በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከፕላኔቶች ባሻገር ምን ይገኛል?

ከፕላኔቶች ባሻገር ምን ይገኛል?

ከፕላኔቶች ባሻገር ምን ይገኛል?

ፕላኔት ኤክስ። ይህን ስያሜ ከኔፕቱን በስተጀርባ ሳይኖር አይቀርም ብሎ ለጠረጠረው ገና ላልተገኘው ፕላኔት የሰጠው ፐርሲቫል ሎውል የተባለ የስነ ፈለክ ተመራማሪ ነው። በፍላግስታፍ አሪዞና በሚገኘው የምርምር ጣቢያው ፕላኔት ኤክስን መፈለግ የጀመረው በ1905 ነበር። ሎውል ፕላኔት ኤክስን ሳያገኝ ቢሞትም እርሱ የጀመረው ፍለጋ አላቆመም። በመጨረሻ በ1930 በሎውል የምርምር ጣቢያ ክላይድ ቶምቦ ፕሉቶ የተባለውን ፕላኔት አገኘ። በእርግጥም ፕላኔት ኤክስ ነበር!

ወዲያውኑ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ‘ሌላ ፕላኔት ኤክስስ ይገኝ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ አደረባቸው። ከዚያ በኋላ ለስድስት አሥርተ ዓመታት የተጧጧፈ ፍለጋ ተካሄደ። ፍለጋው በተካሄደባቸው በኋለኞቹ ዓመቶች በጠፈር መንኮራኩሮች ሳይቀር መጠቀም ተችሏል። በሺህ የሚቆጠሩ ንዑሳን ፕላኔቶች፣ ኮከቦች፣ ጋላክሲዎችና ኔቡላዎች ሊገኙ ቢችሉም አዲስ ፕላኔት ግን ሊገኝ አልቻለም።

ይሁን እንጂ ፍለጋው አላቆመም። ሳይንቲስቶች በተራ ዓይን ሊታዩ ከሚችሉት የጠፈር አካላት ሚልዮን ጊዜ እጥፍ ደካማ ብርሃን የሚልኩ የጠፈር አካላትን ለማግኘት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የበለጠ ኃይል ያላቸውን ቴሌስኮፖች መጠቀም ጀመሩ። ይህ ሁሉ ድካማቸው በመጨረሻ ፍሬ አስገኘ። በአሁኑ ጊዜ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ትናንሽ ፕላኔቶች ከፕሉቶ በስተጀርባ ሊታዩ ችለዋል!

እነዚህ ትናንሽ ፕላኔቶች የሚገኙት የት ነው? ወደፊትስ ምን ያህል ፕላኔቶች ይገኙ ይሆን? በእኛ ስርአተ ፀሐይ ውስጥ ከእነዚህ ፕላኔቶች የራቁ አካላት ይገኙ ይሆን?

እጅግ በጣም ሩቅ የሆኑት አካላት

በስርአተ ፀሐይ ውስጥ በፀሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ዘጠኝ ፕላኔቶች አሉ። በተጨማሪም በአብዛኛው በማርስና በጁፒተር መካከል የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ዓለታማ ንዑሳን ፕላኔቶች በጠፈር ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ይጓዛሉ። በተጨማሪም አንድ ሺህ የሚያክሉ ጅራታም ኮከቦች ሊታዩ ችለዋል።

