በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዴት ማቆም እንደምትችል

እንዴት ማቆም እንደምትችል

እንዴት ማቆም እንደምትችል

ትንባሆ ማቆም ብስክሌት መንዳት እንደ መለማመድ ነው። በአንድ ጊዜ ሙከራ ሊሳካ አይችልም። ስለዚህ ማጨስ ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ካደረግህ እስኪሳካልህ ድረስ ተደጋጋሚ ሙከራ ለማድረግ መዘጋጀት ይኖርብሃል። እንደገና ቢያገረሽብህ ፈጽሞ እንደተሸነፍክ አድርገህ አታስብ። ትምህርት የምታገኝበት ተሞክሮ እንደሆነና ወዳወጣኸው ፕሮግራም ለመድረስ በምታደርገው ጥረት አንድ ትንሽ እንቅፋት ብቻ አድርገህ ቁጠረው። ሌሎች ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸው አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል። ለአንተም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ማጨስ ለማቆም አእምሮህን አዘጋጅ

■ በመጀመሪያ ደረጃ ሲጋራ ማቆም ማንኛውም ዓይነት ጥረት ሊደረግለት የሚገባ ነገር እንደሆነ ራስህን ማሳመን ይኖርብሃል። እንድታቆም የሚገፋፉህን ምክንያቶችና ብታቆም የምታገኛቸውን ጥቅሞች ዘርዝር። ካቆምክ በኋላም ቢሆን ይህን ዝርዝር ብትከልስ ቁርጠኝነትህ ይታደሳል። ለማቆም የሚገፋፋህ ትልቁ ምክንያት አምላክን ለማስደሰት መፈለግህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በሙሉ አእምሯችን፣ ልባችን፣ ነፍሳችንና ኃይላችን መውደድ እንደሚገባን ይናገራል። የትንባሆ ሱሰኞች ከሆንን ይህን ማድረግ አንችልም።​—⁠ማርቆስ 12:​30

■ ለምንና መቼ እንደምታጨስ ለይተህ ለማወቅ እንድትችል የማጨስ ልማድህን መለስ ብለህ መርምር። በአንድ የአዘቦት ቀን እያንዳንዱን ሲጋራ መቼና የት እንዳጨስክ ወረቀት ላይ መመዝገቡ ሊረዳህ ይችላል። ይህን ማድረግህ ካቆምክ በኋላ እንደ ገና እንድታጨስ የምትፈተንባቸውን ሁኔታዎች በቅድሚያ እንድታውቅ ያስችልሃል።

የምታቆምበትን ቀን ቁረጥ

■ የምታቆምበትን ቀን ምረጥና ቀን መቁጠሪያህ ላይ ምልክት አድርግ። ከመጠን ያለፈ ውጫዊ ውጥረት የማያጋጥምህን ቀን ምረጥ። ይህ የቆረጥከው ቀን ሲደርስ በአንዴና ሙሉ በሙሉ አቁም።

■ የምታቆምበት ቀን ከመድረሱ በፊት የሲጋራ መተርኮሻዎችን፣ ክብሪቶችንና መለኮሻዎችን አስወግድ። የትንባሆ ሽታ ያለባቸውን ልብሶች በሙሉ አጽዳ።

■ የሥራ ባልደረቦችህ፣ ጓደኞችህና ቤተሰቦችህ ለማቆም በምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲሰጡህና እንዲያበረታቱህ ጠይቅ። ሌሎች አንተ ባለህበት እንዳያጨሱ ለመጠየቅ ወደኋላ አትበል።

■ በምታቆምበት ቀን ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እቅድ አውጣ። እንደ ቤተ መዘክር ወይም ቲያትር ቤት ወዳሉ ማጨስ የማይፈቀድባቸው ቦታዎች ለመሄድ ትችል ይሆናል። አለበለዚያም እንደ ዋና፣ ብስክሌት እንደ መንዳት ወይም በእግር እንደ መሄድ ያለ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ትችላለህ።

