በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛዬ የጎዳችኝ ለምንድን ነው?

ጓደኛዬ የጎዳችኝ ለምንድን ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ጓደኛዬ የጎዳችኝ ለምንድን ነው?

“ጥቂት ጓደኞች ነበሩኝ . . . ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከሌላ ሴት ልጅ ጋር ጓደኝነት ጀመሩ። ከእነሱ ጋር ስቀላቀል ወሬያቸውን ያቆማሉ። . . . ከማንኛውም እንቅስቃሴ ያገልሉኝ ጀመር። አድራጎታቸው ስሜቴን በጣም ጎድቶታል።”—ካረን *

በጣም በሚዋደዱ ጓደኛሞች መካ​ከል እንኳ ይህ ሊከሰት ይችላል። ዛሬ ፈጽሞ የማይነጣጠሉ ጓደኛሞች ነገ እርስ በርስ እንኳ መነጋገር ሊያቆሙ ይችላሉ። የ17 ዓመቷ ኖራ እንዲህ ትላለች:- “ጓደኛ ማለት ትምክህትና እምነት የምትጥሉበት፤ የፈለገው ነገር ቢመጣ እርዳታ ለማግኘት ልትጠጉት የምትችሉት ሰው መሆን አለበት።” አንዳንድ ጊዜ ግን የቅርብ ጓደኛሽ እንደ ቀንደኛ ጠላት ትሆንብሽ ይሆናል።

ችግር ላይ የወደቀ ወዳጅነት

አስደሳች በነበረ ወዳጅነት መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? ሳንድራ ከጓደኛዋ ከሜገን ጋር የተቃቃረችው የምትወደውን ሸሚዟን ባዋሰቻት ጊዜ ነበር። ሳንድራ እንዲህ ትላለች:- “ሸሚዙን ስትመልስልኝ ቆሽሾና እጅጌው ላይ ትንሽ ተቀድዶ ነበር። የማላየው ይመስል ምንም ሳትል ነው የሰጠችኝ።” ሜገን ባሳየችው አሳቢነት የጎደለው ድርጊት ሳንድራ ምን ተሰማት? “ናላዬ ነው የዞረው” ብላለች። “ለንብረቶቼም . . . ሆነ ለስሜቴ ደንታ ቢስ እንደሆነች ተሰማኝ።”

በተጨማሪም አንድ የቅርብ ጓደኛሽ የሚያሳፍርሽን ነገር በማድረጓ ወይም በመናገሯ ስሜትሽ ይጎዳ ይሆናል። ሲንዲ ሰብሰብ ብለው ለነበሩ የክፍል ጓደኞቿ በክፍል ለምታቀርበው በአንድ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ሪፖርት ገና ምንም አለማንበቧን ስትነግራቸው ይህ ሁኔታ አጋጥሟታል። በድንገት ኬት የምትባለው ጓደኛዋ ትዘልፋት ጀመር። “በርከት ያሉ ጓደኞቻችን ባሉበት አዋረደችኝ” ስትል ሲንዲ ታስታውሳለች። “በጣም ነው የተናደድኩባት። ከዚያ በኋላ ግንኙነታችን እንደ ቀድሞው አልሆነም።”

አንዳንድ ጊዜ ወዳጅነታችሁ የሚሻክረው ጓደኛሽ በቅርቡ ከተዋወቀቻቸው ጓደኞቿ ጋር መሆን ስትጀምር ነው። የ13 ዓመቷ ቦኒ እንዲህ ትላለች:- “አንዲት ጥሩ ጓደኛ ነበረችኝ፤ በኋላ ግን ራሳቸውን ከሚያገልሉ ልጆች ጋር ገጠመች። እንዲሁም ችላ ትለኝ ጀመር።” ወይም ጓደኛሽ ካንቺ ጋር እንድትወዳጅ ያደረጋትን ስውር ዓላማ ማስተዋል ጀምረሽ ይሆናል። የ13 ዓመቱ ጆ እንዲህ ይላል:- “እኔና ቦቢ ጥሩ ጓደኛሞች ነበርን። ቦቢ የሚወደኝ ባለኝ ባሕርይ ይመስለኝ ነበር። በኋላ ግን ይወደኝ የነበረው አባቴ የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጅ በመሆኑ የስፖርት ግጥሚያዎችና የሙዚቃ ትርዒቶች መግቢያ በርከት ያሉ ትኬቶች ሁልጊዜ ስለሚያገኝ መሆኑን ተገነዘብኩ።” በዚህ ጊዜ ጆ ምን ተሰማው? “ካሁን በኋላ ቦቢን ጭራሽ አላምነውም!” ሲል ተናግሯል።

