በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤተሰባችን እንደገና አንድ የሆነበት መንገድ

ቤተሰባችን እንደገና አንድ የሆነበት መንገድ

ቤተሰባችን እንደገና አንድ የሆነበት መንገድ

ሎኸስ እና ዩዲት ቬስተርጋር እንደተናገሩት

ቤታቸው ዴንማርክ ውስጥ ያለ ማንኛውም ደስተኛ ቤተሰብ ያለው የተለመደ ዓይነት አቀማመጥ አለው። ፀጥታ በሰፈነበት መንደር ውስጥ የሚገኝ የሚያምር መናፈሻና ምቾት ያለው ቤት ነው። ጤናማና ደስተኛ የሆኑትን የቤተሰቡን ልጆች ምስል የያዘ አንድ ትልቅ ፎቶግራፍ በቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል።

አባትየው ሎኸስ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ነው። ባለቤቱ ዩዲት ደግሞ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ) ናት። ምንም እንኳ ደስተኛ ባልና ሚስት ቢሆኑም ትዳራቸው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እንዲህ ነበር ማለት አይደለም። ሎኸስና ዩዲት በመካከላቸው ተነስቶ የነበረው ችግርና አለመግባባት ለፍቺና ለቤተሰብ መፈራረስ ዳርጓቸው ነበር። አሁን ግን ቤተሰባቸው እንደገና አንድ ሆኗል። እንዴት? የሆነውን ነገር ሁሉ እነሱ ራሳቸው ይናገራሉ።

ሎኸስ እና ዩዲት በትዳራቸው ላይ የደረሰውን ችግርና እንደገና አንድ ሊሆኑ የቻሉበትን መንገድ መናገሩ አያሳፍራቸውም። ተሞክሯቸው ሌሎችን ሊረዳ እንደሚችል ይሰማቸዋል።

ጅምሩ ያማረ ነበር

ሎኸስ:- ሚያዝያ 1973 ገና ስንጋባ ትዳራችን በጣም አስደሳች ነበር። ዓለም በመላ በቁጥጥራችን ሥር የሆነ መስሎን ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ትውውቅ አልነበረንም። ሆኖም ሁሉም ሰው በትጋት ከሠራ ዓለማችንን ለመኖር በጣም የተመቻቸች ቦታ ማድረግ እንደምንችል እርግጠኞች ነበርን። በመሆኑም በብዙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ጀመርን። ማርቲን፣ ቶማስና ዮናስ የተባሉ ጤናማና ደስተኛ የሆኑ ሦስት ወንዶች ልጆች በመውለዳችን የቤተሰባችን ቁጥር በማደጉ ደስታችን ጨመረ።

ዩዲት:- በአንድ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ መሥሪያ ቤት ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ከዚህ በተጨማሪ በፖለቲካና በሠራተኞች ማኅበር እንቅስቃሴዎች ውስጥ እሳተፍ ነበር። ቀስ በቀስ ከፍተኛ ሥልጣን እያገኘሁ ሄድኩ።

ሎኸስ:- እኔ ደግሞ በአንድ ትልቅ የሠራተኞች ማኅበር ውስጥ እሠራ የነበረ ሲሆን ከዚያም እድገት አገኘሁና አንድ ቁልፍ ቦታ ላይ እንድሠራ ተመደብኩ። በሥራው ዓለም ጥሩ እድገት እያደረግን ነበር፤ እንዲሁም ደስታ የተሞላበት ሕይወታችንን ሊያደፈርስ የሚችል አንድም ነገር ያለ አይመስልም ነበር።

እየተራራቁ መሄድ

ሎኸስ:- ይሁን እንጂ ሁለታችንም በየፊናችን ስለምንባዝን አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ። የምንሠራው ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የነበረ ቢሆንም እንኳ የተሰማራነው በተለያዩ መስኮች ነበር። ሦስቱን ልጆቻችንን ግለሰቦች ወይም የሕፃናት መንከባከቢያ ተቋማት እንዲይዙልን እናደርግ ነበር። ሁለታችንም በየራሳችን ጉዳዮች ተጠምደን ስለነበር የቤተሰባችን ሕይወት መመሰቃቀል ጀመረ። ሁለታችንም ድንገት ቤት ብንገናኝ እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ይፈጠር ነበር። ስለዚህም እፎይታ ለማግኘት ስል የአልኮል መጠጥ መጠጣት ጀመርኩ።

