በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀይዋ ፕላኔት ዳግመኛ ስትጎበኝ

ቀይዋ ፕላኔት ዳግመኛ ስትጎበኝ

ቀይዋ ፕላኔት ዳግመኛ ስትጎበኝ

ሁለት “ሰላዮች” ከምድር ሥርዓተ ፀሐይ የቅርብ ጎረቤታችን ወደሆነችው ወደ ማርስ ተልከው ነበር። ግኝቶቻቸው ስለ ቀይዋ ፕላኔት ጂኦሎጂያዊ ቅድመ ታሪክና አሁን ስለምትገኝበት ሁኔታ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለማስገኘት ሊረዱ ይችሉ ይሆናል።

የሰው ልጅ ስለ ማርስ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ካደረበት ረዥም ዘመን አስቆጥሯል። ቅድመ አያቶቻችን በምሽቱ ሰማይ ላይ ከቀሩት ከዋክብት ፈጠን ብላ የምትንቀሳቀሰው ቀይና ደማቅ የጠፈር አካል የተለየ ባሕርይ እንዳላት ተሰምቷቸው ነበር። የጥንቶቹ ባቢሎናውያን፣ ግሪኮችና ሮማውያን ቀይ ቀለም የኖራት ገጿ በአይረን ኦክሳይድ አቧራ የተሞላ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ስላላወቁ ለዚህች ፕላኔት የሞትና የጦርነት አምላኮቻቸውን ስም ሰጥተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የከዋክብት ተመራማሪዎች እጅግ በጣም አቅርበው የሚያሳዩ መነፅሮችን በመጠቀም የእኛን ሥርዓተ ፀሐይ ሲቃኙ ቀይዋ ጎረቤታችን ወቅቶች እንደሚፈራረቁባት፣ በረዷማ ዋልታዎችና ሌሎች ከምድር ጋር የሚያመሳስሏት ገጽታዎች እንዳሏት መገንዘብ ችለዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያዎቹ የማርስ ቅኝቶች የተከናወኑት ሶቪዬት ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ባመጠቋቸው ማርስን በሚዞሩና በማርስ ላይ ባረፉ መንኮራኩሮች አማካኝነት ነው። በሐምሌ 1997 የተካሄደው የማርስ አሳሽ ተልእኮ ግን በሚልዮን የሚቆጠሩ ቴሌቪዥን ተመልካቾችን ትኩረት ስቧል። *

በአሁኑ ጊዜ ማርስ ግሎባል ሰርቬየር የተባለው መንኮራኩር ቀይዋን ፕላኔት የሚመለከቱ መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛል። እነዚህ ተልእኮዎች በጣም በርካታ የሆኑ ጠቃሚ መረጃዎችን ያስገኙ ቢሆንም አሁንም ገና መልስ ያልተገኘላቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ።

ውኃው የሚገኘው የት ነው?

እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱት አንድ የጋራ ጉዳይ ውኃ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት በጣም ሩቅ በሆነ ጊዜ ማርስ አሁን ካላት በጣም የተለየ መልክ እንደነበራት ይገምታሉ። ሞቅ ያለ የአየር ንብረት፣ እርጥበት አዘል አየርና ወራጅ ወንዞች እንደነበሯት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአንድ ምክንያት ውኃው ፈጽሞ ጠፍቶ በምድር ላይ ከሚገኙ በረሃዎች በጣም የሚብስ ደረቅ፣ አቧራማና በንፋስ የተጠረገ ገጽ ሊኖራት ችሏል። ውኃው የት ሄደ? በአሁኑስ ጊዜ ውኃው በየትኛው የማርስ ክፍልና በምን መልክ ይገኛል? ውኃ በማርስ የአየር ንብረትና የአየር ሁኔታ ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል?

በፓሳዴና ካሊፎርኒያ የሚገኘውና በናሳ የጀት ማምጠቂያ ቤተ ሙከራ የማርስ አሰሳ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ኖርማን ኤንስ “ነገሩ የስለላ ሥራ ነው” ይላሉ። “ቁልፉ ማርስ ላይ የነበረው ውኃ ምን እንደሆነ ማወቅ ነው።” የሳይንስ ሊቃውንት በቅርቡ ወደ አንድ ምላሽ እንደሚቃረቡ ተስፋ ያደርጋሉ። ተመራማሪዎቹ ምድርና ማርስ በየሁለት ዓመቱ ባመቺ ሁኔታ ትይዩ በሚሆኑባቸው ጊዜያት አሳሽ ሮቦቶችን በመላክ የማርስን ምሥጢር ቀስ በቀስ ለማወቅ አስበዋል።