በአንዳንድ ሁኔታዎች አንዲት ጓደኛሽ በምሥጢር እንዲያዝ የፈለግሽውን ጉዳይ ለሌሎች ታወራብሽ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አሊሰን አብሯት የሚሠራው ሰው ስላሉበት የግል ችግሮች ለጓደኛዋ ለሤራ ነግራት ነበር። በነጋታው ሤራ እዚያው ሰውዬው ባለበት ጉዳዩን አነሳች። አሊሰን “ጭራሽ እንደዚያ ትቀበጣጥራለች ብዬ አልጠበቅሁም! በጣም አናደደችኝ” ብላለች። የ16 ዓመቷ ሬቸልም አንዲት የቅርብ ጓደኛዋ ሁለቱ በግል የተወያዩበትን ጉዳይ ለሌሎች ባወራችበት ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟታል። ሬቸል “በጣም ተሸማቀቅሁ፤ የካደችኝም መስሎ ተሰማኝ። ‘ካሁን በኋላ ምን ብዬ ምሥጢር ላካፍላት እችላለሁ?’ ስል አሰብኩ” ብላለች።

በተለይ እርስ በርስ የመተሳሰብ፣ የመተማመን እና የመከባበር ስሜት የሚንጸባረቅበት ጓደኝነት የስሜታዊ ድጋፍ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የጠበቀ ወዳጅነት ሳይቀር ውጥረት ሊያጋጥመው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ወዳጅነት ለብዙ ጊዜ አይዘልቅም።” (ምሳሌ 18:​24 የ1980 ትርጉም ) መንስዔው ምንም ይሁን ምን ጓደኛሽ እንደከዳችሽ ሲሰማሽ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንብሽ ይችላል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ወዳጅነት የሚላላበት ምክንያት

በወጣቶችም ሆነ በጎልማሶች መካከል የተመሠረተ የትኛውም ሰብዓዊ ዝምድና ከችግር ነፃ አይደለም። ጉዳዩ ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ እንዲህ ሲል እንደጻፈው ነው:- “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:​2፤ 1 ዮሐንስ 1:​8) ሁሉም ሰው ስለሚሳሳት በሆነ ወቅት ጓደኛሽ ቅር የምትሰኚበትን ነገር ማድረጓ ወይም መናገሯ አይቀርም። አንቺም ጓደኛሽን የጎዳሽበት ጊዜ እንዳለ ትዝ ይልሽ ይሆናል። (መክብብ 7:​22) የ20 ዓመቷ ሊሳ “ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን ማበሳጨታችን አይቀርም” ብላለች።

ከሰብዓዊ አለፍጽምና በተጨማሪ በጉዳዩ ሊካተቱ የሚችሉ ሌሎች ነጥቦችም አሉ። በእድሜና በአስተሳሰብ እየበሰልሽ ስትሄጂ ያንቺም ሆነ የጓደኞችሽ ፍላጎት የመለወጥ አዝማሚያ እንዳለው አስታውሺ። በመሆኑም በአንድ ወቅት በርካታ የጋራ ፍላጎቶች የነበሯቸው ሁለት ሰዎች ቀስ በቀስ ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራራቁ ይሄዱ ይሆናል። በአሥራዎቹ እድሜ የምትገኝ አንዲት ልጅ በጣም የምትወዳትን ጓደኛዋን በተመለከተ እንዲህ ስትል ምሬቷን ገልጻለች:- “እንደ በፊቱ ቶሎ ቶሎ አንደዋወልም፤ ስንነጋገር ደግሞ በየትኛውም ጉዳይ ላይ መግባባት ያቅተናል።”

