ ልል የሆኑ የሻገቱ ፍራፍሬዎች መጣል አለባቸው።

▪ ጠንከር ያለ ፎርማጆ በሚሻግትበት ጊዜ ቢያንስ ቢያንስ ከሻጋታው ከ2-3 ሴንቲ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ የላይኛውን ክፍል ቆርጦ በመጣል ቀሪውን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። ሆኖም የሻገተ ለስላሳ ፎርማጆና እርጎ እንዲሁም የሻገተ ዳቦ፣ ሥጋ፣ የተረፈ ምግብ፣ ለውዝ፣ የኦቾሎኒ ቅቤ፣ ሲረፕ እና የቆርቆሮ ምግቦች መጣል ይኖርባቸዋል።

ድህነት​—⁠ዓለም አቀፋዊ ችግር

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጄምስ ዲ ዎልፈንሶን ሊወገድ ያልቻለው ዓለም አቀፍ ድህነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በቅርቡ ተናግረዋል። ዎልፈንሶን ከምድራችን ስድስት ቢልዮን ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው አሁንም ድረስ በከባድ ድህነት በመማቀቅ ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሜክሲኮ ሲቲው ላ ሆርናዳ ጋዜጣ ዘግቧል። ከምድራችን ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ሕይወቱን የሚገፋው በቀን ከሁለት የአሜሪካ ዶላር በማይሞላ ገቢ ሲሆን አንድ ቢልዮን የሚሆነው ደግሞ እያንዳንዱን ዕለት የሚያሳልፈው ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል። ዎልፈንሶን የዓለም ባንክ ከድህነት ጋር በሚደረገው ውጊያ ባሳየው እመርታ የተደሰቱ ቢሆንም ችግሩ በእጅጉ የተስፋፋ እንደሆነና በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለ የሚጠቁሙ አኃዛዊ መረጃዎች አቅርበዋል። “ድህነት ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን መገንዘብ አለብን” ብለዋል።