ሐዘንን መግለጽ ተገቢ ነው?
ሐዘንን መግለጽ ተገቢ ነው?
ዶክተር ኤሊዛቤት ኩብለር ሮስ ኦን ችልድረን ኤንድ ዴዝ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “እጅግ ብዙ አዋቂ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ታምቆ በኖረ የስሜት ቁስለት እየተሰቃዩ ነው። ስለዚህ ልጆች አልቃሻ ወይም ሴታ ሴት እባላለሁ የሚል ስጋት ሳያድርባቸው ወይም ‘ወንድ ልጅ አያለቅስም’ ተብለው ሳይተቹ ሐዘናቸውን መግለጽ ይገባቸዋል።”
ይህ አባባል ስሜትን መግለጽ እንደ ነውር በሚታይባቸው በአንዳንድ አገሮች ካለው አመለካከት የሚቃረን ነው።
አንድ የቀብር ሥርዓት አስፈጻሚ የታዘቡት
ንቁ! ቃለ ምልልስ ያደረገላቸው ሮበርት ጋልገር የተባሉ የኒው ዮርክ ከተማ የቀብር ሥርዓት አስፈጻሚ የሰጡት አስተያየት ይህንን ንጽጽር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ሐዘንን በመግለጽ ረገድ የአሜሪካ ተወላጅ በሆኑ ሰዎችና ከላቲን አሜሪካ በፈለሱ ሰዎች መካከል ልዩነት ተመልክተው እንደሆነ ተጠይቀው ነበር።
“በእርግጥ ተመልክቻለሁ። ይህን ሥራ በጀመርኩባቸው በ1950ዎቹ ዓመታት ከኢጣሊያ የፈለሱ በርካታ ሰዎች በአካባቢያችን ይኖሩ ነበር። ሰው ሲሞትባቸው በጣም ያለቅሱ ነበር። አሁን ከቀብር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር እንገናኛለን፤ ይሁንና እንደ ድሮው መላቀስ የለም። እምብዛም ሐዘናቸውን ሲገልጹ አይታዩም።”
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት ዕብራውያን ሐዘናቸውንና ስሜታቸውን ይገልጹ ነበር። ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ በጨካኝ አውሬ ተበልቶ ሞቷል ብሎ እንዲያምን በተደረገ ጊዜ ሐዘኑን ለመግለጽ ያደረገውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚገልጸው ተመልከት:- “ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፣ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፣ እንዲህም አለ:- ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።” (ዘፍጥረት 37:34, 35፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ያዕቆብ ስለጠፋው ልጁ ማልቀስ አላሳፈረውም።
የተለየ ባሕል፣ የተለየ የስሜት አገላለጽ
ከቦታ ቦታ የባህል ልዩነት መኖሩ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል በብዙዎቹ የናይጄሪያ አካባቢዎች ቤተሰቦች ብዙ ልጅ የሚወልዱና በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ ሞት
የተለመደ ነገር ቢሆንም በአፍሪካ የ20 ዓመት ልምድ ያላቸው አንድ ደራሲ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል:- “ልጅ በሚሞትበት ጊዜ በተለይ ልጁ በኩርና ወንድ ከሆነ በጣም ይለቀሳል። ልዩነቱ ሐዘናቸው መሪርና ለረጅም ጊዜ የማይቆይ መሆኑ ነው። ለወራትና ለዓመታት አያዝኑም።”በሜዲትራኒያን ወይም በላቲን አሜሪካ አገሮች ሰዎች ውስጣዊ ስሜትን በመግለጽ ረገድ ይሉኝታ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ያድጋሉ። ደስታቸውንም ሆነ ሐዘናቸውን አምቀው አይዙም። ሰላምታቸው በመጨባበጥ ብቻ አያበቃም፤ ከልብ ይተቃቀፋሉ። ሐዘንንም እንዲሁ በልቅሶና በእንጉርጉሮ መግለጽ የተለመደ ነው።
ካተሪን ፋር ዶንሊ የተባሉት ደራሲ እጅግ ያዘነው አባት “የልጁ ሞት ያስከተለበትን ስነ ልቦናዊ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ጮክ ብዬ ባለቅስ ሴታ ሴት እባላለሁ የሚለውንም ፍርሃት መቋቋም አለበት” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ “ልጁን በሞት ማጣቱ የሚፈጥረው ስሜት ስለሚያይል በወቅቱ ሊያሳየው ስለሚገባው ባሕርይ የወጣው ደንብ ትዝ አይለውም። እውነተኛ ውስጣዊ ስሜቱን በመግለጽ ነፍሱን በሐዘን እንባ ማጠቡ ያመረቀዘው ቁስል እንዲደርቅ ቁስሉን ከማፍረጥ ጋር ይመሳሰላል” ሲሉ አስረድተዋል።
እንግዲያው ከሌሎች አገሮች ይልቅ በአንዳንድ አገሮች ሐዘንን መግለጽ ይበልጥ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ማዘንም ሆነ ማልቀስ የደካማነት ምልክት ተደርጎ መታየት የለበትም። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ጓደኛው አልአዛር በሞተ ጊዜ ምንም እንኳን ወዲያው ከሞት እንደሚያስነሳው ቢያውቅም “እንባውን አፍስሶ” ነበር።—ዮሐንስ 11:35
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ያዕቆብ ለጠፋው ልጁ ማልቀስ አላሳፈረውም