እርግጥ ቅራኔ ሳይፈጠር እንዲሁ መራራቅ አንድ ነገር ነው። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ጓደኞቻቸውን የሚጎዱት ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ምክንያት የሚሆነው ቅንዓት ነው። ለምሳሌ ያህል ጓደኛሽ በተፈጥሮ ችሎታዎችሽ ወይም ባገኘሻቸው ስኬቶች የተነሳ መጥፎ ስሜት አድሮባት ይሆናል። (ከዘፍጥረት 37:​4 እና ከ1 ሳሙኤል 18:​7-9 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ቅንዓት . . . አጥንትን ያነቅዛል።” (ምሳሌ 14:​30) ቅንዓት፣ ምቀኝነትና ጠብ ይወልዳል። መንስዔው ምንም ይሁን ምን ጓደኛሽ ከጎዳችሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

እርቅ እንዲሰፍን ማድረግ

ሬቸል እንዲህ ትላለች:- “በመጀመሪያ ግለሰቡን/ቧን አጤንና ሆን ብለው ያደረጉት መሆን አለመሆኑን ለማወቅ እጥራለሁ።” አክብሮት የጎደለው ንግግር ወይም ድርጊት ዒላማ እንደሆንሽ ሲሰማሽ በጊዜው በተሰማሽ ስሜት ላይ ብቻ ተመሥርተሽ ምላሽ አትስጪ። ከዚህ ይልቅ ትዕግሥተኛ በመሆን ነገሩን በጥሞና አስቢበት። (ምሳሌ 14:​29) አንቺን ለመጉዳት የታቀደ መስሎ ለተሰማሽ ነገር በችኮላ አጸፋ መመለስሽ በእርግጥ ሁኔታውን ሊያሻሽለው ይችላልን? ጉዳዩን ካመዛዘንሽ በኋላ መዝሙር 4:​4 ላይ የሚገኘውን ምክር ለመከተል ትመርጪ ይሆናል:- “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ፤ በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ።” ከዚያም ‘ፍቅር የኃጢአትን ብዛት እንዲሸፍን’ ለማድረግ ትመርጪ ይሆናል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​8

ይሁን እንጂ የተጎዳሽበትን ድርጊት እንዲሁ ችላ ብለሽ ማለፍ እንደማትችይ ከተሰማሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ጊዜ ልጅቷን ቀርበሽ ማነጋገርሽ የተሻለ ሊሆን ይችላል። “ሁለታችሁ ብቻችሁን ሆናችሁ ጉዳዩን በውይይት ፍቱት” ሲል የ13 ዓመቱ ፍራንክ ተናግሯል። “ይህ ካልሆነ ቂም መያዛችሁ አይቀርም።” የ16 ዓመቷ ሱዛንም ተመሳሳይ አመለካከት አላት። “ማድረግ ያለባችሁ ከሁሉ የተሻለው ነገር እምነት ትጥሉባቸው የነበረ ቢሆንም እንደጠበቃችኋቸው ሆነው እንዳላገኛችኋቸው መንገር ነው” ብላለች። ጃክሊንም ቅራኔዎችን በግል ቀርቦ በማነጋገር መፍታቱን ትመርጣለች። “ነገሩን ሳላድበሰብስ ለማውጣት እሞክራለሁ። በአብዛኛው ግለሰቡ በግልጽ ስለሚያነጋግራችሁ ወዲያውኑ ችግሩን መፍታት ትችላላችሁ” ብላለች።

