ሥር የሰደደ በሽታ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሲከሰት
ሥር የሰደደ በሽታ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሲከሰት
በደ ቶይ ቤተሰብ ላይ የሚንጸባረቀው ደስታ ወደ ሌሎች ሰዎችም የሚጋባ ነው። እርስ በርስ ያላቸውን የጋለ ፍቅር መመልከቱ የሚያስደስት ነው። እንዲሁ ሲታዩ ምንም ዓይነት ችግር ያሳለፉ አይመስሉም።
ብራም እና አን የመጀመሪያ ልጃቸው የሆነችው ሚሼል ሁለት ዓመት ሲሆናት በዘር የሚተላለፍ ጡንቻዎችን የሚያመነምን ሥር የሰደደ በሽታ እንደያዛት ተገነዘቡ።
እናትዬዋ አን “አካልን የሚያሽመደምድ ሥር የሰደደ በሽታን እንዴት መቋቋም እንደምትችል ባላሰብከው ሁኔታ ለመማር ትገደዳለህ። የቤተሰብ ሕይወት እንደ ቀድሞው እንደማይሆን ትገነዘባለህ” ስትል ተናግራለች።
ይሁን እንጂ ሌላ ሴት ልጅና አንድ ወንድ ልጅ ከተወለዱ በኋላ በዚህ ቤተሰብ ላይ ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ። አንድ ቀን ሦስቱ ልጆች ከቤት ውጭ እየተጫወቱ ሳለ ሁለቱ ሴቶች ልጆች ወደ ቤት እየሮጡ መጡና “እማዬ! እማዬ!” እያሉ መጣራት ጀመሩ። “ቶሎ ነይ፣ ኒል የሆነ ነገር ሆኗል!” አሏት።
አን እየሮጠች ወጥታ የሦስት ዓመት ልጅዋን ኒልን ስትመለከት ጭንቅላቱ ወደ አንድ ወገን አዘንብሏል። ጭንቅላቱን ማቃናት አቅቶት ነበር።
“በጣም ደነገጥኩ” ትላለች አን በማስታወስ፣ “ችግሩ ምን እንደሆነ ወዲያው ገባኝ። ጤናማ የነበረው ይህ ትንሽ ልጅ እንደ ታላቅ እህቱ ጡንቻን በሚያመነምን በሽታ በመያዙ በቀሪው ሕይወቱ የሚገጥመውን ፈታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ተገደደ።”
“የገጠሙን እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ጤናማ የነበረውን የቤተሰባችንን ደስታ ገፈፉት” በማለት አባትዬው ብራም ይናገራል።
በመጨረሻም ሚሼል ጥሩ ሕክምና ሲደረግላት የቆየች ቢሆንም እንኳ ሕመሟ ባስከተላቸው ሌሎች የጤና ችግሮች ሳቢያ ሕይወቷ አለፈ። በዚያን ወቅት ዕድሜዋ ገና 14 ዓመት ነበር። ኒል በሽታው ካስከተለበት ችግር ጋር መታገሉን ቀጥሏል።
ይህ ሁኔታ እንደ ደ ቶይ ቤተሰብ ያሉ ሥር በሰደደ በሽታ የሚሠቃይ አባል ያላቸው ቤተሰቦች የሚገጥሟቸውን ተፈታታኝ ችግሮች እንዴት መቋቋም ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሥር የሰደዱ በሽታዎች በቤተሰቦች ላይ የሚያደርሱትን አንዳንድ ተጽዕኖዎች እንመርምር።