ከእነዚህ አካላት በሙሉ ከፀሐይ በጣም ርቀው የሚጓዙት የትኞቹ ናቸው? እንደ እውነቱ ከሆነ ጅራታም ኮከቦችን የሚወዳደር የለም።

ጅራታም ኮከብ ተብሎ የተተረጎመው “ኮሜት” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል ኮሚቲስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ባለ “ረዥም ፀጉር” ማለት ነው። ይህም በጣም ደማቅ ከሆነው ከጅራታም ኮከቦቹ አናት በስተኋላ የሚታየውን ረጅም ጅራት ያመለክታል። ጅራታም ኮከቦች ለብዙ አጉል እምነትና ፍርሃት ምክንያት ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜም እንኳ አንዳንድ ጅራታም ኮከቦችን የተመለከቱ ሰዎች የመናፍስት መገለጥ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ይህም እምነት የመነጨው ጅራታም ኮከቦች መናፍስት ናቸው ከሚለው የቆየ እምነት ነው። ይህን ያህል ሊፈሩ የቻሉት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ጅራታም ኮከቦች በታዩባቸው አንዳንድ ወቅቶች አንዳንድ አሳዛኝ ክስተቶች ስለተፈጸሙ ነው።

ጅራታም ኮከቦች አሁንም ቢሆን ለአጉል ግትር እምነቶች መንስኤ መሆናቸው አልቀረም። በመጋቢት ወር 1997 በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርንያ ሄቨንስ ጌት የተባለው ኑፋቄ 39 አባላት ሄል-ባፕ የተባለችው ጅራታም ኮከብ ወደ ፀሐይ በተጠጋችበት ጊዜ አንድ ላይ ሆነው ራሳቸውን ገድለዋል። ለምን? ከዚህች ጅራታም ኮከብ በስተጀርባ የሚገኝ አንድ ባዕድ የጠፈር አካል ሊወስዳቸው እንደመጣ ስላመኑ ነበር።

ይሁን እንጂ ጅራታም ኮከቦችን በተመለከተ ምክንያታዊ ያልሆነ አመለካከት የነበራቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አርስቶትል ጅራታም ኮከቦች በሰማይ ላይ የሚታዩ በሪ የጋዝ ክምችቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ከጥቂት መቶ ዘመናት በኋላ ሴኒካ የተባለው ሮማዊ ፈላስፋ ጅራታም ኮከቦች በጠፈር አካላት ዙሪያ የሚዞሩ አካላት እንደሆኑ ጠቁሟል።

ቴሌስኮፕ ከተፈለሰፈና የኒውተን የስበት ሕግ ከታወቀ ወዲህ የጅራታም ኮከቦች ጥናት የተወሰነ ሕግና ሥርዓት ያለው ሳይንስ ሊሆን ችሏል። በ1705 ኤድመንድ ሃሊ ጅራታም ኮከቦች በፀሐይ ዙሪያ በጣም ረዥምና ሞላላ በሆነ መስመር እንደሚዞሩ አሳወቀ። በተጨማሪም በ1531፣ 1607 እና 1682 የታዩት ጅራታም ኮከቦች ተመሳሳይ የጉዞ መሥመር እንዳላቸውና ሁሉም የታዩት በ75 ዓመት ልዩነት እንደሆነ ገለጸ። እነዚህ በተለያዩ ጊዜያት የታዩት ጅራታም ኮከቦች ሦስት የተለያዩ ኮከቦች ሳይሆኑ በሂደት ላይ የሚገኝ አንድ ጅራታም ኮከብ መሆኑን ሃሊ አረጋገጠ። ይህ ኮከብ በኋላ የሃሊ ኮሜት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በአሁኑ ጊዜ ተመራማሪዎች ጅራታም ኮከቦች ከ1 እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ወርድ ያለው ጠጣር እምብርት እንዳላቸው አውቀዋል። ይህ የጅራታም ኮከቦች እምብርት ጥቁርና ቆሻሻ መልክ ያለው ግግር በረዶ ሲሆን በአብዛኛው በረዶ ከሆነ ውኃና የአቧራ ቅንጣቶች የተገነባ ነው። በ1986 ጂዮቶ በተባለችው የጠፈር መንኮራኩር ከቅርብ ርቀት የተነሳው የሃሊ ኮሜት ፎቶግራፍ እንደሚያሳየው ከጅራታም ኮከቦች በኃይል የሚወጣ ጋዝና አቧራ አለ። ከምድር ሲታይ ደማቅ ሆኖ የሚታየው የጅራታም ኮከቦች ጭንቅላትና ጅራት ይህ የጋዝና የአቧራ መፈትለክ ነው።

