በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በየቀኑ አስፕሪን ልውሰድ ወይስ አልውሰድ?

በየቀኑ አስፕሪን ልውሰድ ወይስ አልውሰድ?

በየቀኑ አስፕሪን ልውሰድ ወይስ አልውሰድ?

የሚከተለው አንድ ሐኪም የተናገረው እውነተኛ ታሪክ ነው። ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም አሳዛኝ ችግር ነው።

መላው ቤተሰብ ተጨንቋል። ሐኪሙን ሳይቀር በጣም አስጨንቆታል። “ደሙ በአፋጣኝ ካልቆመ ደም መስጠት ሳይኖርብን አይቀርም” በማለት ሐኪሙ ተናገረ።

በሽተኛው ሆድ ዕቃው በመድማቱ ምክንያት ደም ሲፈሰው በርካታ ሳምንታት ሆኖታል። ችግሩ የጨጓራ ብግነት እንደሆነ ተነግሮታል። ተስፋ የቆረጠው ሐኪም “ምንም ዓይነት መድኃኒት እንዳልወሰድክ እርግጠኛ ነህ?” በማለት ጠየቀው።

“ምንም መድኃኒት አልወሰድኩም። ብቻ አርተራይትስ ስላለብኝ ይህን የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልገውን መድኃኒት እወስዳለሁ” በማለት መለሰለት።

ሐኪሙ ወዲያው ጆሮዎቹን ቆም አደረገ። “እስቲ ልየው” አለ። መድኃኒቱ ከምን እንደተቀመመ የሚያሳየውን መግለጫ በጥንቃቄ ተመለከተና የሚፈልገውን ነገር አገኘ። አሴቲልሳልሲሊክ አሲድ አለበት! የችግሩ ቁልፍ ተገኘ። በሽተኛው አስፕሪን የሚገኝበትን መድኃኒት መውሰድ አቁሞ ጨጓራ የሚያድን መድኃኒትና ብረት ሲሰጠው ደሙ መፍሰሱን አቆመ። የደም ሴሎቹ ቁጥርም ቀስ በቀስ ወደ መደበኛው መጠን ተመለሰ።

በመድኃኒት ምክንያት የሚከሰት መድማት

ዛሬ በመድኃኒት ምክንያት የሚከሰት የጨጓራና የአንጀት መድማት ከባድ የጤና እክል ሆኗል። ለዚህ ችግር በምክንያትነት የሚጠቀሱ ብዙ መድኃኒቶች ቢኖሩም ዋነኞቹ ለአርተራይትስና ለሌሎች የሕመም ስሜቶች ማስታገሻነት የሚወሰዱ መድኃኒቶች ናቸው። ነንስቴሮይዳል አንቲ ኢንፍላማቶሪ ድራግስ ወይም (NSAIDS) በሚባል የቡድን ስም የሚጠሩ መድኃኒቶች ከእነዚህ የሚካተቱ ናቸው። ስሞቹ እንደየአገሩ ሊለያዩ ይችላሉ።

አስፕሪን ብዙውን ጊዜ ያለ ሐኪም ትእዛዝ ከሚወሰዱ መድኃኒቶች መካከል የሚገኝ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየቀኑ አስፕሪን የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። ለምን?

አስፕሪን ያገኘው ተወዳጅነት

በ1995 ሃርቫርድ ሄልዝ ሌተር “አስፕሪን አዘውትሮ መውሰድ ሕይወት ያድናል” የሚል ጽሑፍ አወጣ። ተመራማሪዎች ከዚያ ወዲህ የተደጋገሙ በርካታ ጥናቶችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማጣቀስ “የልብ ድካም ወይም የደም በአንጎል ውስጥ መፍሰስ አጋጥሞት የሚያውቅ ወይም አንጃይና የተባለ የልብ በሽታ ያለበት ወይም የልብ ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ሰው ለመድኃኒቱ አለርጂክ ካልሆነ በቀን ከግማሽ እስከ አንድ ሙሉ የአስፕሪን እንክብል መውሰድ አለበት” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። *

ሌሎች ተመራማሪዎችም በልብ ድካም የመያዝ አዝማሚያ የሚታይባቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶችና ተመሳሳይ አዝማሚያ የሚታይባቸው ሴቶች አስፕሪን ቢወስዱ እንደሚጠቅማቸው ይናገራሉ። ከዚህም በላይ በየቀኑ አስፕሪን መውሰድ በደንዳኔ አንጀት ካንሰር የመያዝን አጋጣሚ እንደሚቀንስና የስኳር በሽተኞች በርከት ያለ አስፕሪን ለረዥም ጊዜ ቢወስዱ በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ስኳር እንደሚቀንስ የሚያመለክቱ ጥናቶች አሉ።

አስፕሪን እነዚህን ያስገኛል የሚባልለትን ጥቅሞች የሚያስገኘው እንዴት ነው? ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም አስፕሪን አርጊ ሕዋሰ ደም (platelets) የሚባሉት በደም ውስጥ የሚገኙ ሕዋሳት የማጣበቅ ባሕርያቸው እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ደም እንዳይረጋ በማድረጉ እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። ይህም ወደ ልብና አንጎል የሚሄዱ ትናንሽ ደም ቅዳ ቧንቧዎች እንዳይዘጉ ስለሚረዳ በዋነኞቹ አባላካላት (organs) ላይ አደጋ እንዳይደርስ ይከላከላል።

