በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቋንቋዎች ለሐሳብ ልውውጥ እንደ ድልድይ ወይም እንደ አጥር ሊሆኑ ይችላሉ

ቋንቋዎች ለሐሳብ ልውውጥ እንደ ድልድይ ወይም እንደ አጥር ሊሆኑ ይችላሉ

ቋንቋዎች ለሐሳብ ልውውጥ እንደ ድልድይ ወይም እንደ አጥር ሊሆኑ ይችላሉ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“ማንኛውም ታሪክ ቢሆን ቋንቋውን የመመርመርን ያህል የአንድን ሕዝብ የመከራና የደስታ ታሪክ፣ ማኅበራዊ አደረጃጀት፣ እምነትና ስሜት በትክክል ሊያስገነዝብ አይችልም።”​—⁠ማርቲን አሎንሶ

የቋንቋ አመጣጥ፣ ልዩነትና እድገት በታሪክ ዘመናት ሁሉ የብዙ ምሁራንን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው። ይህም ትኩረታቸው ለቋንቋ ምስጋና ይግባውና እንደ አብዛኞቹ የታሪክ መዛግብት ተጠብቆ ቆይቶልናል። የሰው ልጅ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚጠቀምበት ዋነኛና ከፍተኛ መሣሪያ ቋንቋ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የቋንቋ ሊቃውንት በመላው ዓለም ቀበሌኛዎችን ሳይጨምር 6, 000 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ ይገምታሉ። በተናጋሪዎች ብዛት ረገድ 800 ሚልዮን ተናጋሪዎች ያሉትን የቻይና ማንዳሪን ቋንቋ የሚተካከል የለም። ከዚያ የሚቀጥሉት ብዙ ተናጋሪ ያላቸው አራት ቋንቋዎች፣ ደረጃቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው ሊሆን ባይችልም እንግሊዝኛ፣ ስፓንኛ፣ ሂንዲና ቤንጋሊ ናቸው።

የተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎቻቸው ድንገት በሚገናኙበት ጊዜ ምን ይሆናል? በአንጻሩ ደግሞ አንድ ሕዝብ ከሌሎች ተነጥሎ በሚኖርበት ጊዜ ቋንቋው ምን ይሆናል? የሐሳብ ልውውጥ ድልድዮችም ሆኑ አጥሮች እንዴት እንደሚፈጠሩ እንመልከት።

ፒጂን፣ ክሪዎል እና የሥራ ቋንቋ

ቅኝ አገዛዝ፣ በሁለት አገሮች መካከል የሚደረግ ንግድ፣ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለመኖር መገደድ ሕዝቦች የጋራ ቋንቋ በማጣታቸው ምክንያት በመካከላቸው ያለውን የቋንቋ መራራቅ የሚያገናኝ ድልድይ እንዲፈጥሩ አነሳስተዋቸዋል። በዚህ ምክንያት ለመግባባት የሚያስችል ቀለል ያለ ቋንቋ መጠቀም ይጀምራሉ። ውስብስብ የሰዋስው ሕጎችን አስወግደው ለጋራ ጉዳዮቻቸው ብቻ በሚጠቅሟቸው ጥቂት ቃላት ብቻ ይገለገላሉ። በዚህ መንገድ ፒጂን ቋንቋዎች ተፈጠሩ። ፒጂን ያልተወሳሰበ ቀላል ቋንቋ ነው ቢባልም የራሱ የሆነ የሥነ ልሳን ሥርዓት አለው። ይሁን እንጂ ለቋንቋው መፈጠር ምክንያት የሆነው ነገር ሲጠፋ ቋንቋውም ሊሞት ይችላል።

ፒጂን የአንድ ሕዝብ ዋነኛ ቋንቋ በሚሆንበት ጊዜ አዳዲስ ቃላት ይጨመሩና የሰዋስው ሥርዓት በአዲስ መልክ ይደራጃል። በዚህ ጊዜ ቋንቋው ክሪዎል ይሆናል። ክሪዎል ከፒጂን በተለየ የአንድን ሕዝብ ባሕል ያንጸባርቃል። በዛሬው ጊዜ መሠረታቸውን እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፖርቱጊዝ፣ ስዋህሊና ሌሎች ቋንቋዎችን ያደረጉ በደርዘን የሚቆጠሩ ፒጂኖችና ክሪዎሎች በመላው ዓለም ይነገራሉ። እንዲያውም አንዳንዶች በፓፑዋ ኒው ጊኒ እንደሚነገረው እንደ ቶክ ፒስንና ባቫኑዋቱ እንደሚነጋገረው እንደ ቢስላማ ያሉት በአገሮች ውስጥ ዋነኛ ቋንቋዎች ሆነዋል።