የጅራታም ኮከቦች ቤተሰብ

በፀሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሁለት የጅራታማ ኮከቦች ቤተሰቦች አሉ። ጅራታም ኮከቦች የተለያየ ምድብ የሚሰጣቸው ፀሐይን አንድ ጊዜ ለመዞር በሚወስድባቸው የጊዜ መጠን ነው። እንደ ሃሊ ኮሜት ያሉት የአጭር ጊዜ ጅራታም ኮከቦች ፀሐይን ከ200 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አንድ ጊዜ ይዞራሉ። የሚዞሩበት መሥመር ምድርና ሌሎች ፕላኔቶች ፀሐይን ከሚዞሩበት የጠፈር መሥመር ብዙም የራቀ አይደለም። አንድ ቢልዮን የሚያህሉ የአጭር ጊዜ ጅራታም ኮከቦች ሲኖሩ ብዙዎቹ ፀሐይን የሚዞሩት በቢልዮን የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀው ከኔፕቱንና ከፕሉቶ በስተጀርባ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደ ኤንከ ኮሜት ያሉት ጅራታም ኮከቦች ወደ ፕላኔቶች በመጠ​ጋታቸው ምክንያት ወደ ፀሐይ ቀረብ ብለው ይሽከረከራሉ።

የረዥም ጊዜ ጅራታም ኮከቦች የጉዞ መስመርስ? እነዚህ ከአጭር ጊዜ ጅራታም ኮከቦች በተለየ ሁኔታ ፀሐይን የሚዞሩት ከሁሉ አቅጣጫ ነው። በቅርቡ በአስደናቂ ሁኔታ የታዩት የሃያኩታኬ ጅራታም ኮከብና የሄል-ቦፕ ጅራታም ኮከብ ከእነዚህ መካከል የሚመደቡ ናቸው። ይሁን እንጂ ከሺህ ዓመት ወዲህ ዳግመኛ ይታያሉ ተብሎ አይጠበቅም!

በስርአተ ፀሐይ ውጪኛ ክፍል የሚንቀሳቀሱ በጣም ብዙ የረዥም ጊዜ ጅራታም ኮከቦች አሉ። ይህ የከዋክብት ሠራዊት የኦርት ዳመና የተባለ ስም ተሰጥቶታል። ይህ ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950 የዚህን የጅራታም ኮከቦች ዳመና መኖር ካሳወቀው ሆላንዳዊ የስነ ፈለክ ተመራማሪ ስም የተወሰደ ነው። በዚህ ደመና ውስጥ ምን የሚያክሉ ጅራታም ኮከቦች ይኖራሉ? የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች አንድ ትሪሊዮን እንደሚያክሉ ይገምታሉ! ከእነዚህ ጅራታም ኮከቦች አንዳንዶቹ የሚጓዙት ከፀሐይ አንድ የብርሃን ዓመት ያህል ወይም ከዚያ በላይ ርቀው ነው። * ይህን በሚያክል ከፍተኛ ርቀት አንድ ዙር ለማከናወን ከአሥር ሚልዮን ዓመት በላይ ሊፈጅ ይችላል!

የትናንሽ ፕላኔቶች ጭፍራ

በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተገኙ ትናንሽ ፕላኔቶች የሚገኙት ከፕሉቶ በስተጀርባ የአጭር ጊዜ ጅራታም ኮከቦች በሚገኙበት አካባቢ ነው። ከ1992 ወዲህ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች 80 የሚያክሉ ትናንሽ ፕላኔት መሰል አካላት አግኝተዋል። ከ100 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ወርድ ያላቸው በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ፕላኔት መሰል አካላት ሳይኖሩ አይቀሩም። እነዚህ ትናንሽ ፕላኔቶች የካውፐር ሰቅ የተባለ የጋራ ስም ተሰጥቷቸዋል። ይህንንም ስያሜ ያገኙት ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት የዚህን ሰቅ መኖር ገምቶ በነበረው ሳይንቲስት ስም ነው። የካውፐር ሰቅ አካላት ከዓለትና ከበረዶ ግግር የተገነቡ ሳይሆኑ እንደማይቀር ይታመናል።

