በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክራባት—ጥንትና ዛሬ

ክራባት—ጥንትና ዛሬ

ክራባት—ጥንትና ዛሬ

ወንዶች አንገታቸውን የማስዋብ ፍላጎት ካደረባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። ለምሳሌ በ1737 ከዘአበ ገደማ ላይ የግብፁ ፈርዖን ለዮሴፍ የወርቅ ሐብል ሰጥቶት ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 41:​42

ዛሬ በብዙ የዓለም ክፍሎች ወንዶች ክራባት ያስራሉ። የተለያዩ ምንጮች እንደሚጠቁሙት የመጀመሪያዎቹ የክራባት ዓይነቶች መለበስ የጀመሩት በ16ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ በእንግሊዝና በፈረንሳይ አገሮች ነው። ወንዶች ደብሌት ተብሎ የሚጠራ ጥብቅ ያለ ኮት ይለብሱ ነበር። በተጨማሪም የተሸነሸነ ጌጠኛ የአንገት ልብስ አንገታቸው ላይ ይለብሱ ነበር። ይህ የአንገት ልብስ አብዛኛውን ጊዜ ሙሉውን አንገት የሚከብ ወፍራምና ዝርግ የሆነ ጠርዝ ነበረው። ከነጭ ጨርቅ የሚሠራ ሲሆን ቅርጹን እንደያዘ እንዲቆይ ማጠንከሪያ ይደረግለታል።

ቀስ በቀስ ይህ ዓይነቱ የአንገት ልብስ ትከሻ ላይ በሚተኛ ኮሌታ ተተካ። ይህ ኮሌታ ነጭ ሲሆን ሙሉ ትከሻን የሚሸፍንና ወደታች ወረድ የሚል ነበር። እነዚህ ኮሌታዎች ቫንዳይክስ ተብለው ይጠሩ ነበር። ፒውሪታንስ የተባሉት ሃይማኖታውያን ይለብሷቸው ነበር።

በ17ኛው መቶ ዘመን በተለመደው ረዥም ኮት ሥር ሰደርያ የሚባል ረዥም የውስጥ ኮት መለበስ ተጀመረ። ለባሹ አንገቱን የአንገት ልብስ ወይም ክራባት በተባለ ጨርቅ ይጠመጥም ነበር። ይህ ጨርቅ ከአንድ ጊዜ በላይ አንገት ላይ ከተጠመጠመ በኋላ የተቀረው ዘርፍ ሸሚዝ ላይ ይንጠለጠላል። የ17ኛው መቶ ዘመን የቀለም ቅብ ሥዕሎች እንደሚያሳዩት አንደነዚህ ዓይነቶቹ ክራባቶች ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈው ነበር።

ክራባቶች ከወፍራም ጥጥ ጨርቅ፣ ከስስ ሊኖና ከዳንቴል ጭምር ይሠሩ ነበር። ከዳንቴል የሚሠሩት ውድ ዋጋ ያወጣሉ። የእንግሊዙ ዳግማዊ ጀምስ ዘውድ በጫነበት በዓል ላይ አድርጎት ለነበረው ክራባት 36 ፓውንድ ከ10 ሽልንግ እንደከፈለ ይነገራል። ይህ በዚያ ዘመን በጣም ብዙ ገንዘብ ነበር። አንዳንድ ከዳንቴል የሚሠሩ ክራባቶች ሰፊ ነበሩ። በዌስትምንስተር አቤ የሚገኘው የዳግማዊ ቻርልስ ሐውልት ክራባቱ 15 ሳንቲ ሜትር ወርድና 86 ሳንቲ ሜትር ቁመት እንደነበረው ያሳያል።

ክራባቶች በተለያየ ዓይነት አስተሳሰር ይታሰሩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ክራባቱ ከቦታው እንዳይነቃነቅ በቀጭን ሐር ከተያያዘ በኋላ ከአገጭ ግርጌ በትልቁ ተሸምቅቆ ይቋጠራል። እንዲህ ዓይነቱ የአንገት ልብስ ሶሊቴር ይባል ነበር። ይህ ቋጠሮ የዘመናችንን ቢራቢሮ መሳይ ክራባት ይመስል ነበር። ቢያንስ አንድ መቶ የሚያክሉ የክራባት አስተሳሰሮች እንደነበሩ ይነገራል። በወንዶች አለባበስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል የሚባለው ቦ ብራመል አንድ ክራባት ለማሰር ሙሉ ጠዋት ያሳልፍ እንደነበረ ይነገራል።

በ1860ዎቹ ዓመታት ረዥም ዘርፎች የነበሩት የአንገት ልብሶች የዘመናችንን ክራባት መምሰል ጀመሩ። ፎር ኢን ሃንድ ተብሎም ይጠራል። ይህ ስያሜ የተገኘው ባለ አራት ፈረስ ሰረገላ ነጂዎች የሚያዘወትሩት አስተሳሰር ስለነበር ነው። ኮሌታ ያላቸው ሸሚዞች የተለመዱ ሆኑና ክራባቱ ከአገጭ ሥር ይታሰርና ዘርፎቹ ሸሚዙ ላይ ይንጠለጠላሉ። ዘመናዊው ክራባት ብቅ ያለው በዚህ ጊዜ ነበር። በ1890ዎቹ ዓመታት ደግሞ የቢራቢሮ ቅርፅ ያለው ሌላ ዓይነት ክራባት ተወዳጅ እየሆነ መጣ።

በዛሬው ጊዜ ክራባት ለአንድ ወንድ ቁመና ማማር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። እንዲያውም አንዳንዶች የአንድን እንግዳ ሰው የክራባት ዓይነት በመመልከት ብቻ ስለማንነቱ መገመት ይቻላል ይላሉ። ስለዚህ ንጹሕ የሆነና ከሸሚዝ፣ ከሱሪና ከኮት ጋር የሚስማማ ቀለም ያለው ክራባት ብታስር ጥሩ ይሆናል።

በሚገባ ተስተካክሎ የታሠረ መሆን ይኖርበታል። ምናልባት በጣም የተለመደው አስተሳሰር ፎር ኢን ሃንድ የሚባለው ሳይሆን አይቀርም። (ገጽ 14 ላይ ያለውን ስዕላዊ መግለጫ ተመልከት።) ንጹሕና ማራኪ ከመሆኑም በላይ ጥሩ መልበስ አስፈላጊ ለሚሆንባቸው ወቅቶች ተስማሚ ነው። ሌላው የተለመደ አስተሳሰር ትንሽ ሰፋ የሚለውና ዊንድ ሶር የሚባለው አስተሳሰር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ከቋጠሮ ግርጌ ሰርጎድ ያለ ቅርጽ ይኖረዋል።

ብዙ ወንዶች ክራባት ሲያስሩ አይመቻቸውም። ጉሮሯቸውን ስለሚጫናቸው አይወዱትም። ይሁን እንጂ እንዲህ ይሰማቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ችግሩ ይበልጥ የሚመነጨው ከሸሚዛቸው አንገት ልክ እንደሆነ ተገንዝበዋል። እንዲህ ያለ ችግር ካለብህ የሸሚዝህ አንገት ልክህ መሆኑን አረጋግጥ። መጠኑ ትክክል ከሆነ ክራባት ያሰርክ መሆኑ እንኳ ትዝ አይልህም።

በብዙ አገሮች በሥራ ቦታና ጥሩ መልበስ አስፈላጊ በሚሆንባቸው ቦታዎች ክራባት ማሰር ተገቢ እንደሆነ ይታሰባል። በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያን ወንዶች በመደበኛ አገልግሎት በሚሰማሩባቸው ጊዜያት ክራባት ያስራሉ። አዎን፣ በአንድ ወንድ አንገት ላይ የተጠመጠመ ቁራጭ ጨርቅ ለሰውዬው ክብርና ግርማ ሊጨምርለት ይችላል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፎር ኢን ሃንድ የተባለው የክራባት አስተሳሰር *

1 ከቀጭኑ የክራባቱ ጫፍ ወደ 30 ሴንቲ ሜትር ከፍ ብለህ ሰፊውን የክራባት ክፍል ከላይ በማድረግ አደራርበህ ያዝ፤ ከዚያም ሰፊውን የክራባቱን ክፍል በጀርባ በኩል አዙረው።

2 ሰፊውን ክፍል በላይ በኩል አዙረህ ከታች ወደ ላይ በቀዳዳው አሾልከው።

3 ያሾለከውን የክራባቱን ጫፍ ላላ አድርገህ በያዝከው ቋጠሮ ውስጥ ወደ ታች አሳልፈው።

4 ቀጭኑን የክራባቱን ክፍል ይዘህ ቋጠሮውን ቀስ ብለህ አጥብቀው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ሸሚዝና ክራባት (እንግሊዝኛ) ከተባለ መጽሐፍ የተወሰደ።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክራባት አስተሳሰር ዓይነቶች ከ17ኛው መቶ ዓመት እስከ ዘመናችን