በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፕሮፓጋንዳ ወጥመድ እንዳትያዝ ተጠንቀቅ!

በፕሮፓጋንዳ ወጥመድ እንዳትያዝ ተጠንቀቅ!

በፕሮፓጋንዳ ወጥመድ እንዳትያዝ ተጠንቀቅ!

“ሞኝ ሰው ማንኛውንም ነገር ያምናል።”— ምሳሌ 14:​15 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

በማስተማርና ፕሮፓጋንዳ በማሠራጨት መካከል ይህ ነው የማይባል ትልቅ ልዩነት አለ። ማስተማር እንዴት ማሰብ እንዳለብህ ያመለክታል። ፕሮፓጋንዳ ግን ምን ማሰብ እንዳለብህ ይናገራል። ጥሩ አስተማሪዎች የአንድን ርዕሰ ጉዳይ ሙሉ ገጽታ ከማቅረባቸውም በላይ ነፃ ውይይት እንዲደረግበት ያበረታታሉ። የፕሮፓጋንዳ ሰዎች ግን የእነርሱን አመለካከት ብቻ እንድታዳምጥ ይጎተጉታሉ እንጂ ነፃ ውይይት እንዲደረግ አያበረታቱም። አብዛኛውን ጊዜ ዓላማቸውና ፍላጎታቸው በእርግጠኝነት ምን እንደሆነ አይታወቅም። ቃላትን በመሰነጣጠቅ ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ይጠቀሙባቸዋል ሌሎቹን ደግሞ ይሰውሯቸዋል። በተጨማሪም ውሸትና ከፊል እውነትነት ባላቸው ነገሮች ላይ በማተኮር ሐቁን ያጣምማሉ። ዒላማቸው የማሰብ ችሎታህን ሳይሆን ስሜትህን ማነሳሳት ነው።

የፕሮፓጋንዳ ሰው የሚያስተላልፈው መልእክት ትክክለኛና የሥነ ምግባር ድጋፍ ያለው ከተከተልከው ደግሞ ከበሬታና እውቅና የሚያስገኝልህ መስሎ እንዲታይህ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ያሉትን ብትከተል አዋቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንደምትቆጠር፣ ይህን አቋም ለመውሰድ የመጀመሪያው ሰው እንደማትሆን፣ ምቾትና የተደላደለ ኑሮ እንደምታገኝ ሊያሳምኑህ ይሞክራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉም” ከሚላቸው ሰዎች ራስህን እንዴት መጠበቅ ትችላለህ? (ቲቶ 1:​10) ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዳንዶቹን ካወቅህ የሚያጋጥሙህን መልእክቶች ወይም መረጃዎች ማመዛዘን አያቅትህም። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉህ አንዳንድ መንገዶች እነሆ።

መራጭ ሁን:- ሙሉ በሙሉ ክፍት የሆነ አእምሮ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ፈሳሽ እንደሚያሳልፍ ቧንቧ ነው። ማንም ሰው አእምሮው በመርዝ እንዲበከል አይፈልግም። በጥንት ዘመን ጥሩ አስተማሪና ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ብሏል። (ምሳሌ 14:​15) ስለዚህ መራጮች መሆን ያስፈልገናል። የሚቀርብልንን ሁሉ በጥንቃቄ መርምረን የትኛውን እንደምንቀበልና የትኛውን ደግሞ እንደምንጥል መወሰን ያስፈልገናል።

ይሁን እንጂ አስተሳሰባችንን ሊያሻሽሉልን የሚችሉ እውነታዎችን ለመቀበል እስከሚያስቸግረን ድረስ ጠባቦች ለመሆን አንፈልግም። ታዲያ ትክክለኛው ሚዛን ሊኖረን የምንችለው እንዴት ነው? አዳዲስ መረጃዎችን የምንመዝንበት መለኪያ እንዲኖረን በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ አንድ ክርስቲያን ታላቅ ጥበብ የሚያገኝበት ምንጭ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ለአስተሳሰቡ አስተማማኝ መመሪያ ይሆንለታል። በአንድ በኩል አእምሮው ክፍትና አዳዲስ መረጃዎችን የሚቀበል ነው። እንደነዚህ ያሉትን መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መለኪያነት ከመዘነ በኋላ እውነት ሆኖ ያገኘውን ነገር የአስተሳሰቡ ክፍል ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ አእምሮው ከመጽሐፍ ቅዱስ እሴቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጩ መረጃዎችን መመልከት ይችላል።

በማስተዋል ችሎታ መጠቀም:- ማስተዋል “ስል የሆነ የማመዛዘን ችሎታ” ነው። “አእምሮ አንዱን ነገር ከሌላው የሚለይበት ችሎታ ነው።” የማስተዋል ችሎታ ያለው ሰው ስውር የሆኑ አስተሳሰቦችንና ነገሮችን ተመልክቶ ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት ይችላል።

በማስተዋል ችሎታ መጠቀም “ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ” ለማታለል “በመልካምና በሚያቈላምጥ ንግግር” የሚናገሩ ሰዎችን ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል። (ሮሜ 16:​18) ማስተዋል አግባብነት የሌላቸውን ወይም አሳሳች የሆኑትን መረጃዎች አብጠርጥረህ እንድታወጣና የአንድን ጉዳይ ፍሬ ነገር እንድትለይ ያስችልሃል። ይሁን እንጂ አሳሳች የሆነ አንድን ነገር እንዴት ለይተህ ለማወቅ ትችላለህ?

