በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት እየረከሰ መጥቷልን?

ሕይወት እየረከሰ መጥቷልን?

ሕይወት እየረከሰ መጥቷልን?

“ሕይወት ርካሽ የሆነበት ዓለም ነው። ሞትን በጥቂት ብሮች መግዛት የሚቻል ከመሆኑም በላይ ለመሸጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማግኘቱም በጣም ቀላል ሆኗል።”​—⁠ዘ ስኮትስማን

በሚያዝያ 1999 ሁለት ጎረምሶች በዩናይትድ ስቴትስ፣ ሊትልተን፣ ኮሎራዶ በሚገኘው ኮሎምቢን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥቃት ፈጽመው 15 ሰዎች በመግደላቸው መላው ዓለም ተደናግጦ ነበር። ጥቃቱን ከፈጸሙት ወጣቶች መካከል አንደኛው የራሱ የኢንተርኔት ገጽ እንዳለውና በዚህ ገጹ ላይ “የሞቱ ሰዎች አይጨቃጨቁም!” የሚል ጽሑፍ አስፍሮ እንደነበር በምርመራ ወቅት ሊታወቅ ችሏል። ሁለቱም ወጣቶች በዚሁ ጊዜ ሞተዋል።

ግድያ በየትም አካባቢ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች በየዕለቱ ይገደላሉ። በዚህ ረገድ የአንደኛነቱን ቦታ የያዘችው ደቡብ አፍሪካ ስትሆን በ1995 ከ100, 000 ነዋሪዎቿ መካከል 75ቱ ተገድለዋል። በአንድ የደቡብ አሜሪካ አገር ሕይወት በጣም ከመርከሱ የተነሳ በ1997 ከ6, 000 የሚበልጡ ሰዎች በፖለቲካ ምክንያት ተገድለዋል። የቅጥር ነፍስ ግድያ የተለመደ ነገር ሆኗል። ስለዚሁ አገር የተጠናቀረ አንድ ሪፖርት “በልጆች ላይ የሚፈጸም ግድያ በሚያስደነግጥ መጠን ጨምሯል። በ1996 የተገደሉት ልጆች ቁጥር 4, 322 ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል” በማለት ይገልጻል። ይሁን እንጂ ልጆችም ራሳቸው ሌሎች ልጆችንና የገዛ ወላጆቻቸውን ይገድላሉ። በእርግጥም ሕይወት ረክሷል።

“የግድያ ባሕል” የተስፋፋው ለምንድን ነው?

እነዚህ ሁሉ መረጃዎችና አኃዞች ምን ያመለክታሉ? ሰዎች ለሕይወት ያላቸው አክብሮት እየቀነሰ መሄዱን ያሳያሉ። የሥልጣን ጥመኞችና የገንዘብ ረሃብተኞች ሰዎችን ሲገድሉ ምንም ዓይነት የጸጸት ስሜት አይሰማቸውም። የዕፅ ቱጃሮች በትእዛዛቸው ሙሉ ቤተሰቦችን ያስገድላሉ። እንደ “መምታት፣” “ማስወገድ፣” “መመንጠር፣” ወይም “መጨረስ” ያሉትን ቃላት በመጠቀም የግድያ ድርጊታቸውን አስከፊነት ለመቀነስ ይሞክራሉ። ዘር የማጥፋትና ዘር የማጥራት ወንጀሎች በተገዳዮች ቁጥር ላይ የራሳቸውን ድርሻ ከማከላቸውም በላይ የሰብዓዊ ሕይወትን ዋጋ አራክሰዋል። በዚህም ምክንያት ግድያ በመላው ዓለም በሚገኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዕለታዊ ዜና ሆኗል።

