በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቴሌቪዥን አጠቃቀም ረገድ አስተዋይ መሆን

በቴሌቪዥን አጠቃቀም ረገድ አስተዋይ መሆን

በቴሌቪዥን አጠቃቀም ረገድ አስተዋይ መሆን

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ግምገማ ቡድን ኖት ኢን ዘ ፓብሊክ ኢንተረስት—ሎካል ቲቪ ኒውስ ኢን አሜሪካ በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት ላይ ቴሌቪዥን ‘የተረት አባት፣ ሞግዚትና የሰዎችን አስተሳሰብ የሚቀርጽ’ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው በማለት ይገልጻል። “የቴሌቪዥን ኘሮግራም ዙሪያችንን ከቦናል። . . . ልክ እንደ ሲጋራ ጭስ አካባቢያችንን ሞልቶታል።” የሲጋራ ጭስ ወደ ውስጥ መሳብ ጎጂ እንደሆነ ሁሉ ምርጫ ያልተደረገባቸውን የቴሌቪዥን ኘሮግራሞች ሁሉ ለሰዓታት መከታተል በተለይ በሕፃናት ላይ ጉዳት ያስከትላል።

በቴሌቪዥን የሚታየውን ወንጀልና ዓመፅ አስመልክቶ ይኸው ሪፖርት እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “በዓመፅ የተሞሉ የቴሌቪዥን ምስሎችን መመልከት በልጆች የመማር ችሎታና ለሌሎች በሚያሳዩት አሳቢነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ ጠበኛ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ምርምር የተደረገባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።” በ1992 የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር እንደገለጸው ከሆነ “በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ዓመፅ የወጣቶችን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል አስጊ ሁኔታ ነው።”

በልጆቻችሁ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የቴ​ሌቪዥን ኘሮግራሞችን መቆጣጠር የምትችሉት እንዴት ነው? ሪፖርቱ ቴሌቪዥንን ይበልጥ በማስተዋል በመጠቀም ረገድ ምን ማድረግ እንደሚሻል የተለያዩ የሕዝብ የጤና ድርጅቶች የሰጧቸውን አንዳንድ አስተያየቶች አስፍሯል። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን እነሆ:-

ቴሌቪዥን የማየት ልማዳችሁ በኘሮግራም የሚመራና ገደብ የተበጀለት ይሁን። ልጆች መቼ መቼ እንደሚያዩ ወስኑ። እነርሱ ክፍል ውስጥ ቴሌቪዥን አታስቀምጡ።

ልጆች በኘሮግራሙ ላይ የሚያዩአቸውን ቦታዎች ፈልገው ማግኘት እንዲችሉ ከቴሌቪዥኑ አጠገብ ሉል አስቀምጡላቸው።

እውነታውን ከማይጨበጠው ሕልም መለየት እንዲችሉ ለመርዳት ልጆቻችሁ ቴሌቪዥን ሲመለከቱ አብራችኋቸው ሁኑ። አብዛኛውን ጊዜ ከአሥር ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በእነዚህ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል አይችሉም።

ቴሌቪዥኑን አመቺ ከሆነው ቦታ ላይ አንስታችሁ ቁልፍ ባለው ቁም ሳጥን ውስጥ አስቀምጡት። እንዲህ ማድረጋችሁ ቴሌቪዥኑን መክፈትና ከአንዱ ወደ ሌላው ጣቢያ መቀያየሩን ትንሽ አስቸጋሪ ያደርገዋል።