በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰውነትን ስለ መበሳት ምን ማለት ይቻላል?

ሰውነትን ስለ መበሳት ምን ማለት ይቻላል?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ሰውነትን ስለ መበሳት ምን ማለት ይቻላል?

‘ከንፈራቸውንና ሌሎች የሰውነ​­ታቸውን ክፍሎች የተበሱ ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት “ወይኔ! እንዴት ያምራል!” ስል አሰብኩ።’​—⁠ሊሳ

እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላት ሊሳ ብቻ አይደለችም። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው፣ ቅንድባቸው፣ ምላሳቸው፣ ከንፈራቸውና እምብርታቸው ላይ ሳይቀር ጉትቻና ጌጥ ያደርጋሉ። ይህ ልማድ ሰውነትን መበሳት ተብሎ ይጠራል። *

ሄተር የተባለችው የ16 ዓመት ወጣት ይህን ልማድ የመከተል ጉጉት አድሮባታል። እምብርቷ ላይ ጌጥ ብታደርግ “በጣም እንደሚያምርባት” ሆኖ ተሰምቷታል። የአሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ጆ ደግሞ በክብደት ማንሻ ቅርጽ የተሠራ የወርቅ ጌጥ ምላሱ ላይ አድርጓል። ሌላዋ ወጣት ደግሞ “ሰዎችን ጉድ የሚያሰኝ” “በጣም አስገራሚ” ነገር ማድረግ ስለፈለገች ቅንድቧን መበሳት መርጣለች።

ሰውነት ላይ ጌጣጌጥ ማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣ ልማድ አይደለም። ጥንት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላካዊ ፍርሃት የነበራት ርብቃ የምትባል ሴት አፍንጫዋ ላይ ጌጥ ታደርግ ነበር። (ዘፍጥረት 24:​22, 47) እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ሲወጡ የጆሮ ጉትቻ አድርገው ነበር። (ዘጸአት 32:​2) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ጌጣጌጥ ያደርጉ የነበረው ጆሮአቸውንና አፍንጫቸውን በመብሳት ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ታማኝ ባሪያዎች ለጌቶቻቸው ያደሩ ለመሆናቸው ምልክት ሆኖ እንዲያገለግል ጆሯቸውን ይበሱ ነበር። (ዘጸአት 21:​6) በሌሎች ጥንታዊ ባሕሎች ዘንድም መበሳት ጉልህ ስፍራ ነበረው። አዝቴኮችና ማያዎች ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምላሳቸውን ይበሱ ነበር። በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ ሕንዶች ዘንድ ከንፈርን መብሳት እስካሁን ድረስ በእጅጉ የተስፋፋ ልማድ ነው። ሜላኔዥያውያን እንዲሁም ሕንዶችና ፓኪስታኖች አፍንጫ ላይ የሚንጠለጠሉ ጌጣጌጦች ማድረጋቸው የተለመደ ነገር ነው።

በምዕራቡ ዓለም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ሰውነትን መበሳት በጥቅሉ በሴቶች ለምለም ጆሮ (earlobe) ላይ ብቻ የተወሰነ ልማድ ነበር። አሁን ግን በሁለቱም ጾታዎች የሚገኙ በአሥራዎቹ እድሜ ያሉ ልጆችና ወጣቶች ማንጠልጠል በሚቻልበት በየትኛውም የሰውነታቸው ክፍል ላይ ጌጣጌጥ ያደርጋሉ።

የሚበሱበት ምክንያት

ብዙዎች የሚበሱት የዘመኑ ፋሽን እንደሆነ ስለሚሰማቸው ነው። ሌሎች ደግሞ መልካቸውን የሚያሳምርላቸው ይመስላቸዋል። እውቅ ሞዴሎች፣ የስፖርት ኮከቦችና ዝነኛ አቀንቃኞች ሰውነት ላይ የሚደረግ ጌጣጌጥ መጠቀማቸው ይህ ወረት እንዲዛመት እንዳደረገ የታወቀ ነው። ለአንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ይህ ልማድ በራስ የመመራት ዝንባሌያቸውን የሚገልጹበት፣ የግለኝነት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩበትና ከሰው የተለዩ መሆናቸውን የሚናገሩበት መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ይመስላል። የአንድ ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ጆን ሊዮ እንዲህ ብለዋል:- “ወላጆቻቸውን ለማበሳጨትና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በግርምት ለማስደመም ሲሉ ብዙ ቦታ ላይ መበሳትን ሥራዬ ብለው የያዙት ይመስላል።” ስሜታቸውን በዚህ መንገድ እንዲገልጹ የሚገፋፋቸው እርካታ ማጣት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ እምቢተኝነትና የዓመፀኛነት ባሕርይ ሊሆን ይችላል።

እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ወይም ስሜታዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ብለው የሚበሱም አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ወጣቶች ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት የሚያሳድግላቸው ይመስላቸዋል። በልጅነታቸው ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው አንዳንድ ወጣቶች በሰውነታቸው ላይ ያላቸውን የበላይነት የሚገልጹበት መንገድ አድርገው ይመለከቱታል።

በጤና ላይ ሊከሰት የሚችል ጉዳት

ሆኖም ሁሉም ዓይነት ሰውነትን የመበሳት ልማድ ጉዳት የለውም? በሕክምናው መስክ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች አንዳንዱ ጉዳት እንደሚያስከትል ይናገራሉ። ራስን በራስ መብሳት ለጤና አደገኛ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። እንዲሁም ባለሙያ ነው የሚባል ሰው ጋር ሄዶ መበሳትም የራሱ ጉዳት ሊኖረው ይችላል። አብዛኞቹ ሙያውን የሚማሩት ከጓደኞቻቸው፣ ከመጽሔቶች ወይም ከቪዲዮ ፊልሞች በመሆኑ በቂ ሥልጠና የላቸውም። ከዚህ የተነሳ የንጽሕና አጠባበቅ ዘዴዎችን ካለመጠቀማቸውም በላይ ሰውነትን ከመብሳት ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉትን ጉዳቶች አይረዱ ይሆናል። እንዲሁም ሰውነትን በመብሳት ሙያ የተሰማሩ በርካታ ሰዎች የሰውነት ብልቶችን በተመለከተ ያላቸው እውቀት ውስን ነው። ያልሆነ ቦታ ላይ መብሳት ብዙ ደም መፍሰስ ሊያስከትል ስለሚችል ይህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በስህተት ነርቭ መንካት ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ በበሽታ የመለከፍ አደጋ ነው። ያልተቀቀለ የሕክምና መሣሪያ እንደ ሄፐታይተስ፣ ኤድስ፣ ነቀርሳና መንጋጋ ቆልፍ የመሳሰሉ ቀሳፊ በሽታዎችን ሊያስተላልፍ ይችላል። ጀርም ማስወገጃ ዘዴዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜም እንኳ ድርጊቱ ከተከናወነ በኋላ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል እምብርት ላይ መበሳት ልብስ በሚለበስበትም ሆነ በሚወልቅበት ጊዜ ስለሚነካካ የሕመም ስሜት ያስከትላል። በመሆኑም ቁስሉ እስኪሽር እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ ሊወስድ ይችላል።

የአፍንጫና የጆሮን ልማፅም (cartilage) መበሳት ለምለም ጆሮን ከመበሳት ይበልጥ አደገኛ መሆኑን ሐኪሞች ይናገራሉ። በአሜሪካ የሚገኘው በፊት ላይ የሚደረግ የማስዋቢያና የማስተካከያ ቀዶ ሕክምና አካዳሚ ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በላይኛው የጆሮ ክፍል ላይ የሚደረጉ ቀዳዳዎች በጣም ሊታሰብባቸው ይገባል። ከበድ ያሉ ኢንፌክሽኖች የላይኛው ቆልማማ የጆሮ ክፍል ባጠቃላይ እንዲቆረጥ ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲሁም አፍንጫ ላይ ጉትቻ ማድረግ አደገኛ ነው። በዚህ አካባቢ የሚፈጠር ኢንፌክሽን በአቅራቢያው ያሉትን የደም ሥሮች ሊበክልና ወደ አንጎል ሊሰራጭ ይችላል።” ጽሑፉ እንዲህ ሲል ደምድሟል:- “[ሰውነትን የመበሳት ልማድ] በለምለም ጆሮ አካባቢ ብቻ ቢወሰን ይመረጣል።”