በዚህ ሁሉ ላይ በቴሌቪዥን መስኮቶችና በፊልም መድረኮች ላይ ትልቅ ከበሬታ ተሰጥቶት የሚታየውን ዓመፅና ድብድብ ስንጨምር ኅብረተሰባችን ግድያን ማዕከል ባደረገ ብልሹ ባሕል እንደተዋጠ ያሳያል። በዚህ ረገድ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ የሚከተለውን ብሏል:- “በሃያኛው መቶ ዘመን የኋለኛው አጋማሽ ላይ ሞት በሚያስገርም ሁኔታ በብዛት የሚወሳ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። ከዚያ በፊት ግን በአብዛኛው ሳይንሳዊ ግፋ ቢል ደግሞ ፍልስፍናዊ ውይይቶች በሚደረጉባቸው አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ ርዕስ ነበር።” በካታሎንያ የሰብዓዊ ባሕል ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሴፕ ፌሪክግላ “ግድያ በማኅበረሰቦቻችን ዘንድ የመጨረሻ የተወገዘ ነገር መሆኑ ቀርቶ በጣም ውጤታማ የሆነ የሰዎችን አስተሳሰብ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ሆኗል።”

ምናልባት በመጀመሪያ ደረጃ ጉልህ ሆኖ የሚታየው የዚህ “የግድያ ባሕል” ባሕርይ ከሰብዓዊ ሕይወትና ከሥነ ምግባር እሴቶች የበለጠ ዋጋ ያለው ሥልጣን፣ የበላይነትና ገንዘብ ነው የሚለው እምነት ነው።

ይህ “የግድያ ባሕል” የተስፋፋው እንዴት ነው? ወላጆች ይህን ዙሪያቸውን የከበባቸውንና ልጆቻቸውን የሚነካ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቆጣጠር ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በሚቀጥሉት ርዕሶች እንደነዚህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሕይወት ዋጋው ምን ያህል ነው?

▪ “[ህንድ፣ ሙምባይ ውስጥ] የሚገኙ የወንጀለኛ ቡድን አባላት የሆኑ ወጣቶች ገንዘብ ለማግኘት ካላቸው ጉጉት የተነሳ 5, 000 ሩጲ [115 ዶላር] ለማግኘት ሲሉ የሰው ሕይወት ለማጥፋት ይዋዋላሉ።”​—⁠ፋር ኢስተርን ኢኮኖሚክ ረቪው

▪ “ሲጋራ ስጠኝ ሲለው እምቢ ያለውን አንድ መንገደኛ ገደለው።”​—⁠ሳንቲያጎ ቺሊ ውስጥ ላ ቴረሴራ ላይ የወጣ ርዕሰ ዜና

▪ “ሩስያ ውስጥ [በ1995] የግድያ ውል ለመዋዋል በአማካይ 7, 000 የአሜሪካ ዶላር ይጠየቅ ነበር። . . . በሩስያ የኮምኒስት ሥርዓት ከወደቀ በኋላ በታየው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ የግድያ ውል በእጅጉ ጨምሯል።”​—⁠ሮይተርስ ሞስኮ ኒውስ ን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ

▪ “በብሩክሊን አንድ የርስት ደላላ . . . ነፍሰ ጡር የሆነችውን ሚስቱንና እናቷን እንዲገድልለት ለአንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ወጣት ለመክፈል ከተዋዋለው 1, 500 ዶላር ውስጥ የተወሰነውን ከፍሏል በሚል ተወንጅሎ ተይዟል።”​—⁠ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ

▪ ‘እንግሊዝ ውስጥ ለግድያ የሚከፈለው ገንዘብ መጠን እያሽቆለቆለ ነው። ለእንዲህ ዓይነቱ ዓላማ የሚከፈለው ገንዘብ የዛሬ አምስት ዓመት 30, 000 ፓውንድ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ይህ የገንዘብ መጠን አሽቆልቁሎ ከ5, 000 እስከ 10, 000 ፓውንድ በመድረሱ የብዙዎችን አቅም የሚመጥን ሆኗል።’​—⁠ዘ ጋርዲያን

▪ ‘ማፊያ በባልካን አገሮች ከሚገኙ አረመኔ የሆኑ ወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር ከቁጥር የሚገባም አይደለም። እነዚህ አዲስ ደንብና አዳዲስ መሣሪያዎች ያሏቸው አዲስ ዓይነት ወንጀለኞች ናቸው። ቦምብና አውቶማቲክ ጠመንጃዎች የሚታጠቁ ከመሆኑም በላይ እነዚህን መሣሪያዎች ከመጠቀምም ወደኋላ አይሉም።’​—⁠ዘ ጋርዲያን ዊክሊ