የእነዚህ አነስተኛ ፕላኔቶች መገኘት ሳይንቲስቶች ስለ ውስጠኛው የስርአተ ፀሐይ ክፍል ላይ ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ አስከትሏልን? አዎን፣ በእርግጥ አስከትሏል። በአሁኑ ጊዜ ፕሉቶ፣ የፕሉቶ ጨረቃ የሆነችው ካረን፣ የኔፕቱን ሳተላይት የሆነችው ትራይተንና አንዳንድ በውስጠኛው የስርአተ ፀሐይ ክፍል የሚገኙ በረዷማ አካላት ከካውፐር ሰቅ የመጡ እንደሆነ ይታመናል። እንዲያውም አንዳንድ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ፕሉቶ ከዋና ዋናዎቹ ፕላኔቶች መካከል ልትመደብ አይገባትም እስከ ማለት ደርሰዋል።

እነዚህ ሁሉ የመጡት ከየት ነው?

ጅራታም ኮከቦችና አነስተኛ ፕላኔቶች በካውፐር ሰቅ ውስጥ በብዛት ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው? የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች እነዚህ የጠፈር አካላት ሊገኙ የቻሉት ቀደም ሲል ከነበሩና አንድ ላይ ከተጣመሩ የአቧራ ቅንጣቶችና ግግር በረዶ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት በጣም ተራርቀው የሚገኙ በመሆናቸው አድገው ትላልቅ ፕላኔቶች ሊሆኑ አይችሉም።

በተጨማሪም የረዥም ጊዜ ጅራታም ኮከቦች በስርአተ ፀሐይ ውስጥ ያላቸው ቦታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚህ ጅራታም ኮከቦች በአንድ ላይ ያላቸው ክብደት ከምድር ክብደት 40 ጊዜ ይበልጣል። አብዛኞቹ የተፈጠሩት በስርአተ ፀሐዩ መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን በውጪኛው የጋዝ ክምችት ፕላኔቶች አካባቢ እንደሆነ ይታሰባል።

እነዚህን ጅራታም ኮከቦች አሁን ወደሚገኙበት ረዥም ርቀት አሽቀንጥሮ የወረወራቸው ምንድን ነው? እንደ ጁፒተር ያሉት ትላልቅ ፕላኔቶች ኃይለኛ በሆነው የስበት ኃይላቸው አሽቀንጥረው እንደወረወሯቸው ግልጽ ነው።

በጅራታማ ኮከቦች ላይ ተጨማሪ ምርምር ማካሄድ

ጅራታም ኮከቦች እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የስርአተ ፀሐይ ክፍሎች የሚመደቡ አካላት ናቸው። በእነዚህ አስደናቂ አካላት ላይ ተጨማሪ ምርምር ሊደረግ የሚችለው እንዴት ነው? አልፎ አልፎ አንዳንድ ጅራታም ኮከቦች ወደ ውስጠኛው የስርአተ ፀሐይ ክፍል ሲመጡ በቅርብ ሊጠኑ ችለዋል። አንዳንድ የጠፈር ምርምር ድርጅቶች በሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት በጅራታም ኮከቦች ላይ ምርምር ለማድረግ በርካታ የጠፈር መንኮራኩሮችን ለመላክ አቅደዋል።

ወደፊት እኛ ባለንበት ስርአተ ፀሐይ ውስጥ ምን ሊገኝ እንደሚችል ማን ያውቃል? በፀሐይ ዙሪያ ስለሚዞሩት የጠፈር አካላት የተገኙት አዳዲስ ግንዛቤዎችና ግኝቶች በኢሳይያስ 40:​26 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 አንድ የብርሃን ዓመት ብርሃን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጓዘው ርቀት ሲሆን 9.5 ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር ይደርሳል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጅራታምና የተወርዋሪ ኮከቦች ዝናብ