ዩዲት:- እርግጥ ሁለታችንም የምንዋደድና ልጆቻችንንም የምንወድ ብንሆንም እንኳ ፍቅራችንን በተገቢው መንገድ አላዳበርነውም ነበር። ፍቅራችን መዳከም ጀመረ። ግንኙነታችን ይበልጥ እየሻከረ ሄደ፤ በዚህም የተነሳ ልጆቹ ከፍተኛ ስቃይ ደረሰባቸው።

ሎኸስ:- ቤተሰባችንን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ሥራዬን መልቀቅ ግድ ሆነብኝ። በ1985 እንኖርበት የነበረውን ከተማ ለቅቀን አሁን ወዳለንበት መንደር መጣን። ለጥቂት ጊዜ ሁኔታዎች መሻሻል ያሳዩ ቢሆንም እንኳ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በየግል ጉዳዮቻችን ላይ ብቻ ማተኮራችንን አላቆምንም ነበር። በመጨረሻም 16 ዓመት ያስቆጠረው ትዳራችን የካቲት 1989 በፍቺ አከተመ። ቤተሰባችን ፈረሰ።

ዩዲት:- ቤተሰባችን ተበታትኖና ልጆቹ ሲሰቃዩ መመልከቱ በጣም የሚያሳዝን ነበር። በመካከላችን ከፍተኛ መቃቃር ተፈጥሮ ስለነበር ልጆቹን ተከፋፍሎ በማሳደግ ረገድ እንኳ ስምምነት ላይ ልንደርስ አልቻልንም። በመሆኑም ሦስቱንም ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጠኝ።

ሎኸስ:- እኔና ዩዲት ሊፈርስ ተቃርቦ የነበረውን ቤተሰባችንን ከውድቀት ለማዳን በተወሰነ መጠን ተፍጨርጭረን ነበር። አልፎ ተርፎም አምላክ እንዲረዳን ጸልየን ነበር። ሆኖም ስለ አምላክ እምብዛም የምናውቀው ነገር አልነበረም።

ዩዲት:- ያቀረብነው ጸሎት መልስ ባለማግኘቱ አምላክ ጸሎት አይሰማም ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደረስን። ከዚያ በኋላ ግን አምላክ ጸሎት እንደሚሰማ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በመመልከታችን አመስጋኞች ሆነናል።

ሎኸስ:- እኛ ራሳችን ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንዳለብንና ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገን ፈጽሞ ተሰምቶን አያውቅም ነበር። ስለዚህ መፋታታችን የማይቀር ጉዳይ ሆነ።

ሎኸስ ያልተጠበቀ ለውጥ አደረገ

ሎኸስ:- ብቻዬን በምኖርበት ጊዜ ሁኔታዎች ፈጽሞ ባልጠበቅሁት መንገድ ተለወጡ። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሁለት መጽሔቶች ሰጡኝ። ከዚህ በፊት ግን ምሥክሮቹ ገና ሲመጡ አንደማልፈልግ እነግራቸው ነበር። ሆኖም እነዚያን መጽሔቶች ሳነብ ምሥክሮቹ በእርግጥ በአምላክም ሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያምኑ ተገነዘብኩ። ይህ በጣም አስገረመኝ። ክርስቲያን ስለመሆናቸው ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም።

በዚህ ጊዜ ከአንዲት ከተዋወቅኋት ሴት ጋር አብሬ መኖር ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ሴትዬዋ ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክር እንደነበረች አወቅሁ። ጥያቄዎች ሳቀርብላት ይሖዋ የአምላክ ስም መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየችኝ። አሃ፣ “የይሖዋ ምሥክሮች” ማለት “የአምላክ ምሥክሮች” ማለት ነው!