በቅርቡ የተላኩት ጥንድ “ሰላዮች” ከእነዚህ የሚቆጠሩ ሲሆኑ አንደኛው የማርስን ዋልታ እየዞረ የአየር ሁኔታዋን የሚከታተል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኬሚስትሪ ሙከራዎችን እዚያው ማርስ ላይ እያካሄደ ሳይንቲስቶች የማርስን ከርስ በይበልጥ መረዳት የሚያስችላቸውን መረጃ ይልካል። የአንደኛው ስም ማርስ ክላይመት ኦርቢተር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማርስ ፖላር ላንደር ይባላል።

ከላይ ሆኖ መመልከት

ማርስ ክላይሜት ኦርቢተር ኬፕ ካናቭራል ፍሎሪዳ ከሚገኘው የኬኔዲ የጠፈር ማዕከል ታኅሣሥ 11, 1998 መጥቃ ዘጠኝ ወራት የሚፈጀውን የማርስ ጉዞ ጀምራለች። በ400 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ሆና እየዞረች የማርስን ከባቢ አየር፣ ገጿንና የዋልታዎቹን ሁኔታ እንድትከታተል ተደርጋ ተሠርታለች። ክትትሉ ለአንድ ሙሉ የማርስ ዓመት ማለትም 687 የምድር ቀናት ይቆያል።

የክላይሜት ኦርቢተር ተልእኮ በማርስ ላይ ያለውን የከባቢ አየር አቧራና ተን መከታተልን ይጨምራል። በተጨማሪም ኦርቢተር በፕላኔቷ ላይ የሚካሄዱትን የወቅቶች ለውጥ የመከታተል ችሎታ አላት። የማርስን ገጽ የሚያሳዩት ዝርዝር ፎቶግራፎች ለሳይንቲስቶች ስለ ፕላኔቷ ጥንታዊ የአየር ሁኔታ ፍንጭ የሚሰጡ ጠቃሚ መረጃዎች ያስገኙ ይሆናል። ከዚህም ሌላ እነዚህ መረጃዎች በማርስ ከርስ ውስጥ የውኃ ክምችት የሚገኝበትን ቦታ ለተመራማሪዎች ሊጠቁሙ ይችላሉ።

በተጨማሪም ኦርቢተር ባልንጀራዋ ለሆነችው ለማርስ ፖላር ላንደር እንደማስተላለፊያ ጣቢያ ሆና ታገለግላለች። ፖላር ላንደር የመጠቀችው ጥር 3, 1999 ሲሆን በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ማርስ ላይ እንደምትደርስ ፕሮግራም ተይዞላት ነበር። ይሁን እንጂ ይቺ መንኮራኩር ከፍተኛ ውጤት ያለው ሥራ ልታከናውን የምትችለው የት ብታርፍ ነው?

የት ትረፍ?

በማርስ አሰሳ ረገድ ዋነኛው ትኩረት የውኃ ጥያቄ እንደሆነ አስታውስ። ውኃን የሚመለከቱ ጥናቶችን ለማድረግ በጣም አመቺ የሆነው ስፍራ የት ነው? በምድር ላይ የአየር ሁኔታን፣ የአየር ንብረትንና የውኃ ዑደትን የሚመለከቱ ጥናቶች የሚደረጉት በተለያዩ በርካታ ቦታዎች በተለያዩ መሣሪያዎች አማካኝነት የተካሄዱ በሺህ የሚቆጠሩ ጥናቶችን በማነጻጸር ነው። በሌሎች ፕላኔቶች ላይ የሚደረጉ ጥናቶች ግን በተመረጡ ጥቂት ቦታዎች ላይ ማተኮር አለባቸው። የማርስን ገጽ እንደ ልብ መመርመር ስለማይቻል የሳይንስ ተመራማሪዎች የትኛውን መሣሪያ በየትኛው ቦታ ላይ እንደሚልኩ ሲወስኑ በጣም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።

የማርስን የአየር ንብረት ለማጥናት በጣም አመቺ የሆነው ቦታ ማርስ ፓዝፋይንደር ከሁለት ዓመታት በፊት አርፋበት ከነበረው ድንጋያማ ደለል በጣም የተለየ ቢሆንም የዋልታዎች አካባቢ ነው። የወቅቶች ልዩነት በጣም የሚፈራረቀው በዋልታዎች አካባቢ ነው። በወቅቶች መፈራረቅ ምክንያት የሚፈጠሩ የአቧራ ሞገዶች በዋልታዎች ረገድ ስስ የሆነ የአቧራ ደለል እንዲከማች ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። የክረምቱ ወቅት ሲመጣ አቧራው ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድና ከውኃ በረዶ ሥር ወደ በረዶነት ይለወጣል። በበርካታ ዓመታት ውስጥ ብዙ ደለሎች በዚህ መንገድ ተነባብረዋል። የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ራልፍ ሎረንስ “የማርስ የአየር ንብረት ታሪክ በእነዚህ የደለል ንብብሮች ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል” ይላሉ። በዚህ አዲስ ክልል ውስጥ የሚደረገው አሰሳ በማርስ ላይ በሚደረገው ምርምር ረገድ ትልቅ እርምጃ እንደሚያስገኝ ሊቃውንት ያምናሉ። እንዴት? ላንደር ካረፈች በኋላ ምን ታደርጋለች?