በሰማይ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያልፍ የአንድ ተወርዋሪ ኮከብ ብርሃን ስታይ ጅራታም ኮከብ ይሆን ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ሊሆን ይችላል። አንድ ጅራታም ኮከብ ወደ ፀሐይ በሚጠጋበት ጊዜ ከግግር በረዶ የተሠራው እምብርቱ ቀስ በቀስ ይፈራርስና የሚፈነጣጠሩ ዓለቶች ወይም ሰማይ ወረዶች (meteoroids) ይለቀቃሉ። እነዚህ ጠጣር ዓለቶች በጅራታም ኮከቦች እንዳለው የአቧራ ቅንጣት ቀላል ስላልሆኑ በፀሐይ ነፋስ ተጠርገው አይወሰዱም። ከዚህ ይልቅ ከእናትዬዋ ጅራታም ኮከብ ጎን ሆነው ፀሐይን የሚዞሩ ግባሶ ይሆናሉ።

እነዚህ ሰማይ ወረዶች በየዓመቱ ወደ ምድር ይዘንባሉ። በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የታየው የሊዮኒድ የተወርዋሪ ኮከቦች ዝናብ ቴምፐል-ተትል ከተባለችው ጅራታም ኮከብ ተስፈንጥረው በወጡ አካላት የተፈጠረ ነበር። ይህ ዝናብ በየ33 ዓመቱ ይታያል። በ1966 የታየውን የሊዮኒድ ዝናብ የተመለከቱ የጠፈር አጥኚዎች በደቂቃ ከ2, 000 በላይ ተወርዋሪ ኮከቦችን እንዳዩ ተናግረዋል። በእርግጥም ከፍተኛ ዝናብ ነበር! በ1998 በጣም አንጸባራቂ የሆኑ የእሳት ኳሶች የታዩ ሲሆን በኅዳር ወር በጣም አስደናቂ የሆነ ትእይንት ማየት ይቻላል።

[በገጽ 24-26 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]

1. ሄል-ባፕ የተሰኘችው ተወርዋሪ ኮከብ በ 1997

2. ኤድመንድ ሃሊ

3. ፐርሲቫል ሎውል

4. ሃሊ ኮሜት በ1985

5. ሃሊ ኮሜት በ 1910

6. ከሃሊ ኮሜት ላይ ጋዝና አቧራ በኃይል ሲወጣ

[ምንጭ]

1) Tony and Daphne Hallas/Astro Photo; 2) Culver Pictures; 3) Courtesy Lowell Observatory/Dictionary of American Portraits/Dover

4) Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin; 5) National Optical Astronomy Observatories; 6) the Giotto Project, HMC principal investigator Dr. Horst Uwe Keller, the Canada-France-Hawaii telescope

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

7. የተለያዩ ጅራታም ኮከቦች ምህዋሮች

ኮሁቴክ የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ

ሃሊ ኮሜት

ፀሐይ

መሬት

ኤንከ የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ

ጁፒተር

[ሥዕል]

8. ሹማከር-ሊቪ 9 የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ በ1994 ከጁፒተር ጋር ከመላተሟ በፊት 21 ቦታ ተሰባብራ ነበር

9. የፕሉቶ ገጽ

10. ኮሁቴክ የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ፣ 1974

11. አይዳ የተሰኘችው ንዑስ ፕላኔትና ዴክትል የተሰኘችው ጨረቃዋ

[ምንጭ]

8) Dr. Hal Weaver and T. Ed Smith (STScI), and NASA; 9) A. Stern (SwRI), M. Buie (Lowell Obs.), NASA, ESA; 10) NASA photo; 11) NASA/JPL/Caltech