በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወዠቡ ማግስት በፈረንሳይ የተካሄደ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ከወዠቡ ማግስት በፈረንሳይ የተካሄደ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ከወዠቡ ማግስት በፈረንሳይ የተካሄደ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ፈረንሳይ የሚገኘው የንቁ ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ፍሮንሷዝ ለምድጃው የሚሆን እንጨት ለማምጣት በሩን ከፈተች። “ዓይኔን ማመን አቃተኝ። ደጃፉ ድረስ ውኃ ሞልቷል፤ በአትክልት ቦታው መግቢያ በኩል ደግሞ ኃይለኛ ጎርፍ እየመጣ ነበር” ስትል ታስታውሳለች። ባለቤቷ ትዬሪ እስከ አንገቱ የሚደርሰውን ጎርፍ አቋርጦ ከጋራዥ መሰላል ይዞ መጣ። ሁሉም ኮርኒሱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ትዬሪ ጣራውን ቀድዶ ከፈተው። ባልና ሚስቱ እንዲሁም ሦስቱ ልጆቻቸው በውኃ በስብሰውና በፍርሃት ተውጠው የሚያድናቸው እስኪደርስላቸው ድረስ አራት ሰዓት ሙሉ ሲጠባበቁ ቆዩ። በመጨረሻ የፈረንሳይ ፖሊስ ሄሊኮፕተር አይቷቸው ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ቦታ ወሰዳቸው።

በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ሞልተው የፈሰሱት ወንዞች ግድቦችንና ድልድዮችን አፈራርሰዋል። አንዳንዴ ከ10 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ጭቃ የሞላው ጎርፍ በፊቱ የሚያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ወስዷል። ከመኪናቸው መውጣት አቅቷቸው አሊያም በተኙበት ሰጥመው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ30 ይበልጣል። ከሞት የተረፈች አንዲት ሴት አስደንጋጭ የሆነውን የኅዳር ወር ምሽት “ከመጨረሻው ዘመን” ጋር አመሳስላዋለች። ሦስት መቶ ሃያ ዘጠኝ ከተማዎችንና መንደሮችን ያቀፈው መላው የደቡብ ምዕራባዊ ፈረንሳይ ክልል የአደጋ ቀጣና እንደሆነ ታወጀ።

ከዚያም የከፋ ሊመጣ ነው

ደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ከደረሰበት አደጋ ገና ሳያገግም ሌላ የተፈጥሮ አደጋ ተከሰተ። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የተፈጠረ በጣም ዝቅተኛ የከባቢ አየር ግፊት ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ አስነሳ። የመጀመሪያው ዓውሎ ነፋስ ሰሜናዊውን ፈረንሳይ በታኅሣሥ 26, 1999 የመታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቀጣዩ ቀን ምሽት በደቡባዊው ክፍል ላይ ጥፋት አደረሰ። የነፋሱ ፍጥነት በሰዓት ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሆነ ተመዝግቧል። ይፋዊ ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ፈረንሳይ ቢያንስ ከ17ኛው መቶ ዘመን ወዲህ እንዲህ ባለ ዓውሎ ነፋስ ተመትታ አታውቅም።

ኤሌን ዓውሎ ነፋሱ በተነሳበት ወቅት የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። “በጣም ፈርቼ ነበር” ስትል ታስታውሳለች። “ባለቤቴ በሞተር ቢስክሌቱ ወደ ቤት እየመጣ ነበር፤ ውጭ በአየር ላይ የሚበሩ የዛፍ ቅርንጫፎች ይታዩኝ ነበር። ልጁን ሳያይ መሞቱ ነው ብዬ አሰብኩ። ባለቤቴ ገና ቤት ከመድረሱ ቤታችን በውኃ መጥለቅለቅ ጀመረ። በመስኮት በኩል ዘልለን ወጣን።”

ፈረንሳይ ውስጥ ሰጥመው አሊያም የጣራ ጡብ፣ ጭስ ማውጫ ወይም ዛፍ ወድቆባቸው 90 የሚያክሉ ሰዎች ሞተዋል። በነፍስ አድን ሥራ የተሰማሩትን በርካታ ሲቪል እና ጦር ሠራዊት ጨምሮ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ክፉኛ ተጎድተዋል። በተጨማሪም ዓውሎ ነፋሱ አጎራባች አገሮችን የመታ ሲሆን በብሪታንያ፣ በጀርመን፣ በስፔይን እና በስዊዘርላንድ ከ40 ሰዎች በላይ ሞተዋል።

ያደረሰው ጥፋት

ከ96ቱ የፈረንሳይ ክልላዊ መሥተዳድሮች መካከል 69 የሚሆኑት “በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ቦታዎች” እንደሆኑ በይፋ ተገልጿል። በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት ወደ 70 ቢልዮን ፍራንክ (11 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር) እንደሚጠጋ ተገምቷል። በአንዳንድ ከተማዎች፣ መንደሮችና ወደቦች ላይ የደረሰውን ጥፋት የተመለከቱ ሰዎች የጦርነት ቀጣና የሆኑ አካባቢዎችን አስታውሷቸዋል። መንገዶችና የባቡር ሀዲዶች መሬት ላይ በወደቁ ዛፎች ወይም የኤሌትሪክ ምሰሶዎች ተዘግተዋል። የቤት ጣሪያዎች ተገነጣጥለዋል፣ የግንባታ ክሬኖች ተሰባብረው ወድቀዋል እንዲሁም ጀልባዎች ወደቡ ላይ ተሽቀንጥረው ወድቀዋል። የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችና የፍራፍሬ እርሻዎች በመውደማቸው ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ አትክልተኞች መተዳደሪያቸውን አጥተዋል።

ዓውሎ ነፋሱ በደን የተሸፈኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሄክታሮችን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በማውደም በፈረንሳይ በሚገኙ ጫካዎችና ፓርኮች ላይ ከፍተኛ ጥፋት አስከትሏል። የፈረንሳይ ብሔራዊ የደን ቢሮ ባለው መሠረት በግምት 300 ሚልዮን ዛፎች ወድመዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ያሳለፉ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ዛፎች ተገንድሰዋል አሊያም እንደ ማገዶ እንጨት ተሰባብረዋል። በአኪቴን እና ሎሬን ደኖች ውስጥ ነፋሱ ያለፈበት አቅጣጫ እንደ መቀነት ያለ ሰፊ ጥርጊያ ፈጥሯል።

በደን ጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማራው የይሖዋ ምሥክሩ ቤርናር እንዲህ ብሏል:- “ወዠቡ ካለፈ በኋላ ወደ ጫካው ሄድኩ። ሁኔታው በጣም አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ ባለሁበት ፈዝዤ ቀረሁ! እዚህ የሚኖሩ 80 በመቶ የሚሆኑት የጉባኤያችን አባላት የሚተዳደሩት በደኑ ነው። ሰዎች በተለይ ደግሞ አረጋውያን በጣም ተደናግጠዋል።” በቬርሳይ ቤተ መንግሥት ካሉት ዛፎች መካከል 10, 000 የሚያክሉት ተገንድሰዋል። ኃላፊ ከሆኑት አትክልተኞች አንዱ “የፓርኩን የቀድሞ ገጽታ ለመመለስ ሁለት መቶ ዓመታት ይወስዳል” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

የኤሌትሪክ መስመሮች በመውደቃቸው ምክንያት ከአንድ ስድስተኛ በላይ የሚሆነው የፈረንሳይ ሕዝብ መብራት አጥቷል። ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወዠቡ ከደረሰ በኋላ ለሁለት ሳምንት ያህል መብራትም ሆነ የስልክ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ነበር። አንዳንድ ትንንሽ መንደሮች ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር። ከጉድጓድ ውኃ መቅዳትና ሻማ መጠቀም የተገደዱ ቤተሰቦች 21ኛው መቶ ዘመን ደፍ ላይ እንዳሉ ከማሰብ ይልቅ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ያሉ ሆኖ ተሰምቷቸዋል።

ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ሕንፃዎች፣ ጥንታዊ ቤቶችና ካቴድራሎችም ከወዠቡ አላመለጡም። አሥራ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾችን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖታዊ ሕንፃዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የጉባኤ ስብሰባዎች የተካሄዱት በሻማ ወይም በፋኖስ ነበር።

በግምት ወደ 2, 000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ወዠቡ በንብረታቸው ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ይህም ከዛፎች መገንደስ ወይም ከቤት ክዳኖች መነቀል አንስቶ ወንዞች እስከ አፍጢማቸው ሞልተው በመፍሰሳቸው ምክንያት ቤታቸው እስከ መፈራረስ ደርሷል። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሻሮንት ክልል የ77 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ የይሖዋ ምሥክር ምንም ማድረግ ያልቻለችው ሚስቱ እያየችው ወንዙ ውስጥ ሰጥሟል። ሌሎች ደግሞ ከሞት ለጥቂት ተርፈዋል። የ70 ዓመቱ ዢልቤር እንዲህ ሲሉ ያስታውሳሉ:- “ከሞት መትረፌ ተአምር ነበር። በሩ በድንገት ተበረገደና ከፍተኛ ኃይል ያለው ውኃ መጉረፍ ጀመረ። ወዲያው አንድ ሜትር ተኩል በሚደርስ ውኃ መንሳፈፍ ጀመርኩ። ቁም ሣጥኑ ላይ ተንጠላጥዬ ተረፍኩ።”

አስፈላጊውን እርዳታ መስጠት

የወዠቡ መከሰት በፈረንሳይም ሆነ በመላው አውሮፓ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የትብብር መንፈስ አስገኝቷል። ለ ሚዲ ሊብር የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ብሏል:- “ድርጊቱ የተከናወነው በራስ አነሳሽነትም ሆነ በወዳጅነት ወይም ከሕሊና የተነሳ በጎ አድራጎት መፈጸም ግዴታ የሚሆንበት ወቅት አለ።”

ወዲያው ወዠቡ እንዳለፈ በአካባቢው የሚገኙ ጉባኤዎች አባላትን እንዲሁም ሌሎች በተፈጥሮ አደጋው የተጎዱትን ለመርዳት የይሖዋ ምሥክሮች የነፍስ አድን ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። መደበኛ ሥራቸው የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት የሆነው የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች የፈቃደኛ ሠራተኛ ቡድኖችን አቋቋሙ። በኅዳር ወር በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ከተነሳው ወዠብ በኋላ ለአደጋው ከተዳረጉት ሰዎች ጋር ሆነው ቤቶቻቸውን ያጥለቀለቀውን ጭቃ እና ውኃ አብረው በማጽዳቱ ተግባር 3, 000 የይሖዋ ምሥክሮች በነፍስ ማዳንና በማጽዳት ሥራ ተካፍለዋል። በአንዳንድ መንደሮች ውስጥ በቅድሚያ ከደረሱት ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። ምሥክሮቹ እንደ ትምህርት ቤት፣ ፖስታ ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ የአረጋውያን መኖሪያ ቤት የመሳሰሉ የሕዝብ መገልገያ ሕንፃዎችንና አልፎ ተርፎም የመቃብር ቦታዎችን አጽድተዋል። በአብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች ከነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር በቅንጅት ሠርተዋል።

ሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ሰው እርዳታ ተሰጥቷል። አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል:- “በመንደሩ ያሉ የአንድ ቄስ መኖሪያ፣ ምድር ቤቱን በማጽዳት ረድተናቸዋል።” የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ያደረጉላቸው ሌሎች ሰዎችን በተመለከተ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “ሰዎች እነሱን ለመርዳት ከሰማይ የወረድን ነው የመሰላቸው።” አንድ ባለሥልጣን “ስለ ወንጌሉ ያላቸውን ግንዛቤና ጎረቤቶቻቸውን እንዴት እንደሚረዱ እንድታስተውሉ ያስችላችሁ ይሆናል። እርዳታ ለመስጠት የመጡት ሰዎች ወንጌሉንም ሆነ ሃይማኖታቸውን በተግባር ያሳዩ ይመስለኛል” ብለዋል። ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች:- “ልባችሁ ወደ ቦታው ሄዳችሁ በዚህ መንገድ እርዳታ እንድትሰጡ ያነሳሳችኋል። ለጎረቤቶቻችን አንድ ነገር ማድረግ መቻላችን በእርግጥ አስደስቶናል።”

