በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኃላፊነት የሚሸሹ አባቶች—በእርግጥ ከኃላፊነት ያመልጡ ይሆን?

ከኃላፊነት የሚሸሹ አባቶች—በእርግጥ ከኃላፊነት ያመልጡ ይሆን?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ከኃላፊነት የሚሸሹ አባቶች​—⁠በእርግጥ ከኃላፊነት ያመልጡ ይሆን?

“‘ጸንሼልሃለሁ’ ስትለኝ ክው ብዬ ቀረሁ። ልጁን ማን ሊያሳድግ ነው? እኔ እንደሆንኩ ቤተሰብ የማስተዳድርበት አቅም የለኝም። ስለዚህ ምንም ላደርግ አልችልም።”​—⁠ጂም *

“በየዓመቱ ቁጥራቸው ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሴቶች . . . ይጸንሳሉ” ይላል ከአለን ጉትማከር ተቋም የወጣ አንድ ሪፖርት። ከእነዚህ መካከል “78 በመቶ የሚያክሉት የሚወልዱት ከትዳር ውጪ ነው።”

ድሮ ድሮ ወንዶች የወለዷቸውን ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። ሆኖም ቲንኤጅ ፋዘርስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው “ከትዳር ውጪ መጸነስ [እንደ ዱሮው] እንደ አሳፋሪ ድርጊትና ውርደት መታየቱ ቀርቷል።” እንዲያውም በአንዳንድ ማኅበረሰብ ወጣቶች ዘንድ የልጅ አባት መሆን እንደ ትልቅ ክብር ሊታይ ይችላል! ያም ሆኖ ግን የወለዷቸውን ልጆች ለማሳደግ የገቡትን ቃል የማያጥፉት ጥቂት ወጣት ወንዶች ብቻ ናቸው። ብዙዎቹ ግን ውሎ አድሮ ጀርባቸውን ይሰጣሉ። *

ይሁን እንጂ አንድ ወጣት የፈጸመው የሥነ ምግባር ብልግና ከሚያስከትልበት መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ከሆነ አይችልም። እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።” (ገላትያ 6:​7) ወደፊት እንደምናየው የጾታ ብልግና መፈጸም ብዙውን ጊዜ በወጣት ወንዶችም ሆነ ሴቶች ላይ የዕድሜ ልክ መዘዝ ያስከትላል። ወጣቶች የጾታ ብልግና ከመፈጸም ስለመራቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ግልጽና የማያሻማ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከሚያስከትላቸው መዘዞች ሊርቁ ይችላሉ።

ጥሎ መሄድ​—⁠እንዲህ ቀላል አይደለም

ልጅ ማሳደግ ጊዜን፣ ገንዘብንና የግል ነፃነትን በእጅጉ መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ያንግ አንዌድ ፋዘርስ የተባለው መጽሐፍ አስተያየት ሲሰጥ “አንዳንድ ወጣት ወንዶች እንደልባቸው መሆን የሚያስችላቸው ገንዘብ እንዳያጥራቸው ሲሉ ‘ሌላ ሰው መርዳት’ አይፈልጉም።” ይሁን እንጂ ብዙዎች በራስ ወዳድነታቸው ሳቢያ የሚከፍሉት ዋጋ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል ዛሬ ዛሬ በብዙ አገሮች ያሉ ፍርድ ቤቶችና ሕግ አውጪ አካላት የወለዷቸውን ልጆች በማይረዱ ወንዶች ላይ ጥብቅ እየሆኑ መጥተዋል። አንድ ወጣት አባትነቱ በማስረጃ ከተረጋገጠ የወለደውን ልጅ ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ወጪ ሁሉ እንዲሸፍን ሊገደድ ይችላል። ደግሞም ትክክል ነው። ብዙ ወጣቶች ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሲሉ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ ወይም ዝቅተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለመያዝ ይገደዳሉ። ስኩል ኤጅ ፕሪግናንሲ ኤንድ ፓረንትሁድ የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው “ገና በለጋ ዕድሜው ወላጅ የሆነ ወጣት መደበኛ ትምህርቱን የመቀጠሉ አጋጣሚ እጅግ የመነመነ ነው።” አንድ አባት የልጁን ወጪ መሸፈን ካቃተው ይህ ነው የማይባል ዕዳ ሊከመርበት ይችላል።

