በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ ፍቅርና እሳተ ገሞራ

ክርስቲያናዊ ፍቅርና እሳተ ገሞራ

ክርስቲያናዊ ፍቅርና እሳተ ገሞራ

ካሜሩን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ባለፈው ዓመት በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በካሜሩን አንድ ከባድ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር። የካሜሩን ተራራ ከባሕር ወለል በላይ 4, 070 ሜትር ከፍታ ያለው የእሳተ ገሞራ ተራራ ነው። ይህ ፍንዳታ በ20ኛው መቶ ዘመን በተራራው ላይ ከተከሰቱት ፍንዳታዎች አምስተኛው ሲሆን ከቀድሞዎቹ ፍንዳታዎች ሁሉ ይበልጥ ኃይለኛና አስከፊ እንደሆነ ተነግሮለታል።

አደጋው መጀመሪያ የተከሰተው መጋቢት 27, 1999 ቅዳሜ ዕለት ከቀትር በኋላ ነበር። በቡኤ ከተማ በተራራው ግርጌ የሚኖሩ የዓይን ምሥክሮች እንዳሉት ከሆነ አደጋው ግምቦችን፣ ቤቶችንና ዛፎችን ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ ያናወጠ ነበር። በቀጣዩ ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ላይ እጅግ ከባድና አስከፊ የሆነው ነውጥ አካባቢውን ናጠው። ንዝረቱ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስከምትገኘው ዱአላ ከተማ ድረስ ተሰምቶ ነበር። መጋቢት 30, 1999 ዕለተ ማክሰኞ የታተመው ለ ሜሳዤ “በካሜሩን ተራራ ላይ የተከሰተ ፍንዳታ —⁠250, 000 ሰዎች ለእሳት ተጋልጠዋል” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ወጥቶ ነበር። በመቀጠልም እንዲህ ብሏል:- “ምድሪቱ በሁለት ቀናት ውስጥ 50 ጊዜ የተናወጠች ሲሆን እስካሁን ድረስ 4 ገሞራ ቆሬዎች ተከስተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ድምጥማጣቸው የጠፋ ከመሆኑም በላይ በቡኤ የሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት እንዳልነበረ ሆኗል።”

በቡኤ ከተማ ወደ 80 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ቤት ጨምሮ በርካታ ቤቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። ሆኖም ሕይወቱን ያጣ ሰው የለም።

ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር ሲንጸባረቅ

ይህ ከባድ ፍንዳታ ያወደመውን መልሶ ለመገንባት ወዲያውኑ ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር መንጸባረቅ ጀመረ። የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል በጣም አንገብጋቢ ለሆነው ለዚህ ችግር የሚውል ገንዘብ መደበ። በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች በፈቃደኝነት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በፍቅራዊ መንገድ መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።

የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የምግብ እርዳታ ያደረጉ ሲሆን አንድ ምሥክር 1, 000 ብሎኬቶች ለግሷል። አንድ ሌላ ምሥክር የአልሙኒየም ቆርቆሮዎች በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ አመቻችቷል። ሌላ ምሥክር ደግሞ እንጨት ለማምጣት 16 ኪሎ ሜትር በእግሩ ተጉዟል። ለእጮኛው ወላጆች የሚከፍለውን ጥሎሽ ሲያጠራቅም የነበረ አንድ ወጣት ሠርጉን በማራዘም ያጠራቀመውን ገንዘብ በሞተር የሚሠራ መጋዙን ለማስጠገን ተጠቀመበት። ከዚያም ወደ ጫካ ሄዶ አንድ ቤት ሙሉ በሙሉ ሊያሠራ የሚችል እንጨት ለሦስት ሳምንት ያህል ቆረጠ! ጠንካራ የሆኑ ወጣት ክርስቲያን ወንድሞች እንጨቱን በጭንቅላታቸው እየተሸከሙ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ እንጨቱ በከባድ መኪና ወደሚጫንበት ቦታ አደረሱ።

