በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“ሚስጥራዊ ቫይረስ”

“በዓለም ዙሪያ አንድ ሚስጥራዊ ቫይረስ ለሕክምና የሚለገሰውን ደም እየበከለው ነው” ሲል ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። “ይህ ‘ቲቲ’ የተባለ ቫይረስ አደገኛ ይሁን አይሁን እስካሁን ለማወቅ የተቻለ ባይሆንም የጉበት በሽታ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ።” ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በደሙ ውስጥ በተገኘበት አንድ ጃፓናዊ ታካሚ ስም የመጀመሪያ ፊደላት ቲቲ ተብሎ የተሰየመው ይህ ቫይረስ “በደም ለጋሾችም ሆነ ደም በወሰዱ የጉበት በሽተኞች ላይ” ተገኝቷል። እንዲያውም አንድ ጥናት እንዳመለከተው በካሊፎርንያ ኤች አይ ቪንና ሄፓታይተስ ቢ እና ሲን ጨምሮ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ካልተገኘባቸው 102 ደም ለጋሾች መካከል 8ቱ ይህ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። የኢንፌክሽን መጠኑ በብሪታንያ 2 በመቶ፣ በፈረንሳይ ከ4 እስከ 6 በመቶ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከ8 እስከ 10 በመቶና በጃፓን 13 በመቶ እንደሆነ ተገምቷል። “በዓለም ዙሪያ በቲቲ ቫይረስ ላይ ጥናት እያካሄዱ ያሉት” ሳይንቲስቶች ይላል ጽሑፉ፣ “ሽብር ላለመፍጠር ጥንቃቄ” ቢያደርጉም እንኳ “ቫይረሱ በጤና ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ችግር መኖር አለመኖሩን ለማወቅ” ጥረት እያደረጉ ነው።

በሕንድ እየደረሰ ያለ “ስውር አደጋ”

“በሕንድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጤናና በደኅንነት አጠባበቅ ረገድ መሻሻል የታየ ቢሆንም እንኳ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሁንም ድረስ ‘ስውር አደጋ’ ሆኖ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል” ሲል ዘ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ ዘግቧል። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሚያስከትለው የጤና ችግርና የምርት መጓደል ሳቢያ ሕንድ ከ230 ሚልዮን ዶላር በላይ ታጣለች። ዘገባው እንደሚለው ከሆነ ከአራት ዓመት በታች ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት የሕንድ ሕፃናት መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው፣ ከሚወለዱት ሕፃናት መካከል 30 በመቶዎቹ “የሰውነታቸው ክብደት በጣም ዝቅተኛ” ነው፣ እንዲሁም 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ደም ማነስ አለባቸው። በዓለም ባንክ የማህበራዊ እድገት ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት ሚራ ቻተርጂ “የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የግለሰቦችንና የቤተሰቦችን ሕይወት ማቃወስ ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ከሚውለው ኢንቨስትመንት የሚገኘው ውጤት እንዲቀንስ ያደርጋል እንዲሁም ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ደንቃራ ይሆናል” ብለዋል።