ሌላው ችግር መጥፎ ጠባሳ ሊፈጠር የሚችል መሆኑና ቀዳዳው ላይ የሚደረገው ጌጥ ለሰውነት አለርጂ ሊሆን የሚችል መሆኑ ነው። እንደ ጡት በመሳሰሉ በቀላሉ የሚጎዱ የሰውነት ክፍሎች ላይ የተደረጉ ጌጦች በልብስ ከተያዙ ወይም ከተጎተቱ በቀላሉ ቀዳዳውን ሊቦጭቁት ይችላሉ። በአንዲት ወጣት ልጃገረድ ጡት ላይ ኅብረኅዋሱ ጠባሳ ማውጣቱ የወተት ቧንቧዎችን ሊደፍን የሚችል ሲሆን ሕክምና ካላገኘች ደግሞ ወደፊት ሕፃን ልጅ ማጥባት ሊያስቸግራት ወይም ሊያቅታት ይችላል።

በቅርቡ የአሜሪካ የጥርስ ሕክምና ማኅበር አፍ አካባቢ የመበሳት ልማድን በኅብረተሰብ ጤና ላይ የተደቀነ አደጋ ሲል ገልጾታል። አፍ አካባቢ መበሳት ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ሌሎች አደጋዎችም አሉ:- ጌጡን ከዋጡ በኋላ ጉሮሮ ውስጥ ሊሰነቀር ይችላል፣ በተጨማሪም የምላስ መደንዘዝና የመቅመስ ችሎታ ማጣት፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የደም መፍሰስ፣ የጥርስ መሸረፍ ወይም መሰንጠቅ፣ የምራቅ መጠን መጨመር፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የምራቅ መዝረክረክ፣ የድድ መቁሰል፣ እንዲሁም የመናገር፣ የመተንፈስ፣ የማኘክና የመዋጥ ችግር ሊከሰት ይችላል። ኬንድራ የምትባል አንዲት ወጣት ምላስዋን በተበሳች ጊዜ ምላስዋ “እንደ ፊኛ ተነረተ።” ምላስዋን የበሳት ሰው አገጭ ላይ የሚደረግ ጌጥ መጠቀሙ ችግሩን ያባባሰው ሲሆን ይህም ምላስዋን ተርትሮ ከታች ያለውን ኅብረኅዋስ ቀድዶ ወጣ። ኬንድራ የመናገር ችሎታዋን ልታጣ ምንም አልቀራትም ነበር።

አምላክ እስራኤላውያን ሰውነታቸውን በአክብሮት እንዲይዙና የአካል ክፍላቸውን ከመቁረጥ እንዲርቁ ነግሯቸዋል። (ዘሌዋውያን 19:​28፤ 21:​5፤ ዘዳግም 14:​1) ምንም እንኳ ዛሬ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ሰውነታቸውን በአክብሮት እንዲይዙ አሁንም ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 12:​1) አላስፈላጊ የሆኑ ጤንነትን ለጉዳት የሚዳርጉ ድርጊቶችን ማስወገድ ምክንያታዊ አይደለምን? የሆነ ሆኖ ከጤና በተጨማሪ ልታጤኗቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች አሉ።

ምን ዓይነት መልእክት ያስተላልፋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰውነት መበሳትን በተመለከተ ቀጥተኛ መመሪያ አይሰጥም። ይሁን እንጂ አጋጌጣችን ‘ከእፍረትና ራስን ከመግዛት ጋር’ እንዲሆን ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​9) አንድ ልማድ በአንደኛው የዓለም ክፍል ልከኛ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ቢችልም እንኳ ዋናው ቁም ነገር እናንተ በምትኖሩበት አካባቢ እንዴት ይታያል የሚለው ነው። ለምሳሌ ያህል ሴቶች ጆሯቸውን መበሳታቸው በአንዱ የዓለም ክፍል ተቀባይነት ያለው ነገር ተደርጎ ይታይ ይሆናል። ይሁን እንጂ በሌላ አገር ወይም ባሕል አንዳንዶች በነገሩ ላይደሰቱ ይችላሉ።

