በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓይንህ ፊት የሚንቀሳቀሱ ጉድፍ መሳይ ነገሮች አሉን?

ከዓይንህ ፊት የሚንቀሳቀሱ ጉድፍ መሳይ ነገሮች አሉን?

ከዓይንህ ፊት የሚንቀሳቀሱ ጉድፍ መሳይ ነገሮች አሉን?

አይተሃቸው ታውቅ ይሆናል። ከዓይንህ ፊት የሚንሳፈፉ ትናንሽ ግራጫ መልክ ያላቸው ጉድፍ መሳይ ነገሮች ናቸው። በምታነብበት ወይም ነጣ ያለ ቀለም ያለው ግድግዳ በምትመለከትበት ወይም የጠራ ሰማይ በምታይበት ጊዜ አስተውለሃቸው ይሆናል።

ከእነዚህ ጉድፍ መሳይ ነገሮች አንዱን አጥርተህ ለማየት ሞክረህ ከነበረ ፈጽሞ እንደማይቻል ተገንዝበሃል። ገና ዓይንህን በትንሹ ስታንቀሳቅስ በርረው ይርቁብሃል። ፊት ለፊት የሚታይህ እንኳ ቢሆን ምንነቱን አስረግጠህ ማወቅ አትችልም።

እነዚህ ጉድፍ መሳይ ነገሮች ምንድን ናቸው? በዓይንህ ላይ የሚገኙ ናቸው ወይስ ዓይንህ ውስጥ ያሉ ነገሮች ናቸው? ዓይንህን ሳታንቀሳቅስ የዓይንህን ቆቦች ክድን ክፍት አድርግ። እነዚህ ጉድፍ መሳይ ነገሮቹ እንቅስቃሴያቸውን ከቀየሩ ወይም ከጠፉ ከውጭ ያሉ ናቸው ማለት ነው። ይህ ጽሑፍ አሁን እያብራራ ያለው ስለነዚህ ነገሮች አይደለም።

ሆኖም ምንም ዓይነት ለውጥ ካላሳዩ ወይም አነስተኛ ለውጥ ብቻ ካሳዩ ጉድፍ መሳይ ነገሮቹ ያሉት በዓይንህ ውስጥ የዓይንህን ውስጠኛ ክፍል በሞላው ዝልግልግ ፈሳሽ (vitreous humor) ውስጥ ተንሳፍፈው የሚገኙ ናቸው። የሚገኙት ከዓይን ሌንስ በስተጀርባ በመሆኑ ግልጽ ሆነው አይታዩም። በተጨማሪም ዝልግልዝ ፈሳሹ ከውኃ ብዙም የማይወፍር ስለሆነ በቀጥታ ልታያቸው በምትሞክርበት ጊዜ ሸሽተው ሊጠፉብህ ይችላሉ። ሙስኪ ቮለታንቲዝ የሚል የሕክምና ስም የተሰጣቸውም ለዚህ ነው። ትርጉሙም “በራሪ ዝንቦች” ማለት ነው።

የሚመጡት ከየት ነው?

እነዚህ ጉድፍ መሳይ ነገሮች የሚመጡት ከየት ነው? አንዳንዶቹ ከመወለድህ በፊት የተከናወኑ ሂደቶች ቅሪት ናቸው። አንድ ሕፃን ከተጸነሰ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ወራት የዓይኑ ውስጠኛ ክፍሎች የጭረትነት ባሕርይ ይኖራቸዋል። ሊወለድ በሚደርስበት ጊዜ እነዚህ ጭረቶችና ሌሎች ሴሎች ተለውጠው ዝልግልግ ፈሳሽ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሴሎችና የጭረት ቅንጣቶች ሊቀሩ ስለሚችሉ እየተንሳፈፉ ሊቆዩ ይችላሉ። በተጨማሪም ገና ባልተወለደ ሕፃን ዓይን ውስጥ ሌንሱን የሚመግብ ደም ቅዳ የደም ሥር የሚያልፍበት ከእይታይ ነርቭ (optic nerve) ተነስቶ ወደ ሌንስ የሚደርስ ቦይ አለ። ይህ የደም ሥር እየከሳ ሄዶ አብዛኛውን ጊዜ ሕፃኑ ከመወለዱ በፊት የሚጠፋ ቢሆንም የሚቀሩ ጥቃቅን ቅንጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

