በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ሰማይ የሚያስወጣ ደረጃ

ወደ ሰማይ የሚያስወጣ ደረጃ

ወደ ሰማይ የሚያስወጣ ደረጃ

ፊሊፒንስ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ጠቅላላ ርዝማኔው ታላቁን የቻይና ግምብ አሥር እጅ እንደሚበልጥ ይነገርለታል። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ክፍሎቹ በሙሉ ተቀጣጥለው ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድ መስመር ቢዘረጉ 20, 000 ኪሎ ሜትር ሊደርስ ወይም ምድርን በግማሽ ሊከብብ ይችላል! እንዲያውም አንዳንዶች ስምንተኛው የዓለማችን ድንቅ የሥራ ውጤት ሲሉ ሰይመውታል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በፊሊፒንስ ውስጥ እንዲህ ያለ እጅግ አስደናቂ መስህብ መኖሩን ፈጽሞ ሰምተው አያውቁም። ለመሆኑ ይህ አስደናቂ መስህብ ምንድን ነው? ወደ ሰማይ የሚያስወጣ ደረጃ ተብሎ የሚጠራውና በፊሊፒንስ የተራሮች ሠንሰለት ላይ የሚገኘው የሩዝ እርከን ነው። በሉዞን ተራሮች ላይ የሚገኙት እነዚህ እርከኖች ልዩ ውበትና እጅግ አስደናቂ የሆነ የፈጠራ ችሎታ ይንጸባረቅባቸዋል።

እነዚህ እርከኖች የተሠሩት ለምንድን ነው? ተራሮቹ በጣም ቀጥ ያሉ በመሆናቸው ለግብርና የሚመቹ ዓይነት አይደሉም። አንዳንዱ ቦታ ከ50 በመቶ በላይ ያጋደለ ነው። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ገበሬዎች በዚህ አልተበገሩም። በመሆኑም በ1, 200 ሜትር ወይም ከዚያ በበለጠ ከፍታ ላይ ለምለም በሆኑት ተራሮች ጎንና ጎን በሺህ የሚቆጠሩ እርከኖች ሠርተዋል። አንዳንድ ጊዜ 25፣ 30 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ እርከኖች ልክ ወደ ሰማይ እንደሚያስወጣ ደረጃ በተርታ ተሰልፈው ይታያሉ። እያንዳንዱ እርከን በድንጋይ ካብ በተደገፈ የአፈር ግድብ የተከፋፈለና በውኃ የተሸፈነ ነው። አብዛኞቹ እርከኖች በሩዝ የተሸፈኑና የተራሮቹን ቅርጽ የተከተሉ ናቸው። የተራሮቹ አካላት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ ውስጥ ስርጉድ ያሉ ሲሆኑ ሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ ወደ ውጭ ወጣ ያሉ ናቸው።

እርግጥ የእርሻ እርከኖች የሚገኙት በፊሊፒንስ ብቻ አይደለም። በእርከን የተዘጋጁ የእርሻ ማሳዎች በሌሎች አገሮች በተለይ ደግሞ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎችም ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በፊሊፒንስ የሚገኙት የሩዝ እርከኖች በብዙ መንገዶች ለየት ያሉ ናቸው። የዓለም አቀፍ የሩዝ ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ማርዮ ሞቪልዮን ከንቁ! ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በፊሊፒንስ የሚገኙት የሩዝ እርከኖች በሌሎች አገሮች ካሉት እርከኖች ይበልጥ መጠነ ሰፊ ናቸው። አብዛኛውን የተራራ ሠንሰለት ሸፍነውታል” ሲሉ ተናግረዋል። አብዛኛው እርከን የሚገኘው በኢፉጋኡ አውራጃ ነው። አንድ ሰው የእርከኖቹን ብዛት ሲመለከት በግርምት ይደመማል። እርከኖቹ ለተራሮቹ ቅርጽ ልዩ ውበት ሰጥተውታል።

የዓለማችን ድንቅ የሥራ ውጤት ሊባል ይችላል?

