በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለውን የሥነ ምግባር ደረጃ ጠለቅ ብለህ ብትመረምር አንድ ግልጽ የሆነ አዝማሚያ ትመለከታለህ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች የሥነ ምግባር ደረጃቸው እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

አንዳንድ ግለሰቦች እንደሚሉት ጠቅላላው ሥልጣኔያችንና መላው የሰው ዘር ሊያመልጠው የማይችለው ጥፋት ከፊቱ ተደቅኗል ማለት ነው? ወይስ እነዚህ ለውጦች እንዲሁ በታሪክ ውስጥ ሲታይ የኖረው ተነዋዋጭ ሂደት አካል ከመሆን ያለፈ ትርጉም የላቸውም?

ብዙዎቹ ሰዎች የኋለኛው ዓይነት አመለካከት ነው ያላቸው። በዘመናችን ያለው የሥነ ምግባር ውድቀት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሲታዩ ከኖሩት አዝማሚያዎች የተለየ አይደለም የሚል እምነት አላቸው። ከጊዜ በኋላ አዝማሚያው ተቀልብሶ ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ዳግም እንደሚንሠራፉ እርግጠኞች ናቸው። ይህ አባባላቸው ትክክል ነው?

የ“መጨረሻው ቀን”

ያለውን እውነታ በሥነ ምግባር ጉዳዮች ረገድ ለብዙ መቶ ዘመናት ዋነኛ መመሪያ ሆኖ በስፋት ሲሠራበት ከቆየው መጽሐፍ ማለትም የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ እንመልከተው። በዛሬው ጊዜ ያለውን ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ዘመን አስመልክቶ ከሚሰጠው ትንቢታዊ መግለጫ ጋር ማነጻጸሩ ሁኔታውን በጥልቀት ለማስተዋል ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እጅግ ወሳኝ የሆነ ዘመን የ“መጨረሻው ቀን” ወይም “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” በማለት ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1፤ ማቴዎስ 24:​3 NW ) እነዚህ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት ይህ ጊዜ የአንድን ዘመን ማብቂያና የአዲስ ዘመን መባቻን የሚያመለክት ነው።

የአምላክ ቃል የመጨረሻው ቀን “የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚሆን ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በንቃት የሚከታተሉ ሰዎች የመጨረሻውን ቀን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ የዚህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ወቅት ግልጽ መግለጫ ወይም ጥምር ምልክት ሆነው የሚያገለግሉ በርካታ ዝርዝር ሁኔታዎች ይገልጻል።

በሰዎች ላይ የሚታዩ መጥፎ ባሕርያት

በዛሬው ጊዜ ጎልቶ የሚታየውን አንዱን የዚህ ምልክት ገጽታ ተመልከት:- ‘ሰዎች የአምልኮት መልክ ይኖራቸዋል ኃይሉን ግን ይክዳሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:​2, 5) በታሪክ ውስጥ የአሁኑን ዘመን ያህል ሰዎች ሃይማኖታዊ አመራርን ወደ ጎን ገሸሽ ያደረጉበት ዘመን የለም። ብቸኛው የበላይ ባለሥልጣን አምላክ ነው የሚለው እምነት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ ሰዎች ብቸኛው የእውነት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚለውን አባባል አይቀበሉትም። ሃይማኖቶች አሁንም ያሉ ቢሆንም እንኳ ብዙዎቹ በሰዎች ላይ እምብዛም ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። እንዲሁ ሽፋን ብቻ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሌላውን የምልክቱን ገጽታ እንዲህ ሲል ይጠቅሳል:- “ሰዎች . . . ራሳቸውን የማይገዙ” እና “ጨካኞች” ይሆናሉ እንዲሁም “ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​2, 3፤ ማቴዎስ 24:​12) ‘ጨካኝ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንዱ ትርጉም “ሰብዓዊ ርኅራኄና ስሜት የጎደለው” ማለት ነው። በዛሬው ጊዜ ትንንሽ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ “ጨካኞች” መሆናቸውን እያሳዩ ከመሆኑም በላይ የሚፈጽሟቸው ከባድ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቴክኖሎጂውና በኢኮኖሚው መስክ የታየው ፈጣን ዕድገትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመጣው ስግብግብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ሰዎች የቆዩ የሥነ ምግባር ሥርዓቶችንና ደንቦችን አሽቀንጥረው እንዲጥሉ አድርጓቸዋል። ለሌሎች ደንታ ቢስ በመሆን የቻሉትን ያህል በማጋበስ የራሳቸውን የራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ለማርካት ማጭበርበርን ጨምሮ ያገኙትን ዘዴ ሁሉ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም። ቁማር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱ የራስ ወዳድነት መንፈስ እንደነገሠ የሚያሳይ ሲሆን ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ስለተፈጸሙት ወንጀሎች የሚገልጹት አኃዛዊ መረጃዎችም ለዚህ ጠንካራ ማስረጃዎች ይሆናሉ።

በተለይ በዛሬው ጊዜ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው የምልክቱ ገጽታ የሚከተለው ነው:- “ሰዎች . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​2, 4) ሰዎች ሥጋዊ እርካታ ማግኘት የሚፈልጉ ቢሆንም ከአንድ የትዳር ጓደኛ ጋር ዕድሜ ልክ መኖር የሚያስከትለውን ኃላፊነት መሸከም አለመፈለጋቸው ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። በዚህም ሳቢያ ብዙ ቤተሰቦች ፈራርሰዋል፣ ልጆች ደስታቸው ከመሰረቁም በላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ፍቅራዊ ትስስር አጥተዋል፣ ቤተሰቦች በነጠላ ወላጅ ቀርተዋል፣ እንዲሁም በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በእጅጉ ተበራክተዋል።

ሌላው የምልክቱ ገጽታ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ” ይሆናሉ የሚለው ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​2) ዲ ሳይት የተሰኘው የጀርመን መጽሔት እንዳለው ከሆነ “[በዛሬው ጊዜ ያለው የኢኮኖሚ] ሥርዓት አንቀሳቃሽ ሞተር ራስ ወዳድነት ነው።” ዛሬ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በብዙዎቹ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ገንዘብ ነው። ሰዎች ይህን የራስ ወዳድነት ምኞት ሲያሳድዱ ሌሎቹን የሥነ ምግባር ደንቦች ችላ ይሏቸዋል።

በዓለም ላይ የሚታዩ ክስተቶች

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች የሥነ ምግባር ደንቦች መፈረካከስ የሚገልጽ ከመሆኑም በተጨማሪ በመጨረሻው ቀን በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሥር ነቀል ለውጦች እንደሚከሰቱም ይተነብያል። ለምሳሌ ያህል “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል” ይላል።​—⁠ሉቃስ 21:​10, 11

በ20ኛው መቶ ዘመን ካልሆነ በስተቀር እጅግ ብዙ ሰዎች በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በተከሰቱ ዓለምን የናጡ እጅግ በርካታ መቅሰፍቶች የተጠቁበት ሌላ ዘመን በታሪክ ውስጥ አልታየም። ለምሳሌ ያህል በ20ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱ ጦርነቶች ከ100 ሚልዮን የሚልቁ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን ቀደም ሲል በነበሩት በርከት ያሉ መቶ ዘመናት የጦርነት ሰለባ የሆኑት ሰዎች ቁጥር አንድ ላይ ቢደመር እንኳ ይህን አኃዝ የሚተካከል አይሆንም። በ20ኛው መቶ ዘመን የዓለም ጦርነት የተባሉ ከሌሎቹ ጦርነቶች በሙሉ የተለዩ ሁለት ጦርነቶች ተከስተዋል። ቀደም ሲል እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ግጭቶች ፈጽሞ ተከስተው አያውቁም።

ከበስተኋላ ሆኖ የሚገፋፋ ክፉ ኃይል

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን አማልሎ ከእውነተኛ የሥነ ምግባር ደንቦች በማራቅ የሥነ ምግባር ውድቀት ውስጥ እንዲዘፈቁ የማድረግ ዓላማ ያለው ‘ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባል’ አንድ ኃይለኛ የሆነ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር እንዳለም ይገልጻል። በመጨረሻው ቀን “ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ” ወደ ምድር እንደወረደ ይናገራል።​—⁠ራእይ 12:​9, 12

ዲያብሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘በአየሩ ላይ ማለትም በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን በሚሠራው መንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው አለቃ’ ተብሎ ተገልጿል። (ኤፌሶን 2:​1, 2) ይህ አነጋገር አንዳንድ ጊዜ በአየር ውስጥ ያለን የማይታይ በካይ ነገር ልብ ላንል እንደምንችል ሁሉ ዲያብሎስ ብዙውን ጊዜ ምንም ልብ ሳይሉት በብዙ ሰዎች ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያመለክታል።

ለምሳሌ ያህል ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደ ቪዲዮ፣ ፊልም፣ ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት፣ ማስታወቂያ፣ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ባሉ በርካታ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ ይንጸባረቃል። በተለይ ምንም በማያውቁት ወጣቶች ላይ የሚያተኩረው አብዛኛው መልእክት እንደ ዘረኝነት፣ አስማት፣ ብልሹ ሥነ ምግባርና ዘግናኝ የኃይል ድርጊቶች ባሉ አስከፊና ሰቅጣጭ የሆኑ አዝማሚያዎች የተሞላ ነው።

ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ቀን በሚሰጠው መግለጫና በዘመናችን ባለው ዓለም ውስጥ እየታዩ ባሉት ሁኔታዎች መካከል ያለው ተመሳሳይነት በጣም ያስደንቃቸዋል። እርግጥ ነው፣ ከ20ኛው መቶ ዘመን ቀደም ባሉት ጊዜያትም በአነስተኛ ደረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ ጋር የሚመሳሰሉ አንዳንድ ሁኔታዎች እንደተከሰቱ አይካድም። ይሁን እንጂ የምልክቱን ገጽታዎች በሙሉ ማየት የሚቻለው በ20ኛው መቶ ዘመን ላይና አሁን ደግሞ በ21ኛው መቶ ዘመን ላይ ብቻ ነው።

መጪው አዲስ ዘመን

የሰው ዘር ተጠራርጎ ይጠፋል ብለው የሚያምኑትም ሆኑ ያሉት ሁኔታዎች እንዳሉ ይቀጥላሉ የሚሉት ሰዎች አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ያለው ምድርን እየገዛ ያለው የዓለም ኅብረተሰብ ፍጹም አዲስ በሆነ ኅብረተሰብ እንደሚተካ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል።

ኢየሱስ በርከት ያሉ የመጨረሻው ቀን ምልክት ገጽታዎች ከዘረዘረ በኋላ “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:​31) የኢየሱስ ስብከት ዋና ጭብጥ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ነበር። (ማቴዎስ 6:​9, 10) አምላክ፣ ኢየሱስን በቅርቡ ምድርን በጠቅላላ የሚገዛው የዚህ መስተዳድር ማለትም የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል።​—⁠ሉቃስ 8:​1፤ ራእይ 11:​15፤ 20:​1-6

በመጨረሻው ቀን ፍጻሜ ላይ በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ጠላቶቹ የሆኑትን ዲያብሎስንና አጋሮቹን በማጥፋት በዛሬው ጊዜ ያለውን በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ኅብረተሰብ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይተካዋል። (ዳንኤል 2:​44) በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ወደ ገነትነት በተለወጠች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።​—⁠ሉቃስ 23:​43፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13፤ ራእይ 21:​3, 4

በአሁኑ ጊዜ ያለውን የሥነ ምግባር ውድቀት የሚጸየፉና የመጨረሻው ቀን ጥምር ምልክት በአሁኑ ጊዜ እየተከናወኑ ባሉት ሁኔታዎች ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ ያስተዋሉ ሰዎች ዕጹብ ድንቅ የሆነውን ጊዜ በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ። ይህ ተስፋ ለእኛ ለሰው ልጆች የሚያስበውንና የፍጥረት ሥራው ለሆነችው ለምድር ታላቅ ዓላማ ያለውን ሁሉን ቻይ አምላክ እንድናመሰግን ይገፋፋናል።​—⁠መዝሙር 37:​10, 11, 29፤ 1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያችንና ፈጣሪ ስለ እሱ ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ስለዘረጋው በሥነ ምግባር ንጹሕ በሆነ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ ይበልጥ እንድትማር ይጋብዙሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”​—⁠ዮሐንስ 17:​3

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