በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የግድያ ባሕል” የተስፋፋው እንዴት ነው?

“የግድያ ባሕል” የተስፋፋው እንዴት ነው?

“የግድያ ባሕል” የተስፋፋው እንዴት ነው?

“የስሜትና የአካል ቁስለት ከደረሰባቸው የኮሶቮ ወጣት ስደተኞችና ለዓመፅና ለሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶች ከተጋለጡት የአሜሪካ ሕፃናት መካከል በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ርቀት አለ። በስሜት ረገድ ግን ብዙ ልዩነት አይታይባቸውም።” —⁠ማርክ ካውፍማን፣ ዘ ዋሽንግተን ፖስት

ሁላችንም ወደድንም ጠላን ሞት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይነካናል። የምንኖረው ዓመፅና ግጭት በተስፋፋበት አካባቢ ይሁን ወይም አንፃራዊ መረጋጋት በሰፈነበት ከዚህ ማምለጥ አንችልም።

በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፉ ያሉት የመንፈስ ጭንቀት፣ የስሜት መታወክ፣ የዕፅ ሱሰኝነት፣ ውርጃ፣ ራስን የማጥፋት አዝማሚያ፣ ራስን መግደል፣ የጅምላ ግድያ “የግድያ ባሕል” የሚገለጥባቸው ባሕርያት ናቸው። በሳን አንቶንዮ ቴክሳስ የሚገኘው የትሪኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሶስዮሎጂና አንትሮፖሎጂ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ማይክል ከርል ሞት እንዴት ላለ የተንኮል ዓላማ እንደዋለ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “በደረስንበት በዚህ ሃያኛ መቶ ዘመን [1999] ላይ ሆነን ስንመለከት ሞት የማኅበራዊውን ሥርዓት ሕይወት፣ ጥንካሬና መዋቅር የሚቆጣጠር ማዕከላዊ ኃይል እየሆነ መምጣቱን መገንዘብ እንችላለን። ሃይማኖቶቻችን፣ ፍልስፍናዎቻችን፣ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳቦቻችን፣ ሥነ ጥበባችንና የሕክምና ቴክኖሎጂዎቻችን መሠረታዊ እሳቤያቸውን ያደረጉት ሞትን ነው። ሞት ለኢንሹራንስ ፖሊሲዎችና ለጋዜጦች ማሻሻጫ ሆኗል። ለቴሌቪዥን ተውኔቶች ነፍስ የሚዘራ ኃይል ሆኗል። ኢንዱስትሪዎችን ሳይቀር ያንቀሳቅሳል።” ይህ እንደ ባሕል የተያዘው ግድያ በዚህ በዘመናችን የሚገለጥባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።

የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ

“የግድያ ባሕል” በጦር መሣሪያዎች ሽያጭ በየቀኑ ይገለጣል። የጦር መሣሪያዎች የሚተኮሱት በወታደሮች ላይ ቢሆንም ምንም የማያውቁ ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ ሲቪሎችንም መግደላቸው አልቀረም። የእርስ በርስም ሆነ ሌላ ዓይነት ጦርነት በሚደረግበት ጊዜ ሁሉ ሕይወት በጣም ርካሽ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። አንድ ነፍሰ ገዳይ ወይም አንድ የደፈጣ ተዋጊ የሚተኩሳት አንዲት ጥይት ዋጋዋ ምን ያህል ነው?

በአንዳንድ አገሮች የጦር መሣሪያ ማግኘት በጣም ቀላል በመሆኑ በግለሰቦችና በቡድኖች ላይ የሚፈጸም ግድያ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ጨምሯል። በሊትልተን ኮሎራዶ በሚገኘው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተፈጸመው የተኩስ እሩምታ ወዲህ የጦር መሣሪያዎች በሰፊው የሚሸጡና ለትናንሽ ልጆች እንደ ልብ የሚገኙ በመሆናቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበ ነው። ኒውስዊክ እንደሚለው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ በሰው የሚገደሉ ወጣቶች ቁጥር አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአማካይ በሳምንት 40 ወጣቶች ይገደላሉ። ከእነዚህ መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የሚገደሉት በጥይት ነው። በየዓመቱ በሊትልተን የተፈጸመውን የመሰሉ 150 ግድያዎች ይፈጸማሉ ማለት ነው!

የመዝናኛው ዓለም

ፊልሞችም ግድያ የሚፈጸምባቸው መድረኮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል የአንድ ፊልም ታሪክ ብልግናን፣ ዓመፅን፣ ዕፅ ማስተላለፍን ወይም ለወንጀል መደራጀትን እንደ ጥሩ ነገር አድርጎ በማቅረብ የሕይወትንና የሥነ ምግባርን ዋጋማነት ያራክሳል። ከሞቱ በኋላ በሕይወት ስለኖሩና በሕይወት ያሉ ሰዎችን ተመልሰው ስለጎበኙ ሰዎች በመተረክ ሞትን ከልብ ወለድ ታሪክ ማበልጸጊያ የሚጠቀሙ ፊልሞች አሉ። ይህም ሞት ቀላልና ተራ ነገር ሆኖ እንዲታይ አድርጓል።

አንዳንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ሙዚቃዎችም ከዚህ የተለዩ አይደሉም። የዜና ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በሊትልተን የተፈጸመውን ግድያ የፈጸሙት ልጆች “ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት አስቸጋሪ በሆነውና በሰይጣን ምስል ቁመናው እንዲሁም ዓመፅንና ግድያን” በሚያሞግሱ ዘፈኖቹ እውቅ የሆነው የዚህ ዘፋኝ አድናቂዎች ነበሩ።

በዩናይትድ ስቴትስ ወጣት ልጆች ጉዳት የሚያስከትልባቸው ፊልም እንዳያዩ ለመከልከል ሲባል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚገመግሙባቸውን መሥፈርት መለወጥ አስፈልጓል። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም። ጆናታን ኦረት “መሥፈርቶቹ ወጣት ልጆች የተከለከለውን ነገር ይበልጥ እንዲፈልጉ ገፋፍቷቸዋል” ሲሉ ኒውስዊክ መጽሔት ላይ ጽፈዋል። በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ክሊንተን እነዚህን ፕሮግራሞች የሚያቀርቡበትን ድርጅቶች ለማሳፈርና በመገናኛ ብዙሐን የሚያቀርቧቸውን የዓመፅ ድርጊቶች እንዲቀንሱ ለመገፋፋት ሲሉ በጩቤ መወጋጋት የሚታይባቸውን ፊልሞች፣ ጥላቻንና መገዳደል የሚያሞግሱ ‘የራፕ ሙዚቃዎችን’ እንዲሁም ልጆች ሌሎች “ሰዎችን በመግደል ላይ እንዳሉ እንዲመስላቸው” የሚያደርጉ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጁና የሚያሰራጩ “ትላልቅ ኩባንያዎችንና ሥራ አስኪያጆቻቸውን ስም በአደባባይ ጠርተዋል።”

ግድያ በቪዲዮ ጨዋታዎችና በኢንተርኔት ላይ

ሮበርት ዋሪንግ ዘ ዴዝማች ማኒፌስቶ በተባለው መጽሐፋቸው የመገዳደል ግጥሚያ ጨዋታዎች በወጣቶች ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅ እንደሆኑ ተንትነዋል። * በዚህ ክስተት ዙሪያ በሕቡዕ የሚንቀሳቀስ የተጨዋቾች ማኅበር በማቆጥቆጥ ላይ እንዳለ ሚስተር ዋሪንግ ያምናሉ። እነዚህ ጨዋታዎች ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጡ ሳይሆኑ መገዳደልን ብቻ የሚያስተምሩ ናቸው። ዋሪንግ “በማንኛውም የዓለም ክፍል ከሚገኝ ባላጋራ ጋር መጋጠምና ለማሸነፍ መጣጣር ከፍተኛ ኃይል ያለው ተሞክሮ ነው። በጨዋታው ለመሳብና ለመመሰጥ በጣም ቀላል ነው።” በገሐዱ ዓለም ያለ የሚመስለው ደም አፍሳሽ ትግል ወጣቶቹን አጥምዶ ይይዛቸዋል። አንዳንዶች በኢንተርኔት መገናኘት የማይችሉ ቢሆኑም እንኳን እቤታቸው ባለው ቴሌቪዥን ሊጫወቱ የሚችሉትን የቪዲዮ ጨዋታዎች ይገዛሉ። ሌሎች ደግሞ የቪዲዮ ማጫወቻ ወደሚያከራዩባቸው ቦታዎች ይሄዱና የውጊያ ግጥሚያ ይጀምራሉ።