ሚያዝያ 24 ቀን 60 ፈቃደኛ ሠራተኞች አደጋው በደረሰበት ቦታ በመሰባሰብ የግንባታ ሥራውን ማቀላጠፍ ጀመሩ። በቀጣዮቹ ሳምንታት የመጨረሻ ቀኖች ላይ የፈቃደኛ ሠራተኞቹ ቁጥር 200 ደረሰ። የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ ያላቸው ሦስት ምሥክሮች ሥራ ከዋሉ በኋላ ወደ ግንባታ ቦታው በመምጣት እኩለ ሌሊት እስኪያልፍ ድረስ ሠርተዋል። በዱአላ የሚኖር አንድ ምሥክር ጠዋት ሰብዓዊ ሥራውን ሲሠራ ካረፈደ በኋላ በሞተር ብስክሌቱ 70 ኪሎ ሜትር ተጉዞ በመምጣት ወደ ቤት ከመመለሱ በፊት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሊሠራ ችሏል። ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስድስት ቤቶች ተሠርተው ተጠናቀቁ። በዚህ መካከል የቡኤ ጉባኤ ምንም እንኳ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር ከጉባኤው አባላት ቁጥር በእጥፍ በልጦ የነበረ ቢሆንም በግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባዎቹን ማካሄዱን ቀጥሎ ነበር።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው የተበከለ ውኃን ለማጥራት የሚያገለግሉ ከ40, 000 በላይ የሚሆኑ እንክብሎችን ያከፋፈለ ሲሆን በመርዘኛ ጋዝና በእሳተ ገሞራ አመድ ሳቢያ በተከሰተ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ይሠቃዩ የነበሩ አሥር ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓል። ይህን ክርስቲያናዊ ፍቅር የተመለከቱ ሰዎች ያሳዩት ምላሽ ምን ነበር?

ክርስቲያናዊ ፍቅር ድል አድርጓል

ከአውራጃው የግብርና ልዑካን አንዱ በወንድሞች ከተሠሩት ቤቶች አንዱን ከተመለከተ በኋላ “ቤቱ ራሱ ትልቅ ምሥክር ነው . . . ፍቅርን የሚያንጸባርቅ ነው” ሲል ተናግሯል። አንዲት አስተማሪ “በሕይወቴ ፈጽሞ እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። . . . ይህ በእርግጥም የእውነተኛ ክርስትና ምልክት ነው” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

በግል ተጠቃሚ የሆኑትም እንደዚሁ በእጅጉ ተነክተዋል። ቲሞቲ የተባሉ አቅመ ደካማ የሆኑ አንድ የ65 ዓመት አረጋዊ “አዲሱን ቤታችንን ባየን ቁጥር ዓይኖቻችን የደስታ እንባ ያቀርራሉ። ይሖዋ ላደረገልን ነገር ዘወትር እናመሰግነዋለን” ሲሉ ጽፈዋል። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች አንዲት መበለት ቤቷ በፈራረሰበት ጊዜ ከአራት ልጆቿ ጋር አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ወድቃ ነበር። እንዲረዷት ተቀጥረው የነበሩ ሰዎችም ቆርቆሮዎቿን ሰረቋት። በአካባቢው የተሠማሩት የይሖዋ ምሥክሮች ፈቃደኛ ሠራተኞች አስፈላጊውን እርዳታ አደረጉላት። “ምን ብዬ እንደማመሰግን አላውቅም። ልቤ በደስታ ስሜት ተሞልቷል” ብላለች። የአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ሚስት የሆነችው ኤሊዛቤት “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ፍቅር ያለ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል። ሕያው የሆነውን አምላክ እያገለገልን እንዳለን የሚያሳይ ነው።”

የእሳተ ገሞራው ፍንዳታ እጅግ ኃይለኛ የነበረ ቢሆንም የዚህን የወንድማማች ማኅበር ክርስቲያናዊ ፍቅር ሊያዳፍን አልቻለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ እንደጻፈው “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።”​— 1 ቆሮንቶስ 13:​8

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትፍ ቅላጭ ድንጋይ ጎርፍ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈቃደኛ ሠራተኞች የፈራረሱ ቤቶችን መልሰው ለመገንባት ጠንክረው ሠርተዋል

[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካሜሩን ተራራ