ይህች ሴት በአንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ የሚቀርበውን የሕዝብ ንግግር እንዳዳምጥ ሁኔታዎችን አመቻቸችልኝ። እዚያ የተመለከትኩት ነገር የማወቅ ፍላጎቴን ቀሰቀሰው። ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት በምኖርበት አካባቢ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ሄድኩ፤ ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ተጀመረልኝ። አኗኗሬ ትክክል አለመሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። በመሆኑም አብሬያት ከምኖረው ሴት ተለየሁና ወደተወለድኩበት ከተማ ሄጄ ለብቻዬ መኖር ጀመርኩ። ለተወሰነ ጊዜ ሳመነታ ከቆየሁ በኋላ በዚያ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ቀጠልኩ።

ሆኖም አሁንም ቢሆን አንዳንድ ጥርጣሬዎች ነበሩብኝ። የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጥ የአምላክ ሕዝብ ናቸው? በልጅነቴ የተማርኳቸው ነገሮች ሁሉ ምን ሊሆኑ ነው? ያደግሁት የሰባተኛው ቀን የአድቬንቲስት ተከታይ ሆኜ ስለነበር ከአንድ የአድቬንቲስት አገልጋይ ጋር ተገናኘሁ። በየሳምንቱ ረቡዕ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናኝ ጠየቅሁት። የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በየሳምንቱ ሰኞ ያስጠኑኝ ነበር። ከሁለቱም ወገኖች በአራት ነጥቦች ላይ ግልጽ የሆነ መልስ ማግኘት ፈልጌ ነበር:- የክርስቶስ መመለስ፣ ትንሣኤ፣ የሥላሴ መሠረተ ትምህርትና ጉባኤው እንዴት መደራጀት እንዳለበት። በጥቂት ወራት ውስጥ የነበሩኝ ጥርጣሬዎች በሙሉ ተወገዱ። በአራቱ ነጥቦችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ጭምር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበር። በዚህም የተነሳ በሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ በደስታ መሳተፍ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና ግንቦት 1990 ተጠመቅሁ።

ዩዲትስ?

ዩዲት:- በትዳራችን ውስጥ የተፈጠረው ችግር በጣም ተካርሮ በነበረበት ወቅት እንደገና ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። ሎኸስ የይሖዋ ምሥክር ወደመሆን እያመራ መሆኑን ስሰማ በጣም ተናደድኩ። የመጨረሻው ልጃችን የአሥር ዓመቱ ዮናስ አልፎ አልፎ አባቱን ለመጠየቅ ይሄድ ነበር። ይሁን እንጂ ሎኸስ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ይዞት እንዳይሄድ ከለከልሁት። ሎኸስ ለባለሥልጣናት ይግባኝ ቢልም እንኳ እነሱ የእኔን አቋም ደገፉ።

ከሌላ ሰው ጋር መኖር ጀመርኩ። በተጨማሪም በፖለቲካና በልዩ ልዩ የማኅበራዊ ሥራዎች ውስጥ ይበልጥ መሳተፍ ጀመርኩ። በዚህ ወቅት አንድ ሰው የፈረሰውን ቤተሰቤን እንደገና ስለማቅናት ቢያነሳልኝ ፈጽሞ የምሰማው አይመስለኝም ነበር።

በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አንዳች መጥፎ ነገር ለማግኘት ስል ወደ አንድ የደብር አገልጋይ ሄድኩ። እርሱ ግን ወዲያው ስለ ምሥክሮቹ ምንም እንደማያውቅና ስለ እነርሱ የሚናገር ጽሑፍም እንደሌለው ነገረኝ። ከሁሉ የተሻለው ነገር ከእነርሱ መራቅ ብቻ እንደሆነ ነገረኝ። እርግጥ ነው፣ ይህ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበረኝን መጥፎ አመለካከት እንድለውጥ አልረዳኝም። በኋላ ላይ ግን ጨርሶ ባልጠበቅሁት መንገድ ከእነሱ ጋር የሚያገናኘኝ ሁኔታ ተፈጠረ።

ስዊድን የሚኖረው ወንድሜ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል፤ እንዲሁም በመንግሥት አዳራሹ በሚካሄደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ! ይህም በምሥክሮቹ ላይ የነበረኝን አመለካከት እንድለውጥ አደረገኝ። ሁልጊዜ አስብ እንደነበረው ለዛ ቢስ ሰዎች አለመሆናቸውን ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። ደግና ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ ተጫዋቾች ናቸው።

በዚህ መሀል የቀድሞ ባለቤቴ ሎኸስ ሙሉ በሙሉ ተለውጦ ነበር። ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ከልጆቹ ጋር ጊዜ የሚያሳልፍ፣ ደግና አንደበቱን የሚገታ ሰው ሆኗል፤ በተጨማሪም በፊት ያደርግ እንደነበረው ከልክ በላይ አይጠጣም። ጠቅላላ ባሕሪው ማራኪ ሆኗል! አሁን ሁልጊዜ እንዲሆንልኝ እመኘው የነበረው ዓይነት ሰው ሆኗል። አሁን ዳግመኛ እንደማላገኘውና ምናልባትም አንድ ቀን ሌላ ሴት እንደሚያገባ ሳስበው በጣም ይረብሸኝ ጀመር!

ከዚያም ስውር “ጥቃት” ለመሰንዘር አቀድኩ። በአንድ ወቅት ዮናስ አባቱ ጋር ሳለ አክስቶቹ የእህታቸውን ልጅ የማየት አጋጣሚ ሊኖራቸው ይገባል የሚል ሰበብ በመፍጠር ከሁለት እህቶቼ ጋር ሆኜ ዮናስንና ሎኸስን ለማየት ዝግጅት አደረግሁ። በአንድ የመዝናኛ ሥፍራ ተገናኘን። አክስቶቹ ከልጁ ጋር ሲጫወቱ እኔና ሎኸስ አንድ አግዳሚ ወንበር አገኘንና ተቀመጥን።

ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ገና ማንሳት ስጀምር ሎኸስ በድንገት ከኪሱ አንድ መጽሐፍ አወጣ። መጽሐፉ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የተባለ ነበር። * መጽሐፉን ሰጠኝና ባል እና ሚስት በቤተሰብ ውስጥ ስላላቸው ሚና የሚናገሩትን ምዕራፎች እንዳነብ ሐሳብ አቀረበልኝ። በተለይ ጥቅሶቹን እያወጣሁ እንዳነብ አሳሰበኝ።

ከዚያም እኔና ሎኸስ ከወንበሩ ስንነሳ እጁን ልይዘው ስል ቀስ ብሎ ሸሸኝ። ሎኸስ ስለ አዲሱ እምነቱ ያለኝን አመለካከት ሳያውቅ ከእኔ ጋር አዲስ ቁርኝት የመፍጠር ዓላማ አልነበረውም። ይህ በመጠኑም ቢሆን ቅር ቢያሰኘኝም እንኳ በኋላ ላይ ግን ይህ አመለካከቱ ትክክል እንደሆነና እንደገና የማንጋባ ከሆነ ለእኔው አስቦ እንደሆነ ተገነዘብኩ።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የማወቅ ጉጉቴን ይበልጥ ከፍ አደረገው። በሚቀጥለው ቀን፣ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች የማውቃት አንዲት ሴት ጋር ሄድኩና ስለ ሃይማኖታቸው ማወቅ ስለምፈልግ እርሷና ባለቤቷ መጥተው እንዲያነጋግሩኝ ቀጠሮ ያዝኩኝ። ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ሰጡኝ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን መገንዘብ ቻልኩ። ስለ አንድ ጉዳይ ተወያይተን ወደ ሌላኛው በተሸጋገርን ቁጥር ሁሉም ነገር እውነት መሆኑን ለመቀበል ተገደድኩ።

በዚህ ወቅት ከሉተራን የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ለቅቄ ከመውጣቴም በላይ አደርጋቸው የነበሩትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ አቋረጥኩ። ሲጋራ ማጨስም አቆምኩ። ከሁሉም በላይ የከበደኝ ነገር ይህ ነበር። በነሐሴ 1990 መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩና ሚያዝያ 1991 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ሁለተኛው የሠርጋቸው ቀን

ዩዲት:- አሁን ሁለታችንም የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች ሆነናል። ምንም እንኳ በተለያየ አቅጣጫ ሄደን የነበረ ቢሆንም ሁለታችንም መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተናል። መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ግሩም ትምህርቶች ከቀድሞው የተለየን ሰዎች አድርጎናል። ምናልባትም ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም አሁንም አንዳችን ለሌላው በጥልቅ እናስባለን። ስለዚህ አሁን በድጋሚ ለመጋባት ነፃ ነበርን፤ ያደረግነውም ይኼንኑ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ቃለ መሐላ ገባን፤ በዚህ ጊዜ ግን ይህን ያደረግነው በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነው።

ሎኸስ:- ለማመን አዳጋች ቢመስልም ቤተሰባችን እንደገና አንድ ሆነ! የተሰማንን ደስታ በቃላት መግለጽ አንችልም!

