በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መሞትሽ የማይቀር ነው!”

“መሞትሽ የማይቀር ነው!”

“መሞትሽ የማይቀር ነው!”

ሊአን ካርሊንስኪ እንደተናገረችው

ስፔይን ውስጥ ያለ ደም የሚሰጥ ከሁሉ የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

ዓለም ላይ የፈለጋችሁበት ቦታ መሄድ ብትችሉ የት መሄድ ትመርጡ ነበር? ይህ ለእኔ በቀላሉ ልመልሰው የምችለው ጥያቄ ነበር። በትምህርት ቤት ውስጥ የስፓንኛ አስተማሪ ስሆን ከባለቤቴ ከጄይ እና ከወንድ ልጄ ከጆየል ጋር በዩ ኤስ ኤ፣ ቨርጂኒያ፣ ጋላክ በሚገኘው በስፓንኛ በሚካሄድ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ እሳተፍ ነበር። ከዚህ የተነሳ ስፔይን የመሄድ ጉጉት ነበረኝ። ስለዚህ ወላጆቼ ወደዚያ ይዘውኝ ለመሄድ ሐሳብ ሲያቀርቡልኝ ምን ያህል እንደተደሰትኩ መገመት ትችላላችሁ! ምንም እንኳ ባለቤቴና ልጄ አብረውኝ መሄድ ሳይችሉ ቢቀሩም እኔና ወላጆቼ በቀጥታ ወደ ማድሪድ በሚያመራው አውሮፕላን ላይ ስንሳፈር ታላቁ ምኞቴ የሚፈጸምበት ጊዜ ተቃረበ። ሚያዝያ 21 ማድሪድ ስንደርስ በሰሜናዊው ስፔይን በናቫሬ ወደምትገኘው ኢስቴልያ ወደምትባል አንዲት ትንሽ መንደር በመኪና ለመሄድ መረጥን። ኋለኛው ወንበር ላይ ተደላድዬ ተቀመጥሁና ወዲያው እንቅልፍ አሸለበኝ።

ከዚህ በኋላ ትዝ የሚለኝ ነገር ቢኖር ፀሐይዋ ዓይኖቼ ላይ እያንጸባረቀች ሜዳ ላይ ተዘርግቼ የነበረበት ወቅት ነው። ‘የት ነው ያለሁት? እዚህ እንዴት መጣሁ? በሕልሜ ነው ወይስ በውኔ?’ እነዚህ ጥያቄዎች አእምሮዬ ውስጥ እየተጉላሉ ሳለ አንድ አስከፊ እውነታ ተገለጠልኝ። የሆነ አደጋ ደርሷል፤ ነገሩ ሕልም አልነበረም። የልብሴ የግራ እጅጌ ተቀዳዷል፤ እጆቼንም ሆነ እግሮቼን ማንቀሳቀስ አቃተኝ። መኪናችን መንገድ ዳር ተተክሎ የነበረውን የብረት መከላከያ ጥሶ ወጥቶ 20 ሜትር ቁልቁል እየተገለባበጠ ሲወርድ ከመኪናው ተወርውሬ መውጣቴን ከጊዜ በኋላ ተገነዘብኩ። ደስ የሚለው ነገር እኔም ሆንኩ ወላጆቼ አደጋውን በተመለከተ ምንም የምናስታውሰው ነገር አለመኖሩ ነው።

እርዳታ ለማግኘት ስጮህ የአንድ ትልቅ መኪና ሾፌር ሮጦ ደረሰልኝ። ከዚያም ከመንገዱ በታች ወርዶ ወላጆቼ መውጫ አጥተው ወዳሉበት ወደ መኪናው ሄደ። አብሮት ላለው ሰው “አንቡላንስ ጥራ! መኪናው ውስጥ ያሉት ሰዎች በጣም ተጎድተዋል!” ሲል ጮኾ ተናገረ። ከዚያም መንቀሳቀስ አቅቶኝ ተኝቼ ወዳለሁበት ወደ እኔ መጣና ለመርዳት በማሰብ እግሮቼን ለማቃናት ሞከረ። ከሥቃዩ የተነሳ በጣም ጮኽሁ፤ ክፉኛ መጎዳቴን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘብኩት በዚህ ጊዜ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ በሎግሮኖ ወደሚገኝ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተወሰድኩ። ፖሊሶች ያለሁበትን ቦታና ምን እንደደረሰብኝ በአካባቢው ላሉት የይሖዋ ምሥክሮች በመንገር ደግነት አደረጉልኝ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ያለውን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጨምሮ ከኢስቴልያ እና ከሎግሮኖ ጉባኤዎች ብዙዎች መጥተው አጠገቤ ሆኑ። በእርግጥም በዚህ ሆስፒታል በሥቃይ ላይ በነበርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ከዚህ በፊት ጨርሶ የማላውቃቸው ውድ ክርስቲያን ጓደኞቼ የሚያስፈልገኝን ነገር ለማሟላት ሌት ተቀን ደክመዋል። በተጨማሪም አደጋው ከደረሰ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ከሆስፒታል ለመውጣት በጥሩ ሁኔታ አገግመው ለነበሩት ለወላጆቼም ፍቅራዊ እንክብካቤ አድርገውላቸዋል።