እርግጥ፣ ጓደኛሽን ቀርበሽ የምታነጋግሪው በቁጣ መንፈስ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብሽ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ቁጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 15:​18) ስለዚህ ሁኔታውን ለማስተካከል ከመሞከርሽ በፊት ቁጣው እስኪበርድልሽ ድረስ ታገሺ። ሊሳ በግልጽ እንዲህ ትላለች:- “መጀመሪያ ከፍተኛ ንዴት ይሰማችኋል፤ ሆኖም ንዴታችሁ እንዲበርድላችሁ ማድረግ አለባችሁ። በሰውዬው ላይ ያደረባችሁ ኃይለኛ ንዴት እስኪበርድላችሁ ድረስ ታገሱ። ከዚያ በኋላ ወደ ሰውዬው ሄዳችሁ ቁጭ ብላችሁ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ መወያየት ትችላላችሁ።”

“ሰላማዊ” የሚለው ቃል ቁልፍ ነው። ዓላማሽ ጓደኛሽን በንግግር ለመጉዳት እንዳልሆነ አስታውሺ። ዓላማሽ ጉዳዩን በወዳጃዊነት መንፈስ መፍታትና በተቻለ መጠን ወዳጅነታችሁን ማደስ ነው። (መዝሙር 34:​14) ስለዚህ ከልባችሁ ለመናገር ሞክሩ። ሊሳ እንዲህ የሚል ሐሳብ ታቀርባለች:- “ ‘እኔና አንቺ ጓደኛሞች ነን፤ ሆኖም በመካከላችን እንዴት ችግር ሊፈጠር እንደቻለ አልገባኝም’ ማለት ትችላላችሁ። ከድርጊቱ በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ማወቅ አለባችሁ። ምክንያቱን ካወቃችሁ በኋላ በአብዛኛው ችግሩን ማስወገድ ያን ያህል አይከብዳችሁም።”

ምናልባት ጓደኛሽን በማማትና ሌሎች ለአንቺ እንዲወግኑ ለማድረግ በመጣር አጸፋ ለመመለስ መሞከሩ ፈጽሞ ስህተት ይሆናል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ በሮሜ ላሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ።” (ሮሜ 12:​17) በእርግጥም ጉዳቱ የቱንም ያህል የከፋ ቢሆን አጸፋ መመለስ ነገሮችን ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። ኖራ እንዲህ ትላለች:- “ቂም በቀል ጓደኝነታችሁ ለዘለቄታው እንዲበጠስ ስለሚያደርግ ምንም ጥቅም አያስገኝም።” በአንጻሩ ዝምድናችሁ እንዲቀጥል አቅማችሁ የሚፈቅድላችሁን ሁሉ ማድረጋችሁ “የተሻላችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ እንዲሰማችሁ ያደርጋል” ስትል አክላ ተናግራለች።

ሆኖም እርቅ እንዲሰፍን ላደረግሽው ጥረት ጓደኛሽ ምላሽ ሳትሰጥ ብትቀርስ? በዚህ ጊዜ ወዳጅነት ደረጃው እንደሚለያይ አስታውሺ። የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ጁዲት ማክሊስ “ጓደኛ የተባለ ሁሉ የቅርብ ወዳጅ አይሆንም። የተለያየ ዓይነት ዝምድና ሊኖራችሁ እንደሚችል እወቁ” ብለዋል። የሆነ ሆኖ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የበኩልሽን ድርሻ እንደተወጣሽ ማወቅሽ ሊያጽናናሽ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”​—⁠ሮሜ 12:​18፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

በጠበቀ ወዳጅነት መካከልም እንኳ ችግር ሊከሰት ይችላል። ለሌሎች ያለሽን አመለካከት ሳታዛቢ ወይም ለራስሽ ያለሽን አክብሮት ሳታጠፊ ችግሩን ከተቋቋምሽ እየጎለመስሽ ነው ማለት ነው። ምንም እንኳ ‘አንዳንድ ወዳጅነት ለብዙ ጊዜ የሚዘልቅ’ ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ መኖሩንም’ ያረጋግጥልናል።​—⁠ምሳሌ 18:​24

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በተፈጸመው ሁኔታ ላይ በመነጋገር ወዳጅነታችሁን ማደስ ትችላላችሁ