“የግድያ ግጥሚያ” ጨዋታዎች በእድሜ ክልል የሚመደቡ ቢሆኑም እምብዛም ቁጥጥር አይደረግባቸውም። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው የ14 ዓመቱ ኤዲ “ሰዎች ዕድሜህ አልደረሰም ይላሉ እንጂ [ግጥሚያውን] እንዳንገዛ አይከለክሉንም” ብሏል። እርሱን የሚያስደስተው መተኳኮስ የሚበዛበት ጨዋታ ነው። ወላጆቹ ይህን የሚያውቁና የማይወዱለት ቢሆኑም እንኳን መጫወት አለመጫወቱን አይቆጣጠሩም። አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ወጣት “ይህ የኛ ትውልድ ከማንኛውም ሌላ ትውልድ ይበልጥ ለጭካኔና ለዓመፅ ያለው ስሜት ደንዝዟል። ባሁኑ ጊዜ ልጆችን የሚያሳድጉት ወላጆች ሳይሆኑ ቴሌቪዥኖች ናቸው። ቴሌቪዥን ደግሞ በሕፃናት ልቦና ውስጥ ያለውን የጭካኔ ባሕርይ ያዳብራል” ሲል ደምድሟል። ጆን ሌላንድ በኒውስዊክ መጽሔት ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 11 ሚልዮን የሚደርሱ ወጣቶች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በሆኑበት ባሁኑ ጊዜ ለብዙ ወላጆች ድብቅ የሆነ አዲስ የጎረምሶች ዓለም እየተስፋፋ ነው።”

ወደ ሞት የሚያደርሱ የአኗኗር ልማዶች

“ከግድያ ግጥሚያና” የጭካኔ ድርጊት ከሚያሳዩ ፊልሞች ውጭ ያለው ዓለምስ? በእውነተኛው ዓለም ጉሮሮ ለጉሮሮ የሚተናነቁ እንግዳ አራዊት የሚያጋጥሙ ባይሆንም የብዙ ሰዎች የአኗኗር ልማድ ወደ ጥፋት የሚያመራ ነው። ለምሳሌ ያህል የቤተሰብ አባሎች፣ የጤና ተቋሞችና ሌሎች ባለ ሥልጣኖች የሚሰጡትን ምክርና ማስጠንቀቂያ እየሰሙ ትንባሆ ማጨሳቸውንና አደገኛ ዕፅ መውሰዳቸውን የቀጠሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ሕይወት አብዛኛውን ጊዜ በአጭሩ ይቀጫል። ትላልቅ የንግድ ተቋማትና የዕፅ አስተላላፊዎች የሚያገኙትን ሕገወጥ ትርፍ ለማብዛት ሲሉ ሰዎች ያለባቸውን ተስፋ ቢስነት፣ ጭንቀትና መንፈሳዊ ድህነት እንደ መረማመጃ ድልድይ አድርገው ይጠቀሙበታል።

ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ መገዳደልን እንደ መዝናኛ አድርጎ ያቀርባልን? ወደ ሞት የሚያደርሱ የአኗኗር ልማዶች ተገቢ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራልን? በፍጹም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሞት “ጠላት” ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:​26) ለክርስቲያኖች ሞት የሚያምር ወይም የሚያስደስት ነገር ሳይሆን በኃጢአትና በአምላክ ላይ በማመፅ ምክንያት የሚመጣ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነው። (ሮሜ 5:​12፤ 6:​23) አምላክ ለሰው ልጅ ያወጣው ዓላማ ክፍል ሆኖ አያውቅም።

ሰይጣን ‘የሞት ምክንያት’ እንደሆነ ተገልጿል። በቀጥታ ግድያ የሚፈጽም ባይሆንም ሰዎችን በማሳሳትና በማታለል ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ፣ ሞትና ጥፋት የሚያስከትሉ ምግባሮችን በማስፋፋት፣ በወንዶች፣ በሴቶችና በሕፃናት ልብና አእምሮ ውስጥ እንኳን ሳይቀር የመግደል ዝንባሌ እንዲሰርፅ በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለሚገድል “ነፍሰ ገዳይ” ተብሏል። (ዕብራውያን 2:​14, 15፤ ዮሐንስ 8:​44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:​3፤ ያዕቆብ 4:​1, 2) ይሁን እንጂ ወጣቶች ዋነኛ ዒላማ የሆኑት ለምንድን ነው? እነርሱንስ ለመርዳት ምን ልናደርግ እንችላለን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ይህ ጽሑፍ “የግድያ ግጥሚያ” ተጫዋቾች “እውነተኛ በሚመስሉ ምስሎች እርስ በርስ ለመገዳደል ይገፋፋሉ” ይላል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ይህ የኛ ትውልድ ከማንኛውም ሌላ ትውልድ ይበልጥ ለጭካኔና ለዓመፅ ያለው ስሜት ደንዝዟል”