በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በዓይነቷ ልዩ የሆነችው ፕላኔቷ ምድር

የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሳይንቲስቶች በርቀት የሚገኝ ፕላኔቶች የሚዞሩት ኮከብ የሚኖረውን አነስተኛ ንዝረት በለኩ ቁጥር አዳዲስ ፕላኔቶችን ማግኘታቸውን ቀጥለዋል። ንዝረቱ የሚፈጠረው በፕላኔቱ የስበት ኃይል አማካኝነት ነው። ከ1999 ጀምሮ ከእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውጪ 28 ፕላኔቶች እንደተገኙ ይነገራል። ተገኝተዋል የተባሉት እነዚህ አዳዲስ ፕላኔቶች ከጁፒተር ጋር የሚተካከል ወይም ከዚያ የሚበልጥ መጠን ያላቸው ናቸው። የጁፒተር መጠነ ቁስ ከመሬት 318 ጊዜ ይበልጣል። ፕላኔቶቹ እንደ ጁፒተር ከሂሊየምና ከሃይድሮጅን የተሠሩ ናቸው። የፕላኔቶቹ ምሕዋር በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከምድር ጋር ተመሳሳይ የሆነ መጠን ያላቸው ፕላኔቶች ከእነርሱ ጋር መኖራቸው አጠራጣሪ ነው። ከዚህም በላይ ምድር 150 ሚልዮን ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ክብ ምሕዋር ያላት ሲሆን እነዚህ ፕላኔቶች ግን ኮከቦቻቸውን የሚዞሩት ሞለል ያለ ቅርጽ ባለው ምሕዋር ነው። እንዲያውም አንድ ምሕዋር ከኮከቡ ከ58 ሚልዮን ኪሎ ሜትር እስከ 344 ሚልዮን ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት አለው። “በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ እንደምንመለከተው በቡድን መልክ በደንብ የተደራጁ ክብ ቅርጽ ያላቸው ምሕዋሮች እንደሌሉ ግልጽ እየሆነ መጥቷል” በማለት አንድ የስነ ፈለክ ተመራማሪ ተናግረዋል።

በፉጨት ሐሳብ መለዋወጥ

ከካናሪ ደሴቶች አንዷ በሆነችው በጎሜራ ደሴት የሚኖሩ ስፓኒሽ ተማሪዎች ለብዙ መቶ ዓመታት በአካባቢው የሚገኙ እረኞች ሲጠቀሙበት የኖሩትን የፉጨት ቋንቋ እንዲማሩ ይጠበቅባቸዋል በማለት የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። መጀመሪያ ላይ በተራራማው አካባቢ ከሸለቆዎቹ ወዲህና ወዲያ ማዶ ሆነው ሐሳብ ለመለዋወጥ ሲሉ የፈጠሩት ይህ የጎሜራ ሲልቦ ወይም ፉጨት ከንግግር ክፍለ ቃል ጋር የሚመሳሰሉ ድምፆች አሉት። የሚያፏጩት ሰዎች የድምፁን ቃና ለመለዋወጥ ጣቶቻቸውን አፋቸው ላይ ያደርጉና ፉጨቱ እስከ 3 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ላይ እንዲሰማ ለማድረግ ክብ ቅርጽ ሠርተው እጃቸውን አፋቸው ላይ ያደርጋሉ። በ1960ዎቹ በጣም እየከሰመ ሄዶ የነበረው ሲልቦ በአሁኑ ጊዜ እንደገና በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በደሴቲቱ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ዓመታዊ የፉጨት ቀን አላቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ችግሮችም አሉት። “በፉጨት መግባባት የምትችሉ ቢሆንም ልትነጋገሩት የምትችሉት ነገር ውስን ነው” በማለት ሁዋን ኢቫሪስቶ የተባሉ የአካባቢው የትምህርት ዲሬክተር ተናግረዋል።

