በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዘመናችን ያሉ የዋሻ ነዋሪዎች

በዘመናችን ያሉ የዋሻ ነዋሪዎች

በዘመናችን ያሉ የዋሻ ነዋሪዎች

በሌሶቶ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በዚህ በእኛ ዘመንም ዋሻ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ? በደቡባዊ አፍሪካ በንጉሣዊ መንግሥት በምትተዳደረው በተራራማዋ ሌሶቶ አንዳንድ የዋሻ ነዋሪዎች አሉ። ሃ ኮሜ የተባለው መንደራቸው የሌሶቶ ዋና ከተማ ከሆነችው ከማሴሩ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ግርማ ሞገስ በተላበሱት በማሉቲ ተራራዎች ግርጌ ይገኛል። በበጋ ወራት እነዚህ አቀበታማ አካባቢዎች በደማቅ ቀይ አበቦች ያሸበርቃሉ። የጋለ ብረት

በመባል የሚታወቁት እነዚህ የሚያማምሩ አበቦችና ልምላሜ የተላበሱት ዛፎች አካባቢውን ውበት ያጎናጽፉታል።

በዚያ የሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች የሚከተሉት በጣም ጥንታዊ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ነው። ቤቶቻቸውን የሚሠሩት በተራራው ቋጥኝ ሥር በሚገኙ ዋሻዎች ውስጥ ነው። የፊት ለፊቱ ወፍራም ግድግዳ የሚማገረው በጨፈቃና እንደ ሸምበቆ በመሳሰሉ ነገሮች ነው። ጭቃና እበት አንድ ላይ ይቦካና ግድግዳው ይመረጋል። ይህ ምርጊት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች በሚሆንበት የሌሶቶ ብርዳማ የክረምት ወቅት ከብርድ ይከላከላል። ቤቱ ውስጥ ከወለሉ ትንሽ ከፍ ተደርጎ የተሠራ እሳት የሚነድድበት ኢፎ (“ምድጃ”) የሚገኝ ሲሆን በብርድ ጊዜ እሳት አንድዶ ለመሞቅም ያገለግላል።

የቤቱ ጣሪያ፣ የኋለኛው ግድግዳና አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ጎንና ጎኑ የሚዋቀረው ከዋሻው አለት ነው። ጭቃና እበት አንድ ላይ ተቦክቶ የሚለቀለቅ ሲሆን በየዓመቱ በድጋሚ ይለቀለቃል። ይህ ደግሞ አለቱ እንዲያምርና እንዲለሰልስ ያደርገዋል። የላሞች ቁርበት ውስጡን ለማስጌጥ ከማገልገሉም በተጨማሪ መተኛም ይሆናል።

አንድ ምዕራባዊ ጎብኚ እንዲህ ዓይነቱ ለየት ያለ አኗኗር አስደሳች ይሆንለታል። ዥንጉርጉር ብርድ ልብስ ደረብ ማድረግና ሾጣጣ የስንደዶ ባርኔጣ ማድረግ በአካባቢው የተለመደ ነው። እረኞች አብዛኛውን ጊዜ ባዶ እግራቸውን ሆነው ከብቶች ሲያግዱ ይውላሉ። የመንደሩ ትላልቅ ወንዶች በበቆሎ ማሳቸው ውስጥ ሲሠሩ ወይም ሰብሰብ ብለው የደራ ጭውውት ይዘው ይታያሉ።

የዘመናዊው ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ሥራዎች አልፎ አልፎ በአካባቢው መታየት ጀምረዋል። አንዳንድ ጊዜ በሰማይ ላይ ሲበሩ በሚታዩት ትናንሽ አውሮፕላኖችና ከባድ ማርሽ ባላቸው መኪናዎች ወደ ዋሻዎቹ የሚመጡ እንግዶች ትንሽ ትልቅ ሳይል የሁሉንም የመንደሩን ነዋሪዎች ትኩረት የሚስቡ ናቸው። በአብዛኛው ምግባቸውን የሚያበስሉት ውጭ ሲሆን በሦስት ጉልቻ ላይ ጥቁር ብረት ድስት ጥደው ከሥር እሳት በማንደድ ነው። የማገዶ እንጨት እንደልብ ስለማይገኝ ኩበት፣ ሸምበቆ እንዲሁም ጭራሮ ያነዳሉ። እነዚህ የዋሻ ነዋሪዎች ከሚጠቀሙባቸው የቤት ዕቃዎቻቸው መካከል በቆሎ የሚፈጩበት ባሕላዊ የእጅ ወፍጮና ገንፎ የሚያገነፉበት የእንጨት ማማሰያ ይገኝበታል።

ሌሶቶ፣ የዱር ሰዎች በብዙ ዋሻዎች ውስጥና በመላው አገሪቱ በሚገኙ አለቶች ላይ በቀረጿቸው ሥዕሎች በጣም ትታወቃለች። በሃ ኮሜ በሚገኙ ዋሻዎች ውስጥ መኖር የጀመሩት የዱር ሰዎች ነበሩ። ሥዕሎቻቸው በታንኳና በመረብ ዓሣ ከሚያጠምዱት ሰዎች አንስቶ በአራዊት ምስል የተሠሩ ጭንብሎችን አጥልቀው እስከሚጨፍሩት ድረስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ናቸው። በተጨማሪም ዝንጀሮ፣ አንበሳ፣ ጉማሬና ድኩላ ተስለው ይታያሉ። በሃ ኮሜ ዋሻዎች ውስጥ የነበሩ አብዛኞቹ ሥዕሎች ጠፍተዋል። አሁን የቀረው የዱር ሰዎችን የሥዕል ጥበብ የሚያስታውስ ጥቂት ርዝራዥ ብቻ ነው።

አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ከሃ ኮሜ መንደር ብዙም በማይርቅ ቦታ ላይ የስብከት ሥራውን ያከናውናል። እነርሱም እንግዳ በማስተናገድ የሚታወቁትን እነዚህን የዋሻ ነዋሪዎች አልፎ አልፎ እየሄዱ ያነጋግራሉ። ብዙውን ጊዜ ሞቶሆ የሚባለውን የበቆሎ ገንፎ በጎድጓዳ ሳህን አቅርበው ያስተናግዷቸዋል። በሃ ኮሜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሲሰጣቸው በደስታ ይቀበላሉ። ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት የማስተማር ሥራ ድጋፍ ለመስጠት አትክልት፣ እንቁላልና ሌላም ነገር በመለገስ ጽሑፍ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ።

በዘመናችን ያሉ የዋሻ ነዋሪዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ያላቸው ሲሆን ስለ ሕይወት፣ ስለ ሞትና ስለሚከተሏቸው ባሕላዊ እምነቶች የተለያዩ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይወዳሉ። በአካባቢው በቅንዓት በማገልገል ላይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አግኝተዋል። በዚህ መንገድ የእውነት ዘር በእነዚህ ትሁት ሰዎች ልብ ውስጥ ሥር በመስደድ ላይ ይገኛል።​—⁠ማቴዎስ 13:​8

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሃ ኮሜ