ሌሎች የሐሳብ ልውውጥ ድልድዮች የተለያዩ ሕዝቦች በጋራ የሚጠቀሙባቸው የንግድ ወይም የሥራ ቋንቋዎች ናቸው። የተለያየ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ያላቸው የተለያዩ ሕዝቦች በእነዚህ ቋንቋዎች በጋራ ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ የተለያዩ የአካባቢ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ሳንጎ በሚባል ቋንቋ እርስ በርሳቸው ይግባባሉ። ለዲፕሎማቶች ደግሞ የጋራ ቋንቋ ሆነው የሚያገለግሉት እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ናቸው። በተጨማሪም ፒጂኖችና ክሪዎሎችም የጋራ የሥራ ቋንቋ ሆነው ሊቆጠሩ ይችላሉ።

በአንድ አገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቀበሌኛ የሚባል ከብሔራዊው ቋንቋ ጋር በሚመሳሰል ቋንቋ ሊጠቀሙ ይችላሉ። አካባቢው ከሌሎች በጣም የተገለለ ከሆነ ልዩነቱ ይበልጥ የሰፋ ሊሆን ይችላል። ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ እነዚህ ቀበሌኛዎች ልዩነታቸው በጣም እየሰፋ ስለሚሄድ የተለዩ ቋንቋዎች እስከመሆን ይደርሳሉ። የቋንቋ ሊቃውንት አንድ ቋንቋ የተለየ ቋንቋ ወይም ቀበሌኛ መሆኑን መለየት የሚቸገሩባቸው ጊዜያት አሉ። በተጨማሪም ቋንቋዎች ሁልጊዜ የሚለዋወጡ በመሆናቸው ቀበሌኛዎች ሲሞቱ ከነዚሁ ቀበሌኛዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ባሕሎችና ታሪኮች አብረው ሊሞቱ ይችላሉ።

ቋንቋ መለኮታዊ ስጦታ ነው። (ዘጸአት 4:​11) ቋንቋ በአስደናቂ ሁኔታ ሊለወጥ መቻሉ ይህ ስጦታ ምን ያህል ከሁኔታዎች መለዋወጥ ጋር ሊላመድ የሚችል መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ቋንቋ ባለመኖሩ ማንኛውም ሕዝብ ቢሆን ከሌላው እንደማይበልጥ ከቋንቋ ልንማር እንችላለን። ቋንቋ እንደማንኛውም መለኮታዊ ስጦታ ሁሉ ሕዝቦች በየትኛውም አካባቢ ይኑሩ ወይም ምንም ዓይነት ባሕል ይኑራቸው በእኩልነት የተሰጠ ስጦታ ነው። ከመጀመሪያ አንስቶ የሁሉም ሕዝቦች ቋንቋዎች የተሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓላማቸውን በትክክል አሳክተዋል። ሁሉም ምንም ያህል ሰዎች ይገልገሉባቸው በእኩል ደረጃ ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው።

ታሪካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች

የሰው ልጅ አብሮ የመኖር ፍላጎት ያለው ፍጡር መሆኑን ከቋንቋ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው ሁለት ባሕሎች ግንኙነት በሚፈጥሩበት ጊዜ በባሕሎቹ መካከል የተፈጠረው ይህ ግንኙነት በቋንቋው ውስጥ ተቀርጾ ለትውልድ ይተላለፋል።

ለምሳሌ ያህል ከላቲን የተገኘ ነው የሚባለው ስፓንኛ የአረብኛ ምንጭ ያላቸው በርካታ ቃላት ያሉት መሆኑ የስፓኝ ግዛቶች በስምንተኛው መቶ ዘመን በሙስሊሞች ተወርረው የነበረ መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም ግሪክኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛና ሌሎች ቋንቋዎች በስፓንኛ ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ መመልከት ይቻላል። ከዚህም በላይ በአሜሪካ አሕጉር በሚነገረው ስፓንኛ ላይ የአሕጉሪቱ የጥንት ነዋሪዎች ያሳደሩትን ተጽዕኖ መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ በዚህ አካባቢ በሚነገረው ስፓንኛ የማዕከላዊ አሜሪካ አዝቴኮች ይናገሩ ከነበረው የናሁዋትል ቋንቋ የተገኙ ብዙ ቃላት አሉ።

የአንድን ብሔር ወይም አካባቢ ማንነት በአፍ መፍቻ ቋንቋው መለየት እንደሚቻል ሁሉ የአንድን የሰዎች ቡድን ማንነት ማለትም የሥራውን ዘርፍ፣ ባሕሉን፣ የስፖርት ወይም የወንጀል ቡድን መሆኑን ከቋንቋ አጠቃቀሙ መለየት ይቻላል። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን የቋንቋ ልዩነት ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ይህን የመሰለውን የተለየ ዓይነት ቋንቋ ሊቃውንቱ ዘይቤ ወይም የቋንቋ ፈሊጥ አንዳንዴም የቋንቋ ዘዬ ይሉታል።

