በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ላክቶስ አይስማማህምን?

ላክቶስ አይስማማህምን?

ላክቶስ አይስማማህምን?

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“እኔና ባለቤቴ በሜክሲኮ ፑይብላ ክፍለ ሃገር የሚገኙ ወዳጆቻችንን ለመጠየቅ ሄደን ነበር። አስተናጋጆቻችን የራሳቸው ላሞች ስለነበሯቸው ቁርስና እራት ላይ ትኩስ ወተት አቀረቡልን።

“በመጀመሪያው ምሽት ጥቂት የህመም ስሜት ተሰማን። በሁለተኛው ቀን ግን በጣም አመመን። ሆዴ በጣም በመነፋቱ የተነሳ የደረሰች ነፍሰ ጡር መሰልኩ። ከዚያ በኋላ ሁለታችንም አስቀመጠን።

“ሁለታችንም ላክቶስ እንደማይስማማን ያወቅነው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነበር።”​—⁠ቤርታ

ቤርታ ያጋጠማት ሁኔታ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ምክንያቱም አንዳንዶች እንደሚገምቱት በጉልምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙት የዓለም ሕዝቦች መካከል 75 በመቶ የሚያክሉት ላክቶስ በማይስማማቸው ሰዎች ላይ የሚከሰቱት አንዳንድ ምልክቶች ወይም ሁሉም ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላል። * ይሁን እንጂ ይህ ነገር ምንድን ነው? መንስዔውስ ምንድን ነው? በይበልጥ ደግሞ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል?

አንድ ሰው “ላክቶስ አልተስማማውም” የሚባለው ሰውነቱ ላክቶስ የሚባለውን በወተት ውስጥ የሚገኝ ስኳር ማላምና ማዋሃድ ሲያቅተው ነው። ላክቶስ ደማችን ውስጥ ከመግባቱ በፊት ወደ ግሉኮስ እና ወደ ጋላክቶስ መለወጥ አለበት። ለዚህ ተግባር ላክቴስ የተባለ ኢንዛይም አስፈላጊ ይሆናል። ችግር የሚፈጠረው ከሕፃንነት ዕድሜ በኋላ ሰውነት የሚያመነጨው ላክቴስ እየቀነሰ መሄዱ ነው። ብዙ ትላልቅ ሰዎች የላክቴስ እጥረት ስለሚኖርባቸው ላክቶስ የማይስማማቸው ይሆናሉ።

አንድ ሰው በወተትና በወተት ተዋጽኦዎች አማካኝነት ሰውነቱ ሊያዋህደው ከሚችለው የበለጠ ላክቶስ በሚወስድበት ጊዜ በደንዳኔ አንጀት ውስጥ የሚገኙት ባክቴሪያዎች ላክቶሱን ወደ ላክቲክ አሲድና ወደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ይለውጡታል። ከ30 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መደበኛ የሆኑት የህመም ስሜቶች መታየት ይጀምራሉ። የማቅለሽለሽ፣ የቁርጠት፣ የሆድ መነፋትና የተቅማጥ ምልክቶች ይከሰታሉ። ላክቶስ የማይስማማቸው መሆኑን ያላወቁ አንዳንድ ሰዎች የሚያሽላቸው መስሏቸው ተጨማሪ ወተት ስለሚጠጡ ችግራቸው ይባባሳል።

የላክቶስ አለመስማማት የሚያስከትለው የህመም መጠን ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። አንዳንዶች የጠጡት ወተት መጠን አነስተኛ ከሆነ ምንም ዓይነት ችግር አያስከትልባቸውም። ሌሎች ደግሞ ትንሿ እንኳ የህመም ስሜት ታስከትልባቸዋለች። ምን ያህል ወተት መውሰድ እንደምትችል ለማወቅ አንዳንዶች የሚከተለውን ምክር ይሰጣሉ። መጀመሪያ ትንሽ ብርጭቆ ወተት ጠጣ። ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ በተከታታይ ጊዜያት የምትጠጣውን ወተት እየጨመርክ ተመልከት። የላክቶስ አለመስማማት የሚያስከትለው ህመም የሚያስጨንቅ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት አደጋ የማያስከትል መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

ምን መብላት ምንስ ማስወገድ ያስፈልጋል?