ከሌሎች ምንጮችም ሊመጡ ይችላሉ። በትልቅ ሰው ዓይን ውስጥ ያለው ዝልግልግ ፈሳሽ እንኳ ሙሉ በሙሉ ፈሳሽ አይደለም። ሃያ ሎይድ በሚባል በቀላሉ ሊጎዳ በሚችል ብራና መሳይ ነገር የተሸፈነ ነው። ይህ ብራና መሳይ ነገር ረቲና ከሚባለው በዓይን ውስጠኛ ክፍል የሚገኝና የምታየውን ነገር ተቀብሎ የሚያቆይ ሰሌዳ ጋር ይያያዛል። የሃያሎይድ ብራና ውጭና ጠርዝ ዙሪያውን ከረቲና ጋር ይያያዛል። ከዚህ ጠርዝ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ጭረት መሣይ ነገሮች ወደ ዝልግልግ ፈሳሹ ይዘረጋሉ።

እድሜያችን እየገፋ በሚሄድበት ጊዜ እነዚህ ጭረት መሳይ ነገሮች መኮማተር ይጀምራሉ። በዚህ ምክንያት አንዳንዶቹ ይበጣጠሳሉ። በተጨማሪም ዝልግልግ ፈሳሹ ይበልጥ ስለሚቀጥን የተበጠሱት ጭረት መሳይ ነገሮች እንደልባቸው መንሳፈፍ ይችላሉ። ዝልግልግ ፈሳሽ ራሱ ቀስ በቀስ ስለሚሸበሸብ ከረቲና ራቅ ማለት ይጀምርና በቦታው አንዳንድ የሕዋሳት ፍርስራሾች ይጠራቀማሉ። በዚህ መንገድ እድሜህ እየገፋ ሲሄድ እነዚህን በራሪ ዝንቦች ወዲያና ወዲህ ሲንሳፈፉ ማየት ትጀምራለህ።

ሌላው የትናንሽ ተንሳፋፊዎች ምንጭ የረቲና ደም ሥሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ራስ ሲመታ ወይም ዓይን ከፍተኛ የሆነ ጭነት ሲያርፍበት ከትናንሽ የደም ሥሮች ቀይ የደመ ሕዋሳት ሊፈስሱ ይችላሉ። ቀይ የደም ሕዋሳት የማጣበቅ ባሕርይ ስላላቸው እርስ በርሳቸው እንደ ሰንሰለት ይያያዛሉ። ነጠላ ወይም እርስ በርሳቸው የተያያዙ ሴሎች ወደ ዝልግልግ ፈሳሽ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ረቲና አጠገብ ከቆዩ ደግሞ ሊታዩ ይችላሉ። ቀይ የደም ሕዋሳት ወደ ሰውነት ተመልሰው የመዋሃድ ችሎታ ስላላቸው ቀስ በቀስ ሊጠፉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ በቀላል ጉዳት ምክንያት የሚፈጠሩ ስለሆኑ ሙስኪ ቮለታንቲዝ ናቸው ለማለት አይቻልም።

ሙስኪ ቮለታንቲዝ መኖር አንድ ችግር መኖሩን ያመለክታል? አብዛኛውን ጊዜ አያመለክትም። ጤናማ ዓይን ያላቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ሊያዩዋቸው ይችላሉ፤ ሆኖም ቀስ በቀስ ይለምዷቸውና አብረው መኖር ይጀምራሉ። አንዳንድ ሁኔታዎች ግን አደጋ መኖሩን ሊያመለክቱ ይችላሉ።