እነዚህ እርከኖች ስምንተኛው የዓለማችን ድንቅ የሥራ ውጤት ናቸው ቢባል ማጋነን ይሆናል? እስቲ የሚከተለውን ሐቅ ተመልከት:- እነዚህ እርከኖች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከታየው የእርሻ ፕሮጄክት ሁሉ በግዙፍነታቸው ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በታኅሣሥ 1995 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት የኢፉጋኡ የሩዝ እርከኖችን በዓለም የቅርስ መዝገቡ ውስጥ ለማስፈር ወስኗል። በመሆኑም እርከኖቹ እንደ ሕንዱ ታዥ መሃል፣ እንደ ኢኳዶር ጋላፓጎስ ደሴቶች፣ እንደ ታላቁ የቻይና ግንብና እንደ ካምቦዲያው አንግኮር ዋት ካሉ ከፍተኛ ታሪካዊና ባሕላዊ ጠቀሜታ ካላቸው ሌሎች ሥፍራዎች ጎን ተፈርጀዋል። ሆኖም እንደ ግብፅ ፒራሚዶች ካሉት ጥንታዊ የግንባታ ፕሮጄክቶች በተለየ መልኩ እነዚህ እርከኖች የተሠሩት በባሪያ ጉልበት ሳይሆን በማኅበረሰቡ ጥሮሽ ነው። በተጨማሪም የተተዉ ቦታዎች ሳይሆኑ አሁንም ድረስ በኢፉጋኡ በመልማት ላይ ያሉ ናቸው።

እነዚህን እርከኖች ብትጎበኝ ልብ የሚሰርቅ ውበታቸውን በዓይንህ ልትመለከት ትችላለህ። ሰዎች ከጥቂት ካሬ ሜትሮች አንስቶ እስከ 10, 000 ካሬ ሜትሮች በሚደርሱት እርከኖች ላይ ሲሠሩ ትመለከታለህ። አንዳንድ ሠራተኞች እያንጎራጎሩ ውኃው ወደ ታች እንዲሰርግ በያዟቸው ዱላዎች መሬቱን ወጋ ወጋ ያደርጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሩዝ ይተክላሉ፣ ቡቃያዎቹን እየነቀሉ ሌላ ቦታ ላይ ይተክላሉ ወይም ሰብላቸውን ይሰበስባሉ። አዳዲስ የሩዝ ተክሎች በሚበቅሉበት ጊዜ ጉብኝት ብታደርግ በእርከኖቹ ላይ የሚፈጠረውን የተለያዩ አረንጓዴ ቀለማት ውብ ንድፍ መመልከት ትችላለህ።

በውኃ የራሱ ምርጥ የሩዝ ዘሮች ውኃ በብዛት የማያገኙ ከሆነ ሊበቅሉ አይችሉም። ስለዚህ የረቀቀ የመስኖ መስመር ተዘርግቷል። በተራሮች ላይ የሚገኙት ወንዞች ተጠልፈው ውስብስብ በሆኑ ቦዮችና የቀርከሃ ቱቦዎች አማካኝነት ወደ እርከኖቹ ይፈስሳሉ። በስበት ኃይል አማካኝነት አስተማማኝ የሆነ የውኃ አቅርቦት ከእርከን ወደ እርከን ይሰራጫል። እርከኖቹ በድን ቅርሶች ሳይሆኑ ሕያው የሆኑ ድንቅ የሥራ ውጤቶች ናቸው!

የሠራቸው ማን ነው?

እነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ እርከኖች በአንድ ጀምበር አልፎ ተርፎም በጥቂት ዓመታት ሊሠሩ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ይህ ግንባታ የተካሄደው በዘመናዊ መሣሪያዎች ወይም ማሽኖች እንዳልሆነ አስታውስ። ስለዚህ የእነዚህ እርከኖች ሥራ የተጀመረው አነሰ ቢባል ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በፊት እንደሚሆን ይታመናል።