የላክቶስ አለመስማማት የሚያስቸግርህ ከሆነ ምን ለመብላት እንደምትችልና ምን መብላት እንደማትችል መወሰን ያስፈልግሃል። ይህ በአብዛኛው የሚመካው ላክቶስ በመቋቋም ችሎታህ ላይ ነው። ላክቶስ የሚገኝባቸው ምግቦች ወተት፣ አይስክሬም፣ እርጎ፣ ቅቤና አይብ ናቸው። አንዳንድ እንደ ኬክና የሰላጣ ማጣፈጫዎች የመሰሉ የተዘጋጁ ምግቦችም ላክቶስ ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ ላክቶስ የማይስማማቸው ሰዎች እንደ እነዚህ ባሉት ምግቦች ላይ የተጻፈውን ማስታወቂያ ማንበብ ያስፈልጋቸዋል።

እርግጥ ወተት ዋነኛው የካልሲየም ምንጭ ሲሆን በቂ ካልሲየም አለመውሰድ ደግሞ የአጥንት መቦርቦር ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ላክቶስ የማይስማማቸው ሰዎች ሌሎች የካልሲየም ምንጮችን መፈለግ ይኖርባቸዋል። እንደ ብሮኮሊ፣ ጎመንና ስፒናች የመሰሉ አትክልቶች ካልሲየም አላቸው። በተጨማሪም እንደ ለውዝ፣ ሰሊጥ እንዲሁም እንደ ሰርዲንና ሳልሞን የመሳሰሉ ለስላሳ አጥንት ያላቸው ዓሦች ጥሩ የካልሲየም ምንጮች ናቸው።

ላክቶስ የማይስማማህ ብትሆንም ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ላያስፈልግህ ይችላል። ምን ያህል ብትጠጣ እንደሚስማማህ ከወሰንክ በኋላ ከዚያ መጠን ያላለፈ ወተትና የወተት ተዋጽዖ ልትወስድ ትችላለህ። የሚቻል ከሆነ ሌሎች ምግቦችን ላክቶስ ካላቸው ምግቦች ጋር አቀናጅተህ ውሰድ። በተጨማሪም ለብዙ ጊዜ የቆየ ደረቅ አይብ ያለው የላክቶስ መጠን አነስተኛ ሲሆን ችግር ላያመጣብህ ይችላል። እርጎስ? በእርጎ ውስጥ ያለው የላክቶስ መጠን በወተት ውስጥ ከሚኖረው የላክቶስ መጠን የማያንስ ቢሆንም ላክቶስ የማይስማማቸው አንዳንድ ሰዎች እርጎ ሲወስዱ ምንም ችግር አያጋጥማቸውም። ለምን? በእርጎ ውስጥ ላክቴስን የሚሠሩ ባክቴሪያዎች በመኖራቸው ነው። ይህ ደግሞ ላክቶስ ከሰውነት ጋር እንዲዋሃድ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ስለዚህ ላክቶስ የማይስማማህ ከሆነ አትጨነቅ። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ስለዚህ ሕመም ማወቅህ ሕመሙን በቀላሉ እንድትቆጣጠር ያስችልሃል። ይሁን እንጂ የሚከተሉትን ነጥቦች መዘንጋት የለብህም:-

(1) የሚስማማህ የወተት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ወተትና የወተት ተዋጽዖ ከሌሎች ምግቦች ጋር ውሰድ።

(2) በይበልጥ በቀላሉ ሊዋሃዱ የሚችሉትን እንደ እርጎና የቆየ አይብ የመሰሉ ምግቦችን ተመገብ።

(3) በተቻለ መጠን ከላክቶስ ነፃ የሆኑ የምግብ ውጤቶችን ወይም ላክቴስ የሚገኝባቸውን የምግብ ውጤቶች ተጠቀም።

እነዚህን ምክሮች ከተከተልክ ላክቶስ ሊያስከትልብህ የሚችለውን ችግር መቋቋም ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የላክቶስ አለመስማማት ችግር ከማንኛውም ሕዝቦች ይበልጥ እስያውያንን ያጠቃል። የሰሜን አውሮፓ ተወላጆች በዚህ ችግር እምብዛም አይጠቁም።

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የላክቶስ አለመስማማት ችግር መኖሩን መርምሮ ማወቅ

የላክቶስ አለመስማማት ችግር መኖሩን መርምሮ ለማወቅ የሚያስችሉ በርካታ ዘዴዎች አሉ።

ላክቶስ ይስማማህ እንደሆነ ለማወቅ የሚካሄድ ምርመራ:- በሽተኛው ምንም ዓይነት ምግብ ሳይወስድ ከቆየ በኋላ ላክቶስ ያለበት ፈሳሽ ይጠጣል። ከዚያም የደሙ ናሙና ተወስዶ ላክቶሱ ምን ያህል ከሰውነቱ ጋር እየተዋሃደ እንዳለ ይመረመራል።

የሃይድሮጅን ትንፋሽ ምርመራ:- በሚገባ ያልተዋሃደ ላክቶስ ሃይድሮጅንን ጨምሮ የተለያዩ ጋዞች ይፈጥራል። ይህም በአንጀት በኩል ወደ ደም ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ሳንባ ሄዶ በትንፋሽ ይወጣል።

የሰገራ አሲድ ምርመራ:- በሚገባ ያልተዋሃደ ላክቶስ በደንዳኔ አንጀት ውስጥ አሲዶችን ስለሚፈጥር እነዚህ አሲዶች በሰገራ ምርመራ ሊታወቁ ይችላሉ።

እነዚህ ምርመራዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄዱት ሆስፒታል መተኛት ሳያስፈልግ በተመላላሽነት ነው።