አደገኛ ሁኔታ ሲፈጠር

በድንገት ከወትሮው ይበልጥ ብዙ ጉድፍ መሳይ ነገሮችን ማየት ከጀመርክ አንድ እንግዳ የሆነ ሁኔታ በመፈጠር ላይ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል። በተለይ ከዓይንህ ውስጥ ትናንሽ የብርሃን ነጸብራቆች የሚታዩ ከሆነ ጉዳዩን ይበልጥ አደገኛ ያደርጉታል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፈጠረው ብርሃን ወደ ነርቭ መልእክቶች በሚለወጥበት በረቲና ውስጥ ነው። ብዙ ተንሳፋፊዎችና የብርሃን ነጸብራቆች የሚታዩት አብዛኛውን ጊዜ ረቲና ከቦታው በሚላቀቅበት ጊዜ ነው። ይህ የሚከሰተው እንዴት ነው?

የረቲና ውፍረትና አሠራር እንዲሁም ጥንካሬ ከእርጥብ የሽንት ቤት ወረቀት ጋር ይመሳሰላል። ብርሃን የመለየት ችሎታ ያለው የፊተኛው ገጽ በጀርባ በኩል ካለው ገጽ ጋር የተያያዘ ሲሆን ከዝልግልግ ፈሳሽ ጋር የተያያዘው በፊተኛው ጠርዝና የእይታ ነርቭ በሚገኝበት ቦታ ላይ ብቻ ሲሆን ፎቪያ ሴንቲራሊስት ከሚባለው የዕይታ ማዕከል ጋር ያለው ማያያዣም በጣም ልል ነው። የተቀረው የረቲና ክፍል ቦታውን ጠብቆ እንዲኖር የሚያደርገው ዝልግልግ ፈሳሽ ነው። ዓይን ከፍተኛ የሆነ የመለመጥ ችሎታ ስላለው አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ ምት እንኳ ቢያርፍበት ረቲና አይቀደድም ወይም ከቦታው አይላቀቅም።

ይሁን እንጂ ጠንከር ያለ ምት በአንዳንድ የረቲና ክፍሎች ላይ የሚያዳክም ጉዳት ሊያደርስ ወይም አነስተኛ ቀዳዳ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም ዝልግልግ ፈሳሽና ረቲና በተያያዘበት ቦታ ላይ እንዲህ ያለው ቀዳዳ ሊፈጠር ይችላል። ድንገተኛ እንቅስቃሴ ወይም አደጋ በሚኖርበት ጊዜ ዝልግልግ ፈሳሹ ረቲናውን ስለሚጫነው አነስተኛ ቀዳዳ ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ጊዜ ዝልግልግ ፈሳሹ ከሚገኝበት ክፍል ወደ ረቲና ጀርባ የሚገባው ፈሳሽ ረቲናውን ከተያያዘበት ቦታ ያላቅቀዋል። እንዲህ ባለው ጉዳት ምክንያት ብርሃን የመለየት ችሎታ ያላቸው የነርቭ ሕዋሳት እንደ እሳት ያለ ነገር ይረጫሉ። የብርሃን ነጸብራቅ ሆነው የሚታዩት እነዚህ ናቸው።

በውስጠኛው የረቲና ገጽ የደም ሥሮች ስለሚገኙ አንዳንድ ጊዜ ረቲና በሚላቀቅበት ጊዜ አነስተኛም ሆነ በዛ ያለ ደም መፍሰሱ አይቀርም። የደም ሴሎች ወደ ዝልግልግ ፈሳሽ ውስጥ ገብተው ስለሚንሳፈፉ ብናኝ ነገር መስለው መታየት ይጀምራሉ። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ረቲናው ይላቀቅና የጨለማ ግርዶሽ ይፈጠራል።

ስለዚህ በድንገት በርካታ ጉድፍ መሳይ ነገሮችን ማየት ከጀመርክ በተለይ የብርሃን ነጸብራቆችም አብረው ከታዩ ወዲያው ሳትዘገይ ወደ ዓይን ሐኪም ወይም ወደ ሆስፒታል መሄድ አለብህ! ረቲናው ከቦታው ተላቆ ሊሆን ይችላል። ረቲናው በብዛት ከተላቀቀ መልሶ ማስተካከል አስቸጋሪ ይሆናል።

ከዓይንህ ፊት የሚንቀሳቀሱ ጉድፍ መሳይ ነገሮች ማየት ከጀመርክ ብዙ ዓመት ሆኖሃልን? የብርሃን ነጸብራቆች አብረው የማይታዩ ከሆነ የሚያስጨንቅህ ነገር አይሆንም። ሁሉም ሰው እነዚህ ጉድፍ መሳይ ነገሮች ይታዩታል ለማለት ይቻላል። ችላ ብለህ ብትተዋቸው በእርግጥ ጉድፎቹ ባይጠፉም የዕለት ተዕለት ኑሮህን በምትከታተልበት ጊዜ መኖራቸውን እንኳ መርሳት ትጀምራለህ። የጉድፎቹ መኖር በማየት ችሎታ ላይ ምንም ዓይነት ችግር የማያስከትል መሆኑ ዓይን ከፍተኛ የሆነ አደጋን የመቋቋም ችሎታ እንዲሁም አእምሮ ከሚደርሱበት ድንገተኛ ሁኔታዎች ጋር የመላመድ ችሎታ እንዳላቸው ያሳያል።

ይሁን እንጂ ማንኛውም ተንሳፋፊ ጉድፍ መሳይ ነገሮች የሚታዩት ሰው ምንም የሚያሳስበኝ ነገር የለም ብሎ ከመደምደሙ በፊት በዓይን ሐኪም መመርመር ይኖርበታል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የማየት ችግሮችን በመነጽር አማካኝነት ማስተካከል የተጀመረው እንዴት ነው?

በሐኪም የታዘዘ መነጽር ወይም በዓይን ላይ የሚለጠፍ ሌንስ የምታደርግ ከሆነ ሙስኪ ቮለታንቲዝ ባለውለታዎችህ ናቸው። ፍራንስ ኮርኔሊስ ዶንደርስ የተባለው እውቅ የ19ኛው መቶ ዘመን ሆላንዳዊ ሐኪም የዓይንን አሠራርና በሽታዎችን ለማጥናት የተነሳሳው ስለ ሙስኪ ቮለታንቲዝ የማወቅ ፍላጎት ስላደረበት ነበር። አንዳንዶቹን የሙስኪ ቮለታንቲዝ ምክንያቶች ለማወቅ ከመቻሉም በተጨማሪ በቅርብ ያሉ ነገሮችን ለማየት ያለመቻል ችግር የሚከሰተው በዓይነ ኳስ ማጠር ምክንያት እንደሆነና አስቲግማቲዝም የተባለው አጥርቶ ለማየት ያለመቻል ችግር ደግሞ የኮርኒያና የሌንስ ገጾች ትክክለኛ ቅርጻቸውን በሚያጡበት ጊዜ እንደሆነ ተገንዝቧል። የማየት ችግሮችን በመነጽር አማካኝነት ማስተካከል የተቻለው በእርሱ ጥናት ላይ በመመሥረት ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶንደርስ

[ምንጭ]

Courtesy National Library of Medicine

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በረቲና ላይ ያለ ቀዳዳ

ቀይ የደም ሕዋስ

ከቦታው የተላቀቀ ረቲና

ወደ አእምሮ የሚሄድ እይታ ነርቭ

ሃይሎይድ መምብሬን

ሌንስ

ያይን ብሌን

ዝልግልግ ፈሳሽ

የደም ሥር

መጣኔ ብርሃን

ቀራጼ አካላት