በዓመፅ ድርጊት የተሞሉ የቪዲዮ ጨዋታዎች

በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ የሚገኘው የሳይመን ፍሬዘር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ተመራማሪው ብሬንት ስታፎርድ የቪዲዮ ጨዋታዎች በሚጫወቱ 600 ልጆች ላይ የተካሄደውን ጥናት መሠረት በማድረግ ብዙዎቹ ጨዋታዎች “ልጆቻችን በዓመፅ እንዲደሰቱ እያሠለጠኗቸው” ነው በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ማክሊንስ የተባለ መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው “ከፍተኛ ዓመፅ የሞላባቸውንና እውነት መስለው የሚታዩ ጨዋታዎችን የሚመርጡ አንዳንድ ሱሰኛ ተጫዋቾች በአንድ ምሽት እስከ 1, 000 የሚደርሱ ‘የሰው ምሥሎችን’ ‘ይገድላሉ።’ ብዙውን ጊዜም ጨዋታው ደም መፋሰስ የሚታይበት ትዕይንት ነው።” ዓመፅ የሞላባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች የተጫዋቹን ቀልብ እንዲስቡና “የልጆች አእምሮ ለዓመፅ አልፎ ተርፎም ለግድያ የደነዘዘ እንዲሆን ለማድረግ” ምን ያህል ታስቦባቸው የሚዘጋጁ እንደሆኑ ምርምሩ አረጋግጧል። የቪዲዮ ጨዋታ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ 17 ቢልዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ሲሆን “ለፊልምና ለቴሌቪዥን ወጪ የሚደረገው ገንዘብ በአንድነት ቢደመር እንኳ ይህን አኃዝ አያክልም።” ወላጆች ልጆቻቸው የሚጫወቱት ጨዋታ ምን ዓይነት እንደሆነ ማወቅ እንዳለባቸውና የኃይል ድርጊት ለመፈጸም የመገፋፋት አዝማሚያ ይታይባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ በንቃት መከታተል እንደሚገባቸው ስታፎርድ አጥብቀው አሳስበዋል።

ደስታ የሌላቸው ቄሶች?

ባለፉት ስድስት ዓመታት የፈረንሳይ ኅብረተሰብ ለቄሶች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ሦስት ጊዜ ጥናት ተካሂዶ ነበር። ላ ክርዋ በተባለው የካቶሊክ ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣው ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው 45 በመቶ የሚሆኑት የፈረንሳይ ሰዎች ቄሶች ደስታ ወይም እርካታ ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚል አመለካከት የላቸውም። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች አሁንም ቄሶች ወዳጃዊ ስሜት እንዳላቸውና ለሌሎች ጆሯቸውን እንደሚሰጡ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይሁን እንጂ “ቄሶች እጅግ ጠቃሚ የኅብረተሰቡ አካል እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ፈረንሳውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ” እና “በምድር ላይ ያሉ የአምላክ ምሥክሮች” አድርገው የሚመለከቷቸው 56 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ ጋዜጣው ይገልጻል። ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል ልጁ ወይም ዘመዱ እንዲቀስስ የሚያበረታታው ከ3 ሰው 1ዱ ብቻ ሲሆን አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን ከሚሳለሙት ውስጥ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ማበረታቻ የሚሰጡት 51 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።

ስለ ጦርነት የሚወጡ ዘገባዎች

“በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 27 ጦርነቶች ይካሄዳሉ” በማለት ሳይኮሎጂ ቱዴይ ይናገራል። ለ7 ዓመታት በላይቤሪያ የተደረገው ጦርነት ከ150, 000 በላይ የሚሆኑ ላይቤሪያውያንን ሕይወት እንደቀጠፈና በአንጎላ ለ15 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት 500, 000 ሰዎችን ለሞት እንደዳረገ የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም ሪፖርት አድርጓል። ከ1984 ጀምሮ በቱርክ የደረሰው ግጭት ከ37, 000 የሚበልጡ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን ከ1983 ጀምሮ በስሪ ላንካ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት 60, 000 የሚያክሉ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይነገራል። “ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት ዓመታት በጠቅላላው ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች (ብዙዎቹ ሰላማውያን ሰዎች ናቸው) እንደሞቱ” መጽሔቱ ገልጿል። “በምጣኔ ሀብት የተነሳ . . . ጦርነት የማይቀር ነገር ሊሆን ይችላል። ጦርነት በዓመት 800 ቢልዮን የሚያክል ዶላር የተመደበለት በምድር ላይ ካሉት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛል።” ርዕሰ አንቀጹ “እንደ እኛው ላሉ ሰዎች ፈጽሞ የማንራራ ምን ዓይነት አስገራሚ ፍጥረቶች ነን” ሲል ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ይህን የያዝነውን ዓመት ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት በማለት ሰይሞታል።