እርግጥ ነው፣ በልጆቻቸው ላይ የሚጨክኑት ሁሉም ወጣት ወንዶች አይደሉም። ብዙዎች ገና ከጅምሩ መልካም አሳቢነት ያሳያሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው 75 በመቶ የሚያክሉት በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አባቶች ልጃቸውን ሆስፒታል ሄደው ጠይቀዋል። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ወጣት አባቶች ብዙም ሳይቆዩ ልጅ የማሳደጉ ኃላፊነት ከባድ ሆኖ ይሰማቸዋል።

ብዙዎች ተስማሚ ሥራ ለማግኘት የሚያስችል ሙያ ወይም የሥራ ልምድ እንደሌላቸው ተገንዝበዋል። የኋላ ኋላ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም የሌላቸው መሆኑ ስለሚያሳፍራቸው ኃላፊነታቸውን እርግፍ አድርገው ይተዉታል። ሆኖም አንድ ወጣት በቀሪ ሕይወቱ ሁሉ በጸጸት ሊሰቃይ ይችላል። አንድ ወጣት አባት እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ ልጄ ምን ሆኖ ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ። . . . ከልጄ መለየቴን ሳስበው አዝናለሁ። ሆኖም አሁን ላገኘው አልችልም። ምናልባት አንድ ቀን እርሱ ያገኘኝ ይሆናል።”

በልጆች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት

የወለዱትን ልጅ ላለማሳደግ ከኃላፊነት የሚሸሹ አባቶች በገዛ ልጃቸው ላይ የሠሩት በደል ከሚያስከትልባቸው የኀፍረት ስሜት ጋርም መታገል ይኖርባቸው ይሆናል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አንድ ልጅ አባትም እናትም ያስፈልገዋል። (ዘጸአት 20:​12፤ ምሳሌ 1:​8, 9) አንድ አባት ልጁን ተወ ማለት የአብራኩን ክፋይ ለብዙ ችግር አሳልፎ ሰጠ ማለት ነው። የዩ ኤስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች መምሪያ ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ትንንሽ ልጆች በቃልና በስሌት ትምህርቶች የሚያመጡት ውጤት ዝቅተኛ ነው። ከእነርሱ ትንሽ ከፍ ያሉትና በነጠላ ወላጅ ያደጉ ልጆች ዝቅተኛ ውጤት የማምጣት፣ ከሌሎች ልጆች በበለጠ የጠባይ ችግር የማሳየትና ሥር ለሰደደ የጤናና የሥነ አእምሮ ችግር የመጋለጥ ሁኔታ ይታይባቸዋል። በነጠላ እናት በሚተዳደር ቤተሰብ ሥር ያደጉ ወጣቶች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የመውለድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን የማቋረጥ፣ ለእስር የመዳረግና ወይ ከሥራ ወይ ከትምህርት ሳይሆኑ የመቅረት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።”

አትላንቲክ መንዝሊ የተባለው መጽሔት በማጠቃለያው ላይ እንዲህ ይላል:- “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የማኅበራዊ ሳይንስ ማስረጃ እንደሚያሳየው በወላጆቻቸው እንክብካቤ ሥር ካደጉ ልጆች ይልቅ ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው እንዲሁም ከትዳር ውጪ የተወለዱ ልጆች የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች በድህነት አረንቋ የመያዝ እድላቸው ከሌሎቹ ስድስት እጥፍ ያህል ይበልጣል። ከድህነት ማጥ ለመውጣት ያላቸው ዕድል የዚያኑ ያህል የመነመነ ነው።”