ልጆችና እንቅልፍ

“ወላጆች በትምህርት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆቻቸው በስንት ሰዓት መተኛት እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን ከመተኛታቸው በፊት በሚሠሯቸው ነገሮችም ላይ ገደብ ማበጀት አለባቸው” በማለት ፓረንትስ የተባለ መጽሔት ተናግሯል። “ቴሌቪዥን መመልከት፣ የኮምፕዩተርና የቪዲዮ ጨዋታዎች መጫወት እንዲሁም የኢንተርኔት ገጾችን መዳሰስ የልጆችን አእምሮ ከልክ በላይ ብዙ ሰዓት የሚያሠሩ ንቁ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ከትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ በበርካታ እንቅስቃሴዎች የሚጠመዱ ከሆነ የቤት ሥራቸውን ቶሎ መጨረስ አይችሉም።” የእንቅልፍ ማነስ በትንንሽ ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ለየት ያለ እንደሆነ የተካሄደው ጥናት ያመለክታል። አዋቂዎችን እንቅልፍ እንቅልፍ እንዲላቸውና ድብታ እንዲይዛቸው የሚያደርግ ሲሆን ልጆችን ግን እንዲንቀዠቀዡና እንዲቁነጠነጡ ያደርጋቸዋል። በዚህም የተነሳ በቂ እንቅልፍ ያላገኙ ልጆች ትምህርት ቤት በሚሆኑበት ጊዜ ሐሳባቸውን ማሰባሰብ፣ በትኩረት መከታተል፣ የተማሯቸውን ነገሮች መያዝና ስሌት መሥራት ይቸግራቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው ወደ መኝታ የሚሄዱበትን ጊዜ መወሰን ያለባቸው ሲሆን ይህም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንጂ የሚሠሩት ሲያጡ ወይም ድክም ሲላቸው የሚያደርጉት ነገር አለመሆኑን ማስገንዘብ እንዳለባቸው ኤክስፐርቶች ይናገራሉ።

ኤድስ በዓለም ዙሪያ

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት በመላው ዓለም “ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ማለትም ከብሪታንያ የሕዝብ ብዛት ጋር የሚተካከል ሕዝብ በኤች አይ ቪ ኤድስ የተያዘ ሲሆን 16 ሚልዮን የሚሆኑት ሞተዋል” በማለት የካናዳው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ተናግሯል። “በዘጠኝ የአፍሪካ አገሮች የተካሄደ ጥናት እንደገለጠው ከወንዶች 20 በመቶ የሚበልጡ ሴቶች በበሽታው የተያዙ” ሲሆን “በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወንዶች በአምስት እጥፍ ያህል ይበልጣል።” የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ የጋራ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ፓዮ በምሥራቅ አውሮፓ ያለውን ሁኔታ “ከፍንዳታ” ጋር አመሳስለው ገልጸውታል። “በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኤች አይ ቪ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ያደገ ሲሆን ይህም ከዓለም ከፍተኛ ጭማሪ የታየባት አገር እንድትሆን አድርጓታል።” ይህ የሆነው በዚህ ክልል አደገኛ መድኃኒቶችን በደም ሥራቸው የሚ​ወስዱ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ እንደሆነ ጠበብት ይናገራሉ። በመላው ዓለም በኤች አይ ቪ ኤድስ ከተያዙት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት “በሽታው የያዛቸው በ25 ዓመት ዕድሜያቸው ሲሆን 35ኛውን የልደት በዓላቸውን ከማክበራቸው በፊት ይሞታሉ።”

ለጤና ተስማሚ አድርጎ መጥበስ

“በደንብ ያልበሰለ ሥጋ ለጤና ጠንቅ በመሆኑ ትኩረት ሲሰጠው የኖረ ጉዳይ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከልክ በላይ መጥበስ በተለይ ሥጋን፣ ዶሮንና ዓሣን በአሮስቶ መጥበሻ ማሳረር ይበልጥ ቶሎ ለማይድን በሽታ ሊያጋልጥ እንደሚችል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተነገረ ነው” ሲል የካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ ይገልጻል። ሥጋ በከፍተኛ የሙቀት መጠን በሚጠበስበት ጊዜ ሄትሮሳይክሊክ አሚንስ (ኤች ሲ ኤ ኤስ) ተብለው የሚጠሩ ካንሠር የሚያስይዙ ውሁዶች ይፈጠራሉ። “እንደ ሎሚ ጭማቂ፣ የብርቱካን ጭማቂ ወይም ኮምጣጤ ያለ አሲድ” ያለበት ቀለል ያለ የቅመሞች ድብልቅ መጠቀሙ የተጠበሰው ሥጋ ለጤና እክል የሚያጋልጥ እንዳይሆን ሊረዳ ይችላል ሲል ዘገባው ይጠቁማል። በአሜሪካ የካንሠር ምርምር ተቋም የሚሠሩ ተመራማሪዎች በተደጋጋሚ ባደረጓቸው ሙከራዎች “በቅመሞች ድብልቅ በተዘፈዘፈ ምግብ ውስጥ የሚገኙት የኤች ሲ ኤ ኤስ ውሁዶች በእንዲህ ዓይነቱ ድብልቅ ውስጥ ባልተዘፈዘፈ ምግብ ውስጥ ከተገኙት ውሁዶች ከ92 በመቶ እስከ 99 በመቶ ያነሱ ሆነው ተገኝተዋል። በተጨማሪም ምግቡ ለ40 ደቂቃም ተዘፈዘፈ ለሁለት ቀን ለውጥ አያመጣም።”

የፀሐይ መከላከያ ቅባትና ካንሰር

“የፀሐይ ጨረርን በከፍተኛ ደረጃ የመከላከል አቅም ያላቸው የቆዳ ቅባቶች ሰዎችን በማዘናጋት በቆዳ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸውን ከፍ ሊያደርጉባቸው ይችላሉ” በማለት የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። “ይህ የሚሆነው ሰዎቹ ለረዥም ሰዓት ፀሐይ ላይ በመቆየት ራሳቸውን ይበልጥ ለጨረር ስለሚያጋልጡ ነው።” በሚላን ኢጣሊያ በሚገኘው የአውሮፓ የኦንኮሎጂ ተቋም የሚሠሩ ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ጨረር የመከላከል ኃይሉ 30 የሆነ የቆዳ ቅባት የሚጠቀሙ ሰዎች ጨረር የመከላከል ኃይሉ 10 የሆነ የቆዳ ቅባት ከሚጠቀሙ ሰዎች 25 በመቶ ለሚበልጥ ጊዜ ራሳቸውን ለፀሐይ ያጋልጣሉ። ጥናቱን የጻፉት ፊሊፕ ኦትዬ እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “የፀሐይ ጨረር የሚከላከሉ የቆዳ ቅባቶች የቆዳ ካንሰርን በተለይ ደግሞ ሜላኖማን በመከላከል ረገድ ያላቸው ውጤታማነት በአብዛኛው ሰው ላይ በተጨባጭ የተረጋገጠ አይደለም። ሆኖም ለመዝናናት ተብሎ ፀሐይ ላይ ለረዥም ጊዜ መቆየት የቆዳ ካንሰር ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎች አሉ።” የፀሐይ ጨረርን የሚከላከሉ የቆዳ ቅባቶች የመከላከል ኃይላቸው ምንም ያህል ቢሆን ለረዥም ጊዜ ለፀሐይ መጋለጥ አደገኛ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። በብሪታንያ የጤና ትምህርት ባለ ሥልጣን የካንሰር ዘመቻ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክሪስቶፈር ኒው “ፀሐይ የሚከላከሉ የቆዳ ቅባቶችን መጠቀማችሁን አታቁሙ። ሆኖም እነዚህን ቅባቶች ብትጠቀሙም እንኳ ለረዥም ሰዓት ለፀሐይ አትጋለጡ” በማለት መክረዋል።

የፖስታ አገልግሎት ምትክ አልተገኘለትም

እስከ አሁን ድረስ “ቴክኖሎጂ ደብዳቤ የሚያሳድረውን አንድምታ ምትክ ሊያገኝለት አልቻለም” በማለት ለ ፊጋሮ የተባለ ጋዜጣ ተናግሯል። በ1999 የፈረንሳይ የፖስታ አገልግሎት 25 ቢልዮን ደብዳቤዎችን በመላክ የቀዳሚነቱን ቦታ ይዟል። ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ከንግድ ሥራ ጋር የተያያዙ መልእክቶች ሲሆኑ የቀረው 10 በመቶ ደግሞ የግል ደብዳቤ ነው። ከጠቅላላው ደብዳቤ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ማስታወቂያ የያዙ ሲሆን ደብዳቤው ከደረሳቸው ሰዎች መካከል 98 በመቶ የሚሆኑት ማስታወቂያዎቹን በደንብ እንዳነበቡ ተናግረዋል። በፈረንሳይ ደብዳቤዎችን በየቦታው የሚያደርሱ 90, 000 ሠራተኞች (40 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው) በየቀኑ የሚላኩትን 60 ሚልዮን የሚሆኑ ደብዳቤዎች ለማከፋፈል በየቀኑ 72, 000 ምልልስ ያደርጋሉ።

በጭንቅ ላይ የሚገኙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች

ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ “1999 ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተረገመ ዓመት” ነበር በማለት ዘግቧል። በ1998 የደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች 90 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ውድመት ያደረሱ ሲሆን ከእዚህ ውስጥ 15 ቢልዮን ዶላር የሚሆነውን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍለዋል። ይሁን እንጂ በ1999 በቱርክ እና በታይዋን የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጃፓን የደረሰው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ፣ በሕንድ እና በቬትናም የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹን ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከፍሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሰው በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እየጨመሩ መምጣታቸው በጣም አሳስቧቸዋል። ግንባር ቀደሙ የዓለም የኢንሹራንስ ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ያለው የሙቀት መጠን ሊያስከትለው ስለሚችለው “ከፍተኛ ጥፋት” እና “ሰዎች በአየር ንብረት ላይ እያደረሱት ያሉት ጉዳት ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ” ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ቀሳፊ መኖ

በምዕራብ ሕንድ በምትገኘው በኩች ወረዳ የሚኖሩ አንድ የእንስሳት ቀዶ ሐኪም በቅርቡ 45 ኪሎ ግራም የሚመዝን ላስቲክ ከአንዲት ከታመመች ላም ሆድ ውስጥ ማስወገዳቸውን በኬራላ ሕንድ የሚታተም ዘ ዊክ የተባለ መጽሔት ዘግቧል። ከፌስታሉ በተጨማሪ ጨርቅ፣ የኮከነት ቅርፊት፣ የተጠቀለለ ሽቦና አንድ ቡሎን አግኝተዋል። ብዙውን ጊዜ በሕንድ የሚጠፉ ላሞች ምግባቸውን የሚለቃቅሙት በቆሻሻ ማጠራቀሚያ አካባቢ ሲሆን የተጣለ ላስቲክ ለላሞች አደገኛ ነው። ሌላው ቀርቶ ባለቤት ያላቸው የወተት ላሞች ወደሚሰማሩበት የግጦሽ መስክ እየሄዱ ሳለ በየጥጉ የወዳደቁ ቆሻሻዎችን ይለቃቅማሉ። የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ጃዴጃ እንዳሉት እግርታፍ ከሚባለው ህመም ቀጥሎ በላሞች ላይ ችግር እየፈጠረ ያለው ነገር ላስቲኮችን በመብላታቸው ሳቢያ የሚከሰትባቸው ጠንቅ ነው። የዋጧቸው ላስቲኮች ስለማይፈጩና ሆዳቸው ውስጥ ስለሚቀረቀሩ ማመንዠክ አይችሉም። ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ የገጠማቸው ላሞች ይሞታሉ። ዶክተር ጃዴጃ ይህን ነገር ሊያስተውሉ የቻሉት የሞቱ ላሞችን ቆዳ በሚገፍፉበት ጊዜ በላሞቹ ሆድ ውስጥ በርካታ ላስቲኮችን ያገኙ ጫማ ሠሪዎች በሰጧቸው መረጃ ነው።