ማንኛውንም መረጃ ፈትን:- የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን አስተማሪ የነበረው ዮሐንስ “ወዳጆቼ ሆይ፣ ፈትኑ እንጂ በመንፈስ ተነገረ የሚባለውን ቃል ሁሉ አትመኑ” ብሏል። (1 ዮሐንስ 4:​1 NW ) በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚያገኙትን ሁሉ እንደ ስፖንጅ ይመጣሉ። በዙሪያችን ያለውን ሁሉ አግበስብሰን መዋጥ በጣም ቀላል ነው።

ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ግለሰብ አእምሮውን ስለሚመግበው ነገር የግል ምርጫ ቢያደርግ በጣም ጥሩ ይሆናል። እኛነታችን የተመካው በምንመገበው ምግብ ላይ ነው የሚል አባባል አለ። ይህ አባባል በስጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ምግብ ረገድ ሊሠራ ይችላል። ማንኛውንም ነገር ስታነብ ወይም ስትመለከት ወይም ስታዳምጥ እውነትነት ያለው ወይም ፕሮፓጋንዳ መሆን አለመሆኑን ፈትን።

ከዚህም በላይ የማያዳላ አእምሮ እንዲኖረን ከፈለግን አዳዲስ መረጃዎችን በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ የግላችንን አስተያየት ለመፈተን ፈቃደኛ መሆን ይገባናል። የግላችን አስተያየት አስተያየት ከመሆን እንደማያልፍ መገንዘብ ይኖርብናል። አስተማማኝነቱ አስተያየቶችን በተመሠረትንበት ሃቅ እርግጠኝነት፣ በአስተሳሰባችን ጥራት፣ እንዲሁም ሥራ ላይ ልናውል በመረጥናቸው ደንቦች ወይም እሴቶች ላይ የተመካ ነው።

ጥያቄዎችን ጠይቅ:- ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ‘በሚያባብሉ ቃላት ሊያስቱን’ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። (ቆላስይስ 2:​4) ስለዚህ እኛን ለማሳመን የታሰቡ የክርክር ነጥቦች በሚቀርቡልን ጊዜ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይኖርብናል።

በመጀመሪያ የአመለካከት መጣመም መኖር አለመኖሩን መርምር። መልእክቱ የቀረበበት ዓላማ ምንድን ነው? መልእክቱ ኃይለ ቃል የሞላበትና ግለሰቦችን የሚያንቋሽሽ ከሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው? መልእክቱን ያጀበውን ኃይለ ቃል ነጥለን ብንመለከት የመልእክቱ ክብደት ምኑ ላይ ነው? በተጨማሪም ከተቻለ የተናጋሪዎቹን የቀድሞ ታሪክ ለማጣራት ሞክር። እውነት በመናገር የሚታወቁ ናቸው? በመረጃነት የተጠቀሱ “ምንጮች” ካሉ ማን ወይም ምንድን ናቸው? ያ ሰው ወይም ድርጅት ወይም ጽሑፍ በዚያ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አስተማማኝ እውቀት ወይም መረጃ አለው ብለህ የምታስበው ለምንድን ነው? ስሜት ለማነሳሳት የተደረገ ሙከራ ካለ ‘መልእክቱ ከስሜታዊነት በጠራ አመለካከት ሲታይ ምን ያህል እውነተኛ ነው?’

ብዙሐኑን የምታጅብ አትሁን:- ሁሉ ሰው የሚ​ያስበው ነገር የግድ ትክክል መሆን አለበት ብለህ የማታምን ከሆነ ለየት ያለ አስተሳሰብ ለመያዝ የሚያስችል ድፍረት ሊኖርህ ይገባል። ሌሎች ሰዎች አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ስለያዙ ብቻ አንተም ያንን ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ይኖርብሃል? አንድ አስተሳሰብ ብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ለዚያ አስተሳሰብ እውነተኝነት አስተማማኝ መለኪያ ሊሆን አይችልም። ባለፉት መቶ ዘመናት በብዙሐኑ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ከኖሩ በኋላ ስህተት መሆናቸው የተረጋገጡ አስተሳሰቦች ብዙ ናቸው። ቢሆንም ብዙሐኑን የመከተል ዝንባሌ አሁንም አልቀረም። በዘጸአት 23:​2 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት በጣም ጠቃሚ ነው። “ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል።”

እውነተኛ እውቀትና ፕሮፓጋንዳ

መጽሐፍ ቅዱስ ለጠራ አስተሳሰብ አስተማማኝ መመሪያ እንደሆነ ቀደም ሲል ተጠቅሷል። የይሖዋ ምሥክሮች አለአንዳች ማወላወል ኢየሱስ ለአምላክ “ቃልህ እውነት ነው” ሲል የተናገረውን ቃል እውነተኝነት ይቀበላሉ። (ዮሐንስ 17:​17) ይህ የሆነበት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ “የእውነት አምላክ” በመሆኑ ነው።​—⁠መዝሙር 31:​5

አዎን፣ በዚህ የተራቀቀ ፕሮፓጋንዳ በሚሠራጭበት ዘመን የይሖዋን ቃል አስተማማኝ የእውነት ምንጭ አድርገን ልንመለከት እንችላለን። ይህ ደግሞ ‘በሐሰተኛ ቃላት መጠቀሚያ’ ሊያደርጉን ከሚፈልጉ ሰዎች ይጠብቀናል።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​3 NW

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማስተዋል አግባብነት የሌላቸውን ወይም አሳሳች የሆኑትን መረጃዎች አብጠርጥረህ እንድታወጣ ያስችልሃል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ማንኛውንም ነገር ስታነብ ወይም ስትመለከት እውነትነት ያለው መሆኑን ፈትን

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አስተሳሰብ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ብቻ እውነተኛ አያደርገውም

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል አስተማማኝ የእውነት ምንጭ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን