ፈገግታ—ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!
ፈገግታ—ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!
ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ከልብ ከሆነ የጥርጣሬን በረዶ ያቀልጣል። ለዓመታት ሲከማች የኖረን ጭፍን ጥላቻ ያስወግዳል። በእምነት ማጣትና በጥርጣሬ ደድሮ የነበረን ልብ ያለሰልሳል። ብዙዎች እፎይታና ደስታ እንዲያገኙ ያደርጋል። “ገብቶኛል፣ ችግር የለም” የሚል መልእክት ያስተላልፋል። “ጓደኛ ልንሆን እንደምንችል ይሰማኛል” የሚል ግብዣ ያቀርባል። ለመሆኑ ይህ ነገር ምንድን ነው? ፈገግታ ነው። አንተም የምታሳየው ፈገግታ ሊሆን ይችላል።
ፈገግታ ምንድን ነው? መዝገበ ቃላት ‘መደሰትን ወይም መስማማትን ለመግለጽ ከንፈር ሲሸሽና በመጠኑ ጥርስ ሲገለጥ በፊት ላይ የሚታይ ሁኔታ’ እንደሆነ አድርገው ይፈቱታል። ሞቅ ያለ ፈገግታ ለማሳየት ምሥጢሩ ይኸው ነው። ፈገግታ አንድ ሰው ያለ አንደበት ስሜቱን የሚገልጽበት ወይም ከሌላው ሰው ጋር ልብ ለልብ የሚግባባበት መንገድ ነው። እርግጥ ነው፣ ፈገግታ ንቀትን ወይም ጥላቻን ጭምር ሊገልጽ ይችላል። አሁን ግን መነጋገር የፈለግነው ስለዚህ አይደለም።
በእርግጥ ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ይህን ያህል ለውጥ ያመጣል? አንድ ሰው ፈገግታ ሲያሳይህ ደስ የተሰኘህበትን ወይም ዘና ያልክበትን ጊዜ አታስታውስም? ወይም ደግሞ ሰዎች ፈገግታ ሲነፍጉህ ጭንቅ አይልህም? አልፎ ተርፎም ተቀባይነት እንዳጣህ አይሰማህም? አዎን፣ ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ልዩነት ያመጣል። ፈገግ በሚለውም ሆነ ፈገግ በሚባልለት ሰው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢዮብ ባላጋራዎቹን በተመለከተ “ፈገግ አልኩላቸው፣ እነርሱ ግን አላመኑም። የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 29:24 NW ) የኢዮብ የፊቱ “ብርሃን” ብሩህና ደስተኛ ፊቱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ፈገግታ የሚያሳድረው በጎ ተጽእኖ ዛሬም ቢሆን ይሠራል። ሞቅ ያለ ፈገግታ ከውጥረት ተንፈስ ለማለት ሊረዳ ይችላል። ፈገግታ በፕሬዠር ኩከር ላይ ከምትገኝ ማስተንፈሻ ባልቦላ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ውጥረት ወይም ብስጭት በሚሰማን ጊዜ የሚሰማንን ውጥረት ለማቅለልና ብስጭታችንን ለመቋቋም ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ቶሞኮ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ዝም ብለው እንደሚመለከቷት አስተዋለች። ስታያቸው ቶሎ ብለው ዓይናቸውን ከእርሷ ላይ ስለሚነቅሉ የሚያሽሟጥጧት ሆኖ ተሰማት። ቶሞኮ የብቸኝነትና የሃዘን ስሜት አደረባት። አንድ ቀን አንዲት ጓደኛዋ ሰዎች ሲያይዋት ፈገግ እንድትል ሐሳብ አቀረበችላት። ከዚያም ቶሞኮ ይህን ነገር ለሁለት ሳምንት ያህል የሞከረችው ሲሆን በአጸፋው ሌሎችም ፈገግ ሲሉላት ስትመለከት በጣም ተገረመች! ውጥረቱ ለቀቃት። “ሕይወት የበለጠ አስደሳች ሆነልኝ” በማለት ትናገራለች። አዎን፣ ፈገግታ
በሌሎች ፊት ዘና እንድንልና ይበልጥ ተግባቢ እንድንሆን ይረዳናል።በአንተም ሆነ በሌሎች ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽእኖ
ፈገግታ በአንድ ሰው ስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንድን ሰው ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ሊያደርገው ይችላል። ለአካላዊ ጤናም ጥሩ ነው። “ሳቅ ፍቱን መድኃኒት ነው” የሚል አንድ አባባል አለ። እንዲያውም የሕክምና ባለሙያዎች አንድ ሰው የሚሰማው ስሜት በአካላዊ ሁኔታው ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለ ይናገራሉ። ለረጅም ጊዜ የቆየ ውጥረት፣ መጥፎ ስሜትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ስሜቶች የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያዳክሙ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። በሌላው በኩል ፈገግ ማለት ጥሩ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ሲሆን ሣቅ ደግሞ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያጠናክር ይችላል።
ፈገግታ በሌሎች ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ምክር ወይም ጠበቅ ያለ ማሳሰቢያ እየተሰጠህ ነው እንበል። ምክር የሚሰጥህ ሰው ምን ዓይነት ፊት ቢያሳይህ ትመርጣለህ? የተኮሳተረ ወይም ጭፍግግ ያለ ፊት ንዴትን፣ ቁጣን፣ ፊት መንሳትን ሌላው ቀርቶ ጥላቻን ሊያስተላልፍ ይችላል። በሌላው በኩል ደግሞ ምክር በሚሰጥህ ሰው ፊት ላይ የሚታየው ወዳጃዊ ፈገግታ ይበልጥ ዘና እንድትልና ምክሩን በደስታ እንድትቀበል አያደርግህም? በእርግጥም፣ ፈገግታ ውጥረት በነገሠበት ሁኔታ ውስጥ አለመግባባቶችን ለመቀነስ ይረዳል።
አዎንታዊ ሐሳብ ፈገግታ ማሳየትን ቀላል ያደርገዋል
እርግጥ ነው፣ ብዙዎቻችን በፈለጉት ጊዜ የጥርስ ፈገግታ ማሳየት የሚችሉ ተዋንያንን መምሰል አንፈልግም። ፈገግታችን ተፈጥሯዊና ልባዊ እንዲሆን እንፈልጋለን። አንዲት የትምህርት ቤት ዘጋቢ እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- ‘ዘና ብላችሁ ከልብ ፈገግ ማለታችሁ አስፈላጊ ነው። አለዚያ የምታሳዩት ፈገግታ የጥርስ ፈገግታ ብቻ ሆኖ ይቀራል።’ ታዲያ ከልባችን ፈገግ ማለት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን ይችላል። ንግግራችንን በተመለከተ በማቴዎስ 12:34, 35 ላይ እንዲህ ይለናል:- “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፣ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።”
ፈገግታ የውስጥ ስሜታችንን ያለ አንደበት የምናስተላልፍበት መንገድ እንደሆነ አስታውስ። የምንናገረው ‘በልብ ሞልቶ የተረፈውን’ እንደሆነና “መልካም ነገር” የሚወጣው ‘ከመልካም መዝገብ’ ውስጥ እንደሆነ ካስታወስን ልባዊ ፈገግታም ከውስጥ ስሜታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። አዎን፣ በልባችን ውስጥ ያለው ነገር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ በንግግራችንና በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በፊታችንም ላይ መገለጡ የማይቀር ነው። ስለዚህ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል
ይኖርብናል። ስለ ሌሎች ሰዎች ያለን አስተሳሰብ በፊታችን ላይ በግልጽ ይነበባል። ስለዚህ የቤተሰቦቻችን አባላት፣ በአካባቢያችን የሚኖሩ ሰዎችና የቅርብ ወዳጆቻችን ባላቸው መልካም ባሕርያት ላይ እናተኩር። እንዲህ ካደረግን ለእነርሱ ፈገግ ማለት አይከብደንም። የምናሳየውም ፈገግታ ጥሩነት፣ ምሕረትና ደግነት ከሞላው ልብ የሚወጣ ልባዊ ፈገግታ ይሆናል። ዓይናችን ብሩህ ይሆናል፤ ሌሎችም ፈገግታችን ከልብ እንደሆነ ይገነዘባሉ።ሆኖም አንዳንድ ሰዎች በአስተዳደጋቸው ወይም ያደጉበት አካባቢ ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ምክንያት እንደ ሌሎች ፈገግታ ማሳየት ቀላል ላይሆንላቸው እንደሚችል መገንዘብ አለብን። ለሰዎች ጥሩ ስሜት ያላቸው ቢሆንም እንኳ ፈገግታ ማሳየት ይቸግራቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጃፓናውያን ወንዶች በሌሎች ፊት ረጋ ያሉና ዝምተኛ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም የተነሳ ለማያውቋቸው ሰዎች ፈገግታ የማሳየት ልማድ የላቸውም። በሌሎች ባሕሎችም ተመሳሳይ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ወይም አንዳንድ ግለሰቦች በተፈጥሯቸው ዓይን አፋር ሊሆኑና ለሌሎች ፈገግታ ማሳየት ሊከብዳቸው ይችላል። ስለዚህ ሰዎችን በፈገግታቸው መጠን ወይም ብዛት መገመት አይኖርብንም። አንዱ ሰው ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ ጠባያቸውም ሆነ ከሰዎች ጋር የሚግባቡበት መንገድ ይለያያል።
የሆነ ሆኖ ለሰዎች ፈገግታ የማሳየት ችግር ካለብህ ለምን ለማሻሻል ጥረት አታደርግም? መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። . . . ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” በማለት ምክር ይለግሳል። (ገላትያ 6:9, 10) ለሌሎች “መልካም ሥራን ለመሥራት” ከምትችልባቸው መንገዶች አንዱ ፈገግታ ማሳየት ሲሆን ይህ ደግሞ ከአቅምህ በላይ የሆነ ነገር አይደለም! ሌሎችን በፈገግታ ሰላም ብለህ ጥቂት የማበረታቻ ቃላት ለመሰንዘር ቀዳሚ ሁን። ይህ ባሕርይ በሌሎች ዘንድ በእጅጉ የሚወደድ ይሆናል። በተጨማሪም ይህን ባሕርይ እያዳበርክ በሄድክ መጠን ፈገግታ ማሳየት የበለጠ ቀላል እየሆነልህ ይመጣል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለጥንቃቄ ያህል
ልባዊ ፈገግታ የሚያሳዩት ሁሉም ሰዎች አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነው። አታላዮች፣ አጭበርባሪዎች፣ ይሉኝታ ቢስ ነጋዴዎችና ሌሎች ሰዎች ማራኪ ፈገግታ ሊያሳዩ ይችላሉ። በፈገግታ ሰዎችን መማረክና በቁጥጥር ውስጥ ማዋል እንደሚቻል ያውቃሉ። አጠያያቂ ሥነ ምግባር ወይም መጥፎ የውስጥ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም ፈገግታን ሌሎችን ለማጥመድ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ሆኖም ፈገግታቸው ባዶና አሳሳች ነው። (መክብብ 7:6) ስለዚህ ሰዎችን ከልክ በላይ የምንጠራጠር ባንሆንም እንኳ በዚህ አስጨናቂ በሆነ ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ ስንኖር ልክ ኢየሱስ ራሱ እንደመከረው “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” መሆን ይኖርብናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 10:16
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎችን በፈገግታ ሰላም ለማለት ቀዳሚ ሁን