በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዲስ አልጋ መግዛት ያስፈልግህ ይሆን?

አዲስ አልጋ መግዛት ያስፈልግህ ይሆን?

አዲስ አልጋ መግዛት ያስፈልግህ ይሆን?

በብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

መኝታ አልደላ ብሎህ ስትገላበጥ አድረህ ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ ሰውነትህ ድቅቅ እያለ ትቸገራለህ? እንደዚያ ከሆነ ችግሩ ከአልጋ ሊሆን ይችላል።

አልጋህ ወዳጅ ወይም ጠላት ሊሆንብህ ይችላል። አልጋ ላይ በሚተኛበት አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ የሕይወትህን አንድ ሦስተኛ የምታሳልፈው አልጋ ላይ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ተጀምሮ እስኪያልቅ አንድ አልጋ ብቻ ይኖርሃል ማለት አይደለም። አሁን ያለህ አልጋ በደንብ እያገለገለህ ነውን?

አዲስ አልጋ ያስፈልግሃልን?

ብዙውን ጊዜ አንድ አልጋ ጥሩ ግልጋሎት የሚሰጠው ወደ አሥር ለሚጠጉ ዓመታት ነው። በጣም ወፍራም የሆነ ሰው ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አልጋው ከአገልግሎት ውጪ ይሆንበት ይሆናል። በተጨማሪም ዕድሜህ እየገፋ ሲሄድ ፍላጎትህና ምርጫህም እንደሚለወጥ አትዘንጋ። አዲስ አልጋ ያስፈልግህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ከእንቅልፌ የምነሳው ማጅራቴን ጭምድድ አድርጎኝ ወይም ወገቤን አሞኝ ነው? አልጋዬ በጣም ጠባብ ነው? ፍራሹ የሚቆረቁር ስፕሪንግ ወይም አባጣ ጎርባጣ አለው? አልጋዬ ትንሽ በተንቀሳቀስኩ ቁጥር የሚንቋቋ ወይም ሲጥ ሲጥ የሚል ድምፅ ያሰማል? እኔና ባለቤቴ በእንቅልፍ ልባችን እየተገላበጥን ስንገፋፋ እናድራለን? የአልጋው ርብራብ ወጣ ገባ ወይም የረገበ ነው? የአልጋው እግርና ጎማው ተበልቷልን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ አዲስ አልጋ መግዛት ያስፈልግህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ሊረዳህ ይችላል።

አንድን አልጋ ጥሩ የሚያሰኘው ምኑ ነው?

ጥሩ አልጋ ምቾትና ድሎት ይሰጥሃል። አብዛኞቹ አልጋዎች ፍራሽና ፍራሽ አቃፊ ፍሬም አላቸው። ሆኖም ለምቾትህ ወሳኝ የሆነው ፍራሹ ነው። ፍራሽ የተለያዩ ክፍሎች አሉት። መጀመሪያ ሁሉን በአንድ ከትቶ የሚይዘው ልባስ ወይም የፍራሽ ጨርቅ ይገኛል። ከፍራሽ ጨርቁ ሥር ደግሞ ምቾት የሚሰጥህና የሰውነትህን ወበቅ ወደ ውስጥ የሚስብ ድርብርብ ለስላሳ ድልዳል አለ። ከዚያም በሦስተኛው ደረጃ ፍራሹን ገትሮ የሚይዝና ጥብቅ እንዲሆን የሚረዳ ጥምልል ሽቦ ወይም ስፕሪንግ ይገኛል። የተለያየ ዓይነት የፍራሽ መገተሪያዎች አሉ። ሆኖም በአብዛኛው የስፕሪንጎቹ ቁጥር በበዛና ሽቦዎቹ ወፍራም በሆኑ መጠን ፍራሹ ጥብቅና ምቹ ይሆናል። ዛሬ ዛሬ የስፖንጅ ፍራሽ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። እንደ ስፕሪንግ ፍራሽ ከባድ አይደለም።