ማጨስና ዓይነ ስውርነት

“ማጨስ ዋነኛ የዓይነ ስውርነት መንስኤ ነው” በማለት ካንቤራ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ እና የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ተመራማሪዎች በሰጡት ግምታዊ አኃዝ መሠረት በአውስትራሊያ ከሚገኙት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑት ዓይነ ስውራን መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ለዓይነ ስውርነት የተዳረጉት በማጨሳቸው ምክንያት ነው። ተመራማሪዎቹ ከአውስትራሊያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከአውሮፓ ጠቅሰው ያቀረቧቸው ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሚያጨሱ ሰዎች ከእድሜ ጋር ተያይዞ በሚመጣው ማክዩላ ሉቲያ በሚባለው የዓይን ክፍል ላይ በሚከሰት ችግር ሳቢያ የመታወር ዕድላቸው ከማያጨሱት ሰዎች ከሁለት እስከ አምስት እጥፍ የሚበልጥ ነው። የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዌይን ስሚዝ በሲጋራ ፓኮዎች ላይ “ማጨስ ለዓይነ ሥውርነት ይዳርጋል” የሚል ማስጠንቀቂያ እንዲጻፍ ሐሳብ አቅርበዋል።

ቸልተኛ መሆንና በልጆች ላይ በደል መፈጸም

በጃፓን በ1998 የበጀት ዓመት በልጆች ላይ የተፈጸመው በደል ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ ጨምሮ እንደተገኘ አሳሂ ኢቭኒንግ ኒውስ ዘግቧል። ጠበብት ይህ የሆነው “ልጆቻቸውን የማሳደግ ሸክም ሙሉ በሙሉ በእነርሱ ላይ የወደቀባቸው እናቶች ያለባቸው ውጥረት እየተባባሰ በመሄዱ” እና ሕዝቡ በደል ስለሚፈጸምባቸው ወይም ችላ ስለተባሉ ልጆች የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለበት “ይበልጥ እየተገነዘበ በመምጣቱ” እንደሆነ ገልጸዋል። ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ እንደገለጸው በጃፓን፣ ቤት ውስጥ ወይም የቆመ መኪና ውስጥ ተትተው በመቆየታቸው የሚሞቱ ትንንሽ ልጆች ቁጥር ጨምሯል። አንዳንዴ ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ወላጆቻቸው ፓቺንኮ የተባለውን ቁማር ለመጫወት በሚሄዱበት ወቅት ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ወላጆች ተጠያቂ ሆነው ለክስ አይቀርቡም ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ባለ ሥልጣኖች ለልጆቻቸው በጣም ቸልተኛ በሆኑ ወላጆች ላይ ክስ ለመመሥረት እያሰቡ ናቸው።

የቤት እንስሳ ላላቸው የሚሆን ማስጠንቀቂያ

ለ ሞንድ የተሰኘው የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ በፈረንሳይ ከሚኖሩት ቤተሰቦች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የቤት እንስሳ አላቸው። ይሁን እንጂ በፈረንሳይ ሜዞን-አልፎር በሚገኘው በኮምፓራቲቭ አኒማል ኢሚዩኖሎጂ ተቋም የሚሠራ አንድ የእንስሳት ሐኪም ቡድን በቅርቡ ባደረገው ጥናት በፈረንሳይ የሚገኙት 8.4 ሚልዮን ድመቶችና 7.9 ሚልዮን ውሾች የሚሸከሟቸው ፈንገስና ጥገኛ ተውሳኮች የቤት እንስሳት ያላቸውን ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች እንደዳረጓቸው አመልክቷል። ከእነዚህም መካከል ጭርት (ringworm)፣ ድቡልቡል ትላትሎች (roundworm)፣ እከክ፣ ጭንቁር (leishmaniasis) እና ቶክሶፕላዝሞሲስ ይገኙበታል። ቶክሶፕላዝሞሲስ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶች እንዲጨነግፉ ሊያደርግ ወይም በማሕጸን ውስጥ ባለው ሽል ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ዘገባው በመጨመር በቤት እንስሶች አማካኝነት ስለሚፈጠሩ በርካታ አለርጂዎችና በውሾች ንክሻ ሳቢያ ስለሚከሰት ልክፈት የጠቀሰ ሲሆን በፈረንሳይ በየዓመቱ 100, 000 የሚያህሉ ሰዎች በነዚህ ችግሮች ይጠቃሉ።

