የልጆች አባት መሆን የወንድነት መለኪያ ነውን?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
የልጆች አባት መሆን የወንድነት መለኪያ ነውን?
“‘ከእከሊት ሴት ልጅ ወልጄአለሁ፤ ከእከሊት ደግሞ አንድ ወንድ ልጅ ወልጄአለሁ’ የሚሉ የማውቃቸው [ወንዶች] አሉ። ይህ አነጋገራቸው ልጅ መውለድ ስለሚያስከተለው ኃላፊነት ምንም ግድ እንደሌላቸው ያሳያል።”—ሃሮልድ
በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጃገረዶች ይጸንሳሉ። እነዚህ እናቶች የሚወልዷቸው አብዛኞቹ ልጆች ከትዳር ውጪ የሚወለዱ ናቸው። በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው የልጅ እናት ከሆኑት ከእነዚህ እናቶች መካከል ከአራቱ አንዷ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለተኛ ልጅ ትወልዳለች። አትላንቲክ መንዝሊ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ሁኔታው በዚህ መልኩ ከቀጠለ በዛሬው ጊዜ ከሚወለዱት ልጆች መካከል በወላጅ እናታቸውና አባታቸው እንክብካቤ የማደግ አጋጣሚ የሚያገኙት ከግማሽ ያነሱት ብቻ ይሆናሉ። አብዛኞቹ አሜሪካውያን ልጆች የሚያድጉት በነጠላ እናት በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ነው።”
ከሌሎች ያደጉ አገሮች አንጻር ሲታይ ዩናይትድ ስቴትስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ በሚጸንሱ ልጃገረዶች ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር ትያዝ እንጂ ከትዳር ውጭ መውለድ ዓለም ዓቀፍ ችግር ነው። እንደ እንግሊዝና ፈረንሳይ ባሉ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ከትዳር ውጪ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ ካለው አይተናነስም። በአንዳንድ የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ አገሮች በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የሚወልዱ ልጃገረዶች ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ ካለው ወደ ሁለት እጥፍ ይጠጋል። ይህን ችግር እያባባሰው ያለው ምንድን ነው?
ከችግሩ በስተጀርባ
ይህ ሁኔታ በአብዛኛው ያለንበት ‘አስጨናቂ ዘመን’ ምን ያህል በሥነ ምግባር እንዳዘቀጠ የሚያንጸባርቅ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ባለፉት አሥርተ ዓመታት የፍቺ ቁጥር እጅግ አሻቅቧል። ግብረ ሰዶምና ሌሎች የአኗኗር ዘይቤዎች ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው። ወጣቶች የመገናኛ ብዙኃን የፕሮፓጋንዳ ዒላማ ሆነዋል። የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሙዚቃዎችና የሙዚቃ ቪዲዮ ክሮች፣ ነውረኛ የመጽሔት ዓምዶችና ማስታወቂያዎች፣ ልቅ የጾታ ግንኙነትን የሚያወድሱ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ውርጅብኝ ይዘንብባቸዋል። ውርጃ የሚያስፈጽሙ ወገኖችና የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች እንደልብ የሚገኙ መሆናቸው የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምንም የሚያስከትለው መዘዝ የለም የሚለው እምነት በወጣቶች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስተዋጽዖ አድርጓል። አንድ ያላገባ አባት “እኔ የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንጂ የሚያስከትለውን ኃላፊነት መሸከም አልፈልግም” ብሏል። ሌላው ደግሞ “የጾታ ግንኙነት መዝናኛ ነው” በማለት ተናግሯል።
እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በእጅጉ ተቀባይነት ያገኘው በተለይ በድኻ ወጣቶች ዘንድ ሳይሆን አይቀርም። ጥናት የሚያካሂዱት ኢላይጃ አንደርሰን በመሃል ከተማ
ለሚኖሩ ወጣቶች ቃለ መጠይቅ ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ብዙ ወንዶች ልጆች የጾታ ግንኙነት መፈጸም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚያሳይ ትልቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። የጾታ ግንኙነት መፈጸምን እንደ ትልቅ ጀብዱ ይቆጥሩታል።” በእርግጥም አንድ ያላገባ ወጣት አባት ለንቁ! መጽሔት ሲናገር የጾታ ግንኙነት መፈጸም በአብዛኛው “በክብር እንደሚቀመጥ የዋንጫ ሽልማት” ተደርጎ ይታያል ብሏል። እንዲህ ዓይነት ደንዳና አስተሳሰብ እንዲኖር ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? አንደርሰን ስለሁኔታው ሲገልጹ አብዛኛውን ጊዜ በመሃል ከተማ በሚኖር አንድ ወጣት ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዙት “እኩዮቹ የሆኑ ጓደኞቹ ናቸው። ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት እንደሚገባው መስፈርት የሚያወጡለት እነሱ ናቸው፤ እርሱም እነሱ ባወጡለት በዚያ መስፈርት መሠረት መመራት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ ያስባል።”አንደርሰን እንደተናገሩት ብዙ ወጣት ወንዶች የጾታ ግንኙነት መፈጸምን ከጨዋታ ለይተው አያዩትም፤ “ሌላውን ሰው በተለይ ደግሞ ወጣት ልጃገረዶችን ማታለል መቻል ለእነሱ ጨዋታ ነው።” አክለው ሲናገሩ “ጨዋታው አለባበሱን፣ የፀጉር አበጣጠሩን፣ ቁመናውን፣ የዳንስ ችሎታውንና አነጋገሩን ጨምሮ ልጁ ራሱን የሚያቀርብበትን ሁኔታ ያካትታል።” ብዙ ወጣት ወንዶች “በጨዋታው” አሸናፊ በመሆን ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። ይሁን እንጂ “ልጅቷ በጸነሰች ጊዜ ልጁ ከእርሷ ገሸሽ ይላል” በማለት አንደርሰን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።—ያንግ አንዌድ ፋዘርስ—ቼንጂንግ ሮልስ ኤንድ ኢመርጂንግ ፖሊሲስ በሮበርት ለርማን እና ቲዮዶራ ኡምስ የተዘጋጀ።