በታኅሣሥ ወር በተከታታይ ከተከሰተው ከባድ ዓውሎ ነፋስ በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ለበርካታ ቀናት ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር መገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ባሉ ሽማግሌዎች ተቆጣጣሪነት አስቸኳይ የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ተደራጀ። የተዘጉ መንገዶችና የተበላሹ የስልክ መስመሮች አንዳንድ ጊዜ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኙ ወዳጆች ጋር መገናኘት እንዳይቻል እንቅፋት ፈጥረው ነበር። አንዳንድ ምሥክሮች ግንኙነታቸው ተቋርጦ የነበረውን የጉባኤያቸውን አባሎች ለመርዳት ሲሉ በሚገነደሱ ዛፎች የመመታት አደጋ እያለም እንኳ የወደሙ ደኖችን በእግር ወይም በቢስክሌት አቋርጠው ሄደዋል። የፈቃደኛ ሠራተኞች በድጋሚ ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍትን፣ የመዝናኛ ቦታዎችንና የጎረቤቶቻቸውን ቤቶች እንዲሁም የተዘጉ የጫካ መንገዶችን በመክፈት በትጋት ሠርተዋል።

“በፍቅር መከበብ”

የተፈጥሮ አደጋው በብዙዎቹ በተለይ ደግሞ በልጆችና በአረጋውያን ላይ ከፍተኛ የስሜት መቃወስ አድርሷል። ቤታቸው የፈረሰባቸው ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ኑሮአቸውን መልሰው ለመገንባት ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድባቸው ሲሆን የቤተሰባቸውና የጓደኞቻቸውን ድጋፍ ማግኘትም ያሻቸዋል። በኦድ ክልል ከተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በኋላ የአእምሮ ሕክምና ጊዜያዊ ኮሚቴ አባል፣ ዶክተር ጋብሪኤል ኮተ እንዲህ ብለዋል:- “የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ሰው አባል ከሆነበት ሃይማኖታዊ ቡድን የሚሰጥ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።”

የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ መስጠት ሥነ ምግባራዊም ሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ እንደሆነ ይቆጥሩታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል [በእውነተኛው የክርስቲያን ኅብረተሰብ] መለያየት እንዳይሆን። . . . አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 12:​25, 26

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው በአሁኑ ጊዜ የአንዲት የምታምር ልጅ እናት የሆነችው ኤሌን እንዲህ ትላለች:- “ወዠቡ ካለፈ በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የተበለሻሸውን ሁሉ በማስተካከል ሊረዱን ወደ ቤታችን መጥተዋል። ይባስ ብሎም በወዠቡ የተጎዱ የይሖዋ ምሥክሮችም ሊረዱን መጥተዋል። እርዳታ ያደረጉልን በራሳቸው ተነሳሽነትና ከልባቸው መሆኑ በጣም የሚደነቅ ነበር!”

በጎርፉ ሳቢያ ቤቷ የፈረሰባት ኦዴት የምትባል የይሖዋ ምሥክር ስለ እምነት ጓደኞቿ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “በጣም አጽናንተውኛል። የተሰማኝን ስሜት እንዴት ብዬ እንደምገልጸው አላውቅም። በተደረገልኝ ነገር ሁሉ ስሜቴ እጅግ በጥልቅ ተነክቷል።” ሌላ እህት ደግሞ ከተሰማት የአድናቆት ስሜት የተነሳ “በእርግጥ በፍቅር ተከብበናል!” ስትል የብዙዎችን ስሜት ጠቅለል አድርጋ ገልጻለች።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ጥቁር ማዕበል”

ወዠቡ ከመከሰቱ በፊት ታኅሣሥ አጋማሽ ላይ ኤሪካ የሚባለው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከፈረንሳይ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ 10, 000 ቶን ነዳጅ እንደያዘ ባሕር ውስጥ ሰጠመ። ከብሪታኒ እስከ ቮንዴ የሚደርሰው ወደ 400 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የባሕር ዳርቻ ተበከለ። ማዕበሉ ዘይቱን በማናወጥ እንዲበጣጠስና ብክለቱ እንዲስፋፋ በማድረግ ይህን ስነ ምህዳራዊ ጥፋት ከማባባሱም በላይ ዘይቱን ከውኃው ለመለየት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣትና ጎልማሳ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይህን የማጣበቅ ባሕርይ ያለው ነዳጅ ከዓለቶችና ከአሸዋ ላይ ለማጽዳቱ ሥራ ድጋፍ ለመስጠት ከመላው ፈረንሳይ መጥተዋል።

አደጋው በባሕር ላይ ከፍተኛ ብክለት አስከትሏል። በዚህ ምክንያት የኦይስተርና የሼልፊሽ ኢንዱስትሪዎች ክፉኛ ተጎድተዋል። የስነ አዕዋፍ ተመራማሪዎች እንዳሉት ከሆነ እንደ ፐፊን፣ ገርቢ፣ ጋኔትና በተለይ ደግሞ ጉሊሞት የመሳሰሉ ቢያንስ 400, 000 የሚያህሉ የባሕር አዕዋፋት አልቀዋል። ይህም በመጋቢት 1978 አሞኮ ካዲዝ የተባለው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከብሪታኒ ራቅ ብሎ በሰጠመ ጊዜ ከሞቱት የአዕዋፋት ቁጥር በአሥር እጥፍ የሚበልጥ ነው። አብዛኛዎቹ አዕዋፋት ክረምቱን በፈረንሳይ የወንዝ ዳርቻዎች ለማሳለፍ ከእንግሊዝ፣ ከአየርላንድና ከስኮትላንድ የመጡ ነበሩ። የሮችፎርድ የአእዋፍ ጥበቃ ማኅበር ዲሬክተር እንዲህ ብለዋል:- “ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለ የነዳጅ ብክለት ነው። እስከዛሬ ካጋጠመን ሁሉ እጅግ የከፋ ነው። . . . ጥቂት ቁጥር ያላቸው የወፍ ዝርያዎች ከፈረንሳይ የባሕር ዳርቻዎች ይመናመናሉ ይባስ ብሎም ይጠፋሉ የሚል ስጋት አድሮብናል።”

[ምንጭ]

© La Marine Nationale, France

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኩዛክ ዶድ እንደተደረገው ሁሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሄሊኮፕተር እርዳታ መትረፍ ችለዋል

[ምንጭ]

B.I.M.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድምጥማጡ በጠፋ የወይን እርሻ መሃል አቋርጦ ያልፍ የነበረው ከጥቅም ውጭ የሆነ የባቡር ሀዲድ

[ምንጭ]

B.I.M.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየቦታው ወዳድቀው የሚታዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተጨፈላለቁ መኪናዎች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቪልዴኝ ውስጥ ይህ ሰው መውጫ አጥቶ ለሰባት ሰዓት ያህል ቆይቷል

[ምንጭ]

J.-M Colombier

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክረዝ ዲፓርትመንት እንደ ማገዶ እንጨት ተቆራረጠው የወደቁ የጥድ ዛፎች

[ምንጭ]

© Chareyton/La Montagne/MAXPPP

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቬርሳይ ቤተ መንግሥት መናፈሻ ብቻ 10,000 ዛፎች ተገንድሰዋል

[ምንጭ]

© Charles Platiau/Reuters/MAXPPP

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ሰ ፒዬር ሱር ዲቭ፣ ኖርሞንዲ ይህን ትመስል ነበር

[ምንጭ]

© M. Daniau/AFP

[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን በላ ረዶርት የአረጋውያንን መኖሪያ ቤት (ከላይ) እና በሬሳክ ዶድ የሚገኘውን ማዘጋጃ ቤት ሲያጸዳ (በስተቀኝ)