በማርስ ከርስ ውስጥ ያለውን መመልከት

ላንደር አንድ ሜትር ቁመት፣ ሦስት እግሮችና ሁለት ሜትር ርዝመት ያለው ባለ አካፋ እጅ ያላት መሣሪያ ናት። መሣሪያዋ ሥራዋን የምትጀምረው በማርስ አፈር ላይ ከማረፏ በፊት ነው። ላንደር ወደ ቀይዋ ፕላኔት ከባቢ አየር ልትደርስ ስትል እያንዳንዳቸው የቅርጫት ኳስ የሚያካክሉ ሁለት ክብ መሣሪያዎች ትለቃለች።

እነዚህ ኳስ መሰል መሣሪያዎች በሰዓት 700 ኪሎ ሜትር በሚሆን ፍጥነት ተወርውረው ከማርስ ገጽ ጋር ይጋጫሉ። ኳሶቹ በሚጋጩበት ጊዜ እንዲሰባበሩ ሆነው የተሠሩ በመሆናቸው በሚሰበሩበት ጊዜ ከውስጣቸው ሁለት ትናንሽ መሣሪያዎች ወጥተው አንድ ሜትር የሚያክል ጠልቀው ወደ አፈሩ ይገባሉ። መሣሪያዎቹ ከተቀበሩ በኋላ በጣም ትናንሽ መቆፈሪያዎችን ይሰድዱና የማርስን አፈር ኬሚካላዊ ይዘት ይመረምራሉ። የመጀመሪያው ግብ በመሬቱ ውስጥ በረዷማ ውኃ መኖሩን መከታተል ነው።

እነዚህ መሣሪያዎች ማርስ ገጽ ላይ እንደደረሱ ወዲያው ላንደር ተከትላ በጃንጥላ ትወርዳለች። ላንደር ካሜራዎችና አካባቢ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች የተገጠሙላት ስለሆነች የማርስን ገጽ አቀማመጥና የአየር ሁኔታ ታጠናለች። ቁልቁል በምትወርድበት ጊዜም ሆነ ካረፈች በኋላ ፎቶግራፎች ታነሳለች። የተጫነችው ማይክሮፎን ለመጀመሪያ ጊዜ የማርስ ነፋስ የሚያሰማውን ድምፅ ይቀርጻል። ላንደር ካረፈች በኋላ በሥራ ላይ የምትቆየው ለ90 ቀናት ያህል ነው።

የምርምር ፍላጎት

እርግጥ ነው፣ ማርስ ክላይሜት ኦርቢተርና ማርስ ፖላር ላንደር የሰበሰቧቸውን መረጃዎች ለማጥናትና ለመተንተን ሳይንቲስቶች በዓመታት የሚቆጠር ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ የአሁኖቹ መንኮራኩሮች ስለ ማርስ ለማወቅ የተደረጉ የ16 ዓመት ጥረት ክፍል ናቸው። ከናሳ በተጨማሪ የአውሮፓ፣ የጃፓንና የሩሲያ የጠፈር ድርጅቶች የተካፈሉበት ተልእኮ ነው። ሳይንቲስቶች በተከታታይ በሚከናወኑ ተልእኮዎች አማካኝነት ከማርስ ላይ የአፈር ናሙናዎችን በማምጣትና እዚሁ ምድር ላይ በሚገኙ ቤተ ሙከራዎች ለማጥናት እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ። ይህም በቀይዋ ጎረቤታችን በማርስ የአየር ሁኔታ ላይ የደረሰውን ለማወቅ ያስችል ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በሰኔ 22, 1998 (የእንግሊዝኛ) ንቁ! እትም ላይ “አንድ ሮቦት ማርስን አሰሰ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሕይወት የመጣው ከማርስ ነውን?

