በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሲጋራ ሱስ የተጠመደ ዓለም

በሲጋራ ሱስ የተጠመደ ዓለም

በሲጋራ ሱስ የተጠመደ ዓለም

ቢል ደግ፣ አዋቂና ጠንካራ ሰው ነበር። ቤተሰቡን ይወዳል። ይሁን እንጂ ገና በለጋ እድሜው ሲጋራ ማጨስ ጀመረ። በኋላ ግን ይህን ልማዱን በጣም ጠላው። ሲጋራ እያጨሰ እያለ እንኳን ወንድ ልጆቹን ማጨስ ትልቅ ሞኝነት እንደሆነ እየተናገረ እንዳያጨሱ ያስጠነቅቃል። በጠንካራ እጁ የሲጋራውን ፓኮ ጭርምትምት አድርጎ በመስኮት ከወረወረ በኋላ ከእንግዲህ አላጨስም ብሎ የሚምልባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሲጋራው ይመለስና መጀመሪያ ተደብቆ በኋላም በግልጽ ማጨስ ይጀምራል።

ቢል ከ15 ዓመት በፊት ለበርካታ ወራት በሕመም ከማቀቀ በኋላ ሞተ። ሲጋራ ባያጨስ ኖሮ ዛሬ በሕይወት ሊኖር ይችል ነበር። ሚስቱ ባሏን፣ ልጆቹም አባታቸውን አያጡም ነበር።

የቢል ሞት የቤተሰቡን አባሎች እጅግ ያሳዘነ ቢሆንም እንደርሱ በሲጋራ ጠንቅ የሚሞቱ ሌሎች ብዙ ሰዎች አሉ። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደዘገበው ከሆነ ከትንባሆ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ አራት ሚልዮን ሰዎች ወይም በየስምንቱ ሰኮንድ አንድ ሰው ይሞታል። በመላው ዓለም ከተሰራጩት ሊወገዱ የሚችሉ የበሽታ መንስዔዎች መካከል ዋነኛው ትንባሆ ነው። በአሁኑ ደረጃ ከቀጠለ ሲጋራ በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ በኤድስ፣ በሳንባ ነቀርሳ፣ በወሊድ፣ በመኪና አደጋ፣ በራስ ወይም በሌላ ሰው በሚፈጸም ግድያ ከሚሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ድምር የሚበልጡ ሰዎችን በመግደልና በአካል ላይ ጉዳት በማድረስ የአንደኝነቱን ደረጃ ይይዛል።

ሲጋራ ቀሳፊ ነው። ቢሆንም ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት በመላው ዓለም ቢያንስ 1.1 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሲጋራ እንደሚያጨሱ ይገምታል። ይህም ለአቅመ አዳም ከደረሱ የዓለም ሕዝቦች መካከል ሲሶ የሚሆኑት ያጨሳሉ ማለት ነው።

በአሁኑ ጊዜ የትንባሆ ኩባንያዎች በሚቀርብባቸው ክስ ምክንያት በመቶ ሚልዮን ዶላር የሚቆጠር የገንዘብ ካሳ ቢከፍሉም ይህ ኪሳራ ከሚያገኙት የበርካታ ቢልዮን ዶላር ትርፍ ጋር ሲወዳደር ከቁም ነገር የሚገባ እንዳልሆነ ተንታኞች ይገምታሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በእያንዳንዲቱ ቀን 1.5 ቢልዮን የሚያክሉ ሲጋራዎች በፋብሪካ ተመርተው ይወጣሉ። በመላው ዓለም የትንባሆ ኩባንያዎችና የመንግሥት ሞኖፖል ድርጅቶች በየዓመቱ ከአምስት ትሪልዮን የሚበልጥ ሲጋራ ይሸጣሉ!

እነዚህን የሚያክሉ ብዙ ሰዎች ለሞት የሚዳርግ መሆኑን እያወቁ ይህን ልማዳቸውን እርግፍ አድርገው የማይተውት ለምንድን ነው? ሲጋራ የምታጨስ ከሆንክ ይህን ልማድህን እንዴት ማቆም ትችላለህ? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።