እነዚህ ችግሮች በቡድን ደረጃ የተደረጉ ጥናቶችን ውጤት የሚያመለክቱ ናቸው እንጂ በግለሰብ ደረጃ የግድ ይሠራሉ ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል። ምንም እንኳ ችግር በተሞላ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድጉም ጥሩና ሚዛናዊ ሰዎች የሚሆኑ ብዙ ልጆች አሉ። ያም ሆኖ ግን ልጁን አላሳድግም ያለውን ወጣት ጸጸት ሊያሰቃየው ይችላል። አንድ ያላገባ አባት ስለ ልጁ ሲናገር “በእርግጥም ሕይወቱን እስከ ወዲያኛው [አመሰቃቅዬበት] ይሆናል ብዬ እፈራለሁ” ብሏል።​—⁠ቲንኤጅ ፋዘርስ

መርዳት ያለው ተፈታታኝነት

የወለዱትን ልጅ ከማሳደግ ኃላፊነት የሚሸሹት ሁሉም ወጣት አባቶች አይደሉም። አንዳንድ ወጣት አባቶች ልጃቸውን የማሳደግ የሞራል ግዴታ ስለሚሰማቸው ልጃቸውን ለመርዳት ከልብ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ እንዲህ ቀላል አይደለም። አንደኛ ነገር አንድ ያላገባ አባት ከልጁ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያክል መሆን እንዳለበት የሚወስኑት ልጅቷና ወላጆቿ ስለሚሆኑ እሱ ብዙም ሕጋዊ መብት አይኖረውም። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ጂም “ልጁን በተመለከተ ውሳኔ የመስጠቱ ሥልጣን የማን ነው የሚል ሽኩቻ አለ” በማለት ተናግሯል። ልጁን ለጉዲፈቻ እንደመስጠት ወይም ደግሞ ጽንሱን እንደ ማስወረድ ያሉ አባትየው በጥብቅ የሚቃወማቸው ውሳኔዎች ይወሰኑ ይሆናል። * አንድ ወጣት አባት “ልጁን ለማንም መንገደኛ ሲሰጡ ዝም ብሎ ማየቱ በጣም ይከብዳል። ሆኖም ምንም ምርጫ የለኝም” ሲል ተናግሯል።

አንዳንድ ወጣቶች የልጃቸውን እናት ለማግባት ጥያቄ ያቀርባሉ። * እርግጥ መጋባቱ በመጠኑም ቢሆን ልጅቷን ከኀፍረት ሊያድናትና ልጁም በወላጆቹ እጅ ለማደግ ያለውን አጋጣሚ ሊያሰፋ ይችላል። ከባድ ስህተት መሥራታቸው ነው እንጂ ወጣቶቹ ከልብ ይዋደዱ ይሆናል። ሆኖም አንድ ወጣት ልጅ ወለደ ማለት ባል እና አባት ለመሆን የሚያበቃ አእምሮአዊና ስሜታዊ ብስለት አለው ማለት አይደለም። ወይም ደግሞ ሚስትና ልጅ ለማስተዳደር የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለው ማለትም አይደለም። እርግዝና ስለተከሰተ ብቻ የሚመሠረት ትዳር ዘለቄታ እንደማይኖረው ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ ቸኩሎ ለመጋባት መወሰንም ጥበብ ያለበት መፍትሄ ላይሆን ይችላል።

ብዙ ወጣት ወንዶች ልጃቸውን በገንዘብ ለመርዳት ፈቃደኞች ይሆናሉ። ቀደም ብሎ እንደተገለጸው አባትዬው እንዲህ የማድረግ ፍላጎት ካለው ለረጅም ዓመታት ምናልባትም ለ18ና ከዚያም ለሚበልጡ ዓመታት ሳያስተጓጉል ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል! እናትየውና ልጁ በገንዘብ ረገድ የሚደረግላቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ወደ ድህነት አዘቅት እንዳይወድቁ ይረዳቸዋል።

