በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕሮፓጋንዳ ገዳይ ሊሆን ይችላል

ፕሮፓጋንዳ ገዳይ ሊሆን ይችላል

ፕሮፓጋንዳ ገዳይ ሊሆን ይችላል

“እውነት ጫማውን እስኪያደርግ ድረስ ውሸት የዓለምን አጋማሽ ሊያዳርስ ይችላል።”​—⁠ማርክ ቱዌይን ተናግሮታል ተብሎ የሚታመን

አስተማሪዋ የሰባት ዓመት ተማሪዋን እየገረፈች “አንተ የማትረባ አይሁድ!” በማለት ትሳደባለች። ከዚያም የክፍሉ ተማሪዎች በየተራ ፊቱ ላይ እየተፉ እንዲያልፉ አዘዘች።

የልጁ አያት እህት ልጅ የሆነችው አስተማሪዋም ሆነች ተማሪው ልጁ የአይሁድ ዝርያ እንደሌለው አሳምረው ያውቃሉ። በእምነትም ቢሆን አይሁዳውያን አልነበሩም። ይልቁንም የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አስተማሪዋ አይሁዳውያን በብዛት የሚጠሉ መሆናቸውን እንደ መሣሪያ አድርጋ በመጠቀም ተማሪዋ እንዲጠላ መቀስቀስዋ ነበር። አንድ ቄስ ለአስተማሪዋና ለተማሪዎችዋ የይሖዋ ምሥክሮች ሊጠሉ የሚገባቸው ሰዎች እንደሆኑ ለበርካታ ዓመታት ነግሯቸው ነበር። የልጁ ወላጆች ኮምኒስቶች እና የሲ አይ ኤ ወኪሎች ናቸው ተብለዋል። ስለዚህ የልጁ የክፍል ጓደኞች በየተራ በዚህ “የማይረባ አይሁድ” ፊት ላይ እየተፉ አለፉ።

ይህ ልጅ ዕድሜ አግኝቶ ያሳለፈውን ሁኔታ ለመተረክ በቅቷል። ከ60 ዓመት በፊት በጀርመንና በአጎራባች አገሮች ይኖሩ የነበሩ ስድስት ሚልዮን የሚያህሉ አይሁድ ግን ለዚህ ዕድል አልበቁም። በተሠራጨው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት በናዚ የመርዝ ጋዝ ቤቶችና የማጎሪያ ካምፖች ተገድለዋል። በጣም በተሠራጨ፣ ሥር በሰደደና ለምን ተብሎ በማይጠየቅ ፀረ ሴማዊ ጥላቻ ምክንያት ብዙ ሰዎች በአይሁዳውያን ላይ የደረሰው እልቂት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ እንደሆነ ጭምር አምነዋል። በዚህ መልኩ ፕሮፓጋንዳ ለሕዝባዊ እልቂት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።

አዎን፣ ፕሮፓጋንዳ እንደ ስዋስቲካ የመሰሉትን የጥላቻ ምስሎች በመጠቀም ወይም ለዛ ቢስ በሆኑ ቀልዶች አማካኝነት ይፋ ሊወጣ ይችላል። አምባ ገነኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ቀሳውስት፣ አስተዋዋቂዎች፣ አሻሻጮች፣ ጋዜጠኞች፣ የራዲዮና የቴሌቪዥን ሰዎች፣ የሕዝብ ግንኙነቶች ሠራተኞችና የሰዎችን አስተሳሰብና ጠባይ ለመቀየር የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች በፕሮፓጋንዳ ዘዴዎች አዘውትረው ይገለገላሉ።

እርግጥ የፕሮፓጋንዳዊ መልእክቶች ለጥሩ ዓላማ ሊውሉ የሚችሉበት ጊዜም አለ። ለምሳሌ ሰዎች ሰክረው መኪና እንዳያሽከረክሩ ለማሳሰብ ሊያገለግል ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ በአንድ ጎሣ ወይም ሃይማኖታዊ ቡድን ላይ ጥላቻ ለማነሳሳት ወይም ሲጋራ ለማሻሻጥ ሊያገለግል ይችላል። አንቶኒ ፕራትካኒስ እና ሌሊየት አረንሰን የተባሉ ተመራማሪዎች “በእያንዳንዱ ቀን የተለያየ መልክ ያለው የማሳመኛ መልእክት ውርጅብኝ ይወርድብናል። እነዚህ መልእክቶች ለማሳመን የሚሞክሩት የእሰጥ አገባ መልክ ባለው ክርክርና ውይይት ሳይሆን አንዳንድ ምስሎችን በመጠቀምና በጣም መሠረታዊ የሆኑትን ሰብዓዊ ስሜቶች መሣሪያ በማድረግ ነው። ከፋም ለማ የኛ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ዘመን ሆኗል” ብለዋል።

ባለፉት መቶ ዘመናት ፓሮፓጋንዳ የሰው ልጆችን አስተሳሰብና ድርጊት ለመቆጣጠር መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነው? ራስህን አደገኛ ከሆነ ፕሮፓጋንዳ መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የሚቻልበት ምንጭ ይኖር ይሆን? በእ​ነዚህና እነዚህን የመሰሉ ጉዳዮች በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ይብራራሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሆሎኮስት ጊዜ ፕሮፓጋንዳ በአይሁዳውያን ላይ ስደት ለማነሳሳት አገልግሏል