ባለማጨስ ምክንያት የሚፈጠረውን መጥፎ ስሜት መቋቋም

ከባድ አጫሽ ከነበርክ የመጨረሻውን ሲጋራ ባጨስክ በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ የሲጋራ ጥም ስሜቶች ሊሰሙህ ይጀምራሉ። ብስጩ የመሆን፣ ትዕግሥት የማጣት፣ የጥላቻ ስሜት፣ አለመረጋጋት፣ የጭንቀት ስሜት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መቅበጥበጥ፣ የምግብ ፍላጎት መጨመር እና የሲጋራ አምሮት ሊሰማህ ይችላል። ምናልባት ሐኪምህ እነዚህን ስሜቶች የሚያስታግሱ መድኃኒቶች ሊያዝልህ ይችል ይሆናል። በተጨማሪም ይህን ውጊያ በድል አድራጊነት እንድትወጣ የሚረዱ ነገሮችም አሉ።

■ በመጀመሪያዎቹ አስቸጋሪ ሳምንታት አነስተኛ የካሎሪ መጠን ያላቸውን ምግቦች ተመገብ። ብዙ ውኃ ጠጣ። አንዳንዶች እንደ ካሮት ወይም ሰለሪ ያሉትን ጥሬ አትክልት መክሰስ ማድረግ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። አካላዊ እንቅስቃሴ ካደረግህ ክብደትህ ከመጠን በላይ እንዳይጨምርና ነርቮችህ እንዳይቆጡ ለማድረግ ትችላለህ።

■ እንድታጨስ ከሚፈትኑህ ቦታዎችና ሁኔታዎች ራቅ።

■ እንድታጨስ የሚፈታተኑህን የተሳሳተ አስተሳሰቦች ተከላከል። የትንባሆ አምሮት በሚያስቸግርህ ወቅት እንደሚከተሉት ያሉት አሳቦች ወደ አእምሮህ ይመጣሉ። ‘ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ዛሬ ብቻ አጨሳለሁ።’ ‘አንድ ያለኝ መጥፎ አመል ማጨስ ብቻ ነው!’ ‘ትንባሆ ያን ያህል መጥፎ ነገር ሊሆን አይችልም። አንዳንድ ከባድ አጫሾች ከ90 ዓመት በላይ ኖረዋል።’ ‘ዘላለም አልኖር።’ ‘አለ ትንባሆ ሕይወት ምንም ጣዕም የለውም።’

■ ልትሸነፍ ተቃርበህ ከሆነ ወዲያው ከማጨስ ይልቅ ዘግየት በል። አሥር ደቂቃ ብቻ ብትዘገይ በጣም አጣዳፊ የሆነው አምሮት ሊያልፍልህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከሲጋራ ፈጽሞ መቆራረጥህን ስታስብ በጣም ከባድ ነገር ሆኖ ሊታይህ ይችላል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ለአንድ ቀን ብቻ በማቆም ላይ አተኩር።

■ አምላክን ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ እንዲረዳህ ጸልይ። አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ሕይወታቸውን ከእርሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ለሚጣጣሩ በሙሉ ‘አስፈላጊ በሆነ ጊዜ’ ሁሉ እርዳታ ይሰጣል። (ዕብራውያን 4:​16) ይሁን እንጂ ተአምር እንዲደረግልህ አትጠብቅ። ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።

ሁለተኛ ወደማጨስ አትመለስ

■ በጣም አስቸጋሪ የሚሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ቢሆኑም ከዚያ በኋላም ቢሆን በተቻለህ መጠን ከአጫሾችና እንድታጨስ ከሚገፋፉ ሁኔታዎች ራቅ።

■ ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሳታጨስ ብትቆይም አልፎ አልፎ ባጨስ ምንም አይደለም ብለህ ራስህን አታታልል።

■ “አንድ ሲጋራ ብቻ ላጭስ” የሚለውን ማታለያ አጥብቀህ ተቃወም። አንዱ በቀላሉ ሌሎችን ያስከትልና ወዲያው ሳታስበው ማጨስ ለማቆም ያደረግኸው ጥረት ሁሉ መና ይቀርብሃል። ብትሸነፍና አንድ ሲጋራ ብታጨስ ተጨማሪ ሌላ የምታጨስበት ምክንያት የለም። ልማዱ ቢያገረሽብህም እንደገና አቁም።

በሚልዮን የሚቆጠሩ አጫሾች ለማቆም ችለዋል። ቆራጥና ትጉህ በመሆን አንተም ልታቆም ትችላለህ!