ረቡዕ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ ላይ ዶክተሮች ዳሌዬ ላይ የደረሰብኝን ስብራት በቀዶ ሕክምና ለማስተካከል መጡ። ለዶክተሩ ደም መውሰድ እንደማልፈልግ ነገርኩት። * ምንም እንኳ ልሞት እንደምችል ቢነግረኝም በነገሩ እምብዛም ሳይደሰት ፍላጎቴን ለማክበር ተስማማ። ከቀዶ ሕክምናው በሕይወት ብተርፍም ቁስሉን አለማጽዳታቸውና ከጊዜ በኋላም ፋሻው አለመቀየሩ እንግዳ ነገር ሆነብኝ።

እስከ አርብ ባሉት ቀናት በደሜ ውስጥ ያለው የሄሞግሎቢን መጠን ወደ 4.7 ከመቀነሱም በላይ እየደከምኩም መጣሁ። ዶክተሩ የቀይ ደም ሕዋስ ግንባታ እንዲፋጠን የሚያደርግ ከብረትና ደም ከሚገነቡ ማጠናከሪያዎች ጋር ኢሪትሮፖይቲን (ኢ ፒ ኦ) የተባለ መድኃኒት በመርፌ በመስጠት አማራጭ ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነ። * በዚህ ጊዜ ጄይ እና ጆየል ከእኔ ጋር ነበሩ። በዚህ ወቅት ባለቤቴንና ልጄን በማየቴ በጣም ተደሰትኩ!

ከሌሊቱ 7:​30 ገደማ አንድ ዶክተር መጣና ሁኔታዬ እየተባባሰ ከሄደ ሆስፒታሉ ደም ለመስጠት የሚያስችል የፍርድ ቤት ትእዛዝ ማግኘቱን ለጄይ ነገረው። ጄይ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ብሆን ደም የመውሰድ ፍላጎት እንደሌለኝ ለዶክተሩ ነገረው። ከዚያም ዶክተሩ “እንደዚያ ከሆነማ ትሞታለች!” ሲል መለሰለት።

ጄይ ፍላጎቴን ሊያከብርልኝ ወደሚችል ወደ ሌላ ሆስፒታል እንድዘዋወር ከሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጋር ተነጋገረ። ሆኖም አቋሜን የሚቃወሙት በዚህ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩት ሁሉም አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል አንዲት ዶክተር ሙሉ በሙሉ ፍላጎቴ ተከብሮ ሕክምና እንዳገኝ የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ አረጋግጣልኛለች። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ዶክተሮች ጫና ይፈጥሩብኝ ጀመር። “ቤተሰቦችሽን ጥለሽ መሞት ትፈልጊያለሽ?” ሲሉ ጠየቁኝ። ያለ ደም የሚሰጥ ከሁሉ የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንደምፈልግ አረጋገጥኩላቸው። ዶክተሮቹ እኔን ለመርዳት አልተገፋፉም። አንደኛው “መሞትሽ የማይቀር ነው!” ሲል በድፍረት ነገረኝ።

የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴው ባርሴሎና ውስጥ ያለ ደም ሕክምና ሊሰጠኝ ፈቃደኛ የሆነ ሆስፒታል አገኘ። በሁለቱ ሆስፒታሎች መካከል እንዴት ያለ ትልቅ ልዩነት ነበር! ባርሴሎና በሚገኘው ሆስፒታል ሁለት ነርሶች ቀስ ብለው ገላዬን አጠቡኝና ቀለል እንዲለኝ ረዱኝ። ፋሻውን በሚቀይሩልኝ ጊዜ አንደኛዋ ነርስ ቁስሉ እንደበለዘና የረጋ ደም እንደተጋገረበት ተመለከተች። የአገሯ ሰዎች ባደረጉብኝ ነገር የተነሳ የሐፍረት ስሜት እንደተሰማት ተናገረች።

ሎግሮኖ በሚገኘው ሆስፒታል ሊጀመርልኝ ይገባ የነበረውን ሕክምና ወዲያውኑ ጀመሩልኝ። የተገኘው ውጤት አስገራሚ ነበር። በጥቂት ቀናት ውስጥ ተጎድተው የነበሩት የሰውነቴ ክፍሎች ተጠገኑ፤ የሄሞግሎቢኔ መጠን ደግሞ ወደ 7.3 ከፍ አለ። ሆስፒታሉን ለቅቄ ስወጣ 10.7 ደርሶ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተጨማሪ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በሄድኩበት ጊዜ የሄሞግሎቢኑ መጠን 11.9 ደርሶ ነበር።

ከእነሱ ሐሳብ ጋር ተስማሙም አልተስማሙ የታካሚዎቻቸውን ስሜት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የሆኑ ዶክተሮችና ነርሶች ለሚያደርጉት ጥረት አመስጋኝ ነኝ። የሆስፒታል ሠራተኞች ታካሚው ለሚያምንባቸው ነገሮች አክብሮት ሲያሳዩ ለሰውየው የሚያደርጉለት ሕክምና የተሟላ ይሆናል። እንዲህ በማድረግም ከሁሉ የተሻለ ሕክምና መስጠት ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ምክንያቶች የተነሳ ደም አይወስዱም።​—⁠ዘፍጥረት 9:​4፤ ዘሌዋውያን 7:​26, 27፤ 17:​10-14፤ ዘዳግም 12:​23-25፤ 15:​23፤ ሥራ 15:​20, 28, 29፤ 21:​25ን ተመልከት።

^ አን.9 አንድ ክርስቲያን ኢ ፒ ኦ መውሰድ አለመውሰዱ በግሉ የሚያደርገው ውሳኔ ነው።​—⁠የጥቅምት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴና ከልጄ ጋር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለት የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባላት