ላሞች ለዕረፍት ሲሄዱ!
ላሞች ለዕረፍት ሲሄዱ!
ስዊዘርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
የስዊዘርላንድ ላሞች በየዓመቱ ለዕረፍት እንደሚሄዱ ከዚህ ቀደም ታውቅ ነበር? ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት አያስቸግርህም!
የስዊዘርላንድ ላሞች በረዶና ቅዝቃዜ ያለበትን የክረምቱን ወራት የሚያሳልፉት በበረታቸው ውስጥ ተዘግተው ነው። ክረምቱ አልፎ የጸደይ ወር ሲመጣ ላሞቹ ወደ ውጭ ወጥተው ፍንትው ብለው የበቀሉ አበቦች ባሸበረቁት ለምለም መስክ ላይ ተሰማርተው ማየት በጣም ደስ ይላል። እየዘለሉ ሲቦርቁ ላያቸው በወቅቱና በሁኔታዎቹ መለወጥ የተሰማቸውን ደስታ የሚገልጹ ይመስላሉ።
በግንቦት ወይም ሰኔ መግቢያ ላይ ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ያለው በረዶ ሲቀልጥ ተጨማሪ የግጦሽ መስክ ይገኛል። በዚህ ጊዜ የበጋውን ወቅት በዚያ እንዲያሳልፉ ከብቶቹ ወደ ተራራማ አካባቢዎች ይወሰዳሉ።
ውኃ እንደ ልብ የሚገኝበት የግጦሽ መስክ
በስዊዘርላንድ በተራራማ አካባቢዎች 10, 000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ወደ 10, 000 የሚጠጉ የግጦሽ መስኮች ይገኛሉ። ይህም ከጠቅላላው የአገሪቱ መሬት አንድ አራተኛውን ይሸፍናል ማለት ነው። በመሆኑም ይህን ጠቃሚ የተፈጥሮ ሃብት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል።
ሰውና እንስሳ ተባብረው በከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኙ መስኮችን ከቁጥቋጦዎችና ከጥሻዎች ይጠብቃሉ። ለዚህም ሥራ ገበሬዎች ወደ 500, 000 የሚጠጉ ከብቶችን ለእረኞች ይሰጣሉ። ጊደሮችን ጨምሮ የወተት ላሞች በጭነት መኪናዎች ወይም በባቡር ላይ ተጭነው የዕረፍት ጊዜያቸውን በተራራማዎቹ መስኮች ላይ እንዲያሳልፉ ይወሰዳሉ።
የመኪና መንገዶቹና የባቡር ሐዲዶቹ እስከ ተራራው ጫፍ ድረስ ስለማይወጡ ወደ መጨረሻው አካባቢ የእግር ጉዞ ማድረግ ግድ ነው። የበጋው ወቅት እየገፋ ሲሄድ መንጎቹ ከፍ ወዳለው ቦታ መሄዳቸውን ይቀጥላሉ። ከባሕር ወለል በላይ 2, 000 እና 2, 200 ሜትር በሚደርስ ከፍታ ላይ ከብቶቹ ለምለም ሳሮችንና በተለያየ ዓይነት ቀለማት ያሸበረቁ አበቦችን ያገኛሉ። ከተራራ የሚፈልቁ በርካታ ምንጮች ስላሉ ለመጠጥ የሚሆን የውኃ ችግር አይገጥማቸውም።
ላሞቹ የሚሰጡት ግሩም ወተት አንዳንድ ጊዜ ከተራራው በታች ይወሰድና ለመጠጥ ወይም ለሌላ ተግባር ይውላል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እዚያው በተራራው ጥግ በሚገኙ ጎጆ ቤቶች ውስጥ ቅቤ ወይም አይብ ይሠራባቸዋል። የበጋው ወቅት እየተገባደደ ሲሄድ መንጎቹ ዝቅተኛ ቦታ ላይ ወደሚገኙ የግጦሽ መስኮች ይወሰዳሉ። በመጨረሻም እንደ አየሩ ጠባይ ቢለያይም ብዙውን ጊዜ መስከረም መጨረሻ አካባቢ መንጎቹ የክረምቱን ወቅት ወደሚያሳልፉበት መንደር ተመልሰው የሚሄዱበት ቀን ይመጣል። አዎን፣ የበጋ ዕረፍታቸው የሚያበቃበት ጊዜ ተቃርቧል! ሆኖም በመጀመሪያ አንድ ልዩ የሰልፍ ጉዞ ይደረጋል።
አንድ ልዩ ቀን!
የምርቱ ውጤት ስለሚመዘገብ በሰጡት ከፍተኛ የወተት ምርት መሠረት ከሁሉም በልጠው የተገኙት ላሞች ይጌጣሉ። ከፍተኛ ወተት በመስጠት አንደኛ የወጣችው ላም ወደ ቤት በሚያመራው ጉዞ ሰልፉን እንድትመራ ትደረጋለች። የላሞቹን ራሶች ከወረቀት በተሠሩ በሚያማምሩ አበቦች፣ በሪባኖችና በጥድ ቅርንጫፎች ያስጌጧቸዋል። በብዙዎቹ ላሞች አንገት ላይ የሚንጠለጠለው ቃጭል ከእረፍት መመለሳቸውን ገና ከሩቅ ያበስራል።
እረኞቹ ነጭ ሸሚዝና በጥቁር ክር የተጠለፉ የሐር ካባዎች ለብሰው ለወቅቱ የተለየ ድምቀት ይሰጡታል። በዚህ ወቅት በሸለቆው ሥር የሚኖሩት ገበሬዎች ሰልፈኞቹን በታላቅ ጭብጨባ ለመቀበል በመንገዱ ግራና ቀኝ ቆመው ይጠባበቃሉ።
ከብቶቹ እዚያ ሲደርሱ ቀጣዩን የክረምት ወቅት እንዲያሳልፉ ለየባለቤቶቻቸው ይሰጣሉ። ሆኖም ለእረፍት ወደ ተራራማው አካባቢ የሚሄዱበት ጊዜ ወዲያው ይደርሳል! እንዴት የሚያስደስት ነው!
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]