በኤች አይ ቪ ተይዘው የሚወለዱ ሕፃናት

“በአፍሪካ ከሚወለዱት ሕፃናት መካከል ግማሽ የሚያክሉት ኤድስ አማጭ የሆነው ኤች አይ ቪ ቫይረስ አለባቸው” በማለት ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል። የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ የጋራ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ፒተር ፓዮ እንደገለጹት በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ኤች አይ ቪ እና ኤድስ የሰዎችን የሕይወት ዘመን በ25 ዓመት ቀንሰዋል። አክሎም ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “የኤች አይ ቪ ቫይረስ በከፍተኛ መጠን የተስፋፋባቸው 21 አገሮች በሙሉ የሚገኙት በአፍሪካ ነው። ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አሥሩ ከሕዝቦቻቸው መካከል ቢያንስ ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ ተይዘዋል።” በመላው ዓለም በኤድስ ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ በአፍሪካ የሚሞቱ ናቸው።

“የውሸት ዝናብ”

የቻይና ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው በሺንጂያንግ ዊገር፣ በቱርፓን የውሸት ዝናብ የሚባል እንግዳ የተፈጥሮ ክስተት ተከስቷል። በሰማይ ላይ ጥቁር ደመና እያንዣበበ እንኳ አየሩ ሞቃታማ፣ መሬቱም ደረቅ እንደሆነ ሊቀር ይችላል በማለት ቻይና ቱዴይ ዘግቧል። ዝናብ ከሰማይ የሚወርድ ከመምሰሉም በላይ አንድ ሰው እጁን በአየር ላይ በማወዛወዝ ዝናብ እየዘነበ እንዳለ ለማወቅ ይችላል። ይሁን እንጂ በቱርፓን ያለው የአየር ንብረት በጣም ደረቅ ከመሆኑ የተነሳ ትነት የሚካሄደው ዝናብ መሬት ለመድረስ ከሚፈጅበት ጊዜ በበለጠ ፍጥነት ነው። በመሆኑም ይህ “የውሸት ዝናብ” መሬት ከመድረሱ በፊት ይተንናል።

የኤቨረስት ተራራ ከፍታ ጨመረ

“የዓለም ረዥሙ ተራራ ኤቨረስት ቀደም ሲል ሳይንቲስቶች ያስቡት ከነበረው በላይ ረዝሞ የተገኘ ሲሆን አሁንም ከፍታው በመጨመር ላይ ይገኛል” በማለት በቅርቡ ሮይተርስ ሪፖርት አድርጓል። “ተራራ የሚወጡ ሰዎች እጅግ ውስብስብ የሆኑ የሳተላይት መሣሪያዎችን በመጠቀም ተራራውን የለኩ ሲሆን የኤቨረስት ተራራ ከፍታ 8, 850 ሜትር ወይም 8.9 ኪሎ ሜትር ገደማ ሆኖ አግኝተውታል። . . . ይህም በ1954 ሲለካ ከነበረው 8, 848 ሜትር ርዝማኔ በ2 ሜትር ጨምሯል።” አዲሱ አኃዝ በበረዶ እስከተሸፈነው የተራራው ጫፍ ድረስ ያለውን የተራራውን ከፍታ የሚያመለክት ነው። ከበረዶው ሥር ያለው የተራራው ክፍል ምን ያህል ርዝመት እንዳለው እስካሁን የሚያውቅ የለም። ብሔራዊው የጂኦግራፊ ማኅበር ካርታዎቹ ላይ አዲሱን አኃዝ አስፍሯል። ተራራው ወደ ላይ እያደገ ከመሆኑ በተጨማሪ ጠቅላላው የሂማሊያ የተራራ ሰንሰለት በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ቻይና በየዓመቱ ከ1.5 ሚሊ ሜትር እስከ 6 ሚሊ ሜትር እየሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል።