በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ይለወጣልን?

አምላክ ይለወጣልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ ይለወጣልን?

አንትሮፖሎጂስቱ ጆርጅ ዶርሲ “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ የተገለጸውን አምላክ “አረመኔ አምላክ” ሲሉ ገልጸውታል። አክለውም “ያህዌህ . . . በጣም በጣም መጥፎ አምላክ ነው። እሱ የዘራፊዎች፣ የጨካኞችና የጦረኞች አምላክ ነው።” “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ ያህዌህ ወይም ይሖዋ ተብሎ የተገለጸውን አምላክ በተመለከተ ሌሎችም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ስለሆነም ዛሬ አንዳንዶች ያ ጨካኝ አምላክ የነበረው ይሖዋ ውሎ አድሮ የባሕርይ ለውጥ አድርጎ “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ አፍቃሪና ይቅር ባይ ሆኖ ብቅ እንዳለ ይሰማቸዋል።

ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ የተሰነዘረው ይህ አስተያየት አዲስ አይደለም። በመጀመሪያ ይህን አስተያየት የሰነዘረው በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረውና በተወሰነ መጠን በግኖስቲክ ያምን የነበረው ማርሴዮን ነው። ማርሴዮን “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ አያምንም ነበር። ጠበኛና ተበቃይ፣ እንዲሁም አምላኪዎቹን በቁሳዊ ጥቅም የሚደልል አምባገነን አምላክ እንደሆነ አድርጎ ያስባል። በሌላ በኩል ደግሞ ማርሴዮን “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የተገለጸው አምላክ ፍጹም፣ ንጹሕ ፍቅር፣ ምሕረትና ሞገስ ያለው እንዲሁም ይቅር ባይ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።

ይሖዋ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው ያስተናግዳል

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት ነው። ይህም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ሁሉ እንደሚፈጽም ያመለክታል። ሙሴ አምላክን ስሙ ማን እንደሆነ በጠየቀው ጊዜ ይሖዋ በዚህ መንገድ ትርጉሙን ዘርዘር አድርጎ ገልጾለታል:- “መሆን የምፈልገውን መሆን የምችል።” (ዘጸአት 3:​14 NW ) የእንግሊዝኛው የሮተርሃም ትርጉም ደግሞ “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት አስቀምጦታል።

በመሆኑም ይሖዋ የጽድቅ ዓላማዎቹን ዳር ለማድረስና የገባቸውን ተስፋዎች ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል ወይም መሆን ይችላል። የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ፈራጅ፣ ልዑል፣ ቀናተኛ፣ ሉዓላዊ ጌታ፣ ፈጣሪ፣ አባት፣ ታላቅ አስተማሪ፣ እረኛ፣ ጸሎት ሰሚ፣ የሚቤዥ፣ ደስተኛው አምላክና እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ የማዕረግ ስሞችና መግለጫዎች ያሉት መሆኑ ለዚህ ማረጋገጫ ነው። ፍቅራዊ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ሆኖ ይገኛል።​—⁠ዘጸአት 34:​14፤ መሳፍንት 11:​27፤ መዝሙር 23:​1፤ 65:​2፤ 73:​28፤ 89:​26፤ ኢሳይያስ 8:​13፤ 30:​20፤ 40:​28፤ 41:​14፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:​11

ታዲያ ይህ ማለት የአምላክ ባሕርይ ወይም የአቋም ደረጃዎች ይለዋወጣሉ ማለት ነው? በፍጹም። ያዕቆብ 1:​17 (የ1980 ትርጉም ) አምላክን በተመለከተ ‘እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ የሌለበት’ በማለት ይገልጻል። አምላክ የማይለዋወጥ ከሆነ የሚለዋወጡ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው እንዴት ማስተናገድ ይችላል?

ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎችን የሚወጡ አሳቢ ወላጆች ምሳሌ ይህን ሁኔታ እንድንረዳ ያስችለናል። አንድ ወላጅ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ እንኳ ምግብ አብሳይ፣ ቤት አጽጂ፣ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ፣ ነርስ፣ ወዳጅ፣ መካሪ፣ አስተማሪ፣ ተግሣጽ የሚሰጥና ሌሎችንም ብዙ ሥራዎችን የሚያከናውን መሆን ይችላል። አንድ ወላጅ እነዚህን የሥራ ድርሻዎች በሚያከናውንበት ጊዜ ባሕርይውን አይለዋውጥም፤ እሱም ሆነ እሷ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ከሁኔታው ጋር ራሳቸውን ማስማማት ነው። በይሖዋ ዘንድም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሆኖም ይሖዋ እንደዚህ የሚያደርገው ከሰው እጅግ በላቀ መልኩ ነው። ዓላማውን ለማስፈጸም እንዲሁም ፍጥረታቱን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ሲል የፈለገውን ሁሉ መሆን ይችላል።​—⁠ሮሜ 11:​33

ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በዕብራይስጥም ሆነ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የፍቅርና የምሕረት አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረው ነቢዩ ሚክያስ ስለ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:- “በደልን ይቅር የሚል፣ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቁጣውን ለዘላለም አይጠብቅም።” (ሚክያስ 7:​18) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ ‘እግዚአብሔር ፍቅር ነው’ የሚሉትን በሰፊው የሚታወቁ ቃላት ጽፏል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:​8

በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜ ሆን ብለው ሕጎቹን በሚጥሱና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ በማይሆኑ እንዲሁም ሌሎችን በሚጎዱ ሰዎች ላይ እርምጃ የሚወስድ ጻድቅ ፈራጅ እንደሆነ በሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ተገልጿል። መዝሙራዊው “[ይሖዋ] ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል” ብሏል። (መዝሙር 145:​20) በተመሳሳይ ዮሐንስ 3:​36 እንዲህ ይላል:- “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

የማይለዋወጡ ባሕርያት

አራቱ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ኃይል አይለወጡም። ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” በማለት ነግሯቸዋል። (ሚልክያስ 3:​6) ይህን የተናገረው አምላክ የሰውን ዘር ከፈጠረ ወደ 3, 500 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ጠለቅ ብሎ መመርመር የሚያረጋግጠውም ይህ መለኮታዊ አነጋገር ሐቅ መሆኑን ነው። አምላክ የአቋም ደረጃዎቹና ባሕርያቱ የማይለወጡ መሆናቸውን። ባለፉት መቶ ዓመታት የትኛውም የይሖዋ ባሕርይ እየተለሳለሰ አልመጣም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ባሕርይውን ማሻሻል አያስፈልገውም።

በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው አምላክ በኤደን ገነት ከሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለጽድቅ ያለው ጽኑ አቋም አልቀነሰም ወይም የነበረው ፍቅር አልጨመረም። በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የተንጸባረቁት ባሕርያቱ የማይለዋወጠው የአንዱ ባሕርይው የተለያየ ገጽታ ናቸው። እነዚህም የተከሰቱት የተለየ አቋም ይም ግንኙነት የሚጠይቁ ነገሮችን ለመወጣት ሲል ለተለያዩ ሁኔታዎችና ግለሰቦች ያንጸባረቃቸው ባሕርያት ናቸው።

ስለዚህ የአምላክ ባሕርይ ባለፉት መቶ ዓመታት ፈጽሞ እንዳልተለወጠና ወደፊትም እንደማይለወጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ በማይለወጠው ባሕርይውና በሐሳበ ጽኑነቱ ፍጹም የሆነ አርአያ​ችን ነው። ምን ጊዜም ቢሆን እምነትና ትምክህት የሚጣልበት አምላክ ነው። ሁልጊዜ ልንተማመንበት እንችላለን።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው አምላክ . . .

. . . ራሱ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ያመጣል