በቀጥታ ልጁን በማሳደጉ ሥራ ስለመካፈልስ ምን ለማለት ይቻላል? ይህም ቢሆን ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የሁለቱም ወላጆች እንደገና ሌላ የጾታ ብልግና እንዳይፈጸም በመስጋት ወጣቶቹ ቶሎ ቶሎ እንዳይገናኙ ወይም ከነጭራሹ እንዳይተያዩ ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። ልጅቷም ራሷ ልጅዋ ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር እንዲቀራረብ አትፈልግ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አባትየው ከልጁ ጋር በየጊዜው እንዲገናኝ የሚፈቀድለት ከሆነ ቤተሰቦቻቸው ዳግም ሌላ ስህተት እንዳይፈጸም ለመከላከል የበሰለ ሰው አብሯቸው እንዲሆን ማድረጋቸው ተገቢ ነው።

አንዳንድ ያላገቡ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የበለጠ ለመቀራረብ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ዋና ዋና የወላጅነት ኃላፊነቶችን ለማከናወን ገላ ማጠብ፣ ማጉረስ ወይም ለልጆቻቸው ማንበብ የመሳሰሉትን ተግባሮች እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ተለማምደዋል። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች የሚያውቅ አንድ ወጣት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለልጁ ማስተማር ይፈልግ ይሆናል። (ኤፌሶን 6:​4) ይሁን እንጂ አንድ አባት ለልጁ አንዳንድ ፍቅራዊ እንክብካቤ ማከናወኑ ምንም ካለማድረግ የሚሻል መሆኑ ባይካድም ሁልጊዜ አብሮ ከሚኖር አባት ጋር ግን ፈጽሞ አይተካከልም። የልጁ እናት አንድ ቀን ብታገባ ወጣቱ አባት ልጁን የማሳደጉን ኃላፊነት ሌላ ሰው ሲወስድ ዝም ብሎ ከመመልከት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችልም።

ከትዳር ውጪ ልጅ መውለድ ወላጆቹንም ሆነ ልጁን ከባድ ችግር ውስጥ የሚከታቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ከሚያስከትለው ችግር በተጨማሪ ሕገወጥ የጾታ ግንኙነት መፈጸምን የሚያወግዘውን የይሖዋ አምላክን ሞገስ ያሳጣዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:​3) በአሥራዎቹ ዕድሜ እንደ መጸነስ ያሉትን ከባድ ችግሮች መቋቋም የሚቻል ቢሆንም እንኳ የተሻለው ነገር ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ መሆኑን መረዳት ያሻል። አንድ ወጣት አባት “አንዴ ከጋብቻ ውጪ ልጅ ከወለዳችሁ ሕይወታችሁ ፈጽሞ ይለወጣል” ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ አንድ ወጣት አባት የሠራው ስህተት ካስከተለበት መዘዝ ጋር ዕድሜ ልኩን ይኖር ይሆናል። (ገላትያ 6:​8) አሁንም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ሲል የሰጠው ምክር ጥበብ ያለበት መሆኑን ያረጋግጣል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​18

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.5 በሰኔ 2000 ንቁ! መጽሔት ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . የልጅ አባት መሆን​—⁠የወንድነት መለኪያ ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ። ሳያገቡ የልጅ እናት መሆን በወጣት ሴቶች ላይ ምን ችግር እንደሚያስከትል ለማወቅ በሐምሌ 22, 1985 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ሳያገቡ የልጅ እናት መሆን​—⁠በእኔም ላይ ሊደርስ ይችላልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

^ አን.16 በመጋቢት 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ውርጃ​—⁠መፍትሔ ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17 የሙሴ ሕግ አንዲትን ድንግል በጾታ ያስነወረ ወንድ ሚስት አድርጎ ሊወስዳት እንደሚገባ ይናገራል። (ዘዳግም 22:​28, 29) ይሁን እንጂ የልጅቷ አባት ላይፈቅድ ስለሚችል የግድ ይጋባሉ ማለት አልነበረም። (ዘጸአት 22:​16, 17) ምንም እንኳን ዛሬ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ ሥር ባይሆኑም ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ያክል ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ያስገነዝባል።​—⁠በኅዳር 15, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) “የአንባብያን ጥያቄዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠቡ የተሻለ ነገር ነው