እንዲያውም አንዳንድ አርኪኦሎጂስቶች ሥራው ከ2, 000 ዓመታት በፊት የተጀመረ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው። አንትሮፖሎጂስቶች እርከኖቹን የሠሩት የሩዝ ተክሎችን በውኃ በመሸፈን በእርከን የመትከል ባሕላቸውን ይዘው ከሰሜናዊ ኢንዶቻይናና ከኢንዶኔዥያ ወደ ሉዞን የፈለሱት ሰዎች ናቸው የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ። እርከኖቹ ከተሠሩ በኋላ ቀስ በቀስ አዳዲስ ደረጃዎች ይጨመሩ ነበር።

መጎብኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

አሁን እርከኖቹን በምናባችን ለመጎብኘት እንሞክር። መጀመሪያ አየር ማቀዝቀዣ ባለው አውቶብስ ከማኒላ ተነስተን ኢፉጋኡ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ባናዌ ከተማ እንጓዛለን። ጉዞው ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ይወስዳል። ከዚህ በኋላ የተለያዩ አማራጮች ይኖሩናል። በእግር፣ የጎን መቀመጫ ባለው ባለ ሦስት ጎማ ሞተር ብስክሌት፣ አለዚያም ጂፕኒ በሚባል በፊሊፒንሶች አነስተኛ አውቶብስ ወደተለያዩ ማራኪ ቦታዎች መጓዝ እንችላለን። ፍላጎቱና ብርታቱ ካለን ደግሞ በእግር ብቻ ሊወጣባቸው ወደሚችሉ ተራራማ ቦታዎች ከሚወስዱት መንገዶች አንዱን ተከትለን መሄድ እንመርጥ ይሆናል። እጅግ ማራኪ እይታ ካላቸው እርከኖች መካከል አንዳንዶቹ በእነዚህ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን ተመልካቹ ይህ ሰው ሠራሽ የሆነ ድንቅ የሥራ ውጤት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ እንዲገነዘብ ያደርጉታል።

ጂፕኒ ተሳፍረን ወደ ባታድ መንደር ለመሄድ እንመርጣለን። አሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው ሥፍራ ለመድረስ ወጣ ገባ በሆነው ተራራማ መንገድ ላይ ከአንድ ሰዓት በላይ መጓዝ ይኖርብናል። ከዚያ በኋላ አንድ የእግር መንገድ ተከትለን ተራራውን እንወጣለን። በተለያዩ የተራራ አትክልቶች መሃል አቆራርጠን ቀስ በቀስ በሁለት ከፍተኛ ቦታዎች መካከል ወዳለ ተረተር እንደርሳለን። (ሌላ አቋራጭ መንገድ ያለ ቢሆንም በጣም ቀጥ ያለ በመሆኑ አስቸጋሪ ተራራዎችን የመውጣት ልምድ ለሌላቸው ሰዎች በጣም አደገኛ ነው።) ከዚያም በአንድ ቀጭን መንገድ በመጓዝ ከተረተሩ ቀስ እያልን ወደ ባታድ እንወርዳለን።

በመንገዳችን ላይ የተራራውን ንጹሕ አየር እየሳብን ለሁለት ሰዓት ያህል በእግር ከተጓዝን በኋላ በመጨረሻ ያሰብነው ቦታ እንደርሳለን። እዚያም እንደደረስን ዓይናችን የጎመጀውን ነገር እናገኛለን። ከባታድ ፊት ለፊት ያለው ተራራ ስርጉድ ያለ በመሆኑ እርከኖቹ የአንድ ትልቅ አምፊቴያትር ቅርጽ ይዘው ይታያሉ። ልክ ወደ ሰማይ እንደሚያስወጣ ደረጃ አንዳቸው በሌላው ላይ ተደርበው የሚያምር የተርታዎች ንድፍ ፈጥረዋል። ወደ መንደሩ እየቀረብን ስንሄድ በሣር እንደተሸፈኑ ትልልቅ እንጉዳዮች በመንደሩ ውስጥ ተሰበጣጥረው የሚገኙትን ጥንታዊ አሠራር ያላቸው የኢፉጋኡ ቤቶች እንመለከታለን።