የአምላክ አመለካከት
ይሁንና ልጅ መውለድ በእርግጥ የወንድነት መለኪያ ነውን? የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንዲያው ጨዋታ ነውን? በፈጣሪያችን በይሖዋ አምላክ አመለካከት እንደ ጨዋታ የሚታይ ነገር አይደለም። አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጾታ ግንኙነት ትልቅ ዓላማ እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አፈጣጠር ከተናገረ በኋላ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” (ዘፍጥረት 1:27, 28) አምላክ ልጆች ያለ አባት እንዲቀሩ ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ቋሚ በሆነ የጋብቻ ሰንሰለት አጣመራቸው። (ዘፍጥረት 2:24) በመሆኑም የአምላክ ፈቃድ እያንዳንዱ ልጅ አባትም እናትም እንዲኖረው ነበር።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዶች ብዙ ሚስቶችን ማግባት ጀመሩ። (ዘፍጥረት 4:19) ዘፍጥረት 6:2 አንዳንድ መላእክታዊ ፍጥረታት እንኳን ‘የሰው ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ’ ሲል ይነግረናል። እነዚህ መላእክት እንደ ሰው ሥጋ ከለበሱ በኋላ ተስገብግበው “ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የኖኅ የጥፋት ውኃ እነዚህ አጋንንት ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንዲመለሱ አስገደዳቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ አጋንንት በምድር አካባቢ ብቻ ተወስነው እንዳሉ ይጠቁማል። (ራእይ 12:9-12) ስለሆነም ሰይጣንና አጋንንቱ በዛሬው ጊዜ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። (ኤፌሶን 2:2) ወጣት ወንዶች የማይፈለጉና የማይወደዱ ልጆችን ሲወልዱ ሳያውቁት ለዚህ ክፉ ተጽእኖ እየተንበረከኩ ነው።
ስለሆነም ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚከተለው በማለት የሚናገሩት አለ ምክንያት አይደለም:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው። ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር ጠብቆ መያዝን ይወቅ። እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አረማውያን የፍትወት ምኞት አይኑረው። በዚህ ነገር ማንም ወንድሙን አይበድል፣ ወይም አያታልል፤ ከዚህ በፊት እንደነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ፣ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል።”—1 ተሰሎንቄ 4:3-6 የ1980 ትርጉም
‘ከዝሙት ራቁ’? ብዙ ወጣት ወንዶች በዚህ አባባል ያፌዙ ይሆናል። ደግሞም ወጣት እንደመሆናቸው መጠን ስሜታቸው ኃይለኛ ነው! ይሁን እንጂ ዝሙት መፈጸም ሌሎችን ‘መበደል እና ማታለል’ እንደሆነ ልብ ማለት ይገባቸዋል። አንዲትን ልጃገረድ ዲቃላ አስታቅፎ ያለባል እርዳታ መተው በደል አይደለምን? እንደ ቂጥኝ፣ ጨብጥ ወይም ደግሞ ኤድስ የመሳሰሉ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች ቢይዟትስ? እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ከእንዲህ ዓይነት በሽታዎች መጠንቀቅ ይቻል ይሆናል። ቢሆንም ከጋብቻ በፊት የሚደረገው የጾታ ግንኙነት ልጅቷ ክብረ ንጽህናዋን እንደጠበቀች ትዳር ለመያዝ ያላትን መብት የሚያሳጣ ይሆናል። ስለዚህ ከዝሙት መራቅ የአስተዋይነትና የጉልምስና ምልክት ነው። ‘የገዛ ሰውነትን በቅድስና መያዝና’ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ ራስ ኢሳይያስ 48:17, 18 እንደሚነግረን አምላክ ባወጣቸው ሕጎች አማካኝነት ‘የሚረባንን እያስተማረን’ ነው።
መግዛትንና ቆራጥነትን እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ይሁንና“ወንድ ሁኑ”
ይሁንና አንድ ወጣት በእርግጥ ወንድ መሆኑን ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? ዲቃላ ልጆችን በመውለድ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት አጥብቆ ያሳስባል:- “ንቁ፣ በሃይማኖት ቁሙ፣ ጎልምሱ [“እንደ ወንድ ሁኑ፣ NW ] ጠንክሩ። በእናንተ በኩል ሁሉ በፍቅር ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 16:13, 14
‘እንደ ወንድ መሆን’ ማለት ንቁ መሆንን፣ በእምነት መጠንከርን፣ ደፋርና አፍቃሪ መሆንን እንደሚጨምር ልብ በል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በእኩል ደረጃ እንደሚሠሩ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉትን መንፈሳዊ ባሕርያት የምታፈራ ከሆነ ሰዎች በእውነተኛ ወንድነትህ ሊያከብሩህና ሊያደንቁህ ይነሳሳሉ! እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። ድብደባ አልፎ ተርፎም ሞት ከፊቱ በተጋረጠበት ጊዜ እንኳ ያሳየውን የወንድነት ጥንካሬና ድፍረቱን አስብ። ይሁንና ኢየሱስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚሆንበት ጊዜ የተመላለሰው እንዴት ነበር?
እርግጥ ነው ኢየሱስ ከሴቶች ጋር የሚውልበት አጋጣሚ ነበረው። ብዙ ሴት ተከታዮች ነበሩት፤ አንዳንዶቹ እርሱንና ደቀ መዛሙርቱን ‘በገንዘባቸው ያገለግሏቸው ነበር።’ (ሉቃስ 8:3) በተለይ ደግሞ ከሁለቱ የአልዓዛር እህቶች ጋር ይቀራረብ ነበር። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢየሱስ ማርታንና እኅትዋን ይወድ ነበር’ ሲል ይናገራል። (ዮሐንስ 11:5) ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን የነበረውን ችሎታ፣ ደምግባት ወይም የሚስብ ቁመና እነዚህን ሴቶች አባብሎ ብልግና እንዲፈጽሙ ለማድረግ ተጠቅሞበታልን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ኃጢአት አላደረገም” በማለት ሐቁን አስቀምጦታል። (1 ጴጥሮስ 2:22) በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ ምናልባትም ሴተኛ አዳሪ የነበረች አንዲት ሴት ‘እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ስታርስ፣ በራስ ጠጉርዋም ስታብሰው እግሩንም ስትስመው ሽቱም ስትቀባው’ እንኳን ኢየሱስ ተገቢ ያልሆነ ፀባይ አላሳየም። (ሉቃስ 7:37, 38) ከሴትየዋ ሁኔታ አንጻር ኢየሱስ በቀላሉ የፈለገውን ነገር ሊያደርግባት ይችል የነበረ ቢሆንም እንዲህ የማድረጉ ሐሳብ እንኳ ጨርሶ ወደ አእምሮው አልመጣም! የእውነተኛ ወንድነት መለያ የሆነው ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ እንደነበረው አስመስክሯል። ሴቶችን ወሲባዊ እርካታ እንደሚሰጥ ዕቃ ሳይሆን ፍቅርና አክብሮት ሊቸራቸው እንደሚገባ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር።
ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ የአንዳንድ እኩዮችህን ሳይሆን የክርስቶስን ምሳሌ ከተከተልክ ሌሎችን ‘ከመበደልና ከማታለል’ ይጠብቅሃል። እንዲሁም ዲቃላ በመውለድህ ምክንያት ከሚከተለው አሳዛኝ መከራ ይጠብቅሃል። እርግጥ ነው ከዝሙት ስትርቅ ሌሎች መቀለጃ ሊያደርጉህ ይችላሉ። ሆኖም የአምላክን ሞገስ ማግኘትህ በእኩዮችህ ዘንድ ልታገኘው ከምትችለው ጊዜያዊ ተቀባይነት የላቀ ጥቅም ያስገኝልሃል።—ምሳሌ 27:11
ይሁን እንጂ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ሲመራ የቆየ አንድ ወጣት ከክፉ መንገዱ ቢመለስና ከልብ ንስሐ ቢገባስ? እንዲያ ከሆነ የጾታ ብልግና ፈጽሞ እንደነበረውና ከዚያም ንስሐ እንደገባው እንደ ንጉሥ ዳዊት የአምላክን ይቅርታ እንደሚያገኝ እርግጠኛ መሆን ይችላል። (2 ሳሙኤል 11:2-5፤ 12:13፤ መዝሙር 51:1, 2) ሆኖም ከጋብቻ ውጪ ልጅ ከተጸነሰ ወጣቱ ልጅ ከባድ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበት ይሆናል። ልጅቷን ማግባት ይኖርበታልን? ልጁን በመንከባከብ ረገድ ኃላፊነት ይኖርበት ይሆን? ወደፊት የሚወጣው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምንም መዘዝ አያስከትልም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አላቸው