ወንዶች ሰውነታቸውን መበሳታቸውና ጉትቻ ማንጠልጠላቸው በዓለማችን እውቅ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያግኝ እንጂ በምዕራቡ ዓለም እስካሁን ድረስ ሰፊ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። አንዱ ምክንያት እንዲህ ያሉት ድርጊቶች የእስረኞች፣ ሞተር ብስክሌት የሚነዱ ዱርዬዎች፣ የሮክ አቀንቃኞችና ሌሎችን ማሰቃየት የሚያስደስታቸውና ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሰዎች መለያ ምልክት ሆነው በመቆየታቸው ነው። በብዙዎች ዘንድ ሰውነትን መበሳት በራስ የመመራት መንፈስና የዓመፀኝነት ትርጉም ሲሰጠው ቆይቷል። ብዙዎች አሳፋሪና ነውር አድርገው ይመለከቱታል። አሽሊ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ልጃገረድ እንዲህ ትላለች:- “ክፍሌ ውስጥ ያለ አንድ ልጅ በቅርቡ አፍንጫውን ተበስቷል። በእሱ ቤት በጣም የሚያምርበት መስሎታል። ለኔ ግን አስቀያሚ ሆኖ ነው የሚታየኝ!”

በመሆኑም አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ የታወቀ የገበያ አዳራሽ ከደንበኞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሠራተኞች በሁለቱ ጆሮዎቻቸው ላይ ማድረግ የሚፈቀድላቸው አንድ አንድ ጉትቻ ብቻ እንደሆነና በግልጽ በሚታይ በሌላ የአካል ክፍል ላይ መበሳት የተከለከለ መሆኑን የሚገልጽ ደንብ ማውጣቱ ምንም አያስገርምም። የአንድ ድርጅት ቃል አቀባይ “ደንበኞቻችን ምን ምላሽ እንደሚሰጡ መገመት አይቻልም” ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የሥራ ፈላጊዎች አማካሪ የሆኑ ባለሙያዎች ሥራ መቀጠር የሚፈልጉ ወንድ የኮሌጅ ተማሪዎች “የጆሮ ጉትቻም ሆነ በሌሎች የተበሱ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚደረጉ ጌጣጌጦች ማድረግ እንደሌለባቸው፤ ሴቶች ደግሞ አፍንጫ ላይ የሚደረግ ጌጥ . . . ማድረግ እንደሌለባቸው” ምክራቸውን ይለግሳሉ።

በይበልጥ ወጣት ክርስቲያኖች በወንጌላዊነቱ ሥራ በሚካፈሉበት ጊዜ ጭምር ‘አገልግሎታቸው እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ መስጠት’ ስለማይፈልጉ ሌሎች የተሳሳተ አመለካከት እንዳያድርባቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:​3, 4) መበሳትን በተመለከተ የትኛውም ዓይነት የግል አመለካከት ሊኖራችሁ ቢችልም ገጽታችሁ ስለ አመለካከታችሁና ስለ አኗኗራችሁ በግልጽ የሚያስተላልፈው መልእክት አለ። ታዲያ ምን ዓይነት መልእክት ነው ማስተላለፍ የምትፈልጉት?

በመሠረቱ በዚህ ረገድ ምን እንደምታደርጉ መወሰን ያለባችሁ እናንተና ወላጆቻችሁ ጭምር እንደሆናችሁ የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በዙሪያችሁ ያለው ዓለም በራሱ መንገድ እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱለት” የሚል ጥሩ ምክር ይሰጣል። (ሮሜ 12:​2ፊሊፕስ) ምክንያቱም መዘዙን የምትሸከሙት እናንተው ናችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 እንዲህ ስንል በብዙ አገሮች የተለመደውንና በባሕል ረገድ ተቀባይነት ያገኘውን የመበሳት ልማድ ማመልከታችን አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዛሬው ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያገኘ የመጣውን ቅጥ ያጣ ልማድ ማመልከታችን ነው።​—⁠የግንቦት 15, 1974 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 318-9ን ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰውነትን መበሳት በብዙ ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ ነው