ከማርስ የመጣች ነች ተብላ የምትታመነው ኤ ኤል ኤች 84001 ተብላ የምትታወቀው ተወርዋሪ ኮከብ በ1984 በአንታርክቲካ ተገኘች። በነሐሴ 1996 በጆንሰን የናሳ ጠፈር ጣቢያና በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ድንች የሚያክል መጠን ባለው ድንጋይ ውስጥ በማርስ ላይ ሕይወት እንዳለ የሚጠቁሙ ኦርጋኒክ ውህዶች፣ ማዕድኖችና ወደ ቅሪትነት የተለወጡ ሚክሮቦች መገኘታቸውን አስታውቀዋል። ይህም ሕይወት የመጣው ከማርስ ሊሆን ይችላል የሚል አንደምታ አስከትሏል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የሳይንሱ ማሕበረሰብ አባላት በሙሉ ለማለት ይቻላል ይህ ተወርዋሪ ኮከብ ብቻውን ሕይወት ከማርስ ለመገኘቱ አስተማማኝ ማስረጃ ሊሆን እንደማይችል ይስማማሉ። በሎስ አንጀለስ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዊልያም ሼልፍ “ተመራማሪዎቹ የባዮሎጂያዊ እንቅስቃሴ ቅሪቶችን ያገኙ አይመስልም ብለዋል።” የካስ ዌስተርን ሪዘርቭ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ራልፍ ፒ ሃርቬይ በተመሳሳይ “ማርስ ላይ ሕይወት አለ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ለብዙዎቻችን የሚጥም ቢሆንም ኤ ኤል ኤች [84001] ለዚህ ጽንሰ ሐሳብ ማረጋገጫ አላስገኘም” ብለዋል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 በምድር ላይ ሕይወት እንዴት እንደተገኘ ለሚነሳው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከምዕራፍ 3 እስከ 5 ድረስ ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለአርባ ዓመታት የተከናወነ የማርስ አሰሳ

▪ ሶቭዬት ሕብረት በ1960 የመጀመሪያዎቹን በማርስ ላይ ያነጣጠሩ መንኮራኩሮች አመጠቀች። መንኮራኩሮቹ ወደ ምሕዋሮቻቸው አልደረሱም።

▪ ሐምሌ 14, 1965 ማሪነር 4 ከዩናይትድ ስቴትስ ተልካ በማርስ አኳያ ካለፈች በኋላ ፎቶግራፎችንና ሌሎች መረጃዎችን ወደ ምድር ልካለች።

▪ በ1971 የሶቪዬት ሕብረቷ ማርስ 3 ማርስ ላይ ለማረፍ የመጀመሪያ የሆነችውን የምርምር መሣሪያ ለቅቃለች። የዩናይትድ ስቴትስ የምርምር መንኮራኩር የሆነችው ማሪነር 9 በዚሁ ዓመት ማርስ ላይ ደርሳ አብዛኛውን የማርስ ገጽ ፎቶግራፍ አንስታለች። በተጨማሪም ማሪነር 9 ፎቦስ እና ዳይመስ የሚባሉትን ሁለት ትናንሽ የማርስ ጨረቃዎች ፎቶግራፍ አንስታለች።

▪ በ1976 ቫይኪንግ 1 እና ቫይኪንግ 2 የተባሉ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ መንኮራኩሮች ማርስ ላይ አረፉ። መሣሪያዎቹ ለበርካታ ዓመታት በጣም ውስብስብ የሆኑ ምርምሮች ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

▪ በ1988 የሶቪዬት ሳይንቲስቶች ፎቦስ 1 እና ፎቦስ 2 የተባሉ ሁለት መንኮራኩሮች ወደ ማርስ ልከዋል። ፎቦስ 1 ጉዞዋን ሳታጠናቅቅ ብትቀርም ፎቦስ 2 ማርስ ላይ ደርሳ ያገኘቻቸውን መረጃዎች ለበርካታ ቀናት ልካለች።

▪ በ1992 ዩናይትድ ስቴትስ ማርስ ኦብዘርቨር የተባለችውን መንኮራኩር ልካ ተልዕኮዋን ሳታጠናቅቅ ተበላሽታ ቀርታለች።

▪ ሶጁርነር ሮቨር የተባለውን መንኮራኩር የተሸከመችው ማርስ ፓዝፋይንደር ሐምሌ 4, 1997 ማርስ ላይ አረፈች። ከቀይዋ ፕላኔት የተላኩ በጣም አስደናቂ የሆኑ ባለ ቀለም ፎቶግራፎች ማድረስ ጀመረች።

[ሥዕል]

ማሪነር 4

ከቫይኪንግ ላንደሮች መካከል አንዱ

ፎቦስ 2

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርስ ክላይሜት ኦርቢተር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርስ ፖላር ላንደር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርስ ፓዝፋይንደር ያነሳችው የማርስን ገጽ የሚያሳይ ፎቶግራፍ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ገጽ 23:- Meteorite: NASA photo; background: NASA/U.S. Geological Survey; orbiter and lander: NASA/JPL/Caltech

ገጽ 24 እና 25:- Landscape, Mariner 4, Viking lander: NASA/JPL/Caltech; planet: NASA photo; Phobos 2: NASA/National Space Science Data Center