ሰዎቹ ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ሲሆኑ እያለፍናቸው ስንሄድ እርከኖቹ ላይ እየሠሩ ሰላም ይሉናል። የአካባቢው ሰዎች ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ለመጓዝ በእርከኑ የድንጋይ ካብ ጠርዝ ላይ ቀልጠፍ ብለው ሲሄዱ ስትመለከት ልትገረም ትችላለህ። ሌሎቹ ደግሞ ምቹ በሆኑ ቦታዎች ያስቀመጧቸውን ድንጋዮች በመጠቀም ልክ እንደ ሜዳ ፍየል ያላንዳች ችግር ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ይወጣሉ። ቀረብ ብለን ስንመለከታቸው ባዶ እግራቸውን እንደሆኑ እንረዳለን። በዙሪያቸው ልዩ መስህብ ያለው የተራራ ላይ እርከን ይታያል። የሰው ልጅ የግንባታ ሥራ እንዲህ ከቦታው ጋር ሲጣጣምና ለአካባቢው ውበት ሲጨምር እምብዛም አይታይም።

በጣም ማራኪ አይደለም? እንግዲያው ፊሊፒንስን ከጎበኘህ በቀላሉ ከአእምሮህ ሊፋቅ የማይችለውን ሕያውና ድንቅ የሆነውን ወደ ሰማይ የሚያስወጣ ደረጃ ማየት የምትችልበት አጋጣሚ ሊያመልጥህ አይገባም።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እርከኖቹን ከጥፋት መታደግ

እርከኖቹ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ውበት የተላበሱ ቢሆንም ሕልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል። በተራራማ ቦታዎቹ ላይ ከሚኖረው ወጣት ትውልድ መካከል ብዙዎቹ የሩዝ ገበሬዎች መሆን ስለማይፈልጉ በሌሎች መስኮች ሥራ በማፈላለግ ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ እርከኖቹን ባሉበት ሁኔታ ጠብቀው ማቆየት የሚችሉ ጥሩ ችሎታ ያላቸው በቂ ገበሬዎች እንዳይኖሩ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል።

የዓለም አቀፉ የሩዝ ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት የኢፉጋኡ ተወላጅዋ ኦሮራ አማያኡ ከንቁ! ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አንድ ሌላ አስጊ ሁኔታ ጠቅሰዋል:- “እርከኖቹ ዘወትር በውኃ መራስ ያለባቸው ቢሆንም በደን ምንጠራ ሳቢያ የውኃ እጥረት ተከስቷል።” የውኃ መስመሮቹ ከደረቁ የእርከኖቹ ሕልውና ያከትምለታል ማለት ነው።

የተፈጥሮ አደጋዎችም አልፎ አልፎ ችግር ይፈጥራሉ። በ1990 የተከሰተው የምድር ነውጥ የተራሮቹን ጥጋት በመ​­ደረማመሱ የተወሰኑ እርከኖች እንዳልነበሩ ሆነዋል።

ይሁን እንጂ እርከኖቹን ከጥፋት ለመታደግ አንዳንድ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው። በ1996 የኢፉጋኡ እርከኖች ኮሚሽን እንዲቋቋም መንግሥት ትእዛዝ አስተላልፏል። የዚህ ኮሚሽን ተግባር ምንድን ነው? የውኃ አቅርቦቱንና የአካባቢውን ባሕል እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ቦታዎች ወደ ቀድ​­ሞው ሁኔታቸው መመለስን ጨምሮ ለእርከኖቹ ጥበቃ ማድረግ ነው።

እርከኖቹ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ መካተታቸው የፊሊፒንስ መንግሥት ለቦታው ጥበቃ እንዲያደርግ ይበልጥ ያስገድደዋል። በተጨማሪም ማኒላ በሚገኘው የዩኔስኮ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዲሬክተር የሆኑት ጂን ትዋሶን እንዳሉት ከሆነ “ዩኔስኮም የሩዝ እርከኖቹን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ለሚደረገው ጥረት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል።”

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በፊሊፒንስ የሚገኘው የተራራ ሠንሰለት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]