ይሁን እንጂ በብሔራትና በጎሳዎች ወይም የተለየ ባሕል ባላቸው ሕዝቦች መካከል ጠላትነት በሚፈጠርበት ጊዜ ቋንቋ የሐሳብ ልውውጥ ድልድይ መሆኑ ይቀራል። በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን መራራቅ የሚያጠናክር አጥር ይሆናል።

የቋንቋዎች የወደፊት ዕጣ

የሐሳብ ግንኙነት በጣም ውስብስብ ነገር ነው። በአንድ በኩል በተለይ በመገናኛ ብዙሐን አማካኝነት በቋንቋ ምክንያት የተፈጠሩ አጥሮች የመፍረስ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሆነ ባሁኑ ጊዜ ከ7 ሰዎች መካከል አንዱ እንግሊዝኛን በዋነኛነት ወይም በሁለተኛ ደረጃ ይናገራል። በመሆኑም እንግሊዝኛ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን የሥራ ቋንቋ ሆኗል። በርካታ ሰዎች በዚህ ቋንቋ መጠቀማቸው ሰፊ የሐሳብ ግንኙነትና ጠቃሚ መረጃ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ የቋንቋ አጥሮች ለመለያየት፣ ለጥላቻና ለጦርነት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋ ቢናገር ኖሮ . . . በአገሮች መካከል በጎ ፈቃድ ይስፋፋ ነበር” ይላል። እንዲህ ያለው በጎ ፈቃድ እንዲኖር የጋራ ቋንቋ ከመጠቀም የበለጠ ለውጥ እንደሚያስፈልግ የተረጋገጠ ነው። ሕዝቦች ሁሉ አንድ ቋንቋ እንዲናገሩ ሊያደርግ የሚችለው ጥበበኛ የሆነው የቋንቋ ፈጣሪ ብቻ ነው።

አምላክ ከሰዎች ጋር ለመነጋገር የተጠቀመበት ዋነኛ መሣሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት አጥፍቶ ከሰማይ በሚገዛ በራሱ መንግሥት እንደሚተካ ይናገራል። (ዳንኤል 2:​44) ይህ መንግሥት ሁሉንም የሰው ዘሮች አንድ አድርጎ በዚች ምድር ላይ ሰላምና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ሥርዓት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋል።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:​10-13

በአሁኑ ጊዜ እንኳን ንጹሕ የሆነው መንፈሳዊ ቋንቋ ማለትም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸው እውነት ከሁሉም ቋንቋዎች፣ ብሔራትና የቀድሞ ሃይማኖቶች የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አንድ በማድረግ ላይ ነው። (ሶፎንያስ 3:​9) ስለዚህ በእርሱ አዲስ ዓለም ውስጥ በባቤል ከደረሰው ተቃራኒ በሆነ መንገድ መላው የሰው ልጅ አንድ ቋንቋ እንዲናገር በማድረግ አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቋንቋ አመጣጥ

ጥበበኛው ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ሰማይ በሚገኘው የመላእክት ዓለም ውስጥ ቋንቋ እንዲኖር አድርጓል። (ኢዮብ 1:​6-12፤ 1 ቆሮንቶስ 13:​1) የሰው ልጆችን በፈጠረበት ጊዜም የመነጋገሪያ ቃላትንና እነዚህንም ቃላት የማስፋፋት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። በጩኸትና በማጓራት የሚገለጽ ኋላ ቀር የሆነ ሰብዓዊ ቋንቋ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። ይልቁንም ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ በጽሑፍ ለመስፈር እጅግ ጥንታዊ እንደሆነ ስለሚታወቀው ስለ ሱመሪያን ቋንቋ የሚናገረውን ልብ በል:- “ከፊት፣ ከኋላና ከመሃል የሚገቡ የተለያዩ መስተዋድዳዊ ቅጥያዎች ያሉት የሱመሪያውያን ግስ ቋንቋው እጅግ የተወሳሰበ መሆኑን ያመለክታል።”

በ20ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ገደማ የሰው ልጆች እንዲሠራጩና ‘ምድርን እንዲሞሉ’ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ በመቃወም ሜሶጶጣሚያ በሚገኘው በሰናዖር ሜዳ ዙሪያ ተሰባስበው ለመኖር የባቤልን ሃይማኖታዊ ግንብ መሥራት ጀመሩ። አምላክ የጋራ ቋንቋቸውን በመዘባረቅ አደገኛና ጎጂ የሆነ እቅዳቸውን ባከሸፈበት ጊዜ የቋንቋ ልዩነት ተፈጠረ።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28፤ 11:​1-9

ሁሉም ቋንቋዎች የመጀመሪያው ቋንቋ ዝርያዎች እንደሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አያመለክትም። አምላክ በሰናዖር ብዙ አዳዲስ ቃላትንና የአስተሳሰብ ሥርዓቶችን ስላስገባ የቋንቋዎች መለያየት ሊገኝ ችሏል። በዚህም የተነሳ ሁሉም ቋንቋዎች የተገኙበትን እናት ቋንቋ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በባቤል የዓመፀኞቹን ቋንቋ ዘባርቋል