ሰውነትን በማስጌጥ ረገድ ምክንያታዊ የመሆን አስፈላጊነት
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ሰውነትን በማስጌጥ ረገድ ምክንያታዊ የመሆን አስፈላጊነት
አንዲት ፈረንሳዊት የልብ ወለድ ደራሲ “ለቁመና ከልክ በላይ መጨነቅ አስተሳሰብን ያዛባል” ብለዋል። በእርግጥም ባለፉት መቶ ዓመታት ሰዎች ቁመናቸውን ለማሳመር ሲሉ ያደረጓቸው አብዛኞቹ ነገሮች የማሰብ ችሎታቸውን በትክክል እንዳልተጠቀሙበት ያሳያል። ለምሳሌ ያህል በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ሴቶች ወገባቸው በጣም ቀጭን እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ መተንፈስ እስኪሳናቸው ድረስ ሆዳቸውን ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ የውስጥ ልብስ ይለብሱ ነበር። አንዳንዶች የወገባቸው ቅጥነት ወደ 325 ሚሊ ሜትር ዝቅ እንዳለ ተናግረዋል። አንዳንዶቹ ሴቶች ያደርጉት የነበረው የውስጥ ልብስ በጣም ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ በመሆኑ ጎድናቸው ጉበታቸውን በስቶ ለሞት ዳርጓቸዋል።
ምንም እንኳ ይህ ፋሽን መቅረቱ አስደሳች ቢሆንም ለእንዲህ ዓይነቱ ፋሽን ምክንያት የሆነው ከልክ በላይ ለቁመና የመጨነቅ ስሜት ግን አሁንም አልጠፋም። ዛሬም ቢሆን ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ተፈጥሯዊ መልካቸውን ለመለወጥ ሲሉ አስቸጋሪ አልፎ ተርፎም አደገኛ የሆኑ ድርጊቶች ይፈጽማሉ። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል ጥሩ ሥነ ምግባር ባልነበራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይዘወተሩ የነበሩት የንቅሳትና ሰውነትን የመብሳት አገልግሎት የሚሰጥባቸው የንግድ ቤቶች በትልልቅ የገበያ ማዕከሎችና ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንዲያውም በቅርቡ የመንቀስ ሙያ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ ከመጡት የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎች መካከል ስድስተኛውን ደረጃ ይዟል።
በተጨማሪም መረን በለቀቀ ሁኔታ ሰውነትን የማስጌጥ ልማድ በተለይ በወጣቶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ጡትን፣ አፍንጫን፣ ምላስን አልፎ ተርፎም አባለዘርን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን መብሳት በከፍተኛ ሁኔታ ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል። እንዲያውም አንዳንዶች በዚህ ብቻ የሚረኩ ሆነው አልተገኙም። ሰውነትን እንደ መተኮስ፣ መሸንተፍ * እና ከቆዳ ሥር የተለያዩ ነገሮች እየከተቱ በጉልህ የሚታዩ ቀዳዳዎችና ቋሚ ሰንበሮች በመፍጠር የሰውነት ቅርጽ ማውጣትን የመሳሰሉ በጣም አስደንጋጭ የሆኑ ልማዶችን መከተልም ጀምረዋል።
ጥንታዊ ልማድ
ሰውነትን ማስጌጥ ወይም ማሳመር አዲስ ነገር አይደለም። በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች እንደ ባሕል ተቆጥሮ የሚደረግ ሰውነትን የመተኮስና የመንቀስ ልማድ የተወሰነን የዘር ሃረግ ወይም ጎሳ ለይቶ ለማሳወቅ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲሠራበት ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ አገሮች መካከል ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ጎጂ አድርገው በመመልከት እየተዉት መምጣታቸው ያስደስታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሰውነታቸውን የሚነቀሱ፣ የሚበሱና የሚሸነተፉ ሰዎች ነበሩ። በአብዛኛው አረማውያን ብሔራት ከሃይማኖታቸው ጋር በተያያዘ የሚያደርጓቸው ልማዶች ነበሩ። ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑት አይሁዳውያን የአረማውያንን ልማድ እንዳይከተሉ የከለከለበት ምክንያት ሊገባን ይችላል። ዘሌዋውያን 19:28) አይሁዳውያን የአምላክ “ልዩ ንብረት [NW ]” እንደመሆናቸው መጠን ወራዳ ከሆኑ የሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች ሊጠበቁ ችለዋል።—ዘዳግም 14:2
(ክርስቲያናዊ ነፃነት
ምንም እንኳ የሙሴ ሕግ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ የተላለፉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያቀፈ ቢሆንም ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። (ቆላስይስ 2:14) በመሆኑም ክርስቲያኖች በአጋጌጥ ረገድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሳይጥሱ ምርጫቸውን መከተል ይችላሉ። (ገላትያ 5:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ይሁን እንጂ ይህ ነፃነት የተገደበ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:16
ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስ 6:12 ላይ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ እንደ ክርስቲያን መጠን ያለው ነፃነት ለሌሎች አሳቢነት ሳያሳይ የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት እንደማይሰጠው ተገንዝቧል። ለሌሎች ያለው ፍቅር በባሕርይው ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። (ገላትያ 5:13) “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ጳውሎስ የነበረው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አመለካከት ሰውነቱን በሆነ መንገድ ለማስጌጥ ለሚያስብ ለማንኛውም ክርስቲያን ግሩም ምሳሌ ይሆነዋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች
ክርስቲያኖች ከተሰጧቸው ተልዕኮዎች አንዱ ምሥራቹን መስበክና ማስተማር ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ፊልጵስዩስ 2:15) ከዚህ የተነሳ አንድ ክርስቲያን ቁመናውን ጨምሮ ማንኛውም ነገር ሌሎች መልእክቱን እንዳያዳምጡ እንቅፋት እንዲፈጥርባቸው ማድረግ አይፈልግም።—2 ቆሮንቶስ 4:2
ምንም እንኳ በመበሳትና በመነቀስ ሰውነትን ማስጌጥ በአንዳንዶች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንዲህ በማለት መጠየቅ ይኖርባቸዋል:- ‘በዚህ መንገድ ሰውነቴን ለማስጌጥ መሞከሬ በምኖርበት አካባቢ ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል? ከአንዳንድ መረን የለቀቁ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ጋር ያስመድበኝ ይሆን? ሕሊናዬ እንዲህ እንዳደርግ ቢፈቅድልኝ እንኳ ሰውነቴን መበሳቴ ወይም መነቀሴ በጉባኤው ውስጥ በሚገኙ በሌሎች ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል? “የዓለም መንፈስ” ነጸብራቅ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩት ይሆን? “ጤናማ አስተሳሰብ” ያለኝ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያሳድር ይሆን?’—1 ቆሮንቶስ 2:12፤ 10:29-32፤ ቲቶ 2:12
ሰውነትን ለማሳመር የሚደረጉ አንዳንድ ልማዶች ከበድ ያሉ ሕክምና ነክ ችግሮች ያስከትላሉ። ንጽሕናው ባልተጠበቀ መርፌ መነቀስ ለሄፐታይተስና ለኤች አይ ቪ መዛመት አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉት ማቅለሚያዎች የቆዳ በሽታ ያመጣሉ። ሰውነትን መበሳት የሚያስከትለው ቁስል እስኪሽር ድረስ ብዙ ወራት ሊወስድ የሚችል ሲሆን የሕመም ስሜቱም የዚያኑ ያህል ሊራዘም ይችላል። በተጨማሪም የደም መመረዝ፣ መፍሰስና መርጋት እንዲሁም የነርቭ መጎዳትና ከበድ ያሉ ልክፈቶች ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም በላይ አንዳንዶቹን ለማጥፋት ቢፈለግ እንኳ በቀላሉ ማጥፋት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል አንድን ንቅሳት ለማስወገድ እንደ ስፋቱና እንደ ቀለሙ ዓይነት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና ስቃይ የሚያስከትል ተደጋጋሚ ሕክምና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ሰውነትን መበሳት የዕድሜ ልክ ጠባሳ ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
አንድ ግለሰብ እነዚህን ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ልማዶች ለመከተል መምረጥ አለመምረጡ የግል ውሳኔው ነው። ሆኖም አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው ክርስቲያን መሆን ራስን ለአምላክ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን እንደሚያካትት ይገነዘባል። ሰውነታችን አምላክ እንዲጠቀምበት የቀረበ ሕያው መሥዋዕት ነው። (ሮሜ 12:1) ከዚህ የተነሳ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሰውነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ ሊጎዱት ወይም ሊያበላሹት የሚችሉ የግል ንብረታቸው አድርገው አይቆጥሩትም። በተለይ በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ለመሥራት ብቃቱን ያሟሉ ወንዶች በሚከተሉት ልከኛ ልማድ፣ በጤናማ አስተሳሰብና በምክንያታዊነት የሚታወቁ ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3
ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ የማመዛዘን ችሎታ ማዳበራቸውና በዚያም መጠቀማቸው ‘ከእግዚአብሔር ሕይወት በጣም የራቀው’ ይህ ዓለም የሚከተለውን ራስን በራስ በመጉዳት የመደሰት አጉል ልማድ ከመከተል እንዲርቁ ይረዳቸዋል። (ኤፌሶን 4:18) እንዲህ በማድረግ ምክንያታዊነታቸው በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲታይ ማድረግ ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 4:5
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ለሕክምና ወይም መልክ ለማሳመር ተብሎ ሰውነትን በመሸንተፍና በወጣቶች በተለይ በወጣት ሴቶች በሚዘወተረው ሰውነትን የመቁረጥ ወይም የመተልተል ልማድ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። እንዲህ ዓይነቱ ሰውነትን የመተልተል ልማድ ግለሰቡ የባለሙያ እርዳታ የሚጠይቅ ከበድ ያለ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለበት ወይም በደል እንደደረሰበት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።