ዩዲት:- በሠርጋችን ላይ ልጆቻችን፣ በርካታ ዘመዶቻችንና የቆዩና አዳዲስ ወዳጆቻችን ተገኝተው ነበር። በጣም አስደሳች ወቅት ነበር። ተጋብዘው ከመጡት እንግዶች መካከል ከመፋታታችን በፊት የሚያውቁን አንዳንድ ሰዎች ይገኙበታል። እንደገና አብረን መሆናችን ያስደሰታቸው ከመሆኑም በላይ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን እውነተኛ ደስታ በማየታቸውም ተገርመዋል።

ልጆቹ

ሎኸስ:- ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ ሁለቱ ልጆቻችን ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመወሰን ሲመርጡ በማየታችን ደስታ አግኝተናል።

ዩዲት:- ዮናስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተዋወቀው በልጅነቱ አባቱን ለመጠየቅ ይሄድ በነበረበት ጊዜ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አድናቆት እንዳለው አሳይቷል። “አባዬ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሚመራ” ከእሱ ጋር መኖር እፈልጋለሁ ብሎ የነገረኝ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። ዮናስ በ14 ዓመቱ ተጠመቀ። ትምህርቱን የጨረሰ ሲሆን አሁን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው።

ሎኸስ:- የመጀመሪያው ልጃችን ማርቲን አሁን 27 ዓመት ሆኖታል። ያደረግነውን ለውጥ ማየቱ ብዙ እንዲያስብ አድርጎታል። ከቤት ለቅቆ ከወጣ በኋላ በሌላ የአገሪቱ ክፍል ይኖር ጀመር። ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ለመጠመቅ ዝግጁ ሆነ። ክርስቲያን ሆኖ ለሚያሳልፈው ለወደፊቱ ሕይወቱ ጥሩ እቅዶችን አውጥቷል።

ሁለተኛው ልጃችን ቶማስ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር አይደለም። እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን እንወደዋለን፤ ጥሩ ግንኙነትም አለን። በቤተሰባችን ውስጥ የተከሰተው ለውጥ አስደስቶታል። እንዲሁም ቤተሰባችን እንደገና አንድ ሊሆን የቻለው እኛ ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመማራችን ምክንያት መሆኑን ሁላችንም እንስማማበታለን። አሁን ሦስቱ ልጆቻችንና እኛን ወላጆችን ጨምሮ መላው ቤተሰብ አዘውትሮ በአንድ ጣራ ሥር መሰባሰብ መቻሉ ምንኛ ታላቅ በረከት ነው!

በዛሬው ጊዜ ያለን ሕይወት

ሎኸስ:- እንዲህ ስንል ፍጽምና ተላብሰናል ማለታችን አይደለም። ሆኖም አንድ ነገር ተምረናል፤ ስኬታማ ለሆነ ትዳር ቁልፍ የሆኑት ነገሮች ፍቅር እና እርስ በርስ መከባበር መሆናቸውን አውቀናል። አሁን ትዳራችን የተገነባበት መሠረት በፊት ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ነው። አሁን የምንኖረው ለራሳችን ሳይሆን ለይሖዋ በመሆኑ ሁለታችንም ከእኛ በላይ ባለሥልጣን መኖሩን ተቀብለናል። እኔና ዩዲት በእርግጥ አንድ እንደሆንን ይሰማናል፤ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት እንጠባበቃለን።

ዩዲት:- ይሖዋ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የትዳርና የቤተሰብ አማካሪ ለመሆኑ እኛ ሕያው ማስረጃ ነን ብዬ መናገር እችላለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.30 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር በ1978 የታተመ። መጽሐፉ አሁን መታተሙን አቁሟል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎኸስ እና ዩዲት በ1973 በመጀመሪያው የሠርጋቸው ቀን

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የነበረውን ቤተሰባቸውን ያጡና መልሰው ያገኙ ሦስት ልጆች

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተላቸው እንደገና አንድ የሆኑት ሎኸስ እና ዩዲት በዛሬው ጊዜ