ይሁን እንጂ ጥሩ ፍራሽ ጥሩ ግልጋሎት የሚሰጠው በተለይ ለዚያው የሚመጥን ሆኖ የተዘጋጀ ተስማሚ አልጋ ካገኘ ብቻ ነው። እንደ ሶፋም እንደ መኝታም እንዲያገለግል ተደርጎ የሚዘጋጅ አልጋ አለ። የአልጋው ፍሬም በፍራሹ ውስጥ የታመቀው አየር እንዲወጣ በማድረግ እንደ ትልቅ ሾክ አብዞርቨር ሆኖ ከማገልገሉም በላይ የፍራሹን ዕድሜ ያራዝማል። ሌላው አማራጭ ደግሞ ባለ ርብራብ አልጋ ነው። ባለ ርብራብ አልጋ ከታች ክፍት በመሆኑ ፍራሹ አየር እንዲያገኝ ያስችላል። ባለ ርብራብ አልጋ ድርቅ ያለ ሲሆን የሽቦ አልጋ ግን ያረገርጋል።

ተስማሚ አልጋ መምረጥ

አልጋ በምትገዛበት ጊዜ ልታስብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? የሠራ አልጋ የሌሎች ሰዎች ላብና ሸቀን ስለሚይዝና ተባይ ሊኖረው ስለሚችል አለርጂ፣ አስም ወይም ችፌ ሊያስከትል ይችላል። ለጤናም ሆነ ለደኅንነት ላይበጅ ይችላል።

አዲስ አልጋ ከመግዛትህ በፊት ዋጋውን፣ ጤንነትህን ወይም መጠኑን የመሳሰሉትን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት የምትመርጠውን ብታስብ ጥሩ ነው። ጥሩ አልጋ የሚሸጥባቸው ሱቆችን ዞረህ ለማየት በቂ ጊዜ ለመመደብ ሞክር፤ እንዲሁም በተቻለህ መጠን ስለ እያንዳንዱ ዓይነት አልጋ ወይም ፍራሽ በመጠየቅ በቂ መረጃ ሰብስብ። ብዙውን ጊዜ የአልጋ ዋጋ ውድ ስለሆነ ያገኘኸውን ለመግዛት አትቸኩል።

ከደከመህ ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ልትቸገር ትችላለህ። የምትወደውን ልብስ ልበስ። አልጋውን ለመሞከር አትፈር። ኮትህንና ጫማህን አውልቀህ በእያንዳንዱ አልጋ ላይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጋደም በል። ትከሻህን፣ ሽንጥህንና ወገብህን ይመችህ እንደሆነ በደንብ ለማየት በተለያየ መንገድ እየተኛህ ሞክር።​—⁠ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ለአልጋህ ጥንቃቄ ማድረግ

አልጋህን በጥንቃቄ የምትይዝ ከሆነ በእርግጥም ዕድሜውን ያራዝምልሃል። ሻጩ ምክር እንዲሰጥህ መጠየቅ የምትችል ሲሆን የፋብሪካውን የጥንቃቄ መመሪያ ሥራዬ ብለህ አንብብ። አዲሱን አልጋህን ይዘህ ቤት እንደደረስክ ከተጠቀለለበት አውጣው። እንደዚህ ማድረጉ በእርጥበት ኃይል ሻጋታ እንዳይዝና እንዳይበሰብስ ለመከላከል ይረዳል። ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦችን እነሆ።

● አዲስ ስፕሪንግ ፍራሽ ከገዛህ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ የላይኛውን ወደ ታች ገልብጠው እንዲሁም የራስጌውን ወደ ግርጌ አዙረው። በኋላም በየሦስት ወሩ እንዲሁ አድርግ። ይህም ፍራሹ በሁሉም ወገን የተስተካከለ እንዲሆንና አባጣ ጎርባጣ እንዳይኖረው ይረዳል። የወገብ ህመም ካለብህ በየጊዜው መገልበጥ የማያስፈልገው የስፖንጅ ፍራሽ ቢኖርህ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

● ፍራሽን ማጠፍ ወይም መጠቅለል ጥሩ አይደለም። በምትገለብጥበት ጊዜ ጨርቁ እንዳይሸበሸብብህና እንዳይከብድህ እጀታውን ይዘህ ቀና አድርግ።

● ጠዋት ጠዋት መኝታህ እንዲናፈስና የሰውነትህ ወበቅ እንዲወጣ ብርድ ልብሱንና አንሶላዎቹን ገላልጠህ ለ20 ደቂቃ አቆየው።

● ሊታጠብ የሚችል ሌላ የፍራሽ ጨርቅ በማሰፋት የፍራሽህን ንጽሕና መጠበቅ ትችላለህ። በየጊዜው ከፍራሹም ሆነ ከርብራቡ ላይ አቧራውን ካራገፍክ በኋላ የነካው ቆሻሻና የፈሰሰበት ነገር ካለ ቶሎ ብለህ በሳሙናና በቀዝቃዛ ውኃ አስለቅቅ።

● በፍራሹ ጠርዝ ላይ ሁልጊዜ አንድ ቦታ ላለመቀመጥ ጥረት አድርግ። ልጆችም ሆኑ ሌላ ሰው አልጋው ላይ እንዲዘል አትፍቀድ።

አልጋህ ከሚሰጥህ ጥቅም አንጻር ሲታይ የቱንም ያህል ወጪ ብታወጣበት የሚያስቆጭ አይሆንም። ለአልጋ የምታወጣው ወጪ ለሕይወትህ አንድ ሦስተኛ የሚውል ነው። ይህ ደግሞ በቀሪው ሁለት ሦስተኛው ሕይወትህ ላይ የማይናቅ አስተዋጽዖ አለው። ድጋፍ ሰጪ ወዳጅህን በጥንቃቄ የምትመርጥና የምትይዝ ከሆነ በአጸፋው ጥሩ አገልግሎት ታገኛለህ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሚመችህ አልጋ የትኛው ነው?

ምቾትና ድሎት። ፍራሽ ምቾት እንዲሰጥህ ካስፈለገ እንደ ሳንቃ ደረቅ መሆን የለበትም። እንዲያውም አንድ አልጋ ከመጠን በላይ ድርቅ ያለ ከሆነ የወገብ ህመም ሊያስከትል እንደሚችል ይታመናል። ምቾት የሚሰጥህ የትኛው አልጋ እንደሆነ ሰውነትህ ይንገርህ። በጀርባህ ተንጋለህ ተኛ። እጅህን በጀርባህና በአልጋው መካከል ባለው ክፍተት ስትሰድ እጅህ ልክክ የሚል ከሆነ እንዲሁም በቀላሉ መገላበጥ የምትችል ከሆነ የፍራሹ ጥብቀት ለአንተ ተስማሚ ነው ማለት ነው። ምቹ ፍራሽ በጎንህ ስትተኛ ጀርባህ እንዲጎብጥ አያደርግም። ወፍራም ሰው ትንሽ ጠበቅ የሚል ፍራሽ ያስፈልገዋል።

መጠን። እንደልብ መገላበጥ የሚያስችልህ አልጋ ምረጥ። ሁለት ሰዎች አብረው የሚተኙበት ከሆነ ሁለት ሰው እንደ ልብ ማስተኛት የሚያስችል ስፋት ሊኖረው ይገባል።

የሚመጣጠን አልጋና ፍራሽ። የሚቻል ከሆነ በሚገባ እንዲመጣጠን ተደርጎ ለአንተ ምቾትና ድሎት በሚስማማ መንገድ አንድ ላይ የተዘጋጀ አልጋና ፍራሽ ብትገዛ ይመረጣል። አዲሱን ፍራሽ በአሮጌ አልጋ ላይ የምትጠቀም ከሆነ ፍራሹን ሊጎዳብህ ብሎም ሻጩ የገባውን ዋስትና ሊያሳጣህ ይችላል።

ዋጋ። ብዙ ጊዜ የአልጋው ጥራት በምትከፍለው ገንዘብ መጠን ይመካል። ስለዚህ አቅምህ በፈቀደ መጠን ምርጥ አልጋ ግዛ።

ቦታ። የቦታ ጥበት ካለ የሚታጠፍና ወደ ግድግዳ የሚገባ አልጋ ቢኖርህ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሌላው አማራጭ ደግሞ ማታ ማታ በቀላሉ ወለል ላይ ልትዘረጋው የምትችለውን የጥጥ ፍራሽ ማሠራት ነው። ወይም እንደ ሶፋም እንደ አልጋም እንዲያገለግል ሆኖ የተዘጋጀውን መግዛት ይቻላል።

የጤና ችግር። በተለመደው አልጋ ላይ ስትተኛ ምቾት የማይሰማህ ከሆነ አተኛኘትህን በመቀያየር እንደሚመችህ ልታስተካክለው የምትችለው አልጋ ጥሩ ሊሆን ይችላል። የውኃ ፍራሽ የሰውነትህን ክብደት አደላድሎ ስለሚይዝ የመኝታ አለመመቸት ችግር ላለባቸው አንዳንድ ሰዎች ሊረዳ ይችላል።

የአለርጂ ችግር። ለብናኝ ወይም ለጥጥ አለርጂ ከሆንክ የፋብሪካ ውጤት በሆነ የማይበን ጭረት የተሞላ ፍራሽ ወይም ስፖንጅ ፍራሽ ጥሩ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ባለ ርብራብ የሆነ አልጋ ወይም ውኃ ፍራሽ አለርጂ የሚያስከትሉ ነገሮች ስለማይዝ ይህንንም ግምት ውስጥ ማስገባቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

በዕድሜ የገፉ ሰዎች። አልጋው ጠርዝ ላይ ስትቀመጥ እግርህ መሬት መንካት አለመንካቱን እርግጠኛ ሁን። ደረቅ ፍሬም ያለው አልጋ ስትወጣም ሆነ ስትወርድ እንዳትቸገር ሊረዳህ ይችላል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለጥንቃቄ ያህል

▪ እሳትን የሚቋቋም የሌሊት ልብስ ለብሰህ ተኛ።

▪ መኝታህ አቅራቢያ እሳት ወይም ማሞቂያ አለመኖሩን እርግጠኛ ሁን።

▪ የኤሌክትሪክ ሙቀት መስጫ ብርድ ልብስ የምትጠቀም ከሆነ ጨርቁ እንዳልነተበ፣ እንዳልተጨማተረ፣ የመለብለብ ምልክት እንደሌለው እንዲሁም የኤሌክትሪክ ገመዱ እንዳልተላጠ ሁልጊዜ አረጋግጥ። ብርድ ልብሱን እርጥብ ሳለ አትልበሰው፤ ከዚህ ይልቅ እስኪደርቅ ጠብቅ። ብርድ ልብሱ በርቶ እያለ ከባድ እቃዎችን አታስቀምጥበት።

▪ የሞቀ ውኃ መያዣ ላስቲክ በጣም እየፈላ ባለ ውኃ አትሙላ፤ ወይም በኤሌክትሪክ ሙቀት መስጫ ብርድ ልብስ ውስጥ አትጨምር። አልጋው ላይ የሚተኛ ልጅ ካለ አስቀድማችሁ አውጡት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የፍራሽ ጨርቅ

በአልማዝ ቅርጽ የተሰፋ ድልዳል

ማይክሮክዊልቲንግ

ቁልፍ

ንብርብር ለስላሳ ድልዳል

የውስጥ መገተሪያ

ስፖንጅ

ጥልፍልፍ ስፕሪንጎች

ክፍት ስፕሪንጎች

ንጥልጥል ስፕሪንጎች

[ምንጭ]

Reproduced by courtesy of the Sleep Council

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Reproduced by courtesy of the Sleep Council