አስፕሪን ይህን የሚያክል ጥቅም አለው ከተባለ ሁሉም ሰው ቢወስደው ጉዳቱ ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ገና ያልታወቁ ብዙ ነገሮች አሉ። ምን ያህል መጠን ቢወስድ ጥሩ እንደሚሆን እንኳን ገና ግልጽ አልሆነም። በቀን ሁለት ጊዜ መደበኛ እንክብል ከመውሰድ አንስቶ በየሁለት ቀኑ አንዴ አንድ የሕፃን አስፕሪን እስከ መውሰድ የተለያየ ምክር ይሰጣል። ሴቶች የሚወስዱት መጠን ከወንዶች የተለየ መሆን አለበት? ሐኪሞች እርግጠኛ አይደሉም። ባለ ሽፋን (enteric-coated ) አስፕሪን የተሻለ እንደሆነ ይነገራል፤ አሲዱ የወጣለት አስፕሪን በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ግን ሙሉ ስምምነት ላይ አልተደረሰም።

መጠንቀቅ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

አስፕሪን የአሜሪካ ሕንዶች ከአኻያ ዛፍ ቅርፊት ላይ ያገኙት የተፈጥሮ ቅመም ቢሆንም ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት። በአንዳንድ ሰዎች ላይ የመድማት ችግር የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ አለርጂክ መሆንን ጨምሮ ሌሎች ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ሁሉም ሰው በየቀኑ አስፕሪን መውሰድ እንደማይችል ግልጽ ነው።

በልብ ድካም የመያዝ ወይም በጭንቅላት ውስጥ ደም የመፍሰስ አዝማሚያ የሚታይበት ሰው ግን በየቀኑ አስፕሪን መውሰድ ስለሚያመጣው ጥቅምና ጉዳት ሐኪሙን ማማከር ሊፈልግ ይችላል። በሽተኛው የመድማት እክል እንደሌለበት፣ ለአስፕሪን አለርጂክ እንዳልሆነና የጨጓራ ወይም የአንጀት ችግር እንደሌለበት ማረጋገጥ ይኖርበታል። ሕክምናውን ከመጀመሩ በፊት ሌሎች ችግሮች ሊያስከትልበት ይችል እንደሆነና ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ይጋጭ እንደሆነ ማጣራት አለበት።

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አስፕሪንና አስፕሪን መሰል መድኃኒቶች የማድማት ባሕርይ አላቸው። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው መድማት ወዲያው የማይታወቅ ሊሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሊሄድ ይችላል። በሌሎች መድኃኒቶች ረገድም በተለይ ሥቃይ በሚያስታግሱ መድኃኒቶች ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደነዚህ ያሉትን መድኃኒቶች የምትወስድ ከሆነ ለሐኪምህ መናገር አለብህ። አብዛኛውን ጊዜ የቀዶ ሕክምና ከማድረግህ በፊት ብታቋርጥ ጥሩ ይሆናል። በየጊዜው የደም ምርመራ ማድረግም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ወደፊት ሊያጋጥሙን ከሚችሉ ችግሮች ራሳችንን ብንጠብቅ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ተከተልን ማለት ነው። (ምሳሌ 22:​3) በዚህ የሕክምና ረገድም ጉዳት እንዳይደርስብን ብልህ ሰዎች ሆነን እንገኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ንቁ ! አንደኛውን የሕክምና ዓይነት ከሌላው ይሻላል የሚል ምክር አይሰጥም።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በየቀኑ አስፕሪን ስለመውሰድ እነማን ሊያስቡ ይችላሉ?

● የልብ በሽታ ያለባቸው ወይም ካሮቲድ (በአንገት ላይ የሚገኙ ዋነኛ የደም ስሮች) የሚባሉት ደም ቅዳ ቧንቧዎች የጠበቡባቸው

● በደም ሥራቸው ውስጥ ደም የመርጋት ችግር የገጠማቸው (በአንጎል ውስጥ እንደሚያጋጥመው) ወይም ደም ወደ ሰውነት ክፍል መድረስ በሚሳነው ጊዜ የሚያጋጥም ተመላላሽ ችግር ያለባቸው

● እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን፣ ዝቅተኛ የኤች ዲ ኤል ኮሌስትሮል መጠን፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ከባድ የአልኮል ጠጪ መሆን፣ የልብ በሽታ ወይም በቤተሰብ ታሪክ ውስጥ ደም አንጎል ውስጥ የመፍሰስ አደጋ የደረሰበት (ከ55 ዓመት በፊት የልብ ድካም የገጠማቸው) ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ ያሉ ለልብ በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ያሉባቸው ወይም ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች

● ከእነዚህ ሁኔታዎች ሁለትና ከሁለት በላይ ያሉባቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች

በዚህ ጉዳይ ላይ ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ሐኪምህን ለማማከር ትፈልግ ይሆናል

[ምንጭ]

ምንጭ:- Consumer Reports on Health